ኢራቅ ውስጥ በኢጣልያውያን ላይ የተጣለው ጥቃት | የጋዜጦች አምድ | DW | 13.11.2003
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

የጋዜጦች አምድ

ኢራቅ ውስጥ በኢጣልያውያን ላይ የተጣለው ጥቃት

በኢራቅ በተሠማራው የተጓዳኞቹ ጦር ኃይል እስካሁን ከተካሄደው ጥቃት ሁሉ ትናንት በናዚርያ ከተማ በኢጣልያውያን ላይ የተጣለው እጅግ የከፋ ነበር። በጥቃቱ አሥራ ስምንት ኢጣልያውያን ፖሊስ ወታደሮች እና በርካታ የኢራቅ ዜጎች ተገድለዋል፤ ብዙዎችም ቆስለዋል። ይኸው አሳዛኝ ጥቃት፡ ጠቅላይ ሚንስትር ቤርሉስኮኒ የሚመሩት የኢጣልያ መንግሥት በሚከተለው የኢራቅ ፖለቲካ ላይ ያረፈውን ግፊት፡ በወቅቱ ይበልጡን እንዲጠናከር አድርጎታል። እንደሚታወቀው፡ ኢጣልያ ኢራቅ ውስጥ ከዩኤስ አሜሪካ ጦር ኃይላት ጎን ለመቆም የወሰደችውን ውሳኔ ብዙው የኢጣልያ ሕዝብ አልደገፈውም።

ምንም እንኳን ባለፉት ሣምንታት ኢራቅ ውስጥ የሸማቂዎች ጥቃት ቢበዛም፡ ኢጣልያውያኑ ጥቃቱ ወታደሮቻቸውን እንደማይነካ ተስፋ አድርገው ነበር። ኢጣልያውያኑ ፖሊሶች የሠፈሩባት የደቡብ ኢራቅ ከተማ፡ ናዚሪያ እስከትናንት ድረስ አስተማማኝ ቦታ ሆና ነበር የታየችው። እንዲያውም፡ የኢጣልያ መከላከያ ሚንስትር አንቶንዮ ማርቲኖ ኢራቅ ውስጥ ከሁሉም ከተሞች መካከል ናዛሪያ የተረጋጋች መሆንዋን ነበር ከጥቂት ጊዜ በፊት ያስታወቁት። ኢጣልያውያኑ ፖሊስ ወታደሮጭ የተገደሉበት ድርጊት የሀገሪቱን ሕዝብ ማሳዘን ብቻ ሳይሆን አብዝቶም ነው ያስቆጣቸው። አንዳንዶች ለዚሁ የሀገሮቻቸው የጦር ኃይል አባላት ግድያ ኃላፊነት የተጓደለው አሠራር ተከትለዋል ያሉዋቸውን የኢጣልያ መንግሥት ባለሥልጣናትን ተጠያቂ ሲያደርጉ፡ ሌሎጭ ደግሞ የኢራቅን መልሶ ግንባታ ለመርዳት የሄዱት ዜጎቻቸው የተገደሉበትን ድርጊት በፍፁም ሊረዱት አልቻሉም።

ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት ፍፃሜ በኋላ ይህን ይህል ኢጣልያውያን ፖሊስ ወታደሮች በጦር ሂደት ወቅት ሲገደሉ የትናንቱ የመጀመሪያ ጊዜ ነበር። የጠቅላይ ሚንስትር ሲልቪዮ ቤርሉስኮኒ መንግሥት ባለፉት የክረምት ወራት ነበር ሦስት ሺህ የሀገራቸውን ወታደሮች ወደ ኢራቅ የላከው። በዚያን ጊዜ ተቃውሞው ወገን ወታደሮቹ ካለ ተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ተልዕኮ በኢራቅ ይሠማሩ የተባለበትን ውስኣኔ አጥብቆ ነበር የተቃወመው። ይሁን እንጂ፡ የትናንቱ የናዛሪያ ጥቃት የተለያዩትን የሀገሪቱን ፓርቲዎች ያቀራረበ ሆኖ ነበር የተገኘው። ጊዜው የብሔራዊ አንድነትና የሀዘን እንጂ፡ የፖለቲካ ንትርክ መምሪያ አለመሆኑን የአንድ የተቃውሞው ቡድን መሪ ፍራቼስኮ ሩቴሊ በማስረዳት፡ በወቅቱ ኢጣልያውያኑ በጠቅላላ ከቀሪዎቹ የማቾች ቤተሰብ ጎን መቆሙን የሚያረጋግጥበት ጊዜ መሆኑን ገልፀዋል። የግራ ክንፉ የተቃውሞ ቡድን ብቻ ነው የፖሊስ ወታደሮቹን ግድያ መንሥዔ በማድረግ በቤርሉስኮኒ መንግሥት ላይ ግፊቱን ያጠናከረው። የኢጣልያ መንግሥት አጠራር አሳፋሪ ነው ያሉት የኮሚንስቱ ፓርቲ መሪና የቀድሞው የፍትሕ ሚንስትር አልቪየሮ ዴሊብሬቶ የሀገራቸው ወታደሮች ከኢራቅ እንዲወጡና የኢጣልያ መንግሥት ሥልጣኑን ባጣዳፊ እንዲለቅ ጠይቀዋል።

ምንም እንኳን የኢጣልያ መንግሥት በኢራቅ የጦር ኃይል አባላትዋ የጥቃት ሰለባ ቢሆኑበትም፡ ቤርሉስኮኒ የሚከተሉትን የኢራቅ ፖለቲካ ወደፊትም ሳይቀይሩ እንደሚቀጥሉበት አስታውቀዋል። እርግጥ፡ የተቃውሞ ቡድናት ለብሔራዊ አንድነት ሲሉ በውቅቱ ሒስ ከመሰንዘር ቢቆጠቡም፡ ቤርሉስኮኒ ከባድ የወደፊት ጊዜ እንደሚጠብቃቸው አላጡትም። የኢጣልያ መንግሥት የኢራቅ ጦርነት በይፋ አበቃ ከተባለ በኋላ ወታደሮቹን ወደ ኢራቅ በላከበት ውሳኔው፡ የምትከተለውን መፍቀሬ ዩኤስ አሜሪካ ፖሊሲዋን ለማጉላት ነው የፈለገው፤ ከዚህ በተረፈም በኢራቅ መልሶ ግንባታ የተሠማሩት የኢጣልያ ወታደሮች የጥቃት ሰላባ ይሆናሉ ብለው አልገመተም ነበር፤ ግን፡ የናዚሪያ ጥቃት እክል ባላጣው የኢጣልያ መንግሥት ላይ ተጨማሪ ችግር ነው የጣለበት።