ኢራቅ ሌላ አመት-ሌላ ቃል-ሌላ ተስፋ ግን ሌላ ቦምብ | ዓለም | DW | 26.10.2009
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ዓለም

ኢራቅ ሌላ አመት-ሌላ ቃል-ሌላ ተስፋ ግን ሌላ ቦምብ

«ፖለቲከኞች በተወዛገቡ ቁጥር» ነገረዉ ለጋዜጠኛዉ «ገዳይ ቦምብ ይልኩልናል።» አለ። እያለኸ። የባግዳዱ ምክር ቤት አባል-መሐመድ አል-ሩቢ ግን ተቃራኒዉን ነዉ-የሚሉት።

default«ለኢራቅ ሕዝብ መልዕክት አለኝ።በሰብአዊ ክብርና በነፃነት ላይ ተመስርተሕ ታላቅ ሐገርሕን ዳግም ለመገንባት የምትጠቀምበት አጋጣሚ ተፈጥሮልሐል።የሳዳም ሁሴይን ስርዓት ለእስከ ዘላለሙ ተወግዷል።»

ፕሬዝዳንት ጆርጅ ዳብሊዉ ቡሽ-በድል ማግስት-ሁለት ሺሕ ሰወስት (ዘመኑ በሙሉ እንደ አዉሮጳዉያኑ አቆጣጠር ነዉ።በስድስተኛ- አመት ከንፈቁ ትናንት እንደገና ቦምብ።
ለምንና እና እንዴት-ያፍታ ዝግጅታችን ትኩረት ነዉ-አብራችሁኝ ቆዩ።
-----------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------


የሆነዉ-ሆነ። መሐመድ ራዲሒ-እህቱ እዚያ እንደነበረች ያዉቃል።ከሚሰራበት የፍትሕ-ሚኒስቴር ሕንፃ ተንደርድሮ ወረደ።ወጣም-እህቱን ፍለጋ።የደም ከል-ባለበሰዉ፥ የፅዳጅ-ዉሐ ፍሳሽ ባጨቀየዉ የህንፃ ፍርስራሽ መሐል-የተሸነቀሩ፥የተበታተኑ አስከሬን-የአካላት ቁርጥራጮችን-እያገለባጠ-ይበረብራል።እሕቱ የለችም።«ፀጥታ አስከባሪዎቹ-የት ነበሩ።» ጠየቀ መሐመድ።

አጠገቡ የነበረዉ ግን የሚለዉን ሰምቶ-የሚያሰማ እንጂ መልስ ሊሰጥ የማይቻለዉ-ሰዉ ነበር።ጋዜጠኛ።ቀጠለ-መሐመድ፥-«መንግሥት ፈንጂ የጫኑ መኪኖችን ለይቶ-የሚያሳይ ልዩ መሳሪያ ገዝቷል።ግን አይሰሩም።ፀጥታ አስከባሪዎቹም ሥራቸዉን በአግባቡ አልተወጡም»-እያለ።

እሁድ የስራ-ቀን ነዉ።መሐመድ እና ብዙ ብጤዎቹ በየመስሪያ ቤቱ፥ሌሎችም-በያሉበት ደፋ ቀና ይሉ ይዘዋል።ባግዳድ-ረፍዷል።የጭነት መኪናዉ አንድ ቶን ፥ አዉቶሞቢሉ ሰባት መቶ ኪሎ ግራም ጭኖ።-ርዕሠ-ከተማ ባግዳድን የሚቆጣጠረዉን በብዙ ሺሕ የሚቆጠር ጦርና ፀጥታ-አስከባሪዎችን ግራ-ቀኝ ገምሰዉ ተከታትለዉ ልዩ-ጥበቃ ከሚደረግበት አረብጓዴዉ ቀበሌ ደረሱ።

ጠቅላይ ሚንስትር ኑሪ አል-መሊኪ እና ፕሬዝዳት ጀላል ጠለባኒ እንደ ብዙ የፖለቲካ ወዳጅ-አንጣዎቻቸዉ ሁሉ ልዩ ትኩረታቸዉ የምርጫ-ሕግ ነዉ።ለመጪዉ ጥር የታቀደዉ ምርጫ የሚመራበት ሕግ ይዘት የኢራቅ ፖለቲከኞችን ማወዛገብ ከጀመረ-ሳምንታት አስቆጠረ።

ሺዓ-መራሹ የአል መሊኪ መንግሥት ባለሥልጣናት በዉዝግብ-ክርክሩ አሸናፊ-የሚሆኑበትን ብልሐት ለመቀመር-ስብሰባ ላይ ነበሩ።የባግዳድ ፖለቲከኞች-ሲከራከሩ-ባግዳድ ላመት ግብሯ-ዜጎችዋን ጫዳ አደረገች።በቦምብ።

አዲል ሳሚ-የአንቡላንስ መኪያናዉን እያከነፈ-እያስጓራ እስፍራዉ ደረሰ።መሐመድ ራዲሒ የሚሰራበት የፍትሕ ሚንስቴር ሕንፃ እና የከተማ አስተዳደር ሚንስትር-ሕንፃ በተገተሩበት መሐል ያለዉ አካባቢ-በጢስ ፥ጠለስ ታጥኗል።ሰዉ ያዉ እንደመሐመድ ይተራመሳል።አዲል-እንደ ብዙ ባልደረቦቹ ሁሉ ከአካላት ብጥቅጣቂ፥ ከአስከሬን ዝርር፥ ከፍርስራሽ-ክምር፥ መሐል ቁስለኛዉን-ለመለየለት ይራወጥ ያዘ።
«ፖለቲከኞች በተወዛገቡ ቁጥር» ነገረዉ ለጋዜጠኛዉ «ገዳይ ቦምብ ይልኩልናል።» አለ። እያለኸ። የባግዳዱ ምክር ቤት አባል-መሐመድ አል-ሩቢ ግን ተቃራኒዉን ነዉ-የሚሉት።

«የአጥፍቶ ጠፊዎቹ ኢላማ የመንግሥት መስሪያ ቤት ሕንፃዎች መምታት ነዉ።ይሕ-ጥቃቱ ባጠቃላይ በፖለቲካ ሥርዓታች ላይ ያነጣጠረ ለመሆኑ ግልፅ ምሥክር ነዉ።»

የቀድሞዉ የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዝዳት ጆርጅ ደብሊዉ ቡሽ እና ተባባሪዎቻቸዉ ኢራቅን ካስወረሩበት ከመጋቢት 2003 ጀምሮ-በአጥፍቶ ጠፊ ቦምብ፥ በተፈላሚ ሐይላት ጦር የተገደለዉን ሠላማዊ ሰዉ ቁጥር በትክክል የቆጠረዉ በርግጥ የለም።የብዙዎች ግምት ግን ሲያንስ ከግማሽ-ሚሊዮን ሲበዛ ፣- ከአንድ ሚሊዮን በላይ ይደርሳል-የሚል ነዉ።

ትናንት በሟቾች ቁጥር አንድ መቶ ሐምሳ-አምስት ሰዉ ተጨመረበት።በቁስለኞች ደግሞ ስድስት መቶ።ኢራቅ የተወረረችበት ስደስተኛ አመት ባለፈዉ መጋቢት ሲዘከር-አዲሱ የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዝዳት ባራክ ኦባማ-የአሜሪካን ጦር ቀስ በቀስ ከኢራቅ ለማስወጣት የነበራቸዉን እቅድ ይፋ አድርገዉ ነበር።

የአሜሪካ ጦር አስከቅድሞ ከኢራቅ ከተሞች፥ ቀጥሎ ከመላዉ ኢራቅ እንዲወጣ ለብዙዎች አሳማኝ ምክንያት የነበረዉ የአሽባሪዎች የቦምብ አደጋ መቀነሱ ነበር።ፕሬዝዳት ኦባማ ያኔ እንዳስታወቁትም አሸባሪዎች የሚያደርሱት ጥቃት በርግጥም ቀንሶ ነበር።የኢራቅ ፖለቲከኞች አመራርም ተጠናክሮ ነበር።

«ኢራቅ ዉስጥ አልፎ-አልፎ የሚጣሉት የቦምብ አደጋዎች አሳሳቢ መሆናቸዉን መገንዘብ አስፈላጊ ይመስለኛል።በአንፃራዊ ሲታይ ግን ለምሳሌ ካለፈዉ አመት ጋር ሲነፃፀር ግን የሰላማዊ ሰዎች ግድያና የሚጣሉት ቦምቦች ቁጥር አነስተኛ ነዉ።ሥለዚሕ በፊት እንደነበረዉ አይነት ከፍተኛ ግድያና ሁከት ብዙ አላያችሁም።የኢራቅ ፖለቲካዊ ሥርዓትም እየፀና እና በትክክል እየተንቀሳቀሰ ነዉ»

መሰለ-እንጂ በርግጥ አልሆነም።የትናንቱ-የባግዳድ ዉሎ ሁሉንም አፈረሰዉ ወይም መሰለ።አጥፍቶ ጠፊዎች በሁለት መኪኖች የተጫነዉን ቦምብ ያፈነዱት-ባለሐብቶች መዋዕለ ንዋያቸዉን ኢራቅ ዉስጥ ሥለሚያሰሩበት ሁኔታ ዋሽንግተን ዉስጥ በተነጋገሩ በሳልስቱ ነዉ።
የኢራቅ ፖለቲከኞች ደግሞ የምርጫ ሕግ ዉዝግባቸዉ ለማስወገድ ለመምከር እንደተሰበሰቡ ነዉ።የትናንቱን አደጋ የጣሉት ሐይላት አላማም-የኢራቅ ምክር ቤት እንደራሴ ማሕሙድ ኦስማን እንደሚገምቱት-የሁለቱን ስብሰባዎች አላማ ማደናቀፍ ነዉ።

«አንደኛዉ ከሰወስት ቀን በፊት ዋሽንግተን የተደረገዉ የባለሐብቶች ሥብሰባ ነዉ።(አጥፍቶ ጠፊዎቹ) ባለሐብቶቹ ወደ ኢራቅ እንዳይመጡ ሊነግሯቸዉ ያሰቡ ይመስላል።ሐገሪቱ አስተማማኝ አይደለችም።ፀጥታ አልሰፈነባትም-የሚል መልዕክት ለማስተላለፍ፣-ሁለተኛዉ ደግሞ ሕጉን የምርጫዉን ሕግ በተመለከተ ችግሩን ለማስወገድ ዛሬ ተደርጎ ለነበረዉ የፖለቲካ ምክር ቤት ስብሰባ መልዕክት ለማስተላለፍ ይመስላል።»

መልዕክቱ ሁለቱም-ወይም ሌላም ሊሆን-ላይሆንም ይችላል።አደጋዉ ግን በርግጥ ከባድ ነዉ።ኢራቅ ባለፈዉ ስድስት አመት ቦምብ-ፈንጂ በርግጥ ተለይቷት አያቅም።በሁለት አመት ዉስጥ ግን የትናንቱን ያክል-ሰዉ የገደለ-ያቆሰለ አደጋ ተጥሎ አያዉቅም።

ጠቅላይ ሚንስትር ኑሪ አል-መሊኪ ቦምብ ያረሰዉን አካባቢ ሲጎበኙ እንዳሉት አደጋዉን የጣሉት የአል-ቃኢዳ ጀሌዎችና ሳዳም ሁሴን ይመሩት የነበሩት የባዓዝ ፓርቲ ቅሪቶች ናቸዉ።ፕሬዝዳት ቡሽ የዛሬ ስድስት አመት ላይመጣ ሔደ-ያሉት የሳዳም ሁሴን ሥርዓት ዛሬም ከስድስት አመት በሕዋላ የኢራቅን ፀጥታና ደሕንነት-ማስጋቱ-ነዉ-በርግጥ አስገራሚ-አነጋጋሪም- ነዉ።

እንደራሴ-ማሕሙድ ኦስማን ግን ከጠቅላይ ሚንስትራቸዉ፥ ከባግዳዱ አስተዳዳሪ ከቡሽ፥ ምናልባትም ከኦባም ይልቅ የእሕቱ የጠፋችበትን-ወይም የአምቡላንሱን ሾፌር ስሜት ይጋራሉ።አደጋ ጣዩ-ማሊኪ ያሏቸዉ ወይም ሌላ ማንም-ይሆኑ-ይሆናል።አደጋዉ ለመጣሉ ከዋናዎቹ ምክንያት አንዱ ግን የፖለቲካዉ አለመረጋጋት ነዉ።

«ፀጥታችንን ለማስከበር የፖለቲካ መረጋጋት በጣም አስፈላጊ ነዉ።የፖለቲካ መረጋጋት ኬሌለሕ የፀጥታ መረጋጋት ሊኖርሕ አይችልም።መንግሥትና ምክር ቤቱ ችግሮቻቸዉን እንዲያስወግዱ የሚጠየቁትም ለዚሕ ነዉ።ይሕን ችግር አስወግደዉ የፀጥታዉን ችግር ሊያተኩሩበት ይገባል።የፀጥታዉ ችግር እስካሁን ትኩረት አልተሰጠዉም።»
ኢራቅ ሌላ አመት-ሌላ ቃል-ሌላ ተስፋ ግን ሌላ ቦምብ-ሌላ እልቂት እስከ መቼ-አይታወቅም።

dw,agenturen

ነጋሽ መሐመድ/አርያም ተክሌAudios and videos on the topic