ኢራቅ የሞት፤ሥደት፤ የጥፋት ምድር | ዓለም | DW | 18.08.2014
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

ዓለም

ኢራቅ የሞት፤ሥደት፤ የጥፋት ምድር

ዲክስር ፊልክንስ በቅርቡ እንደፃፉት «ጅአፈሪን ልታስወግደዉ ትችላለሕ» ጠየቁ አሉ ቡሽ።«ምንገዶኝ» የአምባሳደሩ መልስ ነበር።ኢራቅ ሉአላዊት ሐገርናት ተብሎ የለም።ሉአላዊነቷን የሰጧት የሾሙላትን መሪ ሲያስወግዱባት ወይም የሚሹትን ሲሾሙባት ግን ሉዓላዊነቷን መዳፈር አይደለም።ጅአፈሪ ተወገዱ።ኑሪ አል-መሊኪይ ተተኩ።ባለፈዉ ሳምንት ማሊኪይ ተወገዱ።

ሕዳር-አጋማሽ 2003 (ዘመኑ በሙሉ እንደ ጎሮጎሮሳዉያኑ አቆጣጠር ነዉ) ባግዳድ

«የሳዳም ሎሌዎችን በማሸነፋችሁ፤ የኢራቅ ሕዝብ በሠላምና በነጻነት ይኖራል።»የቀድሞዉ የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዝዳናት ጆርጅ ደብሊዉ ቡሽ-ኢራቅ ላሰፈሩት ጦራቸዉ።እና ተብሎ ነበር።ከአሥራ-አንድ አመት በኋላ-ነሐሴ አጋማሽ 2014፤ ዋሽንግተን።«የዘር መጥፋት እርምጃን ለመከላከል እና በየተራራዉ የተሸሸጉ ሰዎችን ለመርዳት ባተኮርንበት (ባሁኑ) ወቅት እንኳን ክርስቲያኖችን ጨምሮ በርካታ ኢራቃዉያን ከየቤታቸዉ እንዲስሰደዱ እየተገደዱ ነዉ።»

ያሁኑ የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዝዳናት ባራክ ኦቦማ።ይሕም ተባለ።የግራ-አጋቢ ሁነት ምድር፤ የግራ አጋቢ መልዕቅት ሰበብ።የአዛኝ እልቂት-ጥፋት ሐገር።ኢራቅ።

ሩሲያ የሶሪያን ፕሬዝዳንት የበሽር አል-አሰድን መንግሥት መደገፏ-ምዕራባዉያን እንደሚሉት የሶሪያዉን ጦርነት ለማስወገድ የጋራ-ዓለም አቀፍ እርምጃ እንዳይወሰድ ትልቅ እንቅፋት ነዉ።የዋሽንግተን ብራስልስ መንግሥታት፤ የሪያድ ቀጠር ነገሥታት የሶሪያን መንግሥት የሚወጉ አማፂያንን ማስታጠቅ ማደራጀታቸዉ ግን በምዕራባዉያን መመዘኛ ተገቢ-ፍትሐዊም ነዉ።

ሩሲያ ምሥራቃዊ ዩክሬን የሸመቁ አማፂያንን መርዳቷ-ከዋሽግተን ብራሥልስ እንደሚሰማዉ ወንጀል ነዉ።የዩክሬንን ሕዝብ የሚያጫርስ ትልቅ ወንጀል።ለዚሕ «ወንጀል» ሩሲያን በተደጋጋሚ ማዕቀብ መቅጣት አስፈላጊ ትክክልም ነዉ።ISIS የተሰኘዉን የኢራቅ አማፂ ቡድንን የሚወጉትን የኢራቅን መንግሥትና የኩርድ ጦርን ማስታጠቅ፤ መርዳት፤ከሁለቱ ሐይላት ጋር አብሮ አማፂዉን መዉጋት ግን ፕሬዝዳንት ኦባማ እንዳሉት ሕጋዊ፤ ተገቢ፤ የፀረ-ሽብር ትግል አካልም ነዉ።

«እነዚሕ አሸባሪ ሐይላት ዘላቂ ከለላ እንዳያገኙ ከአሸባሪዎቹ ጋር ለሚዋጉት ለኢራቅ መንግሥትና ለኩርድ ሐይላት ወታደራዊ ድጋፍና ምክር መስጠታችንን እንቀጥላለን።እየበረታ የመጣዉን የኢራቅን ሠብአዊ ቀዉስ ለማቃለል ከዓለም አቀፉ ማሕበረሰብ ጋር መሥራታችንን እንቀጥላለን።»

ኢራቅ ላይ አሸባሪ የሆኑት ሀይላት ሶሪያ ዉስጥ ዩናይትድ ስቴትስ በምታስተባብረዉ ዓለም ከሚደገፉት አማፂያን ጋር ሆነዉ የበሽር አል-አሰድን መንግሥት ይወጋሉ።

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዲፕሎማቶች፤ ገለልተኛ የሕግ ባለሙያዎች ወይም የፖለቲካ አዋቂዎች ቢጠየቁ በየዝነዉ ዘመን «ኩርዲስታን» የሚባል ነፃ ሐገር ወይም መንግሥት ከዓለም ማሕበር፤ ድርጅት ወይም ካርታ የለም ባይ ናቸዉ።

ሰሜናዊ ኢራቅ ኤርቤል ላይ ግን ከ1992 ጀምሮ የራሱን ባንዲራ-የሚያዉለበልብ ሐገር-አከል አስተዳደር፤ በፕሬዝዳንት የሚመራ፤ በተሟላ ካቢኔ የሚተዳደር፤ በምክር ቤት የተዋቀረ አስተዳደር አለ።ይሕ አስተዳድር የባግዳድ ማዕከላዊ መንግሥት ከሚመራዉ ጦር በቁጥርም፤ በአደረጃጀት በፅናትም የጠነከረ ጦር አለዉ።ጦሩ ፔሽሜርጋ-ይባላል።ሞትን ተጋፋጭ እንደማለት ነዉ ፍቺዉ።በኤርፉርት-ጀርመን ዩኒቨርሲቱቲ የፖለቲካ ጥናት ፕሮፈሰር ፈርሕድ ሰይደር እንደሚሉት ጦሩ በሁለት ይከፈላል።

«ከ1991 ጀምሮ የሁለቱን ቡድናት ወታደሮች ለማዋሐድ ጥረት ሲደረግ ነበር።ይሁንና የፓሪቲዎቹ ፍላጎት አለመጣጣምና የየግል ጥቅምም እንቅፋት በመሆኑ እስካሁን ድረስ ሁለት ፔሽሜሪጋዎች አሉ።የመጀመሪያዉ የኩርዲስታን ዴሚሞክራሲያዊ ፓርቲ የሚመራዉ ፔሽሜርጋ ሲሆን ከ30 ሺሕ እስከ 40 ሺሕ የሚገመት ተዋጊዎች አሉት።ሁለተኛዉ የኩርዲስታን አርበኞች ሕብረት የሚመራዉ ጦር ነዉ።25 ሺሕ ያሕል ተዋጊዎች አሉት።»

ሌሎች የፖለቲካ ተንታተኞች ግን አጠቃላዩን የፔሽምርጋን ጦር ቁጥርን 100 ሺሕ ያደርሱታል።የታጠቀዉ ጦር መሳሪያ ግን ዘመን ያለፈበት የቀድሞዋ ሶቭየት ሕብረት ሥሪት ነዉ።ሁለቱን ጦር የሚመሩት የፖለቲካ ፓርቲዎች በ1992 ሰሜናዊ ኢራቅ ላይ ነፃ አከል መንግሥት እንዲመሠረቱ የረዱ፤ያግባቡና ያስታረቁት የዩናይትድ ስቴትስ፤ የብሪታንያ የፈረንሳይ መንግሥታት ናቸዉ።

በመጀመሪያዉ የፋርስ ባሕረ-ሥላጤ ጦርነት የተዳከመዉ የያኔዉ የኢራቅ መንግሥት ጦር አዲስ አስተዳድር የመሠረቱትን የኩርድ ደፈጣ ተዋጊዎችን እንዳያጠቃ ማዕቀብ ያስጣሉበት፤ ጦሩን እና ተዋጊ ጄቶቹን እንዳያንቀሳቅስ ሰሜናዊ ኢራቅን ከበረራ እግድ ቀጠና ያስደነገጉትም ሰወስቱ ሀያላን መንግሥታት ነበሩ።

አሜሪካ መራሹ ጦር ኢራቅን ዳግም ወርሮ የቀድሞዉን የኢራቅ ፕሬዝዳንት የሳዳም ሁሴንን መንግሥት ካስወገደ በኋላ የባግዳድን ቤተ-መንግሥት ኤርቢል ላይ ነፃ አከል መንግሥት ከመሠረቱት ለአንዱ ለጀላል ጠላባኒን አስረክቦ-በፕሬዝዳትነት ሥልጣን እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ የባግዳድን መንግሥት ሲመሩ ነበር።ይሁንና ኩርዶች ጠለባኒ የሚመሩት ማዕከላዊ መንግሥት አባል እንዲሆኑ ወይም በተቃራኒዉ ሙሉ ነፃነት እንዲቀዳጁ-የዋሽግተን ብራስልስ መንግሥታት አልፈቀዱላቸዉም።

አሜሪካኖች ባግዳድ ላይ በተከታታይ በሚሾሟቸዉ ገዢዎች የተገለሉት የሱኒ ሙስሊሞችን ባብዛኛዉ ያቀፈዉ የኢራቅና የላቬንት (የሶሪያ) እስላማዊ መንግሥት ISIS የተሰኘዉ ፅንፈኛ አማፁፂ ቡድን ምዕራባዊና ማዕከላዊ ኢራቅን ሲቆጣጠር ግን ኩርዲስታን አስተዳደር ከነፃ መንግሥት እኩል እርዳታዉ ይንቆረቆርለት ገባ።ርዕሠ-ከተማ ኤርቢል የዓለም ሐያላንን ዲፕሎማቶች እየተቀበለች ትሸኝ ይዛለች።

ከሁሉም በላይ እሁለት የተገመሠዉ የኩርዶች ጦር ፅንፈኛዉን አማፂ ቡድን ISISን እንዲወጋ የሥለላ፤የጦር መሳሪያ፤እና የተዋጊ ጄቶች ድጋፍ እየጎረፈለት ነዉ።ግራ-አጋቢ ግን የፈጠጠ ሐቅ።2011 ፕሬዝዳንት ባራክ ኦባማ።

«በዘጠኝ ዓመታት ለመጀመሪያ ጊዜ ኢራቅ ዉስጥ የሚዋጋ የአሜሪካ ወታደር የለም።የኢራቅ ጦርነት አብቅቷል።»

ፕሬዝዳንት ባራክ ኦቦማ-በቀደም።«ኢራቅ ዉስጥ በከፈትነዉ ወታደራዊ ዘመቻ ጥሩ ዉጤት ማስመዝገባችን እንደቀጠለ ነዉ።በተራራዎቹ አካባቢ ያለዉ ሁኔታ በእጅጉ ተሻሽሏል።አሜሪካዉያን ባደረግነዉ ጥረት ሊኮሩ ይገባል።ምክንያቱም በጦራችን ክሒል፤ሙያዊ ብቃትና በሕዝባችን ለጋስነት በሲንጃር ተራራ ላይ የነበረዉን የISIS ከበባ ሠብረናል።»

የኩርዶቹ ፔሽሜርጋ ጦር ከምድር፤የአሜሪካ ተዋጊ ጄቶች ከሠማይ ተቀናጅተዉ የISIS ሚሊሺያዎችን እየወጉ ነዉ።ለፔሽሜርጋ ተዋጊዎች ዘመናይ ጦር መሳሪያ በግልፅ በማስታጠቅ ከአዉሮጳ ሕብረት አባል ሐገራት ፈረንሳይ የመጀመሪያዋ ሆናለች።ጀርመንም ፈረንሳይን መከተሏ እንደማይቀር አንዳድ ምንጮች እየተናገሩ ነዉ።

ሰሞኑን ባግዳድና ኤርቢልን ጎብኝተዉ የተመለሱት የጀርመኑ ዉጪ ጉዳይ ሚንስትር ፍራንክ ቫልተር ሽታይን ማየር ግን ኩርዶችን የማስታጠቁን ጉዳይ በዲፕሎማሲ ቋንቋ አደባብሰዉ ነዉ ያለፉት።

«በዚሕም ምክንያት ሁለት ጉዳዮች መከናወን አለባቸዉ የመጀመሪያዉ ሰብአዊ ርዳታ መስጠት አለብን።ርዳታ ማድረስ አለብን።ይሕ አስቸኳይ ነዉ።ሁለተኛዉ ከፕሬዝዳንት ባርዛኒ (የኩርዲስታን መሪ) ጋር ያደረግነዉን ዉይይት በመጠቀም በአስቸኳይ መዉሰድ ያለብትን ዉጤማ እርምጃ አጢነን ከሌሎች አዉሮጳዉያን ጋር በመሆን ኩርዶች ISISን ለማቋቋም የሚያደርጉትን ትግል ለመደገፍ በኛ በጀርመን በኩል ማድረግ የምንችለዉን እንወስናለን።»

አሜሪካ መራሹ ጦር ኢራቅን ሙሉ በሙሉ መቆጣጠሩ በተነገረ ማግሥት ተመሥርቶ የነበረዉን የአሜሪካኖች ጊዚያዊ አስተዳደር የሚመሩት አምባሳደር ፖዉል ብሬሜር ሥልጣናቸዉን ለኢራቃዊዉ ፖለቲከኛ ለኢያድ አላዊ ሲያስረክቡ ኢራቅ ሉአላዊነቷ ተመለሰላት ተብሎ ነበር።ጥር 2004 የጠቅላይ ሚንስትር አላዊ መንግሥት ሐገሪቱን ማረጋጋት በቅጡ ማስተዳደር ም አልቻለም ተብሎ ባመት ከመንፈቁ ከሥልጣን ተወገድ።ግቦት 2005።

አላዊን የተኩት ጠቅላሚንስትር ኢብራሒም አል ጀአፈሪ ከአላዊ የተለዩ አይደሉም በማለት በዋሽግተን ፖለቲከኞች ለመብጠልጠል ጊዜ አልፈጁም ነበር።በኢራቅ የአልቃዳ ቅርንጫፍ የሚባለዉ ቡድን ባንድ በኩል፤ የሺዓ ሚሊሺያዎች አመፅ በሌላ በኩል የአሜሪካ ጦርንና ለአሜሪካ ያደሩ ኢራቃዉያን ፖለቲከኞችን ሲያዋክቧቸዉ ፕሬዝዳንት ቡሽ ኢራቅ ለሚገኙት አምባሳደራቸዉ ለዘልማይ ኻሊልዛድ ስልክ ይደዉላሉ።

ዲክስር ፊልክንስ በቅርቡ እንደፃፉት «ጅአፈሪን ልታስወግደዉ ትችላለሕ» ጠየቁ አሉ ቡሽ።«ምንገዶኝ» የአምባሳደሩ መልስ ነበር።ኢራቅ ሉአላዊት ሐገርናት ተብሎ የለም።ሉአላዊነቷን የሰጧት የሾሙላትን መሪ ሲያስወግዱባት ወይም የሚሹትን ሲሾሙባት ግን ሉዓላዊነቷን መዳፈር አይደለም።ጅአፈሪ ተወገዱ።ኑሪ አል-መሊኪይ ተተኩ።2006።ባለፈዉ ሳምንት ማሊኪይ ተወገዱ።ተረኛዉ ሐይደር አል-አባዲ ናቸዉ።

ሰሜኗን ኩርዶች፤ምዕራብና መሐሏን-ሱኒዎች፤ ደቡብዋን ሺአዎች ለሰወስት የተቃረጧት ጥንታዊቷ፤የተፈጥሮ ሐብታሚቱ፤ ታሪካዊቷ ሐገር ግን እንደ አንድ ሐገር የመቆሟ እዉነት ከታሪክ መዝክር ሊከረቸም ከመጨረሻዉ መጀመሪያ ላይ ነዉ።አል-አባዲ ማንን እንዴት ያስተዳደሩ ይሆን?

ነጋሽ መሐመድ

አርያም ተክሌ

Audios and videos on the topic