አፍሪካን የጋረደዉ የለንደኑ ፍንዳታ | የጋዜጦች አምድ | DW | 13.07.2005
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

የጋዜጦች አምድ

አፍሪካን የጋረደዉ የለንደኑ ፍንዳታ

ባለፈዉ ሳምንት በስኮትላንድ ግሊንኤግሊስ ትኩረቱን በተለይ የአፍሪካን ችግር ለመፍታት አድርጎ የተካሄደዉ የስምንቱ በኢንዱስትሪ የበለፀጉ መንግስታት ጉባኤ በብሪታንያ ዋና ከተማ ለንደን በበርካታ ንፁሃን ዜጎችን ላይ ጉዳት ባደረሰዉ የቦንብ ፍንዳታ ተጋርዶ የረባ ዉጤት አልተገኘበትም ይላሉ የደቡብ አፍሪካ ምሁራን።

አደጋዉ በቴሌቭዥን በየቤቱ፤ በየቡና ቤቱና መዝናኛ ስፍራዉ የታየ ሲሆን በደረሰዉ ፍንዳታም ሁለት ዜጎቿ ከፍተኛ ጉዳት እንደደረሰባቸዉ ነዉ ደቡብ አፍሪካ የምትናገረዉ።
ምንም እንኳን መንግስት የተጎዱትን ዜጎቹን ስም ይፋ ባያደርግም የዜና ምንጮች እንደሚሉት ለንደን ዉስጥ በተለያዩ ሁለት ሃኪም ቤቶች እርዳታ እየተደረገላቸዉ ነዉ።
ጥቃቱንም የደቡብ አፍሪካዉ የዉጪ ጉዳይ ሚኒስቴር ምክትል ሚኒስትር አዚዝ ፓሃድ አረመኔያዊ ተግባር በማለት አዉግዘዉታል።
አደጋዉ እንደተነገረም በዓለም ዓቀፍ ሽብርተኝነት ዙሪያ አስተያየትና በጆሃንሰርግ በሚገኘዉ ዝነኛ ራዲዮ በስልክ ጥሪ በመጠቀም ሲስተናገድ ዉሏል።
በዚህም ሃሳብ ሰጪዎቹ ለፍንዳታዉ ምክንያት ይሆናል በማለት የወሰዱትን ሶስት የተለያየ ሃሳብ ይዘዉ ቀርበዋል።
አንደኛዉ ይህ ፍንዳታ የተፈፀመዉ ብሪታንያና ዩናይትድ ስቴትስ ሙስሊሙ ህብረተሰብ ላይ ጫና እንዲያደርጉ ታስቦ የተደገነዉ ይላል።
ሁለተኛዉ ሃሳብ ደግም የለም ይሄ ድርጊት የምዕራቡን ዓለም ህዝብ ከሙስሊሙ ዓለም ለማጋጨት ታቅዶ የተሸረበ ሴራ ነዉ በማለት ግምቱን ሰንዝሯል።
ሶስተኛዉ ሃሳብ ግን ይህ ድርጊት የአፍሪካን ችግር ታላቅ የመወያያ ነጥብ አድርጎ የተሰበሰበዉን የቡድን ስምንቱን ጉባኤ ቀልቡን ከአፍሪካ ጉዳይ ይልቅ ወደፀጥታና ደህንነት እንዲለዉጥ የተደረገ ነዉ ባይ ነዉ።
በእርግጥም በዚህ ጉባኤ ያለተቀናቃኝ ትኩረት ያገኛል ተብሎ ብዙ የተደከመበት የአፍሪካ የድህነት ጉዳይ እንደታደበዉ እንዳይሄድ ይህ ንፁሃንን ኢላማ ያደረገዉ የቦንብ ፍንዳታ አጨናግፎታል።
የእነዚህን መሪዎች ትኩረት ከአፍሪካን ችግር ላይ ለማስቀየር ታስቦ በለንደን አዉራ ጎዳናዎች ላይ ንፁሃንን በቦምፍ ፍንዳታ የፈጀዉን ይህን የጥፋት ድርጊት አልወደድነዉም ይላሉ የደቡብ አፍሪካዉ የንግድ ህብረት ቃል አቀባይ ፓትሪክ ክራቨን።
ለአይፒኤስ የዜና ወኪል እንደገለፁትም የአፍሪካ ዋና ችግር ድህነትና በልማት ኋላ መቅረት ነዉ በዚህ ድርጊት ተስፋ ቆርጠዉ የበለፀጉት አገራት የገበያ ዕድል ለአፍሪካ እንዲያመቻቹ የጀመሩትን የቅስቀሳ ተግባር አያቆሙም።
በቡድን ስምንቱ ጉባኤ በስፋት እንዲታይ የተፈለገዉ የንግድ እንቅፋት፤ በተለይም ለገበሬዎቻቸዉ የሚያደርጉት ድጎማ እንደታሰበዉ ያልተቃኘ ጉዳይ ነበር።
የብሪታንያዉ ጠቅላይ ሚኒስትር ቶኒ ብሌየር ዓርብ ዕለት በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫም ይህ ርዕሰ ጉዳይ በመጪዉ ታህሳስ ወር ሆንግኮንግ ላይ በሚካሄደዉ የዓለም የንግድ ድርጅት ጉባኤ ላይ ለዉይይት እንደሚቀርብ ነዉ የተናገሩት።
ያም ቢሆን ግን ለአፍሪካ እንዲጨመር የጠየቁት የእርዳታ ገንዘብ መጠን ተቀባይነት አግኝቶ በየዓመቱ ወደ 50ቢሊዮን ዶላር ከፍ ማለት ችሏል።
የብዙዎች ስጋት ደግሞ ገንዘቡስ ከመጪዉ የፈረንጆቹ 2010 ዓ.ም. ጀምሮ ሊሰጥ ይችላል በምን ላይ ይዉል ይሆን የሚል ነዉ።
ምናልባትም ድህነትን ከማስወገድ ላይ ከማተኮር ይልቅ የፀጥታና የደህንነት ጉዳይ ይቅደም ሊባል ይችላል። በዚህ ረገድም በደህነትና በመልካም አስተዳደር ዙሪያ ብዙ ይባል ይሆናል የሚል ግምትም እየተሰነዘረ ነዉ።
የቡድን ስምንቱ አገራት በዚያዉ ዓመት አፍሪካን ማዕከል ያደረገ ዓለም ዓቀፍ አገልግሎት የሚሰጥ 75,000 የሰላም አስከባሪ ጦር ለማስልጠን ተስማምተዋል።
በመግለጫቸዉም በዳርፉር ያለዉን ሁኔታ ለማረጋጋት ለአፍሪካ ህብረት የምንሰጠዉን ድጋፍ በመቀጠል ለሰላም በሚደረገዉ ጥረት የበኩላችንን እናደርጋለን ማለታቸዉ ተጠቅሷል።
በተጨማሪም ወባን ከአፍሪካ ለማጥፋት 1.5ቢሊዮን ዶላር መድበዋል ይህም የ600,000 ህፃናትን ህይወት ይታደጋል የሚል ተስፋ አሳድሯል።
የደቡብ አፍሪካዉ የፓለቲካ ተመራማሪ ሳም ዱቤ ይህ ሊታመን ይችል ይሆናል በንግድ ዘርፉ ግን ፍሬያማ ዉጤት ላይ የሚደርሱ አይመስለኝም በደፈናዉ ገበያቸዉን ለአፍሪካ ምርቶች ዝግ ማድረግ የመረጡ ይመስላል በማለት ለጋዜጠኞች ገልፀዋል።