አፍሪቃ እና የምዕተ ዓመቱ የልማት ግብ | አፍሪቃ | DW | 10.06.2013
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

አፍሪቃ

አፍሪቃ እና የምዕተ ዓመቱ የልማት ግብ

አፍሪቃ ፣ ምንም እንኳን እስከ እአአ እስከ 2015 ዓም ድረስ የምዕተ ዓመቱን የልማት ግብ ማሳካት ባትችልም፣ በልማቱ ዘርፍ ጉልህ መሻሻል ማስመዝገቧ የማይካድ ነው። አፍሪቃ በተለይ የምዕተ ዓመቱ የልማት ግብ ባስቀመጣቸው የመጀመሪያዎቹ አራት መስኮች፣ ማለትም፣ ድህነትን

በማጥፋት፣ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርትን ለሁሉም በማዳረስ፣ የሕፃናትን ሞት በመቀነስ፣ እንዲሁም፣ ወባ፣ የሳምባ ነቀርሳ እና ኤች አይ ቪ ኤድስን የመሳሰሉ ተላላፊ በሽታዎችን በመታገሉ ረገድ ትክክለኛውን ርምጃ በመውሰድ ላይ ትገኛለች። የአፍሪቃ ህብረት፣ የተመድ እና የአፍሪቃ የልማት ባንክ ከጥቂት ጊዜ በፊት በጋራ ያወጡት ዘገባ ይህንን አዎንታዊ ሂደት አረጋግጦዋል። የተመድ እአአ በ 2000 ዓም ለምዕተ ዓመቱ የልማት ግብ ያሰቀመጠው የ 2015 ዓም የጊዜ ገደብ ሊጠናቀቅ 1000 ቀናት ቀርተውታል።


በዓለም የምዕተ ዓመቱን የልማት ግብ በማሳካቱ ጥሩ ውጤት ካስመዘገቡት 20 ሀገራት መካከል 15 ቱ አፍሪቃውያት ሀገራት ናቸው። የተመድ የልማት መርሐ ግብር መሥሪያ ቤት፣ በምሕፃሩ ዩ ኤን ዲ ፒ የፖሊሲ አማካሪ አዮዴሌ ኦዱሶላ እንዳስታወቁት፣ ቡርኪና ፋሶ፣ ሞዛምቢክ፣ ናሚብያ እና ርዋንዳ ቀዳሚውን ቦታ ይዘዋል። በተለይ ርዋንዳ የሴቶችን ተሳትፎ በማሳደጉ ላይ የተጫወተችው ሚና የሚደነቅ መሆኑን ነው የምዕተ ዓመቱ የልማት ግብ ዕቅድን ካረቀቁት መካከል አንዱ የነበሩት ኦዱሶላ የገለጹት።
« በብሔራዊ ምክር ቤቶች ውስጥ የተወከሉትን ሴቶች ቁጥር ብንመለከት፣ ርዋንዳ በዓለም ብዙ ሴቶች እንደራሴዎች ያሉባት ሀገር ሆና እናገኛታለን። በርዋንዳ ምክር ቤት ውስጥ ከተወከሉት እንደራሴዎች መካከል የሴቶቹ ቁጥር 56% ነው። »

Juliette mag am liebsten Englischunterrichtአንዳንዶቹ የምዕተ ዓመቱ የልማት ግቦች ተዛማጅ እንደመሆናቸው መጠን፣ ለምሳሌ ወጣት ልጃገረዶችን በማስተማር የሴቶችን ተሳትፎ ማሳደግ ይቻላል። ሕፃናት በጠቅላላ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት እንዲያገኙ የማድረጉ ዓላማ አፍሪቃ ታሟላዋለች ተብሎ የሚጠበቅ ግብ ነው። የአፍሪቃ ህብረት፣ የተመድ እና የአፍሪቃ የልማት ባንክ ከጥቂት ጊዜ በፊት በጋራ ያወጡት ዘገባ እናዳመለከተው፣ በብዙ አፍሪቃውያት ሀገራት ውስጥ በወቅቱ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት በመከታተል ላይ የሚገኙት ሐፃናት ቁጥር ወደ 90% ከፍ ብሎዋል። ሕፃናቱ የሚጓዙትን መንገድ መቀነስ እና በዚያው በትምህርት ቤታቸው ምግብ እንዲቀርብላቸው መደረጉም ለሕፃናቱ ትምህርት መከታተሉን አመቻችቶላቸዋል። ይሁን እንጂ፣ ይህ ብቻውን በቂ አለመሆኑን ያስረዱት በናይሮቢ፣ ኬንያ በሚገኘው የኮሎምቢያ ዓለም አቀፍ ማዕከል የምዕተ ዓመቱን የልማት ግብ የትምህርት ጉዳይ አማካሪ ወይዘሮ ሱዛን ካሩቲ ወላጆች ልጆቻቸውን ወደ ትምህርት ቤት ለምን መላክ እንዳለባቸው ማሰረዳት ወሳኝ ነው ይላሉ።
« የማህበረሰቡ ቡድን ሰራተኞች አንድም ከቤት ቤት በመዘዋወር ወይም የውይይት መድረክ በማዘጋጀት ስለትምህርት ጥቅም የሚያስረዱባቸውን መዋቅሮች ዘርግተናል። የዚሁ መዋቅር ዓላማ በማህብረሰቡ ያሉትን ቤተሰቦች ሁኔታ እና ፍላጎታቸውን በሚገባ የሚረዱ የማህበረሰቡ አባላት እንዲኖሩ ማድረግ ነው። »ሕፃናትን በለጋ ዕድሜአቸው ለመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ከማስመዝገቡ ጎንም፣ ይህንኑ ትምህርታቸውን እንዲያጠናቅቁ ማበረታታት ወሳኝ ይሆናል። ይሁንና፣ የእስከዛሬ ተሞክሮዎች እንዳሳዩት፣ ልጃገረዶች በተለያዩ ምክንያቶች፣ ለምሳሌ፣ በለጋ ዕድሜአቸው በሚዳሩበት ምክንያት የተነሳ ወደ ትምህርት ቤት አይሄዱም።
« አንዳንዶቹ ልጃገረዶች ለአቅመ ሔዋን በሚደርስበት ጊዜ አዘውትረው ወደ ትምህርት ቤት የማይመጡባቸው ወይም ለወር አበባ የሚያስፈልጋቸው የመፀዳጃ ቁሳቁስ ስለሚጓደላቸው ከትምህርት ቤት የሚወጡባቸው አካባቢዎች እንዳሉ ታዝበናል፤ እና ትምህርታቸውን እንዳያቋርጡ ለማድረግ አስፈላጊውን ርዳታ አቅርበናል። »
ወደ ትምህርት ቤት የሚሄዱት ሕፃናት ቁጥር ከፍ ማለት እና ትምህርታቸውንም በደንብ መከታተላቸው የሚሞገስ ቢሆንም፣ የትምህርቱን ጥራት ማረጋገጥም አስፈላጊ እንደሆነ ወይዘሮ ሱዛን ካሩቲ ገልጸዋል።
« ቀጣይ ትኩረታችን የሚያርፈው ወደ ትምህርት ቤት የሚሄዱትን ሕፃናት ቁጥር በማሳደጉ እና የትምህርቱን ደረጃ በማሻሻሉ ላይ ይሆናል። ምክንያቱም ፣ ለዚህ ጉዳይ አሁኑኑ ትኩረት ካልሰጠን፣ ተማሪዎቹ ወደ ሁለተኛ ደረጃ በሚሸጋገሩበት ሁኔታ ላይ ተፅዕኖ ሊያሳርፍ ይችል ይሆናል። »አፍሪቃውያቱ ሀገራት ጥሩ ውጤት ያስመዘገቡበት ሌላው ዘርፍ በኤች አይቪ ኤድስ፣ በሳምባ ነቀርሳ እና በወባ አንፃር ባደረጉት ትግላቸው ነው። መድሀኒት የተረጨባቸው አጎበሮች ወባን፣ ከኤች አይቪ/ኤድስ ጋ ለሚኖሩ ሕሙማን የሚሰጡት እንክበሎቸም የበሽታዎቹን መስፋፋት ለመግታት የሚደረገውን ጥረት ማገዛቸው ተመልክቶዋል። በተለይ፣ የኤድስ ተሕዋሲ ከእናት ወደ ልጅ እንዳይተላለፍ ከፍተኛ ጥረት መደረጉን የጤና ጥበቃ ጉዳይ አማካሪ ወይዘሮ ሞሪን አዱዳንስ ቢያስታውቁም፣ ገና መሰራት ያለበት ብዙ ጉዳይ መኖሩን አስረድተዋል።
« አሁንም ማስታወስ ያለብን አፍሪቃ ውስጥ በሽታው መስፋፋቱን ወይም ከኤድስ አስተላላፊው ተሕዋሲ ጋ የሚኖሩ ብዙ ሰዎች መኖራቸውን ነው። በተለይ ሴቶች ከወንዶች ይበልጥ በተሕዋሲው የሚያዙበት አጋጣሚ አሁንም እንደበፊቱ ከፍተኛ ነው። በአፍሪቃ ተሕዋሲው በደማቸው ከሚገኝባቸው አዳዲሶቹ ሕሙማን መካከል ሴቶች 60% ይሸፍናሉ። »

የተመድ የምዕተ ዓመት የልማት ግብ ዓላማዎችን ለማሳካት አፍሪቃ ከፍተኛ ጥረት በማድረግ ላይ ብትሆንም፣ በተቀመጠው የጊዜ ገደብ ውስጥ እጅግ የከፋውን ድህነትን እና ረሀብን በግማሽ መቀነስ አይሳካላትም። የጀርመን ዓለም አቀፍ እና ያካባቢ ጥናት ተቋም ተንታኝ ሌና ጊዝበርት ይህን በተመለከተ የወጡ ጥናቶችን በመጥቀስ እንዳስታወቁት፣ እንዳሳዩት፣ አፍሪቃ ጥሩ ውጤት ካስመዘገቡት መካከል ብትቆጠርም፣ የአፍሪቃውያቱ ሀገራት ርምጃ እኩል አይደለም።
« ጋና፣ ዩጋንዳ ፣ ኢትዮጵያ እና ርዋንዳን የመሳሰሉ ሀገራት በተፈጥሮ ሀብታቸው ላይ ብቻ ጥገኛ ያልሆነ ዕድገት አሳይተዋል። ድህነትን በመቀነሱ ረገድ ሌሎች ሀገራት ወደ ኋላ እንደቀሩ ይገኛሉ። ለምሳሌ፣ ከሰሀራ በስተደቡብ ባሉት ኒዠር፣ ቻድ፣ ማሊ ወይም ቡርኪና ፋሶን በመሳሰሉ የሳህል አካባቢ ሀገራት ውስጥ ፀረ ድህነቱ ትግል ንዑሱን ውጤት ነው ያሰገኘው፤ ያስመዘገቡትም ዕድገት እንዲሁ ንዑስ ነው። በምዕራብ እና በማዕከላይ አፍሪቃ በሚገኙት ቶጎ፣ ካሜሩን፣ የማዕከላይ አፍሪቃ ሬፓብሊክን በመሳሰሉት ሀገራት ውስጥ ደግሞ በተለይ በኤኮኖሚ እና በፖለቲካ አለመረጋጋት የተነሳ በጣም ንዑስ ስኬት ነው ያሰገኙት። »

አፍሪቃ የእናቶችን ሞት በመቀነሱ ጥረትዋ ላይ ጥሩ ወጤት ማስገኘቷን የዩ ኤን ዲ ፒ የፖሊሲ አማካሪ አዮዴሌ ኦዱሶላ ገልጸዋል፣ እርግጥ፣ በምዕተ ዓመቱ የልማት ግብ መሠረት፣ ይኸው ቁጥር እአአ በ 2015 ዓም ድረስ ወደ 75% ዝቅ ማለት ነበረበት፣ ግን እስካሁን የተደረሰው 42% ብቻ ነው። ኦዱሶላ እንዳስረዱት፣ በናይጀሪያ የኦንዶ ፌዴራዊ ግዛት ባዘጋጀው « ሴፍ ማዘርሁድ ፕሮግራም» የተባለው መርህግብር ነፍሰ ጡር እናቶች ነርሶች እና ዶክተሮች ወደ ቤታቸው በመሄድ ርዳታ እንዲያደርጉላቸው መጠየቅ እንዲቸሉ የሞባይል ስልክ አድለዋል፤ ሞዛምቢክም የወሊድ ዕለታቸው ለደረሱ ነፍሰ ጡሮች የሚጠባበቁባቸው ቤቶች ትሰጣለች።
« እነዚህ መጠባበቂያ ቤቶች ሴቶቹ በሚወልዱባቸው ሀኪም ቤቶች አቅራቢያ ነው የሚገኙት። ነፍሰ ጡሮች ሊወልዱ ሁለት እና ሦስት ቀናት ሲቀራቸው የሚያርፉባቸው ቤቶች ናቸው። በነዚሁ ቀናት የሚያስልጋቸውን መድሀኒት እና ሕክምና በነፃ ያገኛሉ። »
ደሞዝ እኩል የሚከፈልበት፣ የፆታ እኩልነትን፣ እንዲሁም፣ በገጠሩ እና በከተሞች ማዕከላት መካከል የሚታየውን ልዩነት ለማስወገድ አፍሪቃ እአአ ከ 2015 ዓም በኋላም ጠንክራ መስራት እንደሚገባት አሳስበዋል።

አርያም ተክሌ/ሳራ ሽቴፈን

መሥፍን መኮንን

Audios and videos on the topic