አፍሪካ እርዳታ የበለፀጉት አገራት ለዉጥ ይፈልጋሉ | የጋዜጦች አምድ | DW | 01.07.2005
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

የጋዜጦች አምድ

አፍሪካ እርዳታ የበለፀጉት አገራት ለዉጥ ይፈልጋሉ

በመጪዉ ሳምንት የበለፀጉት አገራት ስኮትላንድ ዉስጥ ሲሰበሰቡ በዓለም ምጣኔ ሃብታቸዉ ለደቀቀዉ አገራት አዲስ የገንዘብ ድጋፍ ይደረግ የሚለዉ ነጥብ ዋነኛ የዉይይት ርዕሰ ጉዳይ እንደሚሆን ይጠበቃል።

በተለይ አፍሪካ በርከት ያለ የልማት የገንዘብ ድጋፍ በምትጠብቅበት በአሁኑ ወቅት እንደ ጀርመን ያሉ የቡድን ስምንት አገራት በቅድሚያ በነዚህ አገራት ዉስጥ የመሻሻል ለዉጥ ማየት እንፈልጋለን እያሉ ነዉ። ለዚህም እስከዛሬ ምን ሰራ በማለት የአፍሪካ የልማት ትብብር በምህፃሩ NEPADን አስተዋፅዖ መመርመር ጀምረዋል።
NEPAD የዛሬ አራት ዓመት በአፍሪካ ህብረት ዉስጥ በደቡብ አፍሪካዉ ፕሬዝደንት ታቦ ምቤኪ፤ በናይጀሪያዉ ዖሊሴንጆን ዖባሳንጆ፤ በሴኔጋሉ አብዱላዬ ዋዴ፤ በግብፁ ሆስኒ ሙባረክና በአልጀሪያዉ አብዱላዚዝ ቡቶፍሊካ ነበር የተቋቋመዉ።
በፈረንጆቹ አቆጣጠር ለመጪዉ 2015 የምዕተ ዓመቱ የልማት ግብ እንደታሰበዉ ለመድረስ የቡድን ስምንት አገራት የተባለዉን የድጋፍ መጠን ለመለገስ ቁርጠኝነት ማሳየት ይኖርባቸዋል ይላሉ ዊስማን ናኩሁሉ የNEPAD ዋና ዳይሬክተር።
አፍሪካዉያን መሪዎች የልማት እርዳታዉ በመጪዎቹ ሶስት ዓመታት በእጥፍ እንዲጨምርና ለአፍሪካ ህብረት የሰላምና የደህንነት መርሃ ግብርም ያላሰለሰ ድጋፍ እንዲደረግላቸዉ ነዉ የሚጠይቁት።
የጀርመኑን ቻንስለር ጌርሃርድ ሽሮደርን በመወከል በቡድን ስምንቱ የአፍሪካ ጉዳይ ጉባኤ የሚገኙት ኡሺ አይት በበኩላቸዉ እኛ ቡድን ስምንቶች የዛሬ አራት ዓመት ኔፓድን ካመሰራረቱ የደገፍነዉ በአህጉሪቱ ለዉጥና መሻሻል ያመጣል በሚል ራዕይ እንጂ የልማት እርዳታ የሚያሰባስብ መሳሪያ ሆኖ ለማየት አይደለም ይላሉ።
እናም ይላሉ ይህ ድርጅት የተመሰረተበትን ዓላማ ለዉጦ ከሆነም ቀደም ብሎ ሊነገረን ይገባል።
አይት ይህን የተናገሩት በርሊን ላይ በጀርመን ተራድኦ ድርጅት ማለትም GTZ አማካኝነት በተዘጋጀዉ የዉይይት መድረክ ላይ ነበር።
እንደሳቸዉ አገላለፅ በቡድን ስምንቱ አገራት መካከል ሁለት ዓይነት አመለካከት አለ። አንዱ ወገን እርዳታዉን እጥፍ እናድርግ በማለት ግፊት የሚያደርግ ነዉ።
ሌላዉ ወገንና የጀርመንም አቋም የሆነዉን ሃሳብ የሚያራምደዉ ደግሞ እርዳታዉን ከመጨመር በፊት የለዉጥ እንቅስቃሴዎችን በተግባር ማየት አለብን የሚል ነዉ።
ከዚህ በመነሳትም የአገራቸዉን አቋም ሲያስረዱ ብዙ ጥሪት ከማፍሰሳችን በፊት በተለይ በአንዳንድ ዘርፎች መሰረታዊ መሻሻሎችን ማየት እንፈልጋለን ብለዋል።
ጀርመን የአፍሪካ አገራት መሪዎች በተለይ በአህጉሪቱ ዉስጥ ሰላምና ደህንነትን የማጠናከር ሃላፊነታቸዉን ተወጥተዉ ማየት ትፈልጋለች።
በዚያም ላይ የግሉን ዘርፍ በማበረታታትና ከሶስት አመታት ወዲህ 2.5 ቢሊዮን ዩሮ የተመደበለት የዉሃዉ ዘርፍ ትብብር መጠናከሩ ለአፍሪካ የድጋፍ ገንዘብ ለመጨመር በግንባር ቀደምትነት ያሰፈረችዉ ጉዳይ ነዉ።
ተቺዎች በበኩላቸዉ የአፍሪካ አገራት እንዲጨመር የተጠየቀዉን ያህል የልማት ገንዘብ ቢያገኙም የማስተናገዱ አቅም የላቸዉም ይላሉ።
ናኩሁሉ ለዚህ ምላሽ ሲሰጡም ከፍተኛ እድገት ያሳዩና የቱንም ያህል የበረከተ የልማት ድጋፍ ቢያገኙ በአግባቡ መጠቀም የሚችሉ የአፍሪካ አገራት እንዳሉ አምናለሁ ብለዋል።
ከዚህም ሌላ የልማት በጀቱ መጨመርም የNEPADን መርሃ ግብር አይለዉጠዉም እንደዉም ወደኋላ ለቀሩት አገራት እንደማበረታቻ የሚሆን ነዉ የሚልም አቋም አላቸዉ።
በሌላ በኩል ደግሞ መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ማህበር ኃላፊ ሪንሃርድ ሄርምለ እንደሚሉት እዳቸዉ በቡድን ስምንቱ አገራት የተሰረዘላቸዉ አገራት የሚያገኙት የእርዳታ ገንዘብ መጠን አነስተኛ ይሆናል በማለት ትችታቸዉን ሰንዝረዋል።
ሄርምለ እንደሚሉት ያ ማለት በዜሮ የሚባዛ የሂሳብ ተጠየቃዊ አካሄድ በመሆኑ ዉጤቱ ሊገባቸዉ አልቻለም።
የአሰራሩን ማብራሪያም ከቡድኑ አገራት ማለትም ብሪታኒያ፤ ካናዳ፤ ፈረንሳይ፤ ጀርመን፤ ጣሊያን፤ ጃፓን፤ ሩሲያና ዩናይትድ ስቴትስ መሪዎች ይጠብቃሉ።
በስኮትላንድ ግሌንኢግልስ ከተማ የቡድን ስምንቱን ጉባኤ ከመጪዉ ማክሰኞ እስከ ሃሙስ የሚያስተናግዱት የብሪታንያዉ ጠቅላይ ሚኒስትር ቶኒ ብሊየር ዋና የመነጋገሪያ ነጥብ አድርገዉ የያዙት የአፍሪካ ልማትና የአየር ጠባይ ለዉጥን ነዉ።
በአንፃሩ ከዕዳ ስረዛዉና የልማት ድጋፍ መጨመሩ ጋር በተያያዘ መልኩ መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶችና አፍሪካዉያን በእርሻዉ ዘርፍ ለምዕራባዉያን የሚደረገዉ ድጎማ ይቆማል በሚል ተስፋ አድርገዋል።
እንደ ናኩሁሉ ገለፃ ከሆነ በዚህ ረገድ NEPAD የሞራል ድል አግኝቷል ከአፍሪካዉያን መሪዎች የሚጠበቀዉ ማንም ሊያየዉ የሚችል መልካም አስተዳደርን አስፍኖ ሙስናን መዋጋት ይሆናል።
አያይዘዉም የቡድን ስምንቱ አገራት መሪዎች የነበራቸዉ አመለካከት እየለዘበ መምጣቱን ጠቁመዉ ያም ሆኖ ምንም ያህል ልገሳ ቢገኝም ዘላቂ መፍትሄ መሆን አይችልም በማለት ነዉ ለአፍሪካ ችግር የልማት ድጋፍ መጨመር ብቻዉን ዉጤት እንደማያስገኝ ያስገነዘቡት።