አፍሪቃ እና ወባ | ጤና እና አካባቢ | DW | 29.04.2014
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

ጤና እና አካባቢ

አፍሪቃ እና ወባ

የዓለም የጤና ድርጅት የወባ በሽታ አፍሪቃ ዉስጥ በያንዳንዷ ደቂቃ አንድ ልጅ ትገድላለች ይላል። ጋዜጠኛ አንትየ ዲክሃንስ እንደምትለዉ ማዕከላዊ አፍሪቃ ሪፑብሊክ ዉስጥ ወባ ዛሬም የበርካታ ሕፃናትን ሕይወት ከሚቀጥፉ በሽታዎች ግንባር ቀደሙ ነዉ።

በወባ ምክንያት በየዓመቱ ሕይወታቸዉ ከሚያልፍ ከ600 ሺህ በላይ ሰዎች አብዛኞቹ ከአፍሪቃ እንደሆኑ ከእነሱ መካከልም ብዙሃኑ ሕፃናት እንደሆኑ መረጃዎች ያመለክታሉ። ወባን ለመከላከል የሚያስችል ክትባት ለማግኘት የተመራማሪዎች ጥረት እንደቀጠለ ቢሆንም ለብዙሃኑ እንደልብ የሚገኝ ይህ መድሃኒት በገበያዉ ላይ ዉሏል የሚለዉ የምሥራች ገና አልተሰማም። እናም ዛሬም በርካታ አፍሪቃዉያን በወባ መጎዳታቸዉ አልተገታም። ምዕራብ አፍሪቃዊቱ ሀገር ቡርኪናፋሶ የወባ በሽታ ክፉኛ ከሚያጠቃቸዉ ሃገራት አንዷ ናት። በርካታ ሕፃናት በየጊዜዉ በበሽታዉ ይሰቃያሉ። ሀገሪቱ በተለይ ትምህርት ቤት የሚሄዱ ልጆች ላይ ያተኮረ መርሃግብር በመዘርጋት ሕፃናቱን ከወባ ለመታደግ ከፍተኛ ጥረቷን ተያይዛዋለች። ቀደም ሲል ሲል ሲዘምሩ ያደመጣችሁት ሕፃናም ዚኒየር በተሰኘችዉ የቡርኪናፋሶ ከተማ የሚገኝ የአንድ ትምህርት ቤት ተማሪዎች ናቸዉ። አብዛኞቹ የስምንት ዓመት ሕጻናት ሲሆኑ ለጉብኝት ክፍላቸዉ የተገኙ ጋዜጠኞችን ነዉ በዝማሬ የተቀበሉት።

በሌሎች የአፍሪቃ ሃገራት እንደሚገኙ ተማሪዎች ሁሉ እነሱም ስለወባ ከመጽሐፍት ብቻ የሚሰሙና የሚማሩ ዓይነቶች አይደሉም። ወባ ምን እንደሆነች እንዴት ያለ ጉዳት በጤናቸዉ ላይ እንደምታደርስ በተግባር ያዉቁታል።

«ወባ ይዞት የሚያዉቅ ማን ነዉ?»

መምህራቸዉ ጠየቋቸዉ። ጥያቄዉን ተከትሎ ሰማንያ የሚሆኑ ልጆች እጃቸዉን አወጡ። ከመካከላቸዉ እስካሁን በወባ በሽታ ያልተያዘ አንድ ተማሪ ብቻ ነዉ።

የቡርኪናፋሶ መንግስት ወባን ለማጥፋት የሚያደርገዉ ትግል ቅድሚያ ከሚሰጣቸዉ ተግባራቱ ዋነኛዉ መሆኑን ይናገራል። ምዝን የአየር እርጥበታቸዉ ከፍተኛ በሆነ አካባቢዎች የሰዎችን ሕይወት በመቅጠፍ አቻ ያልተገኘለት የጤና እክል ይኸዉ የወባ በሽታ ነዉ። 17 ሚሊዮን ነዉ የቡርኪናፋሶ ሕዝብ። ባለፈዉ ጎርጎሪዮሳዊ ዓመት ማለትም በ2013 7 ሚሊዮን ሕዝብ ወባ ታሞ እንደነበር ተመዝግቧል። የሀገሪቱ የጤና ጥበቃ ሚኒስትር ሌኔ ሴብጎ በአምስት ዓመታት ዉስጥ በሀገሪቱ በወባ በሽታ የሚያዘዉን ሰዉ ቁጥር በግማሽ ለመቀነስ ያለመ እቅድ ነድፈዋል። በዚህ መርሃግብርም ትምህርት ቤት የሚሄዱ ሕፃናት ከፍተኛ ጠቃሚ ሚና ሊጫወቱ እንደሚችሉ በቡርኪናፋሶ የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር የብሄራዊ የወባ መቆጣጠሪያ መርሃግብር አስተባባሪ ፓትሪክ ኮምባሪ፤

«ትምህርት ቤት በሚሄዱ ሕጻናት ላይ የምናተኩርበት ምክንያት መምህራኖቻቸዉን ስለሚያዳምጡ ነዉ። መምህራኑ የነገሯቸዉን እነሱም ይደግሙታል፤ በልባቸዉ ያዉቁታል። መምህራኖቻቸዉንም ይከተላሉ።»

ተማሪዎቹን ወባን እንዴት መከላከልና ሲታመሙም ለመዳን የሚችሉባቸዉን ስልቶች ማስተማር የብሄራዊዉ የትምህርት መርሃግብር አካል ነዉ። እያንዳንዱ ተማሪ ፈተናዉን ለማለፍ ወባን የመከላከል ወርቃማ መመሪያዎችን ማወቅ ይኖርበታል። ልጆቹ በቃላቸዉ እስኪይዟቸዉ ድረስም መምህራኑ እነዚህን መመሪዎች ደጋግመዉ ያስረዳሉ።

«ወባን እንዴት ነዉ የምትከላከሉት? የወባ ትንኝ እንዳትነክሰን በመከላከል! ይህ በቂ ነዉ? አይደለም! ትንኟንም መግደል ይኖርብናል!»

በወታደራዊ ስልት ልጆቹ ለመምህራቸዉ መልሶቹን ጮክ ብለዉ ይመልሳሉ። ወባን የመከላከል ወርቃማ መመሪያዎች የቡርኪና ፋሶ ሥርዓተ ትምህርት አካል ከሆነ አስርት ዓመታት ተቆጥረዋል። ሆኖም መንግስት በቅርቡ የማስተማሪያዉን ስልት አሻሽሏል። ቀደም ሲል መምህራን ልጆቹ ማድረግ የማይገባቸዉን ይነግሯቸዉ ነበር አሁን ግን ሊያደርጉ የሚገባቸዉን ደጋግመዉ ያስተምራሉ።

Kampf gegen Malaria in Burkina Faso Gesundheitsminister Léné Sebgo

የቡርኪናፋሶ የጤና ጥበቃ ሚኒስትር

ትምህርቱ በጨዋታ፤ እንደቲያትርም በጭዉዉት ልጆቹ ተሳታፊ እየሆኑ ይቀርባል። ያለ አጎበር የተኙ ሰዎችን ምስል እያሳዩ እንዲህ ማድረግ አይገባም በሚል ያስረዷቸዉ የነበረዉን አቀራረብ ለዉጠዉ መምህራኑ አሁን በአጎበር ተከልለዉ የተኙ ሰዎችን ምስል ያሳያሉ፤ ይህ አዎንታዊ አቀራረብ ነዉ። ልጆቹም መመሪያዉን ይደጋግማሉ። ለዚሁ ጉዳይ አንድ ፈረንሳዊ ባለሙያ በአጭሩ በእንግሊዝኛ «ሞስክ ኪት» የተሰኘዉ ን ማስተማሪያ አዘጋጅተዋል። ተማሪዎቹ እንደዋዛ መመሪያዎቹን እንዲያጠኑ በሚያደርገዉ በዚህ የሰንጠረዥ ጨዋታ ቀይ መስመር ዉስጥ ከገቡ የባህሪ ስህተትን ያመለክታል እና ልጆቹ ምስሉ ምን እንደሚያሳይ እንዲገልፁ ይጠያቃሉ። ለምሳሌ አንድ ሰዉ የወባ መድሃኒት በአካባቢዉ ከሚገኝ ገበያ ሲገዛ የሚያሳይ ምስል ሊሆን ይችላል። እናም ልጆቹ ስለወባ መከላከል የተማሩትን መመሪያ ተከትለዉ በሰንጠረዡ ላይ በመፈለግ መጠቆሚያዋን በአግባቡ ከመድሃኒት ቤት የወባ መድሃኒት የሚገዛ ሰዉ ምስል ላይ ያሳርፋሉ። በዚህ ጨዋታ ከባልንጀሮቹ ቀድሞ ደስተኛ እና ከወባ ነፃ የሆነ መንደር የሚለዉ ክልል ዉስጥ መጠቆሚያዋን ያስገባ አሸናፊ ይሆናል።

«ሞስኪ ኪት» በአይቮሪ ኮስት ትምህርት ቤቶች ሥራ ላይ ከዋለ ከርሟል። ቡርኪናፋሶ ይህን የማስተማሪያ ስልት የቀዳች ሁለተኛ ሀገር መሆኗ ነዉ። ፓትሪክ ካምባሪ አዲሱ ዘዴ በቅርቡ ዉጤት ያስገኛል የሚል ተስፋ አላቸዉ።

«ልጆቹ ቤተሰቦቻቸዉና ጎረቤቶቻቸዉ የወትሮ ልማዳቸዉን እንዲተዉ ማሳመን ይችላሉ ተብሎ ይታመናል። በዚህም ወባን ለማጥፋት የሚደረገዉን ትግል ይደግፋሉ።»

መርሃግብሩ አዲስ ነዉ። በዚያ ላይ መምህራኑን ማሰልጠንና ማስተማሪያዉን ለመግዛት ደግሞ ጠቀም ያለ ገንዘብ እንደሚጠይቅ ካምባሪ ያመለክታሉ። እሳቸዉ እንደሚሉትም ቡርኪናፋሶ በዓመት 12 ትምህርት ቤቶች ይህን የማስተማሪያ ስልት ከነየጨዋታ ዘዴዉ እንዲቀስሙ የማድረግ አቅም ብቻ ነዉ ያላት። እንዲያም ሆኖ ገና ከአሁኑም በማኅበረሰቡ ዉስጥ ለዉጦች መታየት ጀምረዋል። ካምባሪ እንደሚሉትም ለዉጡ በልጆቹ ላይ ይታያል። ልክ የዚነየር ትምህርት ቤት ተማሪ እንደሆነዉ እንደዚህ ታዳጊ ወጣት ማለት ነዉ፤

«ቤት የሚገኘዉ የወባ መከላከያ አጎበሬ ተቀዶብኝ ነበር። ወላጆቼን እንዲቀየይሩልኝ ነገርኳቸዉ። ትምህርት ቤት እንደተማርነዉ ማለት ነዉ። እናም ቤተሰቦቼ በማግስቱ ቀየሩት።»

እንዲያም ሆኖ ግን በልጆቹ ማስተማሪያ ጨዋታ ላይ እንዳለዉ ከወባ ነፃ እንደሆነዉ መንደር ቡርኪናፋሶ ከዚህ በሽታ ላንዴና ለመጨረሻ ጊዜ እስክትገላገል ጊዜ መዉሰዱ አይቀርም።

ወደማዕከላዊ አፍሪቃ ሪፑብሊክ ጎራ ስንልም በተመሳሳይ በወባ በሽታ ስቃይ የተጨነቁ በርካቶችን እናገኛለን። ባንጊ ከተማ በሚገኘዉ ሃኪም ቤት የሕፃናት ክፍል የሚገኙት አልጋዎች ተጠጋግተዉ ተደርድረዋል፤ 300 የሚሆኑት ትንንሾቹ ህመምተኞች ተኝተዉባቸዋል። አብዛኞቹ ታዲያ እንደጃስሚን ቢሳኮኑ የሁለት ዓመት ሴት ልጅ በወባ ምክንያት ነዉ ሃኪም ቤት የገቡት። ሕፃኗ አምስት ቀናት ሆነዋታል ሃኪም ቤት ከገባች። ሆኖም የተሻላት በመጠኑ መሆኑን ያስተዋለችዉ እናት ስጋት ገብቷታል።

«እዚህ ትክክለኛዉ መድሃኒት የለም። በርካቶች ጥቂት ቀናት ከቆዩ በኋላ ይሞታሉ።»

ወባ ማዕከላዊ አፍሪቃ ሪፑብሊክ ዉስጥ ከአምስት ዓመት እድሜ በታች ያሉ ሕጻናት ሕይወት ከሚያልፍባቸዉ በሽታዎች ዋነኛዉ ነዉ። ባለፈዉ ከአንድ ዓመት በላይ በሚሆን ጊዜ ዉስጥ ደግሞ ጭራሽ ሁኔታዉ ተባብሷል። በሙስሊምና ክርስቲያን ታጣቂዎች መካከል በሀገሪቱ የተጀመረዉ ግጭት በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ወገኖችን ከመኖሪያ ቀያቸዉ አሰድዷል። ስደተኞቹ በሚገኙባቸዉ መጠለያ ጣቢያዎች ደግሞ የወባ ወረርሽኝ በተደጋጋሚ ይከሰታል። በሀገሪቱ የወባ መከላከያ መርሃግብር የአንደኛዉ ዘርፍ ተጠሪ ናቸዉ ዣን ሞየን፤

«በግጭቱ ምክንያት እዚህ ከሚገኙት አብዛኞቹ መኖሪያቸዉን አጥተዋል። መጠለያዉ ከመጠን በላይ ሞልቷል፤ በዚህ ምክንያትም የንፅህና ይዞታዉ በጣም የከፋ ነዉ። ከዓለም ዓቀፍ ድርጅቶች በምናገኘዉ ድጋፍ አማካኝነት ለምሳሌ የወባ መከላከያ አጎበር ለማዳረስ እየሞከርን ነዉ።»

በባንጊ አዉሮፕላን ማረፊያ በሚገኘዉ ትልቅ መጋዘን ዉስጥ በርካቶች ተጠልለዋል ሆኖም አንዳቸዉም አጎበር የላቸዉም። 300 ሺ ሰዎች ናቸዉ አብዛኞቹም ነፍሳቸዉን ለማዳን ብቻ ነዉ እዚህ የተጠለሉት። በአካባቢዉ የሚገኘዉ የእርዳታ ድርጅት ድንበር የለሽ ሃኪሞች የህክምና ርዳታ ለብዙዎቹ ይሰጣል። በየቀኑም ህክምና ለማግኘት ረዣዝም ሰልፎችን መጠበቅ ይኖርባቸዋል። ክሌመንት ሽቨል ከሃኪሞቹ አንዱ ናቸዉ፤

«በመጠለያዉ ዉስጥ የኑሯቸዉ ሁኔታ በጣም በጣም አዳጋች ነዉ፤ መጠለያ የለም፤ ዉሃም የለም ማለት ይቻላል፤ ምግብ የለም፤ እናም ሰዎቹ መሠረታዊ የሆነ ርዳታና ነፍሳቸዉን ማቆየት የሚያስችል ህክምና ያስፈልጋቸዋል።»

በየዕለቱ በርካቶች ወባ እንደያዛቸዉ በምርመራ ይረጋገጣል። አሁን የዝናብ ወቅት ተቃርቧል ካለዉ ሙቀት ጋ ተባብሮ የወባ ትንኞች የመራቢያቸዉና በሽታዉም የመስፋፊያዉ ጊዜ ነዉ። የዩኒሴፍ ባልደረባ ሎዉሮ ፉንግ አጎበር በቶሎ ለሰዎቹ መከፋፈል እንደሚኖርበት ያመለክታሉ፤

«በአሁኑ ወቅት አጎበር ማከፋፈሉ በጣም አስፈላጊ ነዉ። ምክንያቱም በሀገር ዉስጥ ከቤት ንብረታቸዉ የተፈናቀሉት ወገኖች የሚገኙበት ሁኔታ እጅግ የከፋ ነዉ። እንዳለመታደል ሆኖ የዝናቡ ወቅት ተዳርሷል ይህ ደግሞ በወባ የሚያዙትን ሰዎች ቁጥር መጨመሩ አይቀርም። እናም የአካባቢዉ ሰዎች ራሳቸዉን ከወባ መከላከል እንዲችሉ አጎበር የማከፋፈሉ ተግባር አስቀድሞ እንዲሆን እንፈልጋለን።»

ባንጊ ከተማ የሕጻንት ሃኪም ቤት ዉስጥ የልጆቹ መኝታዎች በአጎበር ተሸፍነዋል። ልጆቻቸዉን ለመመገብና ለመከታተል ከአጠገባቸዉ የሚገኙት እናቶች ግን ምንም ከለላ ሳይደረግላቸዉ መሬት ላይ ነዉ የሚተኙት። የሁለት ዓመት ሕፃን ልጇ ሕይወት የሚያሳስባት ጃስሚን ቢሳኮኑም ብትሆን ለራሷም መስጋቷ አልቀረም።

«ከሌሎች በሽታዎች ወባ በጣም ከባድ ነዉ። መንግስት እኛን ለመርዳት አንድ ነገር ማድረግ አለበት።»

በአሁኑ ጊዜ በሀገሪቱ ባለዉ አለመረጋጋት ምክንያት የማዕከላዊ አፍሪቃ ሪፑብሊክ የጤና ጥበቃ ስርዓት ወባን ለመዋጋት ያን ያህል እየሠራ ነዉ ማለቱ ይከብዳል። በሀገሪቱ ከሰባት ሕፃናት አንዱ አምስተኛ የልደት በዓሉን ሳያከብር ይቀጠፋል፤ የአብዛኞቹ ሕይወት የሚያልፈዉ ደግሞ በወባ ነዉ።

ሸዋዬ ለገሠ

ተክሌ የኋላ

Audios and videos on the topic