አፍቓኒስታን ከቦን-ጉባኤ እስከ ቦን ጉባኤ | ዓለም | DW | 05.12.2011
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ዓለም

አፍቓኒስታን ከቦን-ጉባኤ እስከ ቦን ጉባኤ

የፕሬዝዳት ሐሚድ ካርዛይ የፀጥታ ጉዳይ አማካሪ ራንጊን ዳድፋር ስፓንታ ባለፈዉ ቅዳሜ እንዳሉት ቦን በአስር አመት ለሁለተኛ ጊዜ ያስተናገደችዉ ጉባኤ ለጀርመንና ለአፍቃኒስታን ትብብር ጥንካሬ አብነት፥ ለአፍቃኒስታን ሕዝብ ደግሞ ሌላ ተስፋ-ፈንጣቂ ነዉ።

default

የዘንድሮዉ ጉባኤ


የዛሬ-አስር አመት ቦን-ጀርመን ተሰየሞ የነበረዉ ዓለም አቀፍ የአፍቃኒስታን ጉባኤ ዕቅድ ዉሳኔዉ አሸባሪዎችን ለማጥፋት ለዘመተዉ የሐያል-ዓለም ጦር የድል ጉጉቱ ስኬት መደላድል፣ ለአፍቃኒስታን ሕዝብ የሰላም-ደሕንነቱ፣ ምኞቱ ቅርበት መሠረት መስሎ፣ «ነዉ» ተብሎም ነበር።ሺዎች-ከነ ድል ጉጉታቸዉ፣ መቶ ሺዎች ከነምኞታቸዉ ተቀብረዋል።የሚሊዮኖች ተስፋ በንኗል።ዓለም ለአፍቃኒስታን ቦን ላይ አንድ ያለዉን ጉባኤዉን ዘጠኜ-ደግሞት በአስረኛ አመቱ ለአስረኛ ጉባኤ-ዛሬ እንደገና ቦን-ተሰበሰበ።ጉባኤዉ መነሻ፣ የአስር ዓመቱ ሒደት ማጣቀሻ፣የአፍቃኒስታን እዉነት-ተስፋ ያፍታ ቅኝታችን ትኩረት ነዉ አብራችሁኝ ቆዩ።

ዋሽንግተን፣ ኦታዋ፣ ለንደን፣ብራስልሶች በኢራን ላይ የጣሉትን ተጨማሪ ማዕቀብ ጥንካሬ፣ የቴሕራኖች ዉግዘት፣ የሞስኮ፣ ቤጂንጎች ተቃዉሞ-ቅሬታ ሳይሰክን የሁሉም ተወካይ ባንድ ጉዳይ፣ እኩል ሊመክሩ አንድ ከተማ-ከተሙ።የአዉሮጳ ሕብረት በኢራን ላይ የጣለዉን ማዕቀብ-ከሌሎች የሕብረቱ አባል ሐገራት አቻዎቻቸዉ ጋር ሆነዉ ባለፈዉ ሐሙስ ያፀደቁት የጀርመኑ ዉጪ ጉዳይ ሚንስትር ጊዶ ቬስተርቬለ እንደ ሌሎቹ ሁሉ የኢራን አቻቸዉንም መጋበዝ ነበረባቸዉ።ጋበዙ።

የቴሕራንና የለንደን ዲፕሎማሲያዊ ግጭት፣ ዉጊያ ቀረሽ ፉከራ፣ ዛቻ በሚንተከተክበት መሐል የኢራኑ ዉጪ ጉዳይ ሚንስትር ዓሊ አክበር ሳሌሕ እንደ ጎረቤት ሐገር ተወካይ፣ብሪታንያዊዉ አቻ-አንጣቸዉ ዊሊያም ሄግ በርካታ ጦር እንዳዘመተ ሐገር ለየተቃራኒ ዓላማቸዉ ሥለሚሻሙባት ሐገር እኩል ሊመክሩ ካንድ አዳራሽ ገቡ።

ያቺ ሐገር ጠላቶችን ወዳጅ አስመሰለች።«ጥሩ መፍትሔ ማግኘት የምንችለዉ የአጎራባች ሐገራት ተሳትፎ ሲኖር ብቻ ነዉ።ኢራን ደግሞ ከነዚያ አንዷ ናት።»

ዉጪ ጉዳይ ሚንስትር ጊዶ ቬስተርቬለ።-ትናንት።ከመራሒተ-መንግሥት አንጌላ ሜርክል እስከ ፕሬዝዳንት ሐሚድ ካርዛይ፣ከዋና ፀሐፊ ፓን ጊ ሙን፣ እስከ የዉጪ ግንኙነት ሐላፊ ካትሪን አሽተን ከአንድ መቶ የሚበልጡ ሐገራትንና ድርጅቶችን የሚወክሉ ጉባኤተኞች ታድመዋል። ቦን። ሥለዚያች ሐገር ይመክራሉ።ይወስናሉም። አፍቃኒስታን።

የአጎራባች ሐገራት ተሳትፎ-ትብብር ቬስተርቬለ እንዳሉት ከሐያላኑ ሐገራት እኩል ጠቃሚ-አስፈላጊ በሆነበት ጉባኤ አንዲት በጣም አስፈላጊ ሐገር ግን አልተወከለችም።ፓኪስታን።ምክንያት-የፓኪስታኑ ዉጪ ጉዳይ ሚንስትር ሒና ራባኒ ኻር በቀደም እንዳሉት የአፍቃኒስታንን የቀርብ ዘመን ፖለቲካዊ ሒደትን የሚዘዉሩት ሐያላንን-ፍላጎት ዋና አስፈፃሚዋ ሐገራቸዉ ሉዓላዊነቷ ተደፍሯል።

«ምንድ ነዉ አንጋፋዉ ቀይ መስመር አልተከበረም።የፓኪስታን ሉዓላዊነት።ቀዩ መስመር ይሕ ነበር።በ(ዉጪ ሐይል) ምድሯ ሊረግጥ፥ የአየር ክልሏን ሊጣስ አይገባም ነበር።እነዚሕ ቀይ መስመሮች ናቸዉ።እነዚሕ (ቀይ መስመሮች) ሊከበሩ ካልቻሉ ወደ ማስመሪያዉ ሠሌዳ ተመልሰን መጀመሪያ እራሳችን እንገምግመዉ፥ ከዚያ በሕዋላ ለናንተ ፍላጎት የሚስማማ-መሆን አለመሆኑን ከናንተ ጋር ሆነን እናየዋለን።»

የዩናይትድ ስቴትስ ጦር የታሊባን ወይም የአል-ቃኢዳ ታጣቂዎች የሚላቸዉን ሐይላት ለመግደል ምዕራባዊ ፓኪስታንን በተደጋጋሚ መደብደቡ-ለኢስላማባድ መሪዎች «ቀይ-መስመር» ያሉት ሉዓላዊነት የመጣሱ ምልክት አልነበረም።የዩናይትድ ስቴትስ የሥለላ ባለሙያዎች ከኢስላማድ-እስከ ካራቺ ካሉ የፓኪስታን ከተሞች የአል-ቃኢዳ አባላት የሚሏቸዉን ሰዎች ለተከታታይ ዓመታት እየለቀሙ-ሲያስሩ-ሲያግዙ ኢስላማድ ባለሥልታናት የሉዓላዊነት ጥያቄ አላነሱም።

የዩናይትድ ስቴትስ ልዩ ጦር ኢስላማባድ ሐምሳ ኪሎ ሜትር ርቀት ድረስ ተጉዞ የአል-ቃኢዳን መሪና መስራች ከኢስላማ ቢን ላደንን ሲገድል-የፓኪስታን መሪዎች ሥለ-ቀይ ነጭ መስመር ያሉት አልነበረም።አፍቃኒስታን የሰፈረዉ አሜሪካ መራሽ ጦር ሔሊኮብተር ባለፈዉ ሳምንት ሃያ-አራት የፓኪስታን ወታደሮችን ሲገድሉ ግን ዉጪ ጉዳይ ሚንስትሩ እንዳሉት የፓኪስታን ሉዓላዊነት ተደፈረ።

እንደ አብዛኞቹ አዳጊ ሐገራት ሁሉ የቀዝቃዛዉ ጦርነት ወቅት የነበረዉ የአፍቃኒስታን ፖለቲካዊ ታሪክ የሞስኮ-ዋሽንግተን ሽኩቻ ዉጤትነቱ አያነጋግርም።የሶቬት ሕብረትን ጦር ከአፍቃኒስታን ከማስወጣት፣ እስከ ምዕራባዉያኑ ድል፣ ታሊባንን ወደ ሥልጣን ከማዉጣት፥ ከስሥልጣን እስከ ማስወገድ፥የአል-ቃኢዳ ተዋጊዎችን እስከ መግደል-ማሰር የነበረና ያለዉ የዋሽግተንና የተከታዮችዋ ፍላጎት አስፈፃሚዋ ግን ፓኪስታን ነች።

የካቡል ቤተ-መንግሥትን እንቅስቃሴን በዋሽግተን-ለንደኖች ወቅታዊ ፍላጎት ልክ እየመጠነች የምታራምደዉ ፓኪስታን ከ-እስካሁን «ዉለታዋ» ይልቅ የወደፊቷ አፍቃኒስታንን ምዕራቦች በሚሹት ጎዳና ለመዘወር-ወይም በተቃራኒዉ ለማሾር ጎርብትናዉ፣ የዘር ትስስሩ፣ የሥለላ ወታደራዊ ቅርበት፥ ብልሐት አቅሙም አላት።

የዚች ሐገር በጉባኤዉ አለመወከል-ግሩንሔልመ የተሰኘዉ የጀርመን ግብረ ሰናይ ድርጅት ሐላፊ ሩፐርት ኖይዴክ ባለፈዉ ሳምንት እንዳሉት የጉባኤዉን ፋይዳ በገሚስ ይቀንሰዋል።

«ጉባኤዉ ምዕራባዉያን መንግሥታትን ስብስብ ከሐፍረት ለማዳን ሲባል መደረጉ አይቀርም ብዬ አስባለሁ።ግን ገሚስ ጉባኤ ነዉ።ምክንያቱን ለዚሕ አካባቢ የሚመደቡት ዲፕሎማቶች ራሳቸዉ የአፍ-ፓክ ነዉ-የሚባሉት፥የአፍቃኒስታንና የፓኪስታን ጉዳይ ተጠሪዎች እንደማለት።እና አሁን አፍግ-ፓክ የሚባል ጉባኤ የለም።የሚካሔደዉ የአፍግ ብቻ ነዉ።ሥለዚሕ የሚገኘዉ ዉጤት ግማሽ ድል ነዉ።»

የፓኪስታን የረጅም ጊዜ ጠላት ሕንድ ግን የጉባኤዉ ሙሉ ተካፋይ ናት።ሕንድ የተማሩት ኻሚድ ካርዛይ ፓኪስታንን ራቅ-ገፋ እያደረጉ ከሕንድ ጉያ ከተሸጎጡ ቆዩ።በቅርቡ ደግሞ ካርዛይ ከሕንድ ጋር በጦር የመደጋጋፍ ዉል ተፈራርመዋል።አፍቃኒስታን ከዩናይትድ ስቴትስ በስተቀር ከሌላ ሐገር ጋር በጦር የመደጋጋፍ ዉል አልነበራትም። ሕንድ ሁለተኛዋ ሆነች።

ካርዛይ ከሕንድ ጋር ያደረጉትን ሁሉ ያደረጉት በዋሽግተኖች ፍቃድና ይሁንታ እንደሆነ ኢስላማባዶች ያደረጉትን ያክል ያዉቁታል።የቴሕራንና የለንደን ጠላቶችን ቦን ላይ ባንድ ያሳደመችዉ አፍቃኒታን የኢስላማባድና የዋሽግተን ጥብቅ ወዳጆችን አቀይማ አራራቀቻቸዉ።ተራራማይቱ፣ የተዋጊ አንገዛም ባዮቹ ሐገር ጠላቶችን እያወዳጀች፣ወዳጆች ስታጣላ ያሁኑ በርግጥ የመጀመሪያዋ አይደለም።

ከታላቁ እስክንድር እስከ፣ ቻንድራ ማወሪን፣ ከጌን ግየስ ካሕን እስከ ኩሽኖች፣ ከጋዝኖቪድስ እስከ ሳፍረዲሶች፣ ከሩሲያዎች፣ እስከ ብሪታንያዎች እስከ ሶቬቶች በየዘመናቸዉ ጠላቶቻቸዉን ድል ለማድረጋቸዉ ጮቤ ረግጠዉ ሳያበቁ-ያ ምድር እያዳለጣቸዉ የመዉደቃቸዉ ሰበብ-ምክንያትም የዚያች ሐገር አቀማመጥ፥ ሕዝብ ባሕል-ታሪክነቱ ሊጤን ይገባል።

ዩናይትድ ስቴትስ መስከረም አስራ-አንድ ሁለት ሺሕ አንድ (ዘመኑ በሙሉ እንደ ጎርጎሮሳዉያኑ አቆጣጠር ነዉ) ኒዮርክና ዋሽግተንን ያሸበሩ ሐይላትን ለማጥፋት ጦር ስታዘምት ከሩቆቹ ቢቀር ከቅርብ ቀዳሚዎቿ ሥሕተት ብዙ ተምራለች ነበር-የብዙዎቹ ጠንካራ ተስፋ እምነት።


አሜሪካኖች ዘመቻ-ፅናተ ነፃነት ባሉት ዉጊያ በወራት እድሜ ታሊባን እና አል-ቃኢዳን ደቁሰዉ ካቡልን በተቆጣጠሩ ማግስት ቦን ላይ የተጠራዉ የአፍቃኒስታን ጉባኤ፣ አሜሪካኖች በጦርነት የያዙትን ሐገር እንደቀዳሚዎቻቸዉ እንግዛ ከማለት ይልቅ፥አፍቃኒስታንን ለታማኝ ታዛዣቸዉም ቢሆን ለአፍቃኖች ለማስረከብ የመዘየዳቸዉ፣ ዓለምን ከጎናቸዉ የማሰለፋቸዉ እማኝ መስሎ ነበር።

በጅምር ድል ማግስት የተጀመረዉ ጉባኤ ፍፃሜም-የያኔዉ የጀርመን መራሔ መንግሥት ጌርሐርድ ሽሮደር ያኔ-እንዳሉት ጦር ላዘመቱት ሐይላት የሙሉ ድል፥ ለአፍቃኖች የሠላም መረጋጋት ሥርፀት ተስፋ ፈንጣቂም መስሎም ነበር።

«የአፍቃኒስታን ሕዝብ ከብዙ ዓመታት ጦርነት፥ ሽብር፥ ሥቃይና ዉርደት በሕዋላ ከምንም በላይ አስፈላጊ የሆኑት የሠላምና የምጣኔ ሐብት እድገት ተጨባጭ መፃኤ እድል ይኖረዋል።»

ጉባኤዉ የካቡልን ቤተ-መንግሥት ያስረከባቸዉ ሐሚድ ካርዛይ ዛሬም-እዚያዉ ናቸዉ።ያኔ-የሠላም ብልፅግና ተስፋዉን ከልቡ ከተቀበለዉ የአፍቃኒስታን ሕዝብ ግን ከሰላሳ-አምስት ሺሕ በላይ አልቋል። ካርዛይ ባለፉት አስር አመታት እንደ ፕሬዝዳት የሚመሩት መንግሥት ጦር ደግሞ ከአስር-ሺሕ በላይ ባልደረቦቹን መሰዋት ግድ ነበረበት።ታሊባን-አል-ቃኢዳን አጥፍቶ በአፍቃኒስታን-ሠላም ብልፅግና ለማስፈን የዘመተዉ የዉጪ ጦር በበኩሉ ከአራት ሺሕ የሚበልጡ አባላቱን ሕይወት ገብሯል።

አፍቃኒስታንና የዉጪዉ ጦር በእስካሁን ዘመቻዉ ፕሬዝዳት ጆርጅ ደብሊዉ ቡሽ በሁለት ሺሕ አንድ ሲሆን ከነነብሱ-ካልሆነ አስከሬኑን ግዳይ ለመጣል-የዛቱ በመቶ ሺሕ ጦር ያዘመቱበት ኦስማ ቢላደንን ጨምሮወደ አርባ ሺሕ የሚጠጋ የታሊባንና የአል-ቃኢዳ ታጣቂዎችን ገድሏል።

ታሊባን ዛሬም በአስረኛ አመቱ እንደ ጠንካራ ደፈጣ ተዋጊ ቡድን የዓለምን ምርጥ ጦር ገትሮ ይዟል።የጦርነት እልቂት፥ የፍጅት-ሥደቱን አዙሪት ያስቆማል የተባለዉ የቦን ጉባኤ እቅድ-ዉሳኔ የጫረዉ ተስፋ መብነን የጀመረዉ አፍቃኒስታኑ ዘመቻ ጀማሪ፥ አስተባባሪ፥ የበላይ መሪ ዩናይትድ ብሪታንያን አስከትላ ኢራቅን ስትወር ነበር።ሁለት ሺሕ ሰወስት።

በኢራቅ ወረራ ሰበብ መብነን የጀመረዉን የአፍቃኒስታን የሠላም ተስፋ ጨርሶ ከመጥፋት ለማደን ዓለም በሁለት ሺሕ አራት በርሊን፥ በሁለት ሺሕ ስድስት ለንደን፥ በሁለት ሺሕ ሰባት ሮም፥ በሁለት ሺሕ ስምንት ፓሪስ፥ በሁለት ሺሕ ዘጠኝ ሞስኮ፥ በዚሑ ዓመት ዘ-ሔግ፥ በሁለት አስር-እንደገና ለንደን፥ በሁለት ሺሕ አስራ-አንድ ኢስታቡል ላይ እየተሰበሰበሰ ሥለ አፍቃኒስታን ሲበጥስ ሲቀጥል-አስር ዓመት ደፈነ።

ተደጋጋሚዉ ጉባኤ-እቅድ ዉሳኔ አጓጉል ባርቆ ከዕልቂት-ፍጅት የፀዳ ብዙ ታሪክ የሌላትን ሐገር እንበለ-ተስፋ የማስቀረቱ አንዱ ምክንያት አሜሪካኖች አንዱን ጦርነት ሳያስወግዱ በሌላ የመማገዳቸዉ እብሪት፥ ከድር-ድር ዉይት ይልቅ በሐይል የመታበያቸዉ ማን አሕሎኝነት ነዉ።የቀዳሚዎቻቸዉን ስሕተት የመደግማቸዉ ጥፋት።በዱዉስቡርግ የኒቨርስቲ የደቡብ እስያ የፖለቲካ አዋቂ ዮኸን ሒፕለር እንደሚሉት የአፍቃኒስታን የሠላም-ብልፅግና ተስፋ፥ የተስፋ ቃል-እተገባለት፥ ተስፋ እየተደረገበት ተስፋዉ-የጨነጎለዉ የሚባል-የሚደረገዉ ሁሉ ግልፅ መርሕ ሥለሌለዉ ነዉ።

«ምንም አይነት እዉነተኛ ፅንሰ-ሐሳብ አልነበረም።ዲሞክራሲን ለማስረፅ ይሁን፥ አሸባሪነትን ለመዋጋት፥ ወይም ሐገርን ዳግም መገንባት ግልፅ አልነበረም።ብዙ ነገር ተብሏል።ግልፅ ግን አይደለም።እስካለፈዉ አንድ አመት ድረስ ግን ሁነኛ ሥልት ለመቀየስ ቁርጠኝነቱ አልነበረም።»

ካለፈዉ አንድ ዓመት ወዲሕ የታየዉ አሜሪካ መራሹ የዉጪ ጦር እስከ ሁለት አስራ-አራት ባለዉ ጊዜ ከአፍቃኒስታን ለመዉጣት መወሰኑ ነዉ።የአፍቃኒስታን መሪዎች ባለፉት አስር-አመታት ለሕዝባቸዉ የሰጡትን ተስፋ-ዛሬም ከቦን ደገሙት።የፕሬዝዳት ሐሚድ ካርዛይ የፀጥታ ጉዳይ አማካሪ ራንጊን ዳድፋር ስፓንታ ባለፈዉ ቅዳሜ እንዳሉት ቦን በአስር አመት ለሁለተኛ ጊዜ ያስተናገደችዉ ጉባኤ ለጀርመንና ለአፍቃኒስታን ትብብር ጥንካሬ አብነት፥ ለአፍቃኒስታን ሕዝብ ደግሞ ሌላ ተስፋ-ፈንጣቂ ነዉ።

Afghanistan Konferenz 2011 Bonn

ካርዛይና ሜርክል

«በዚሕ ጉባኤ የተሻለች አፍቃኒስታንን ለመመስረት ለፉት አስር አመታት የተደረገዉን የጋራ ትብብርና ተራድኦ እናረጋግጣለን።ከዚሕም በተጨማሪ በዚሕ ጉባኤ አፍቃኒስታን ዉስጥ በጋራ የምናከናዉነዉ ምግባር አዲስ ምዕራፍ ይጀመራል።ትብሩ የአፍቃኒስታንን ፀጥታ የማስከበሩን ሐላፊነት በማሸጋገሩ ሒደት፥ መልካም አስተዳደርን በመስረቱ መርሕ ላይ የተመሠረተ ነዉ።በሌላ አገላለፅ አፍቃኒስታን ሉዓላዊነትዋን ሙሉ በሙሉ የምትጎናፀፍበት፥ ሐላፊነትንም የምትረከብበት ነዉ።»

የጉባኤዉን አዳራሽ በሩቅ-ርቀት አራት ከአራት ሺሕ የሚበልጡ ሰልፈኞች ከሩቁ ከበዉታል። ሠልፈኞቹ አፍቃኒስታን የሠፈረዉ የዉጪ ጦር በአስቸኳይ እንዲወጣ፥ ሰብአዊ መብትና የሕዝብ ነፃነት እንዲከበር ይጠይቃሉ።ካዳራሹ የታደሙት ደግሞ ከሁለት መቶ ሺሕ የሚበልጠዉን የአፍቃኒስታን ጦርና ፖሊስ ሠራዊት፥ የአፍቃኒስታን-ሠላምና ልማት ለማጠናከር ሥለሚሰጡት ድጋፍ ርዳታ፥ ከታሊባን ጋር ሥለሚደረገዉ ድርድር ይነጋገራሉ።ሌላ-ቃል-ሌላ ተስፋ።

ነጋሽ መሐመድ ነኝ ቸር ያሰማን።

አርያም ተክሌ

Audios and videos on the topic