አፍሪቃ እና የሳውዲ ዐረቢያ ተፅዕኖ | አፍሪቃ | DW | 11.11.2017
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

አፍሪቃ

አፍሪቃ እና የሳውዲ ዐረቢያ ተፅዕኖ

ባለፀጋ የሆኑ የሳውዲ ተወላጆች በአፍሪቃ መስጊዶችን ለማሰራት በብዙ ሚልዮን የሚቆጠር ገንዘብ ያፈሳሉ። ይሁንና እነዚህ ሳውዲዎች በሚቀጥሩዋቸው አክራሪ ሰባኪዎች የአህጉሩን ፀጥታ እያናጉ ነው በሚል ከአህጉሩ ተወላጆች ወቀሳ ይሰነዘርባቸዋል።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 12:09

የሳውዲ ዐረቢያ ተፅዕኖ በአፍሪቃ

በሴኔጋል መዲና ዳካር የሚገኝ የአንድ መስጊድ ባህላዊ የሀይማኖት አባት ሙሀመድ ንዲያይን የመሳሰሉ አፍሪቃውያን በቅሬታ እንደሚገልፁት የሳውዲ ባለፀጎች አላማ እምነታቸውን በአፍሪቃ በማስፋፋት ላይ ብቻ የተወሰነ አይደለም ። እንደ ንዲያይ አስተያየት፣ በአፍሪቃ እየጨመረ መጥቷል የሚሉት የሳውዲ ቱጃሮች እና የሳውዲ ዐረቢያ መንግሥት ተፅዕኖ ሙስሊም መዕመናን ሀይማኖታቸውን በነፃ እንዳይከተሉ ስጋት ደቅኖባቸዋል።

«ጥላቻቸው በግልጽ እንደሚታይ መናገር እችላለሁ። በኛ ዘንድ ሞራላዊ ተቀባይነት ያለውን ሁሉ ማጥፋት ነው የሚፈልጉት። ለምሳሌ፣ እኛ ባህላዊ የሀይማኖት አባቶች ጥቅም እንደሜለን እና እንደማናስፈልግ ወጣቶቻችንን ለማሳመን ይሞክራሉ።  ከዚህ በተጨማሪም፣ ልጆች ወላጆቻቸውን እንዲይታዘዙ፣ እንዲሁም፣በማንኛውም ማህበራዊ ደንብ እና መመሪያ አንጻር እንዲያምፁም ያደርጋሉ።

እንደ ባለፀጎቹ የሳውዲ ዐረቢያ ተወላጆች በአፍሪቃ የእስልምና እምነት ላይ በገንዘባቸው አማካኝነት ተፅዕኖ ያሳረፈ አንድም ወገን እንደሌለ ባህላዊ የሀይማኖት አባት ሙሀመድ ንዲያይ  አስታውቀዋል። በአህጉሩ እጅግ ድሀ እና ኋላ ቀር በሚባሉ አካባቢዎች መስጊዶችን፣ የቁርዓን ትምህርት ቤቶችን እና ሀኪም ቤቶችን ገንብተዋል፤ ሰባኪዎችን ልከዋል፤ ለአፍሪቃውያን ወጣቶችም በባህረ ሰላጤው ሀገራት ነፃ የስነ መለኮት ትምህርት ዕድል ሰጥተዋል፣ ይሰጣሉም። በገንዘባቸውም ሀይማኖታዊ ድርጅቶችን እና የዋሀቢ ሀራጥቃን ርዕዮት እና ንዲያይ ሳላፊስት የሚሉትን አስተሳሰብ የሚያራምዱ ሰዎችን ወደ አፍሪቃ ይልካሉ።

 
በዐረባውያን እና አፍሪቃውያን መንግሥታት መካከል ከብዙ ምዕተ ዓመታት ወዲህ የጠበቀ ኤኮኖሚያዊ እና ሀይማኖታዊ ግንኙነት አለ። ከነዳጅ ዘይት እና ከተፈጥሮ ጋዝ ሀብታቸው ከፍተኛ ገቢ ያስመዘገቡት ዐረባውያቱ ሀገራት፣ በተለይ፣ ሳውዲ ዐረቢያ ተፅዕኖዋን በሳህል አካባቢ በሚገኙ አፍሪቃውያት ሀገራት ውስጥ በጉልህ አሳድጋለች። የሳውዲ መንግሥት እና በግል የሚነቀሳቀሱ የሳውዲ ተወላጆች ማሊ፣ ሴኔጋል ወይም ናይጀሪያን በመሳሰሉ ሀገራት ውስጥ የፊናንስ ድጋፍ ያደርጋሉ። ይህንን ድጋፋቸውንም እንደ ሀይማኖታዊ ግዴታቸው ይመለከቱታል፣ ምክንያቱም፣ ችግረኞችን መርዳት ከአምስቱ የእስልምና ምሰሶዎች መካከል አንዱ በመሆኑ።  ይሁንና፣ ይኸው የሳውዲ መንግሥት እና የሳውዲ ተወላጆች ርዳታ በነፃ የሚሰጥ ሳይሆን ቅድመ ግዴታ አርፎበታል። ለምሳሌ ሴኔጋላውያኑ ኢማሞች በሳውዲ ዐረቢያ እንደሚሰለጥኑ እና ወደ ትውልድ ሀገራቸው ሲመለሱ ስለ ወግ አጥባቂው እስልምና እንደሚሰብኩ ባህላዊ የሀይማኖት አባት ሙሀመድ ንዲያይ አመልክተዋል። 

« ከሴኔጋል ወደ ሳውዲ ዐረቢያ፣ ካታር፣ ኩዌት የሄዱ አንዳንድ ወጣቶች በጣም አክራሪ አመለካከት ይዘው ነው የሚመለሱት። ይህ ወላጆቻቸውን ሳይቀር አስገርሟል። »
በሳህል አካባቢ ከሚኖረው ሕዝብ መካከል ብዙው ምሥጢራዊ እና መንፈሣዊ የሚባለውን የሱፊ አስተምህሮ ይከተላል። ይሁንና፣ ወግ አጥባቂዎቹ ሳውዲዎች ይህንን እንደ እስልምና እምነት አይቆጥሩትም።  በሶማልያ መንግሥት አንፃር የሚዋጋው አሸባብ፣ በማግሬብ ሀገራት የሚንቀሳቀሰው አክሚ ወይም የናይጀሪያ ዓማፂ ቡድን ቦኮ ሀራምን የመሳሰሉ አሸባሪ ቡድኖችም ይህንኑ የወግ አጥባቂዎቹ ሳውዲዎች ትክክለኛ አድርገው የሚመለከቱትን ርዕዮት ይከተላሉ። ብሩህ የወደፊት ዕድል እንደሌላቸው የሚሰማቸው እና ስራ አጥ የሆኑ ወጣቶች አዘውትረው የባለፀጎቹ ሙስሊሞች ርዳታ ወጥመድ ውስጥ ይገባሉ፣ እንደ ባህላዊ የሀይማኖት አባት ሙሀመድ ንዲያይ አስተያየት።  በየመስጊዶች ምግብ እና መጠጥ በነፃ ይታደላል። 


« አነጋገራቸው ራሱ አክራሪነታቸውን ያሳያል። እኛ በምንከተለው የእስልምና ሀይማኖት ከምናውቀው የተለየ ፅንፍ የያዘ ክርክር እና ውይይታ ያካሂዳሉ። ይህ ስጋት መደቀኑን ጠቋሚ ነው፣ ምክንያቱም፣ እስካሁን የታዩ ዓመፆች ሁሉ የተጀመሩት እንዲህ ነው። ልክ በማንኛውም ጊዜ ሊፈነዳ እንደተቃረበ የተዳፈነ እሳተ ጎመራ ነው። እና በነዚህ ሰዎች ውስጥ የታመቀው ቁጣ በሚገነፍልበት ጊዜ ለኛ ጥሩ አይሆንም፣ እንዴት እንደሚያበቃም የሚያውቅ የለም። እግዚአብሔር ከዚህ ይጠብቀን።  »  

በወግ አጥባቂ የሳውዲ ሰባኪዎች ስብከት ፅንፍ የያዙ የአክራሪው አንሳር ዲን ቡድን አባላት በጎርጎሪዮሳዊው 2012 ዓም በሰሜን ማሊ የቲምቡክቱ ከተማ በርካታ ከፍተኛ ሀይማኖታዊ ትርጓሜ ጭምር የያዙ ጥንታውያን ቅርሶችን ማፍረሳቸውን ንዲያይ ቢያስታውሱም፣ የፅንፈኞቹ እንቅስቃሴ በወቅቱ ቀንሷል ይላሉ።
« በማሊ የታየውን ቀውስ ተከትሎ በተወሰደው ርምጃ እና ባረፈው ዓለም አቀፍ ግፊት ሰበብ ባካባቢው ሁኔታዎች መረጋጋት አሳይተዋል። በዚህም የተነሳ እነዚህ ንቅናቄችም ትኩረት ውስጥ እንዳይገቡ በማለት እንቅስቃሴአቸውን ለመቀነስ ሞክረዋል። »

ይሁንና፣ በሀምበርግ የሚገኘው የጀርመን ዓለም አቀፍ እና አካባቢያዊ ጥናት ተቋም፣ በምህፃሩ የጊጋ ባልደረባ የንስ ሀይባኽም ልክ እንደ ባህላዊው የሀይማኖት አባት ሙሀማዱ ንዲያይ፣  በአፍሪቃ የገንዘብ ርዳታ የሚሰጡት ወግ አጥባቂዎቹ  የሳውዲ ተወላጆች ትክክለኛ የሚሉትን የእስልምና እምነት ማስፋፋት ብቸኛው ዓላማቸው አይደለም ይላሉ። ለዚህ አባባላቸው ግን ሀይባኽ የሰጡት ምክንያት ከንዲያይ ይለያል። እንደ ሀይንስ ሀይባኽ አስተያየት፣ የሳውዲዎቹ ርዳታ የሀገራቸውን የምግብ ዋስትና በዘላቂነት የማረጋገጥ ዓላማ የያዘ ነው።
የሳውዲ ተወላጆች አፍሪቃ ውስጥ በተለይ፣ በግብርናው ዘርፍ ትልልቅ ፕሮዤዎችን መጀመር ይፈልጋሉ። በብሪታንያውያኑ ዕለታዊ ፋይናንሻል ታይምስ ዘገባ መሰረት፣ የሳውዲ ዐረቢያ መንግሥት በጎርጎሪዮሳዊው 2016 ዓም ወደ አራት ቢልዮን ዶላር ወረት አፍስሷል። 


« አፍሪቃ በወቅቱ ለሳውዲ ምርት እና ወረት ጥሩ ገበያ ሆና እየሆነች መጥታለች። ይህን ተከትሎም የሳውዲ ዐረቢያ አልጋ ወራሽ መሀመድ ቢን ሳልማን  በሀገሪቱ ኤኮኖሚዊ  እና ፖለቲካ ላይ ተሀድሶ ለማድረግ እየሞከሩ ነው። ለዚህም አፍሪቃ ዋና ሚና ይዛለች።» 

የነዳጅ ዘይት ዋጋ በአሁኑ ጊዜ  እየቀነሰ በመምጣቱ የሳውዲ ዐረቢያ የበጀት ሚዛን ጉድለት ደርሶበታል። ስለዚህ አልጋ ወራሽ መሀመድ ቢን ሳልማን ለሀገራቸው ሌላ የገቢ ምንጭም ማዘጋጀት አስፈላጊ ሆኖ አግኝተውታል። ርዕይ 2030 በሚለው እቅዳቸውም አማካኝነት በሚቀጥሉት 13 ወራት የሀገሪቱን ኤኮኖሚ ዘርፎች ለማስፋፋት ወስነዋል። አልጋ ወራሹ ከጥቂት ጊዜ በፊት በመዲናይቱ ሪያድ በተካሄደ የኤኮኖሚ መድረክ ላይ ባሰሙት ንግግር  የመንግሥታቸውን  እጅግ ወግ አጥባቂ መስመር ለዘብተኛ ለማድረግ፣ ብሎም፣ በዓለም እና በተለያዩት ሀይማኖቶች አኳያ ግልጽ የሆነ ለዘብተኛ እስልምናን እንደገና ለማስተዋወቅ ማሰባቸውን ገልጸዋል። ይሁንና፣ ለዘብተኛ እስልምና ሲሉ ምን ማለታቸው መሆኑን አልጋወራሹ በግልጽ አልዘረዘሩም።  

ይህ አነጋገራቸው በተግባር ከተተረጎመ፣ ይላሉ የጀርመናውያኑ ፖለቲካ ጥናት ተቋም፣ ጊጋ ባልደረባ የንስ  ሀይባኽ ፣ ይህ በዓለም ለሳውዲ አልጋወራሽ ያለውን አመለካከት ከማሻሻል ጎን የውጭ ባለወረቶች ወደ ሳውዲ በመሄድ ገንዘባቸውን እንዲያሰሩም ሊያደርግ ይችል ይሆናል። ይህ እውን ይሆን ዘንድ፣ በመጀመሪያ በሳውዲ ህብረተሰብ ውስጥ ያለው ወግ አጥባቂው መዋቅር መፍረስ ይኖርበታል። በተለይ ፣ በየትምህርት ቤቶች እና ዩኒቨርሲቲዎች ያሉ መምህራን አስተሳሰብን በጥቂት ቀናት መቀየር አይቻልም፣ ይህ ትልቅ ተግዳሮት ነው የሚሆነው።  በዚህም የተነሳ የሳውዲ ዐረቢያ መንግሥት አሁን በአፍሪቃ እየተስፋፋ ነው የተባለውን አክራሪ እስልምናን ለማለዘብ ያሰማው እቅዱን ገቢራዊ ማድረጉ ቀላል  ስለማይሆን  የእቅዱን መሳካት ሀይባኽ አብዝተው  ተጠራጥረውታል። ምክንያቱም፣ በግል ገንዘባቸውን በአህጉሩ የሚያሰሩ የሳውዲ ባለፀጎች የራሳቸውን አክራሪ ዓላማ ነው የሚያራምዱት። 

«የምናውቀው የሳውዲ ንጉሣዊ መንግሥት ባለስልጣናት አፍሪቃ ውስጥ የሽብር ተግባር ለማስፋፋት በሚፈልጉ ድርጅቶች አንፃር ርምጃ ለመውሰድ እየሞከረ ነው። ይህ ግን ዞሮ ዞሮ በገዢው መንግሥት ፀጥታ ላይ ስጋት ሊደቅን ይችላል። »


እርግጥ፣ የሳውዲ መንግሥት አሸባሪ ድርጅቶችን እንደሚታገል ቢያስታውቅም፣ ፅንፈኝነትን ለማስፋፋት የሚደረገውን ድጋፍ፣ በተለይ ገንዘብ በእጅ የሚሰጥበትን ዓይነቱን ርዳታ መቆጣጠሩ እጅግ አዳጋች እንደሚሆን ሀይባኽ ገልጸዋል። 

በሴኔጋል የጋስቶን ዩኒቨርሲቲ የሀይማኖት ትምህርት የሚያስተምሩት ባክሪ ሳምቤ የሳውዲ አልጋወራሽ መሀመድ ቢን ሳልማን ርዕይ 2030 የተባለው እቅድ በአፍሪቃ ላይ አዎንታዊ ውጤት ይኖረዋል ባል ናቸው። 
« ይህ ወሳኝ ተፅዕኖ በማሳረፍ በዋሀቢቶች እና በሳላፊስቶች ንቅናቄ አቋምን ጥንካሬ ይቀንሳል። እና አንዱ ባንዱ አንፃር ርምጃ ሊወስዱ አይችሉም። ይሁንና፣ ይህ ከሳውዲ ዐረቢያ ጋር ያለውን ትብብር ይቀይረዋል።»
ይሁንና፣ ሴኔጋላዊው የዩኒቨርሲቲ መምህር ባክሪ ሳምቤም ይህ አክራሪ ሳውዲ ዐረቢያም ሆነ አፍሪቃ ውስጥ አክራሪ እስልማናን ያጠፋል ብለው አያስቡም። 

አርያም ተክሌ/ግዌንዶሊን ሂልዘ
ልደት አበበ

Audios and videos on the topic

ተዛማጅ ዘገባዎች