ኢራን የኑክሌር ዉዝግብና የጉብኝት ግብዣ | ዓለም | DW | 06.01.2011
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ዓለም

ኢራን የኑክሌር ዉዝግብና የጉብኝት ግብዣ

የጉብኝቱ ጊዜ አልተቆረጠም።የአዉሮጳ ሕብረት እንደ ሕብረት መልዕክተኞቹን መላክ-አለመላኩም ገና በዉል አልታወቀም።መጋበዙን ግን አረጋግጧል።ኒዮርክ ታይምስ እንደዘገበዉ ኢራንን በግንባር ቀደምትነት የምትዋገዝ-አለምን የምታሳድመዉ ዩናይትድ ስቴትስ ከተጋባዦቹ ሐገራት ዝር ዝር ዉስጥ የለችበትም

default

አንዱ የዩራንየም ማብላያ

06 01 11

ኢራን ከምዕራባዉያን ሐገራት ጋር የምትወዛገብባቸዉን የኑክሌር ተቋሟት የዉጪ አምባሳዳሮች እንዲጎበኙ ጋብዛለች።ግብዣዉን አንዳዶች የተቀበሉት ቢመስሉም የአዉሮጳ ሕብረት ግን መቀበል አለመቀበሉን ለማስታወቅ እያቅማማ ነዉ።አንድ የሕብረቱ ኮሚሽን ቃል አቀባይ እንዳስታወቀዉ ሕብረቱ ኢራን በደብዳቤ ላቀረበችዉ ግብዣ በይፋ መልስ አልሰጠም።ይሁንና ቃል አቀባዩ አክሎ እንዳስታወቀዉ ተቋማቱን መጎብኘትም ሆነ መፈተሽ የሚገባቸዉ የአለም አቀፉ የአዉቶሚክ ተቆጣጣሪ ባለሥልጣን ባለሙያዎች ናቸዉ ብሎ ሕብረቱ ያምናል።ሽቴፋን ቩርስትል ያጠናቀረዉንና የዜና አገልግሎት ዘገቦችን ነጋሽ መሐመድ አጠናቅሯቸዋል።


ግብዣዉ ለአዉሮጳ ሕብረት አባላት፥ በመበልፀግ ላይ ለሚገኙት ሐገራት እና ሥለ ኢራን የኑክሌር መርሐ-ግብር ከኢራን ጋር ለሚደራደሩት 5+1 ለተሰኘዉ ቡድን አባል ሐገራት ነዉ-የተሰራጨዉ። የተባበሩት መንግሥታት የአዉቶሚክ ተቆጣጣሪ ባለሥልጣን (IAEA-በእንግሊዝኛ ምሕፃሩ እንዳስታወቀዉ የኢራን ባለሥልጣናት ለማስጎብኘት ያቀዱት ናታንዝ የሚገኘዉን የኑክሌር ማብላያ እና አርክ ያለዉን የኑክሌር ዉሐ ማጣሪያ ተቋማትን ነዉ።

ኢራን ኑክሌር ቦምብ ትሠራበት ይሆናል ተብሎ ይጠረጠር በነበረዉ በቡሻሒሩ ተቋም የሚብላላ ዩራንዬሟን ሩሲያ ዉስጥ እንዲብላላ ከፈቀደች ወዲሕ የዩናይትድ ስቴትስና የሌሎች ምዕራባዉያን ሐገራት ጥርጣሬ ወደ ሁለቱ፥ በተለይ ደግሞ ወደ ናታንዙ ተቋም ዞሯል።ኢራን ግን የኑክሌር ተቋማቷ በሙሉ ለኤሌክትሪክ ሐይል ማመንጫና ለሌሎች ሰላማዊ አገልግሎቶች የሚዉል በማለት ትከራከራለች።

የኢራን ባለሥልጣናት የዉጪ አምባሳደሮቹን ለጉብኝት የጋበዙበት ምክንያትም ጥርጣሬዉን ለማርገብ ነዉ-ባዮች ናቸዉ።በአለም አቀፉ የአዉቶሚክ ተቆጣጣሪ ባለሥልጣን የኢራን አምባሳደር ዓሊ አስጋር ሶልታኒይሕ ባለፈዉ ማክሰኞ እንዳስታወቁት ሐገራቸዉ አምባሳደሮቹን የጋበዘችዉ የኑክሌር መርሐ-ግብሯ ለሰላማዊ አገልግሎት የሚዉል መሆኑን ማወቅ ለሚፈልጉ ወገኖች ለማሳወቅ ነዉ።

የኢራን ዉጪ ጉዳይ ሚንስቴር ቃል አቀባይ ራሚን ሜሕማንፓራሳት አምባሳደራቸዉ ቪየና ላይ ያሉትን ከቴሕራን ደገሙት።

«አዲሱ የኢራን እርምጃ፥ ማለትም የአዉቶሚክ ተቋማቶቻችንን እንዲጎበኙ የተለያዩ ሐገራት አምባሳደሮችን መጋበዛችን ለመልካም ፍቃዳችን ተጨማሪ ማረጋገጪያ ነዉ።ከዚሕም በተጨማሪ ተባብረን ለመስራት ያለንን ፍላጎት ይመሰክራል።የኑክሌር መርሐ ግብራችን አላማም ሰላማዊ አገልግሎት መሆኑን አመልካችም ነዉ።»

የጉብኝቱ ጊዜ አልተቆረጠም።የአዉሮጳ ሕብረት እንደ ሕብረት መልዕክተኞቹን መላክ-አለመላኩም ገና በዉል አልታወቀም።መጋበዙን ግን አረጋግጧል።ኒዮርክ ታይምስ እንደዘገበዉ ኢራንን በግንባር ቀደምትነት የምትዋገዝ-አለምን የምታሳድመዉ ዩናይትድ ስቴትስ ከተጋባዦቹ ሐገራት ዝር ዝር ዉስጥ የለችበትም።የጀርመን ዉጪ ጉዳይ ሚኒስቴር በበኩሉ ጀርመን እስከ ትናንት ድረስ የግብዣዉ ደብዳቤ አልደረሳትም ብሏል።

የኢራን ወዳጅ የሚባሉት ሩሲያና ቻይናን የመሳሰሉት ሐገራት መገባዛቸዉ፥ ግብዣዉን መቀበላቸዉም ብዙ አላጠራጠረም።አንድ የዩናይትድ ስቴትስ ዉጪ ጉዳይ ሚንስቴር ቃል አቀባይ ግን ግብዣዉን አለም አቀፉን ማሕበረሰብ ለመነጣጠል ያለመ በማለት አዉግዞታል።እንደ ቃል አቀባዩ ዩናይትድ ስቴትስም እንደ አዉሮጳ ሕብረት ሁሉ ኢራን የኑክሌር ተቋማቷን ማሳያትና ማስፈተሽ ያለባት ለአለም አቀፉ አዉቶሚክ ተቋም ባለሙያዎች መሆን አለበ ባይናት።

በያዝነዉ የጎርጎሮሳዉያን ጥር ማብቂያ ሥለ ኢራን የኑክሌር መርሐ ግብር ኢስታንቡል-ቱርክ ዉስጥ ድርድር ይደረጋል።የኢራኑ ፕሬዝዳት ማሕሙድ አሕመዲንጃድ ግን ሐገራቸዉ አቋሟን እንደማትቀይር በይፋ አስታዉቀዋል።ይሁንና ታዛቢዎች እንደሚገምቱት ኢራን እንደ ወዳጅ በምትጎራበታት በቱርክ በኩል የማካካሻ ሐሳብ ከቀረበላት አልቀበልም አትልትም።

ነጋሽ መሐመድ

አርያም ተክሌተዛማጅ ዘገባዎች