ኢህአዴግ ጠቅላይ ሚኒስትር ለመምረጥ በሚቀጥለው ሳምንት ይሰበሰባል | ኢትዮጵያ | DW | 24.02.2018
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

ኢትዮጵያ

ኢህአዴግ ጠቅላይ ሚኒስትር ለመምረጥ በሚቀጥለው ሳምንት ይሰበሰባል

የኢትዮጵያ ህዝቦች አብዮታዊ ዲሞክራሲያዊ ግንባር (ኢህአዴግ) አዲስ ጠቅላይ ሚኒስትር ለመምረጥ በመጪው ሳምንት እንደሚሰበሰብ አንድ የኦህዴድ ባለስልጣን ገለጹ፡፡ ስብሰባው እንዲካሄድ ቀነ ቀጠሮ የተያዘው ለረቡዕ ነው ተብሏል፡፡

የኦሮሞ ህዝቦች ዴሞክራሲያዊ ግንባር (ኦህዴድ) የማዕከላዊ ኮሚቴ ጽህፈት ቤት የህዝብ አስተያየት እና ፐብሊሲቲ ዘርፍ ኃላፊ አቶ ካሳሁን ጎፌ ለፈረንሳይ ዜና አገልግሎት እንደተናገሩት በጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ ተተኪ ላይ ውሳኔ የሚሰጠው 180 አባላት ያሉበት የኢህአዴግ ምክር ቤት ነው፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ስልጣናቸውን ለመልቀቅ እንደሚፈልጉ ያስታወቁት ባለፈው ሳምንት ሐሙስ የካቲት 8 ቀን 2010 ዓ.ም ነበር፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከስልጣናቸው እንደሚነሱ ለወራት ሲነገር ቢቆይም የስልጣን መልቀቂያቸውን ያሳወቁት ፓርቲያቸው የመተማመኛ ድምጽ ከነፈጋቸው ከአንድ ቀን በኋላ እንደሆነ ስማቸው እንዳይገለጽ የጠየቁ አንድ ባለስልጣን ጠቅሶ የዜና ወኪሉ ዘግቧል፡፡

ከጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም የስልጣን መልቀቂያ በኋላ ስልጣኑን ለመረከብ የገዢው ግንባር አባል ፓርቲዎች ሲሻኮቱ መቆየታቸውን ዘገባው ጠቁሟል፡፡ ኦህዴድ ባለፈው ሐሙስ ዶ/ር አብይ አህመድን የድርጅቱ ሊቀመንበር አድርጎ የመረጠ ሲሆን ሹመቱም ለጠቅላይ ሚኒስትርነት እንዲወዳደሩ መንገዱን ለመጠርግ ነው ተብሎ ታምኖበታል፡፡ የኦህዴዱ አቶ ካሳሁን “ለጠቅላይ ሚኒስትር ደረጃ የሚሆን ዕጩ ተወዳደዳሪ ለማቅረብ ተዘጋጅተናል” ሲሉ ለዜና ወኪሉ ተናግረዋል፡፡ “የሁሉም ፓርቲዎች ፍላጎት ከሆነ ዶ/ር አብይ ይመረጣሉ” ሲሉም አክለዋል፡፡

በፌደራል ደረጃ በሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ሚኒስትርነት ያገለገሉት ዶ/ር አብይ ወደ ኦሮሚያ ክልል የተዘዋወሩት በጥቅምት 2009 ዓ.ም ነበር፡፡ በወቅቱ በምክትል ፕሬዝዳንትነት ማዕረግ የኦሮሚያ ክልል የከተማ ልማት እና ቤቶች ቢሮን በኃላፊነት እንዲመሩ ተሹመው ነበር፡፡ የዛሬ ስድስት ወር ደግሞ የኦህዴድ ጽህፈት ቤት ኃላፊነትን ተረክበው ሲሰሩ ቆይተዋል፡፡ ለጠቅላይ ሚኒስትርነት ይታጫሉ ተብሎ ስማቸው በተደጋጋሚ ሲነሳ የነበሩት አቶ ለማ መገርሳ ከኦህዴድ ሊቀመንበር ነት ወደ ምክትል ሊቀመንበርነት ተዛውረዋል። አቶ ለማ የኦህዴድን ሊቀመንበርነት ለዶ/ር አብይ ቢያስረክቡም በኦሮሚያ ክልል ፕሬዝዳትነታቸው ይቀጥላሉ። 

ተስፋለም ወልደየስ

ልደት አበበ

ተዛማጅ ዘገባዎች