1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል
ኤኮኖሚ

አፍሪካ ኋላ የምትቀርበት ልዕለ-ኃያላኑ የተፋጠጡበት 5ጂ

ረቡዕ፣ መስከረም 14 2012

ጥናቶች እንደሚጠቁሙት ​​​​​​​በሚቀጥሉት ስምንት አመታት 4 ቢሊዮን ሕዝብ የገመድ አልባ የተንቀሰቃሽ ስልክ ግንኙነት አምስተኛ ትውልድ (5G) ቴክኖሎጂ ተጠቃሚ ይሆናል። እስከ መጪው ጥር ወር መጨረሻ ድረስ ይኸው ቴክኖሎጂ በ25 አገራት ሥራ ይጀምራል። አሜሪካ፣ ቻይና፣ ደቡብ ኮሪያና ጃፓን ቀዳሚ ናቸው። ከሰሐራ በታች ያሉ አገራት ይዘገያሉ

https://p.dw.com/p/3PmPv
Spanien Barcelona 5G
ምስል Reuters/R. Marchante

አሜሪካ እና ቻይና በ5ኛው ትውልድ ቴክኖሎጂ የበላይ ለመሆን ፉክክር ገጥመዋል

ቻይና እስከ መጪው ጥር ወር መጨረሻ በ50 ከተሞች 50,000 የገመድ አልባ የተንቀሰቃሽ ስልክ ግንኙነት አምስተኛ ትውልድ (5G) ቴክኖሎጂ አገልግሎት መስጫ ጣቢያዎች ለመገንባት አቅዳለች። የአገልግሎት መስጫ ጣቢያዎቹ በጉጉት የሚጠበቀውን እና ቻይና ከአሜሪካ ፉክክር የገጠመችበትን ቴክኖሎጂ አገልግሎት ለማሳለጥ የታቀዱ ናቸው።

5ጂ የሚለው መጠሪያ ለአምስተኛ ትውልድ ገመድ አልባ የተንቀሰቃሽ ስልክ ግንኙነት የተሰጠ አጭር መጠሪያ ነው። ተንታኞች እንደሚሉት ይኸ ቴክኖሎጂ የወደፊቱ ዓለም «የልብ ትርታ» ሊሆን ዳር ዳር እያለ ነው። እንደ የዓለም የኤኮኖሚ ፎረም ያሉ ተቋማት በተለይ የናጠጡት አገሮች በብርቱ የሚፎካከሩበት የገመድ አልባ የተንቀሰቃሽ ስልክ ግንኙነት አምስተኛ ትውልድ (5G) ቴክኖሎጂ    ለዓለም የርስ በርስ ግብይት በቢሊዮኖች የሚቆጠሩ ትስስሮች በመፍጠር ሁነኛ ሚና ይጫወታል የሚል ተስፋ አላቸው። የተሽከርካሪ ማምረቻ፤ የጤና፤ የማከፋፈያ ዘርፎች በአገልግሎቱ ይሻሻላሉ ተብለው ከሚጠበቁ እጅግ ጥቂቶቹ ናቸው። በተለይ ለአሽከርካሪ አልባ መኪኖች፣ ለሰው አልባ ፋብሪካዎች እና በርቀት ሊፈጸሙ የሚችሉ ቀዶ የቀዶ ጥገና ሕክምና መሻሻል ገና ካሁኑ ተስፋ ተጥሎበታል።

ለዚህ ደግሞ ቻይና እና አሜሪካ በቴክኖሎጂው የበላይ ሆኖ ለመገኘት አንዳቸው ከሌላቸው የበረታ ውድድር ውስጥ ገብተዋል። ውድድሩን በበላይነት ያጠናቀቀ አገር በዘርፉ በሚኖረው የበላይነት፤ በሚፈጥረው የስራ ዕድል፣ በአገራቱ አጠቃላይ አመታዊ የምርት መጠን ሊያበረክት በሚችለው ጥቅም አሸናፊነቱን አጥብቆ ይፈልገዋል። ለዚህም ይመስላል ካለፈው ሚያዝያ ወር ጀምሮ የደቡብ ኮሪያ እና የአሜሪካ ኩባንያዎች አገልግሎቱን ቀድሞ በማስጀመር ረገድ የበረታ ፉክክር ውስጥ የገቡት።

China Huawei 5G Netz
ምስል picture-alliance/dpa/Z. Min

በፊች ሶሉሽንስ ኩባንያ የቴሌኮም ገበያ ተንታኙ ዴክስተር ቲልየን የ5ጂ ቴክኖሎጂን በፉክክር ከጀመሩት ገንዘብ፣ የሰለጠነ የሰው ኃይል እና የቴክኖሎጂ ዝግጅት ካላቸው አገራት ባሻገር በመላው ዓለም የማዳረሱ ሥራ ረዥም ጊዜ እንደሚፈጅ ይናገራሉ። ሥራው «አብዮት አይደለም» የሚሉት ዴክስተር ቲልየን ቢያንስ «በእኛ ጥናት መሠረት በ2019 መገባደጃ 25 አገሮች የ5ጂ አገልግሎት መሥጠት ይጀምራሉ ብለን እንጠብቃለን። ዩናይትድ ስቴትስ፣ ካናዳ፣ ቻይና፣ ደቡብ ኮሪያ፤ ጃፓን እና ከአውሮፓ ደግሞ ፊንላንድ እና ኖርዌይ ሥራ ያስጀምራሉ ። አውስትራሊያ እና ደቡብ አፍሪካም እንዲሁ። 5ጂ አብዮት አይደለም። በሒደት ተግባራዊ የሚሆን ነው። በመሆኑም አብዛኞቹ አገሮች ከ2025 በኋላ 5ጂ ሥራ ያስጀምራሉ» ሲሉ ተናግረዋል።

በሰከንድ 10 ጊጋ ባይት መረጃ ማስተላለፍ ይችላል ተብሎ የሚጠበቀው የገመድ አልባ የተንቀሰቃሽ ስልክ ግንኙነት አምስተኛ ትውልድ (5G) ቴክኖሎጂ   አሁን በብዙ አገሮች በሥራ ላይ ከሚገኘው አራተኛ ትውልድ በመቶ እጥፍ የላቀ አገልግሎት እንደሚያቀርብ ይነገርለታል። የአራተኛው ትውልድ ዋንኛ ትኩረቱ ተንቀሳቃሽ ስልኮች እና መሰል ቁሳቁሶች ላይ ሲሆን የገመድ አልባ የተንቀሰቃሽ ስልክ ግንኙነት አምስተኛ ትውልድ ግን ተሽከርካሪዎች እና ግዙፍ ማሽኖችን ጨምሮ በርካታ የሰው ልጅ የሥራ መሳሪያዎችን ሊያገናኝ ይችላል።  ዴክስተር ቲልየን እንደሚሉት ከስምንት አመታት በኋላ ግማሽ ያክሉ የዓለም ሕዝብ የዚሁ ግልጋሎት ተጠቃሚ ይሆናል ተብሎ ይጠበቃል።

Hannover Industriemesse 2019 Aufbau
ምስል picture-alliance/dpa/C. Gateau

«በ2028 ዓ.ም. 4 ቢሊዮን ተጠቃሚዎች ይኖራሉ ብለን እንጠብቃለን። ይኸ ከዓለም ሕዝብ 45 በመቶ ገደማ ማለት ነው። ከሌሎች አገሮች በተለየ ቻይና አገልግሎቱን በፍጥነት ሥራ ላይ ልታውል ትችላለች። ቻይና የ4ጂ ቴክኖሎጂ በስዊድን እና በኖርዌይ ሥራ ላይ ከዋለ በኋላ ዘግይታ በ2014 ነበር የተቀላቀለችው። ነገር ግን በአምስት አመታት ውስጥ የተጠቃሚዎች ቁጥር በቻይና አንድ ቢሊዮን ደርሷል። ስለዚህ ቻይና በዚህ ዓመት ወይም በሚቀጥለው አመት ሥራ ላይ ብታውል እንኳ ከዓለም አኳያ ከፍ ያለ የተጠቃሚዎች ቁጥር ይኖራታል»

ከስድስት አመታት በፊት በአዲስ አበባ አራተኛውን ትውልድ (4G) በመላው ኢትዮጵያ ደግሞ ሶስተኛውን ትውልድ (3G)  ለማስፋፋት የ700 ሚሊዮን ዶላር  ውል ገብቶ የነበረው የቻይናው ሑዋዌ ኩባንያ የገመድ አልባ የተንቀሰቃሽ ስልክ ግንኙነት አምስተኛ ትውልድ (5G) ቴክኖሎጂ  የበላይ ለመሆን በሚደረገው ፉክክር የተሻለ ዕድል እንዳለው ይነገራል። ሑዋዌ የአምስተኛው ትውልድ ቴክኖሎጂን ለማስፋፋት የሚያገለግሉ ቁሳቁሶች በማምረት አሜሪካና አውሮፓን ጨምሮ በዓለም ገበያ ቀዳሚ ሆኖ ቆይቷል። ኩባንያው እና ምርቶቹ ደኅንነታቸው የተጠበቁ አይደለም የሚል ክስ የምታቀርበው አሜሪካ በፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ትዕዛዝ በገበያዋ እንዳይሳተፍ እገዳ ጥላለች። አሜሪካ የሑዋዌ ምርቶች የቻይና መንግሥት ቁሳቁሶቹን የሚጠቀሙ አገራትን እንዲሰልል አድርገው የተሰሩ ናቸው የሚል ክስ ጭምር ታቀርባለች። በእርግጥ ኩባንያው ክሱን ያስተባብላል። የፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ አስተዳደር የኩባንያውን ምርቶች የሚጠቀሙ አገራት ተመሳሳይ እርምጃ እንዲወስዱ ግፊት ሲያደርግ ቆይቷል። ኩባንያው በቻይና እና በአሜሪካ መካከል በተቀሰቀሰው የንግድ ጦርነት ዋንኛ መወዛገቢያ ጉዳይ ሆኖ ዛሬ ድረስ ዘልቋል። የሑዋዌ መሥራች ሬን ጄንግፌይ ግን ኩባንያቸው በአሜሪካ ገበያ የተጣለበት ዕገዳ ቢያስቆጫቸውም ለትራምፕ አስተዳደር እጅ የመስጠት ምልክት አላሳዩም።

Italien Mailand Graffito von TvBoy zu Handelsstreit Trump Xi
ምስል AFP/M. Medina

ሬን ጄንግፌይ «አሜሪካ እና አውስትራሊያ 5ጂ እጅግ የተሻሻለ መሆኑን ካተረዱ እና በደኅንነቱ ላይ ጥርጣሬ ካላቸው አሜሪካ የሑዋዌን 5ጂ ተያያዥ ቁሳቁሶች ባትገዛ ይሻላታል። መላው ዓለም ቴክኖሎጂውን ተጠቅሞ ስለ ደኅንነቱ ሲመሰክር መግዛት ይችላሉ።» ባይ ናቸው።

ሑዋዌ ለሚያመርታቸው ምርቶች ከዚህ ቀደም ከአሜሪካ የሚገዛቸውን ግብዓቶች ራሱ ማምረት መጀመሩን ባለፈው ነሐሴ ይፋ አድርጓል። ይኸ ኩባንያው በአሜሪካ ተፎካካሪዎቹ ላይ የነበረውን ጥገኝነት ሙሉ በሙሉ እንዲያስወግድ አሊያም እንዲቀንስ አግዞታል። የሑዋዌ አማካሪ ሪቻርድ ግሪፊትዝ የሚሉትም ይኸንኑ ነው። «እኛ እንደ ሑዋዌ ያለን የተሻለ ብልጫ የሚያስፈልጉንን በሙሉ ራሳችን ማምረት ጀምረናል። ለምናመርታቸው ምርቶች የሚያስፈልገንን ቺፕስ ጨምሮ እያንዳንዱን ቁሳቁስ የሚሰራ ማምረቻ አለን። ለ5ጂ ቴክኖሎጂ እና ለግብዓቶቹ የሚያስፈልጉንን ዕቃዎች ለማግኘት በየትኛውም ኩባንያ በየትኛውም አገር ላይ ጥገኛ አይደለንም። ሁሉንም በራሳችን መስራት እንችላለን» ብለዋል።

Huawei-Gründer Ren Zhengfei
ምስል picture-alliance/dpa/V. Yu

ዓለም የሶስተኛውን ትውልድ  እና የአራተኛውን ትውልድ ቴክኖሎጂዎች ሲያስፋፋ ሑዋዌ ዛሬ የፈረጠመው ኃይል እና ጉልበት አልነበረውም። ባለፈው አመት ለሥራ ከተሰማራባቸው 170 አገራት 107 ቢሊዮን ዶላር ገቢ ማግኘቱን የገለጸው ኩባንያ በአምስተኛው ትውልድ  ቴክኖሎጂ ግን ከቀዳሚዎቹ ጎራ ተሰልፏል። ተንታኞች እንደሚሉት ኩባንያው በዚህ ዕድገቱ ከቀጠለ እና በዓለም ገበያ የአምስተኛ ትውልድ ቴክኖሎጂን በማስፋፋቱ ረገድ የበላይነት ካገኘ ከአሜሪካ ይልቅ ቻይና የበረታ ተደማጭነት ይኖራታል። የኩብንያው መሥራች ሬን ጄንግፌይ እንደሚሉት ሑዋዌ ወደ 80,000 ገደማ ሰራተኞቹ በጥናትና ምርምር ላይ ያተኮሩ ናቸው። የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ፈጠራዎችን የሚከታተለው አይፒሊቲክስ (IPlytics) የተባለ የጀርመን ኩባንያ መረጃ እንደሚጠቁመው ሑዋዌ ከተወዳዳሪዎቹ በላይ በርካታ የአምስተኛው ትውልድ ቴክኖሎጂ ፈጠራዎችን በባለቤትነት አስመዝግቧል። ይኸ የአሜሪካኖቹን ጨምሮ ሌሎች ተወዳዳሪ ኩባንያዎች የፈጠራ ሥራዎቹን ለመጠቀም ከሑዋዌ እንዲሸምቱ ያስገድዳቸዋል።

ከሰሐራ በታች ከሚገኙ የአፍሪካ አገራት መካከል ደቡብ አፍሪካ እና ሌሴቶ ቴክኖሎጂውን በመሞከር ረገድ ከቀዳሚዎቹ ተርታ ተሰልፈዋል። ዴክስተር ቲልየን «ከሰሐራ በታች የሚገኙ አገራት ይኸን ቴክኖሎጂን ለመጠቀም እና ሥራ ላይ ለማዋል እጅግ ይዘገያሉ።  በበርካታ አገራት ገበያዎች የ4ጂ ቴክኖሎጂ ሥራ ላይ አልዋለም። አብዛኞቹ 3ጂ አሊያም 2ጂ ቴክኖሎጂን በመጠቀም ላይ ናቸው። ስለዚህ ረዥም ጊዜ ይወስድባቸዋል። ነገር ግን በዚህ ቀጠና የተለዩ ነገሮች አሉ ሬይን የተባለ ኩባንያ በደቡብ አፍሪካ እንዲሁም ቮዳኮም በሌሴቶ የ5ጂ ቴክሎጂን ሙከራ ጀምረዋል። ከዚህ በተጨማሪ ኬንያ፣ ሞሪሽየስ እና ናሚቢያ ከሌሎቹ ቀደም ብለው ሥራ ላይ የማዋል ዕቅድ አላቸው። ይኸ ግን ከአኅጉሩ አኳያ እጅግ ትንሽ ገበያ ነው» ብለዋል። መቀመጫውን ስዊድን ያደረገው ኤሪክሰን ወደ አረቡ ዓለም በሚያደሉት የሰሜን አፍሪካ አገራት በመጪዎቹ ሁለት አመታት ቴክኖሎጂውን ሥራ ላይ ለማዋል ዕቅድ እንዳለው አስታውቋል።

እሸቴ በቀለ

ኂሩት መለሰ