ኢሰማኮ ሀገር አቀፍ የስራ ማቆም እንደሚጠራ አስጠነቀቀ | ኢትዮጵያ | DW | 27.10.2017
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

ኢትዮጵያ

ኢሰማኮ ሀገር አቀፍ የስራ ማቆም እንደሚጠራ አስጠነቀቀ

የኢትዮጵያ የሰራተኞች ማህበራት ኮንፌዴሬሽን አሁን በስራ ላይ ያለውን የአሰሪና እና የሰራተኛ አዋጅን ለመተካት በተዘጋጀ ረቂቅ ህግ ላይ ከመንግስት ጋር ለመደራደር ያቀረበው ጥያቄ ተቀባይነት ካላገኘ ሀገር አቀፍ የስራ ማቆም እንደሚጠራ አስጠንቅቋል፡፡ ከስራ ማቆሙ በፊት ሀገር አቀፍ ሰላማዊ ሰልፍ ሊካሄድ እንደሚችልም አሳውቋል፡፡

አውዲዮውን ያዳምጡ። 05:11

ኮንፌዴሬሽኑ ከመንግስት ጋር መደራደር ይሻል

የኢትዮጵያ ሰራተኞች ማህበራት ኮንፌዴሬሽን (ኢሰማኮ) ትላንት ባካሄደው የጠቅላይ ምክር ቤት ስብሰባ ካስተላለፋቸው ውሳኔዎች መካከል የአሰሪና እና የሰራተኛ ጉዳይ የህግ ረቂቅን የተመለከተው አንዱ እንደሆነ የኮንፌዴሬሽኑ ፕሬዝዳንት አቶ ካሳሁን ፎሎ ለዶይቼ ቬለ ገልጸዋል፡፡ በአዲስ አበባ መስቀል አደባባይ አካባቢ በሚገኘው የኮንፌዴሬሽኑ ጽህፈት ቤት በተካሄደው በዚሁ ስብሰባ ምክር ቤቱ የኮንፌዴሬሽኑን ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ የህግ ረቂቁን አስመልክቶ ያቀረበውን ዘገባ አዳምጧል፡፡

በረቂቅ ህጉ ላይ በተካተቱ 19 አንቀጾች ላይ ልዩነት ያለው ኮንፌዴሬሽኑ ይህንኑ ዘርዝሮ የሚኒስትሮች ምክር ቤት አባላት ለሆኑ 32 ሚኒስትሮች በደብዳቤ መላኩን የኮሚቴው ዘገባ ጠቅሷል፡፡ ሚኒስትሮቹ “ጉዳዩን በጥሞና አይተው እንዲያስተካክሉላቸው” እንደጠየቁ አቶ ካሳሁን ለምክር ቤቱ ገልጸዋል፡፡ ምክር ቤቱ በምላሹ ያሳለፈውን ውሳኔ ደግሞ እንዲህ ያብራራሉ፡፡

“ምክር ቤቱ መጀመሪያ በዋናነት ያስቀመጠው ከመንግስት ጋር እንድትወያዩ የሚል ነበር፡፡ ነገር ግን መንግስት ለውይይት ዝግጁ ካልሆነ፣ ለውይይት በሩን የማይከፍት ከሆነ የኢሰማኮ ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ሀገር አቀፍ ሰላማዊ ሰልፍ እንዲጠራ ኃላፊነት ተሰጥቶታል፡፡ ከዚያም በሶስተኛ ደረጃ ሰላማዊ ሰልፍ ወጥተንም፣ ይሄ ነገር የማይስተካከል ከሆነ አጠቃላይ ሰራተኛውን በማስተባበር አጠቃላይ የስራ ማቆም እርምጃ እንዲወሰድ፣ የኢሰማኮ ስራ አስፈጻሚ ይሄን ኃላፊነት ወስዶ እንዲጠራ፣ ከአደራ ጭምር ለኢሰማኮ ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ሙሉ ውክልና ተሰጥቷል” ሲሉ አቶ ካሳሁን ለዶይቼ ቬለ ተናግረዋል፡፡

የሰላማዊ ሰልፉን እና የስራ ማቆም እርምጃውን እንዲጠራ ኃላፊነቱን የተረከበው የኢሰማኮ ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ፕሬዝዳንቱን አቶ ካሳሁንን ጨምሮ 10 አባላት ያሉበት ነው፡፡ ኮሚቴው የኮንፌዴሬሽኑን መደበኛ ስራም ያከናውናል፡፡ አቶ ካሳሁን ቀጣዩ ስራቸው በትላንትናው ዕለት ጥቅምት 16 የተላለፈውን የአቋም መግለጫ ከጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ጀምሮ ለሚኒስትሮች እና ለሚመለከታቸው አካላት እንዲደርስ ማድረግ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡ ከዚያ በኋላ የመንግስትን ምላሽ እንደሚጠበቁ ለዶይቼ ቬለ ተናግረዋል፡፡

ከመንግስት እሺታ ወይም እምቢታ ጋር ለተሳሰረው የሰላማዊ ሰልፍም ሆነ የስራ ማቆሙ እርምጃ ኮንፌዴሬሽኑ የጊዜ ሰሌዳ አላስቀመጠም፡፡ “መንግስት ምን ይላል? የሚለውን ነገር እንጠብቃለን፡፡ ይህን ካወቅን በኋላ፤ በተሰጠን አደራ መሰረት እየገመገምን በየጊዜው አስፈላጊ የሆኑ እርምጃዎች የሚወሰዱበትን ሁኔታ እናመቻቻለን” ይላሉ አቶ ካሳሁን፡፡   

ውሳኔውን 86 አባላት ያሉት የኢሰማኮ ጠቅላይ ምክር ቤት ይወስን እንጂ በዚህ ጉዳይ ላይ አጠቃላይ በኢትዮጵያ ውስጥ ያሉ የመሰረታዊ ማህበራት አመራሮች መወያየታቸውን አቶ ካሳሁን ይናገራሉ፡፡ ኢሰማኮ በአሰሪና እና ሰራተኛ ጉዳይ አዋጅ ላይ ማሻሻያ ለማድረግ ላለፉት ስምንት ዓመታት ከመንግስት ጋር ሲነጋገር ቆይቷል፡፡ ኮንፌዴሬሽኑ ከበርካታ ንግግሮች በኋላ የተስማመበት የህግ ረቂቅ በ2008 ዓ.ም ወደ ሚኒስትሮች ምክር ቤት እንዲላክ ተስማምቶ ነበር፡፡ በዓመቱ የሚኒስትሮች ምክር ቤት የህግ ረቂቁን እንደገና መልሶ ውይይት እንዲደረግበት ማዘዙን አቶ ካሳሁን ይናገራሉ፡፡ ያኔ ልዩነቶች መከሰታቸውንም ያብራራሉ፡፡

“በ2009 ዓ.ም እንደገና ለውይይት ወደ እኛ ሲመጣ ረቂቁ ምን ይዞ መጣ? በ2008 ዓ.ም የተወያየንባቸውን አንቀጾች በማሻሻል ወይም በመቀየር፣ ሌላ አዳዲስ አንቀጾችን በመጨመር፣ እንደ አዲስ ረቂቁ በሰራተኛ እና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር በኩል ደረሰን፡፡ የሰራተኛን መሰረታዊ መብቶች የሚነኩ አሁን የተቃወምናቸው አንቀጾች ተካተውበት ነው የመጡት፡፡ እነዚህ በ2008 ዓ.ም ውይይታችን ላይ አልነበሩም” ብለዋል የኮንፌዴሬሽኑ ፕሬዝዳንት፡፡     

ኢሰማኮ አሁን እያወዛገበ ባለው የህግ ረቂቅ ላይ የተካተቱ እና “የሰራተኛውን መሰረታዊ መብቶች ይጎዳሉ” ያሏቸውን አንቀጾች ለይቶ ለሰራተኛ እና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ማስገባቱን አቶ ካሳሁን ይናገራሉ፡፡ ለሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ በላኩት ማብራሪያ እንደ አዲስ አንዲጨምርላቸው የሚፈልጓቸውን ማሻሻያዎችን ማካተታቸውንም ያስረዳሉ፡፡ ከዚያ በኋላ በህግ ረቂቁ ላይ በነበረ ውይይት ግን ምንም የተቀየረ ነገር አለመኖሩን እና ከሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ጋር ስምምነት ላይ መድረስ እንደተሳናቸው ገልጸዋል፡፡ አቶ ካሳሁን ኢሰማኮ ተቃውሞውን ከገለጸባቸው አንቀጾች ውስጥ ሁለቱን በምሳሌነት ያነሳሉ፡፡

“ለምሳሌ ‘አንድ ሰራተኛ በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ ሁለት ቀን ካረፈደ ያለማስጠንቀቂያ ከስራ ይባረራል’ [ይላል]፡፡ ይሄ ማለት የኢትዮጵያን ተጨባጭ ሁኔታ ያላገናዘበ ነው፡፡ ስንት ደቂቃ? የሚለው የለም፡፡ በወር ውስጥ አንድም አምስትም ደቂቃ ካረፈደ የሚባረር ከሆነ ችግር ነው የሚገጥመን፡፡ ለአሰሪውም ከባድ ነው፡፡ የተረጋጋ የኢንዱስትሪ ሰላምም አይፈጥርም፡፡ ሌላው ‘ያለበቂ ምክንያት አንድም ቀን መቅረት’ አይችልም ነው፡፡ ያለበቂ ምክንያት ማለት ምን ማለት ነው? ማነው በቂ ምክንያት የሚለው? ስራ ሁሉ ከተቋረጠ በኋላ፤  ይህን ሰራተኛ ‘ይሄ በቂ ምክንያት ነው፤ አይደለም’ የሚለውን በፍርድ ቤት ተከራክሮ ካልሆነ በስተቀር የሚመልሰው የለም፡፡ ስለዚህ ይሄ ‘በቂ ምክንያት የሚለው ተዘርዝሮ ይቀመጥ ወይም ደግሞ በቂ ያልሆኑ የተባሉ ምክንያቶች ተዘርዝሮ ይቀመጥ’ ሲባል ‘አይ ሁለቱን በህግ ዘርዝሮ ማስቀመጥ አይቻልም’ ተባለ” ሲሉ ስለማይስማሙባቸው አንቀጾች ያስረዳሉ፡፡   

ኢሰማኮ ከዚህ ሌላ የዓመት የእረፍት አወሳሰድን ጨምሮ በአጠቃላይ በህግ ረቂቁ 19 አንቀጾች ላይ ከመንግስት ጋር መደራደር እንደሚፈልግ ፕሬዝዳንቱ ጨምረው ገልጸዋል፡፡ በኢትዮጵያ የአሰሪና ሰራተኛ ጉዳይ አዋጅ በተለያዩ ጊዜያት ማሻሻያ ሲደረግበት ቆይቷል፡፡ አዋጁ አሁን ስልጣን ላይ ያለው መንግስት በ1985 ዓ.ም ያሻሻለው ሲሆን በ1996 ዓ.ም በድጋሚ ማስተካከያ ተደርጎበታል፡፡ ከሁለት ዓመት በኋላም በህጉ የተወሰኑ አንቀጾች ላይ ለውጥ መደረጉ የሚታወስ ነው፡፡    

ተስፋለም ወልደየስ

አርያም ተክሌ

Audios and videos on the topic