አፍቃኒስታን ጦርነትና ሽብር | ዓለም | DW | 24.04.2017
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

ዓለም

አፍቃኒስታን ጦርነትና ሽብር

ትራምፕ «የተሳካ» ያሉት ተልዕኮ ጦራቸዉ ደቡባዊ ናንጋርተር-አቺን የተባለዉን የአፍቃኒስታን ተራራማ አካባቢን በግዙፍ ቦምብ መደብደቡን ነዉ።ቦምቡ የኑክሌር አረር ከሌላቸዉ ቦምቦች ሁሉ እጅግ ትልቁ ነዉ።9800 ኪሎ ግራም ይመዝናል።ከዚሕ ዉስጥ 9164 ኪሎ ግራሙ ፈንጂ ነዉ።ከዘጠኝ ሜትር በላይ ይረዝማል።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 12:52

የአፍጋኒስታን ጦርነትና የሰሞኑ ጥቃት

የዩናይትድ ስቴትስ መራሹ ዓለም አቀፍ ጦር አፍቃኒስታን ከዘመተ ዘንድሮ አስራ-ስድስተኛ ዓመቱን ያዘ።ዘንድሮም እንደያኔዉ አሜሪካ አዲስ፤ ልዩ፤ ግዙፍ ቦምቧን ሳይቀር አፍቃኒስታን ላይ ታዘንባለች።አዲሱ ፕሬዝደንቷ በጦራቸዉ ዉጊያ ገድል ይኮራሉ።ለጀግና ወታደራቸዉ ልዩ ኒሻን ያጠልቃሉ። ይሸልማሉ።ፕሬዝደንት አሽረፍ ጋኒ የወታደሮቻቸዉን አስከሬን ይቆጥራሉ።አፍቃን ያልቃል።ሌላ ዓመት።ሌላ እልቂት።የማያበራ ጦርነት።እንዴት? ላፍታ አብረን እንጠይቅ።

                            

ዩንያትድ ስቴትስ የመጀመሪያዉ እና ሁለተኛዉ የዓለም ጦርነት በሚባለዉ ጦርነት ግንባር ቀደም ተዋጊ ነበረች።በኮሪያዎች ጦርነት ደቡብ ኮሪያን ደግፋ እነ ኢትዮጵያን አስከትላ ተዋግታለች።ቬትናም ተዋግታለች።ሊቢያን ወግታለች።ኢራቅን ካንዴም ሁለቴ ወርራለች።ሊቢያን ወግታለች።ሶሪያን እየደበደበች ነዉ እንደ አፍቃኒስታን ግን ረጅም ጊዜ የፈጀባት ጦርነት የለም።15 ዓመት ከመንፈቅ።ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ ግን የአሜሪካ ጦር አፍቃኒስታን ዉስጥ ተገቢ ዉጊያና ጥቃት አሁን

ነዉ-የጀመረዉ ባይ ናቸዉ።«ባለፉት ስምንት ሳምንታት የተደረጉትን ካለፉትን ስምንት ዓመታት ጋር ብታወዳድሩት ብዙ ልዩነት ታያላችሁ።ጦሩ ዉስጥ በጣም ጠንካራ መሪዎች አሉን።ጠንካራ ጦር አለን።እንኮራባቸዋለን።ይሕ ደግሞ በጣም የተሳካ ተልዕኮ ነበር።»

ትራምፕ «የተሳካ» ያሉት ተልዕኮ ጦራቸዉ ደቡባዊ ናንጋርተር-አቺን የተባለዉን የአፍቃኒስታን ተራራማ አካባቢን በግዙፍ ቦምብ መደብደቡን ነዉ።ቦምቡ የኑክሌር አረር ከሌላቸዉ ቦምቦች ሁሉ እጅግ ትልቁ ነዉ።9800 ኪሎ ግራም ይመዝናል።ከዚሕ ዉስጥ 9164 ኪሎ ግራሙ ፈንጂ ነዉ።ከዘጠኝ ሜትር በላይ ይረዝማል።

ይሕ ግዙፍ ቦምብ ከአስራ-ሁለት ቀን በፊት ሐሙስ አመሻሽ ላይ ከአየር እየተምዘገዘገ ተራራማዉን ቀበሌ አጋየዉ።ያዩ እንደሚሉት አካባቢዉ የዉጪዉ ወደ ዉስጥ የዉስጡ ወደ ዉጪ ተገለባብጧል።

                           

«ትናንት ማታ ከምሽቱ አንድ ሰዓት አካባቢ ያ ነገር ተወረወረ።ለግማሽ ሰዓት ያክል አካባቢዉ በእሳት ነደደ።ቦምቡ በወደቀበት ሥፍራ ሰላማዊ ሰዎች አይኖሩም።አካባቢዉ ተራራማ ነዉ።ምሽጉ ሶቬቶች እዚሕ ከነበሩበት ጊዜ ጀምሮ ነበር።ይሁንና ምሽጉ ካለበት ጉብታ ግርጌ መንደሮች አሉ።ISIS ሥለሚከለክል ወደ አካባቢዉ መጠጋት እንችልም።የISISን (ሸማቂዎች) ቁጥር በተመለከተ የማዉቀዉ ነገር የለም።ግን ከ40 እስከ ዘጠና የሚደርሱ የISIS አባላት ባካባቢዉ መሽገዋል የሚባል ወሬ ሰምቻለሁ።አካባቢዉ (በጥቃቱ) ሙሉ በሙሉ ተገለባብጧል።»

የአካባቢዉ ነዋሪ ማሌክ ዩኑስ።

የቀድሞዉ የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዝደንት ጆርጅ ደብሊዉ ቡሽ መስከረም 20፤ 2001 (ዘመኑ በሙሉ እንደ ጎርጎሪያኑ አቆጣጠር ነዉ) ጦራቸዉን አፍቃኒስታን ሲያዘምቱ  የኒዮርክና የዋሽግተን ከተሞችን ያጠቁ

አሸባሪዎችን እና ደጋፊዎቻቸዉን ለመበቀል ብለዉ ነበር።የዘመቻዉ ዒላማ ዩናይትድ ስቴትስን በማሸበር የተጠረጠሩትን የአልቃኢዳ አሸባሪዎችን እና የታሊባን ደጋፊዎቻቸዉን መበቀል ሥለነበር አብዛኛዉ ዓለም ደግፎት ጦሩን አዝምቶም ነበር።

በ2009 ቡሽን የተኩት ፕሬዝደንት ባራክ ኦባማ በ2012 እንዳስታወቁት እስከዚያ ጊዜ ድረስ በተደረገዉ ዉጊያ አብዛኞቹ የአልቃኢዳ አመራር አባላት ተደምስሰዋል።ታሊባን መዳከሙን አስታዉቀዉም ነበር።ኦባማ፤ ባግራም አፍቃኒስታን የአየር ኃይል ጦር ሠፈር።

                            

«ባለፉት ሰወስት ዓመታት ሁኔታዉ ተለዉጧል።የታሊባንን ጥንካሬ ሰብረናል።ጠንካራ የአፍቃኒስታን ፀጥታ ኃይል ገንብተናል።ከአልቃኢዳ ሰላሳ መሪዎች መካከል 20ዎቹን ደምስሰን የቡድኑን አመራር አጥፍተናል።ከአንድ ዓመት በፊት ደግሞ እዚሕ አፍቃኒስታን ከሚገኘዉ የጦር ሰፈር የዘመቱ ወታደሮቻችን ኦሳማ ቢን ላደንን ገድለዋል።አል-ቃኢዳን ለማሸነፍ እና ዳግም እንዳያንሰራራ ለማስወገድ  የነደፍኩት ዓላማ ግቡን ከሚመታበት ደረጃ ደርሷል።»

አላበሉም።አልቃኢዳ ተደምስሷል።ታሊባን ግን እንዳለ ነዉ።ኦባማን የተኩት የዶናልድ ትራምፕ ዕቅድ እና አላማ አልቃኢዳን ማጥፋት አይደለም።አልቃኢዳን የተካዉን እራሱን እስላማዊ መንግሥት ISIS የሚለዉን ቡድን-እንጂ።ትራምፕ የሚያዙት ጦር ISIS አባላት ያላቸዉ ሸማቂዎች ለመዉጋት የተለመደዉ ጦር መሳሪያ አልበቃዉም።

አፍቃኒስታን የሠፈረዉ የሰሜን አትላንቲክ ጦር አዛዥ ጄኔራል  ጆን ኒኮልሰን እንዳሉት ጦራቸዉ አሸባሪዉ ቡድን የመሸገበትን ሥፍራ ለመያዝ ካለፈዉ መጋቢት መጀመሪያ ጀምሮ ያደረገዉ ዉጊያ ሁሉ አልተሳካለትም።እና «የቦምቦች ሁሉ እናት» ያለዉን ልዩ ቦምብ ፈለገ።

                              

«ከመጋቢት መጀመሪያ ጀምሮ በደቡባዊ ናንጋርሐር ግዛት ተደጋጋሚ የጥቃት ዘመቻ ከፍተን ነበር።ይሁንና ባካባቢዉ በተቀበሩ ፈንጂዎች እና ምሽጎች ምክንያት ለመጀመሪያ ጊዜ ከፍተኛ  እንቅፋት ገጥሞናል።ሥለዚሕ እንቅፋቱን ለመቀነስ እና የደቡባዊ ናንጋርሐር ጥቃታችንን ለመቀጠል ባሁኑ ወቅት ይሕ ተገቢዉ መሳሪያ ነዉ።(ቦምቡን) በተገቢዉ ዒላማ ላይ የምንጥልበት ተገቢዉ ታክቲካዊ ጊዜ አሁን ነዉ።የደቡብ ጥቃታችንን እንድንቀጥል አስችሎናል።»

በተገቢዉ ጊዜ፤ በተገቢዉ ኢላማ ላይ የተጣለዉ ተገቢ ቦምብ ሰላሳ-ስድስት የISIS ሸማቂዎች መግደሉ ተገምቷል።የሞተ-የቆሰለዉን የአካባቢዉን ሰላማዊ ነዋሪ የቆጠረዉ የለም።

እስካሁን አዉዳሚዉን የአዉቶሚክ ቦምብ  ሰዉ ባለበት ሥፍራ ያፈነዳች ብቸኛዋ ሐገር፤

ብቸኛዋ የዓለም ልዕለ ኃያል ሐገር ናት።ዩናይትድ ስቴትስ።በአዉቶሚክ ቦምብ በመታት ደግሞ ሔሮሺማና ናጋሳኪ ጃፓን የመጀመሪያዎቹ ናቸዉ።ነሐሴ 1945።የኑክሌር አረር የሌለዉ ግዙፍ ቦምብ በመጣልም ዩናይትድ ስቴትስ የመጀመሪያዋ ሆናለች።በግዙፉ ቦምብ በመመታት አፍቃኒስታን አንደኛ ሆነች።

 

የአሜሪካዉ ጄኔራል ተገቢዉን ቦምብ በተገቢዉ ኢላማ ላይ ለመጣል ታክቲክ ሲነድፉ የታሊባን መሪዎችም «ተገቢ» የሚሉትን  ከባድ ዱላ በተገቢዉ ኢላማቸዉ ላይ ለማሳረፍ ስልት ሲቀምሩ ነበር።ጥቃቱ ማዛር ኢ ሸሪፍ ላይ ያነጣጠረ ነበር።የስልታዊቷ ሐገር ሥልታዊ እና ሰወስተኛ ትልቅ ከተማ ናት።

ከረጅም ጊዜ ጀምሮ ታሒሪዶች፤ ሳፋሪዶች፤ ሳማኒዶች ጋዛናቫዶች፤ ጉሪዶች፤ ቲሙሪዶች፤ ቡካራዎች ሲመቻቸዉ አብረዉ፤ ሳይመቻቸዉ አንዳቸዉ ሌላቸዉን እያስገበሩ ሰፍረዉባል።ባለፉት አስራ-አምስት ዓመታት ደግሞ የአሜሪካ ፤ የተባባሪዎችዋ ሐገራት እና የአፍቃኒስታን መንግሥት ጦር መናኸሪያ ሆናለች።ባለፈዉ አርብ ከትላልቆቹ የአፍቃኒስታን ጦር ሠፈር አንዱን የታሊባን ቦምብ አጋየዉ።

ያዩ እንዳሉት የጦሩ አባላት ለጁመዓ ሶላት እንደታደሙ፤ አካላቸዉ ላይ ቦምብ ያገለደሙ፤ በቅጡ የታጠቁ እና የአፍቃኒስታን ጦር መለያ (ዩኒፎርም) የለበሱ ሸማቂዎች ከጦር ሠፈሩ ሰተት ብለዉ ገቡ።ጦር ሠፈሩ ሰባት የፍተሻ ኬላዎች አሉት ታጣቂዎቹን ግን አንድም ሥፍራ-አንድም ሰዉ አላቆማቸዉም።ሶላቱ አበቃ።አካባቢዉ በፍንዳታ እና ተኩስ ይታበጥ ገባ።

 

 «የጁመዓ

ሶላታችንን እንዳበቃን የአፍቃኒስታን ብሔራዊ ጦር ዩኒፎርም የለበሱ ታጣቂዎች ተኩስ ከፈቱብን።የሐገሪቱ ጠላቶች ናቸዉ።አላዉቅም።ብቻ መኪኖቻቸዉን እንዲያስገቡ እግቢዉ ዉስጥ ያለ ሰዉ ሳይረዳቸዉ አልቀረም።ዋናዉ በር ከታለፈ በኋላ ሰባትና ስምንት የሚሆኑ የፍተሻ ኬላዎች አሉ።ከዉስጥ ተባባሪ ባኖራቸዉ ኖሮ ይኽን ሁሉ የፍተሻ ሥፍራ አልፈዉ መስጊዱ ጋ መድረስ ባልቻሉ ነበር።»

ባፍታ በተጠናቀቀዉ ጥቃት አንድ መቶ አርባ የአፍቃኒስታን ወታደሮች ተገደሉ።በብዙ መቶ የሚቆጠሩ ቆሰሉ።ፕሬዝደንት አሽረፍ ጋኒ አስከሬን ቆጠራ-ቀበራዉ፤ ቁስለኛ ጥየቃዉ ቀለል ሲልላቸዉ ዛሬ መከላከያ ሚንስትራቸዉን እና የጦር ኃይል ጠቅላይ ኤታ ማዦር ሹማቸዉን  ሽረዋል።የፕሬዝደንቱ ቢሮ ዛሬ እንዳስታወቀዉ መከላከያ ሚንስትር አብዱላሕ ሐቢቢ እና ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም ጄኔራል ቀዳም ሻሕ ሻሒም ከስልጣን የተወገዱት የማዛር ኢ ሸሪፉን ጥቃት ባለመከላከላቸዉ ነዉ።

አሜሪካኖች ያሰለጠኑ እና ያስታጠቁት የአፍቃኒስታን ወታደር ማዛር ኢ ሸሪፍ ጦር ሠፈሩ ዉስጥ በቦም ጥይት ሲቆላ የአሜሪካዉ ፕሬዝደንት በአፍቃኒስታኑ ጦርነት አንድ እግሩን ያጣ አሜሪካዊ ወታደር ኒሻን ይሸልሙ ነበር።ጥንታዊቱ ተራራማይቱን ሐገር ግሪኮች፤ ፋርሶች፤ ቱርኮች፤ ሞንጎሎች፤ አረቦች፤ ሕንዶች፤ ብሪታንያዎች፤ ሶቭዬት ሕብረቶች ገድለዉ፤ አጋድለዉ፤ ገዝተዉ ተሸንፈዉባታል።አሜሪካኖች መግደል-ማጋደል-መገደል ከጀመሩባት አስራ-አምስት ዓመት ከመንፈቋ።እስካሁን ከ3530 በላይ የአሜሪካ የተባባሪዎችዋ ሐገር ወታደሮች ተገድለዋል።ከ140 ሺሕ በላይ አፍቃናዊ አልቋል።ግድያ እልቂቱ እንደቀጠለ ነዉ።እስከመቼ?ነጋሽ መሐመድ ነኝ ቸር ያሰማን።

ነጋሽ መሐመድ

አርያም ተክሌ

 

 

 

Audios and videos on the topic