ኢራቅ የጦርነት ማግሥት ጦርነት ሐገር | ዓለም | DW | 06.03.2017
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

ዓለም

ኢራቅ የጦርነት ማግሥት ጦርነት ሐገር

የኢራቅ መንግሥት ከ70 ሺሕ በላይ እግረኛ እና ሜካናይዝድ ጦር አዝምቷል።የኢራቅ ኩርዶች ፔሽ ሜርጋ ከሚሉት ጦራቸዉ አርባ ሺሕ አሰልፈዋል።የኢራንና የሒዝቡላሕ ሚሊሺዎች፤ የአሜሪካና የሌሎች ምዕራባዉያን ሐገራት ጦር ብዛት በዉል አልተነገረም። ከሁለት እስከ አራት ሺሕ የሚገመቱ የአይሲስ ተዋጊዎች ሞሱል ዉስጥ መሽገዋል ተብሎ ይገመታል።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 13:30

ኢራቅ በጦርነት ማግሥት

ከ400 ዓመተ-ዓለም ጀምሮ አሲሪያዎች፤ ባቢሎኖች፤ፋርሶች፤ ሮሞች፤ አረቦች፤ ቱርኮች፤አዉሮጶች እየገደሉ-ገዝዋታል፤ እየገዙ-ተሸንፈዉi እየተገዙ ሞተዉባታል።ኤል ሞሱል-እንደ አረቦቹ።ወይም መዉሲል እንደ ኩርዶች፤ ወይም እንደ ቱርኮቹ ሙሱል።ከ2003 ጀምሮ አሜሪካኖች፤ አዉሮጶች፤ አረቦች ኩርዶች ተዋግተዋባታል።ሺዎችን ፈጅተዉባታል።ዛሬም ኩርዶች፤ አረቦች፤ ፋርሶች፤ አሜሪካኖች ይጋደሉባታል።ሕፃናት፤ ሴቶች፤ አቅመ ደካሞች ያልቁ፤ ይራቡ፤ ይሰደዱባትል።እስከ መቼ? 

 ጀላል ሱልጣን ኢራቃዊ ነዉ።በሙያዉ ልብስ ሰፊ።ሞተር ቢስክሌት መንዳት ይወዳል። እሱ እና ብጤዎቸዉ ማሕበር መስርተዉ በትርፍ ጊዚያቸዉ ሞተር ቢስስክሌት ይጋልባሉ።«አደገኛ ነዉ» ይላል ጄላል።ግን ያደርጉታል።

«ስንጓዝ ሰባና ሰማንያ ሆነን ነዉ።በእርግጥ አደገኛ ነዉ።ግን ዘላለም መፍራታችንን አቁመናል።ዉጪ ሐገር ያለ ሰዉ ኢራቅ የቦምብ፤የሽብር፤ የአይ ኤስ እና የመሳሰሉት ሐገር ናት ብሎ ነዉ የሚያስበዉ።እኛ ግን ነፃነታችንን እንወዳለን።ኢንሻአላሕ በሐገራችን ነፃነትና ደሕንነነት ዳግም ይስፋናል።»

የጄላል ተስፋ፤ የሚሊዮን ብጤዎቹ ምኞች፤ ፀሎትና ጉጉት ገቢር የሚሆንበት ጊዜ በርግጥ አይታወቅም።

ኢራቅ ግን  ዩናይትድ ስቴትስ መራሹ የምዕራብ ሐገራት ጦር  ከወረራት ከ2003 (ዘመኑ በሙሉ እንደ ጎርጎሪያኑ አቆጣጠር ነዉ) ጀምሮ ሠላም መረጋጋት ሰፍኖባት አያዉቅም።ከዉጊያ፤ ጦርነት፤ ከቦምብ ፍንዳታ-ሽብር ሌላ-ሌላ ነገር ብዙም አይደረግም-አይሰማባትምም።አስራ-አራት ዓመት።

የዉጪዉ ሰዉ ኢራቅን በቦምብ-ፍንዳታ ሽብር፤ በጦርነት ዉጊያ የእልቂት ማዕከልነት ቢፈርጃት እዉነት አለዉ።የፈጠጠ ሐቅ።ተስፋ ግን ጥሩ ነዉ።አንዳዶች እንደሚሉት ተስፋ ከሌለ ሕይወት ትርጉም የላትም።

 

 የሞሱሏ ወይዘሮም ተስፋ አላት።የአራት ልጆች እናት ናት።እስዋም፤ አራቱ ልጆችዋም ቆስለዋል።ሁሉም ሆስፒታል ተኝተዋል።«ሮብ ቀን ነዉ።አስር ሰዓት ግድም።ልጆቼ እቤት ዉስጥ ነበሩ።እኔ ደግሞ በረንዳ ላይ ቆሜ ነበር።ከሩቅ የተተኮሰ ባዙቃ እቤታችን አጠገብ ሮኬት ፈነዳ እና የሆነ ዘይት የሚመስል ነገር አለበሰን።»

የዓለም ቀይ ጨረቃና ቀይ መስቀል ማሕበር ሠራተኞች እንደሚሉት ሰዎቹ ላይ የተረጨዉ ዘይታማ ነገር መርዛማ (ኬሚካዊ) ንጥረ ነገር ሳይሆን አይቅም።ሞሱል አጠገብ የምትገኘዉ የኢርቢል ከተማ ሆስፒታል ሐኪሞችም በኬምካዊ መሳሪያ የተጎዱ 10 ሰዎችን ማከማቸዉን ባለፈዉ አርብ አስታዉቀዋል። አምስቱ ሴትዮዋና ልጆቻቸዉ ናቸዉ።ከልጆቻቸዉ አንዱ ደግሞ  ገና የሁለት ወር ሕፃን ነዉ።

ኬሚካዊዉን ንጥረ ነገር የተኮሰዉ ወገን በዉል አይታወቅም።የዩናይትድ ስቴትስ እና የብሪታንያ መሪዎች ከአስራ-አራት ዓመት በፊት ኢራቅን ለመዉረራቸዉ ከሰጡት የሐሰት ምክንያት አንዱ ፕሬዝደንት የሳዳም ሁሴንን የኬሚካዊ ጦር መሳሪያ ለማስፈታት የሚል ነበር።ከቦምብ ሚሳዬል፤ ከታንክ አዳፍኔ አረር የተረፈዉ የኢራቅ ዜጋ ግን ዛሬም በኬሚካዊ መሳሪያ ይንጨረጨራል።አስራ-አራተኛ ዓመቱ።ካሁኑ አልፎ የወደፊቱ ትዉልድም ያልቃል።

 

ዋሽንግተን ለንደን፤ ቴሕራን-ቴል አቪቮች ደጋግመዉ እንደነገሩን እስከና በ2003 ኬሚካዊ ጦር መሳሪያ ታጣቂ፤ አሸባሪ ደጋፊና አረመኔዉ ሳዳም ሁሴይን ነበሩ።ከስልጣን ተወገዱ-ተገደሉም።

ያኔ የዋሽግተን ለንደኖች ቃል-ተስፋ ያመነዉ ኢራቃዊ ተስፋ፤ ምኞች ጉጉቱም ባፍታ በነነ።የኢራቅ አል-ቃኢዳ፤የሙጃሒዲን ምክር ቤት፤የኢራቅ አንቂ ንቅናቄ የተባሉት እና ሌሎችም አሸባሪ ቡድናት ተፈለፈሉ።

ሽብር፤ እልቂት፤ ስደት ግፉም ቀጠለ።ከመሐል ባግዳድ፤ ከደቡብ   ባስራ፤ ከምዕራብ ፋሉጃሕን የሚያነደዉ እሳት አሁን ከ2014 ጀምሮ ሰሜን ኢራቅን እያጋየ ነዉ።በየጊዜዉ ስማቸዉን የሚቀያይሩት አሸባሪ ቡድናት እራሱን የኢራቅና የሶሪያ እስላማዊ መንግስት (ISIS በእንግሊዝኛ ምሕፃሩ) በሚለዉ ቡድን ሥር ከተጠቃለሉ ወዲሕ አዲስ መልክና ባሕሪ የያዘዉ ሽብር፤ ጦርነት እና ዉጊያ ሺዎችን ፈጅቷል።ብዙ ሺዎችን አሰድዷል።ብዙ አካባቢዎችን አጥፍቷል።አሁን በጥንታዊቱ፤በትልቂቱ በሚሊዮኖቹ ከተማ ሞሱል ላይ ጠንቷል።

የኢራቅ መንግሥት ጦር፤ ከኢራቅ ኩርዶች ጦር፤ የኢራን ሚሊሺያ፤ የዩናይትድ ስቴትስና የተባባሪዎችዋ ምዕራባዉያን መንግሥታት ጦር የርዳ-ተረዳዳ  ግንባር ፈጥረዉ ሞሱልን ከISIS እጅ ለማስለቀቅ ጥቃት ከከፈቱ አራተኛ ወራቸዉ።

እርግጥ ነዉ በዉጊያዉ መሐል የዩናይትድ ስቴትሱ ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ ኢራቃዉያን ወደ ዩናይትድ ስቴትስ እንዳይገቡ አግደዋል።እገዳዉ በፍርድ ቤት ዉሳኔ ቢታገድም  ኢራቆች ዩናይትድ ስቴትስ እንዳይገቡ ትራምፕ ያገዱበት ምክንያት አሸባሪዎች አሜሪካ እንዳይገቡ ለማገድ ነዉ።ኢራቅ ዉስጥ አሸባሪዎች እንዴት ተፈለፈሉ ብሎ የሚጠይቅ ካለ፤ ማዘር ጆንስ የተባለ አንድ መፅሔት አጭር መልስ ነበረዉ።

«ዩናይትድ ስቴትስ ኢራቅን ከወረረች ወዲሕ ኢራቅ ዉስጥ አሸባሪነት ከመቶ በ600 ጨምሯል።» ኢራቃዊዉ አሜሪካ እንዳይገባ ታግዷል።አምስት ሺሕ የአሜሪካ ጦር ግን ዛሬም ኢራቅ ዉስጥ ሰፍሯል።ዛሬም ከ2003 ጀምሮ እብዙ ሥፍራ ከተከፋፈሉት ኢራቆች አንዱን (መንግሥትን) ደግፎ ከሌሎቹ ጋር ይዋጋል።

«ከኢራቅ ወታደራዊ ጥንቅር ጋር በቅርብ በመተባበር እየሠራን ነዉ።ምሥራቃዊ ሞሱል ላይ በተደረገዉ ዉጊያ የድርሻችንን ተወጥተናል።አማካሪዎቻችን (ከኢራቅ ጦር) ጥንቅር ጋር ተካትተዋል።»

በኢራቅ የአሜሪካ ጦር አዛዥ ጄኔራል ስቴፈን ታዉንሴንድ።ባለፈዉ ወር ባግዳድን የጎበኙት የዩናይትድ ስቴትስ መከላከያ ሚንስትር ጄምስ ማቲስም ይሕንኑ አረጋግጠዋል።ማቲስ በ1991 አሜሪካ መራሹ ሕብረ ብሔር ጦር ኢራቅን ሲወጋ የአንድ የባሕር ሐይል ብርጌድ  አዛዥ ነበሩ።በ2003 የአሜሪካ ጦር ኢራቅን ለመዉረር

ሲዘጋጅ ወረራዉን በመቃወም ለያኔዉ መከላከያ ሚንስትር ለዶናልድ ራምስፌልም አስተያየት ከሰጡ  ስምንት ከፍተኛ የጦር ጄኔራሎች አንዱ ነበሩ።እርግጥ ነዉ የያኔዉ ጄኔራል እንደ ሌሎቹ ሰባት ባልጀሮቻቸዉ ወረራዉን በይፋ አልተቃወሙም ነበር።ጡረታ ከወጡ በኋላ በሰጡት አስተያየት ግን ወረራዉን «የስልት ስሕተት» ብለዉታል።ዘንድሮ እንደ መከላከያ ሚንስትር ባግዳድን ሲጎበኙ ግን ስልታዊዉ ስሕተት የሚታረምበት ሥልት ይኑር-አይኑራቸዉ ያሉት ነገር የለም።የነበረዉ ጦርነት ይቀጥላል እንጂ።

«በከተማይቱ ዉስጥ ሥለሚደረገዉ ጥቃት ዝርዝር ዉስጥ መግባት አልፈልግም።በዉጊያዉ ለሚሳተፉት ወታደሮች እተዋለሁ።ይሁንና በዉጊያዉ በቅርብ እንደምንሳተፍ መግለፅ እወዳለሁ።የአሜሪካ ወታደሮች ተሳትፎ በምስራቃዊ ሞሱል በነበረዉ ጥቃት እንደነበረዉ ይቀጥላል።የተባባሪዎቹ መንግሥታት ጦርም ይሕን ዘመቻ በቅርብ እየደገፉ ነዉ።አይሲሲን ለማጥፋት የምናደርገዉን ጥረት እናፋጥናለን።»

ዩንይትድ ስቴትስን ከነባር ጠላትዋ ኢራን፤ በአሸባሪነት ከምትወነጅለዉ ሒዝቡላሕ ጋር ባንድ ግባር ያሰለፈዉ የሞሱል ዉጊያ እንደቀጠለ ነዉ።አራተኛ ወሩን የያዘዉን ዉጊያ በመሸሽ ከግማሽ የሚበልጠዉ የከተማይቱ ነዋሪ ወደ ሌላ ሥፍራ ተሰድዷል።ከ750 ሺሕ የሚበልጥ ሕዝብ ግን አሁንም ከተማይቱን ለቅቆ መዉጣት አልቻለም።

የኢራቅ  እና የዩናይትድ ስቴትስ መንግሥታት አሸባሪዉ ቡድን የሞሱልን ነዋሪዎች አንደ ሰብአዊ ጋሻ እየተጠቀመባቸዉ ነዉ በማለት ይወነጅላሉ።የባግዳድ መሪዎች እና የዋሽግተን ደጋፊዎቻቸዉ፤ አሸባሪዉ ቡድን ሰላማዊ ሰዎችን በመያዣ አለያም በሰብአዊ ጋሻነት እንደሚጠቀምባቸዉ ለማወቅ የሞሱል ጥቃት እስኪከፈት የጠበቁበት ምክንያት በርግጥ እንቆቅልሽ ነዉ።

የሞሶል ሕዝብ ግን እያለቀ-እየተሰደ የተረፈዉ መዉጪ እየፈለገ ነዉ።የኢራቅ መንግስት ጦርና ተባባሪዎቹ በቅርቡ በተቆጣጠሩት በከተማይቱ ምሥራቃዊ ክፍል የሚኖረዉ ሕዝብ ዛሬም ከሞት እና ከሽብር ሥጋት አለመላቀቁ ነዉ ግራዉ።

ባለፈዉ ሳምንት የኢራቅ

መንግስት ጦር አዛዦች በሚያዘወትሩት ምግብ ቤት ዉስጥ አንድ አጥፍቶ ጠፊ ባፈነዳዉ ቦምብ አስር ሰዎች ተገድለዋል።ከሰላሳ በላይ ቆስለዋል።ከአጥፍቶ ጠፊ ቦምቦች በተጨማሪ የአሜሪካ ሰዉ አልባ አዉሮፕላኖች በሚሳዬል፤የኢራቅ ጦርና አይሲስ ተዋጊዎች በሞርታር፤ አነጣጥሮ ተኳሾች በጥይት፤ምሥራቃዊ ሞሱልን እየቀጠቀጡት ነዉ።

ከኢራቅ ጦር አዛዦች አንዱ ጄኔራል ፋላሕ አል ኦቤይዲይ ትናንት እንዳሉት ግን መላዋ ሞሱል ነፃ ስትወጣ ሁሉም ሰላም ያገኛል።መላዉ ሞሱልን ነፃ ለማዉጣት ደግሞ ጦራቸዉ አዲስ ጥቃት ጀምሯል።

«የልዩ ዘመቻዉ ጦር  ሁለተኛ ብርጌድ ዛሬ በደቡባዊ ቀጠና በአል ሰሞድ ግንባር አዲስ ጥቃት ከፍቷል።ወታደሮቹ በዋዲ አል ሐጀር እና በባግዳድ አዉራ ጎዳና በኩል አድርገዉ አል-ሰሞንድን ለመቆጣጠር ተንቀሳቅሰዋል።ኢንሻአላሕ፤ በጥቂት ሰዓታት ዉስጥ አል-ሰሞንድን ተቆጣጥረን ወደ አል ሞንሱር እናመራለን።»

በሞሱል ዉጊያ የኢራቅ መንግሥት ከ70 ሺሕ በላይ እግረኛ እና ሜካናይዝድ ጦር አዝምቷል።ሰሜናዊ ኢራቅ ላይ  የመንግስት ዉስጥ መንግሥት የመሰረቱት ኩርዶች ፔሽ ሜርጋ ከሚሉት ጦራቸዉ አርባ ሺሕ አሰልፈዋል።የኢራንና የሒዝቡላሕ ሚሊሺዎች፤ የአሜሪካና የሌሎች ምዕራባዉያን ሐገራት ጦር ብዛት በዉል አልተነገረም። ከሁለት እስከ አራት ሺሕ የሚገመቱ የአይሲስ ተዋጊዎች ሞሱል ዉስጥ መሽገዋል ተብሎ ይገመታል።ዉጊያዉ ቀጥሏል።

 

ነጋሽ መሐመድ

አርያም ተክሌ

 

 

 

Audios and videos on the topic