አፍሪቃ እና ትችት የቀረበበት የትምህርት ስርዓቷ | አፍሪቃ | DW | 05.03.2016
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

አፍሪቃ

አፍሪቃ እና ትችት የቀረበበት የትምህርት ስርዓቷ

ልማትን ማራመድ በምትፈልገው አፍሪቃ የትምህርቱ ስርዓት እንደሚፈለገው አለመዳበሩን ጠበብት ይናገራሉ። በደቡብ አፍሪቃ ከዘጠኝ ግዛቶች መካከል በአራቱ ከ213,000 የሚበልጡ ተማሪዎች የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ማጠናቀቂያውን ፈተና አያልፉም።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 08:59
አሁን በቀጥታ እየተሰራጨ ያለ
08:59 ደቂቃ

ትምህርት በአፍሪቃ

በደቡብ አፍሪቃ ከጠቅላላ ተማሪው 25% የ2ኛ ደረጃ መልቀቂያ ፈተና የሚወድቅበት እውነታ እንደ ብሔራዊ ችግር የሚታይ እጅግ አሳሳቢ ክስተት መሆኑን ነው የሀገሪቱ የትምህርት ሚንስትር ኦንዢ ሞትሼክጋ ከጥቂት ጊዜ በፊት ለአንድ የሀገራቸው ጋዜጣ ያስታወቁት።

በደቡብ አፍሪቃ የሚገኘው የሽቴልንቦሽ ዩኒቨርሲቲ የትምህርት ሂደት ተመራማሪ ሴርቫስ ፋን ደር በርግ በጠቀሱት አስደንጋጭ መዘርዝር መሰረት፣ በ2002 ዓም ትምህርት ቤት ከገቡት 1,2 ሚልዮን ልጆች መካከል ግማሽ የማይሞሉት ነበሩ ትምህርታቸውን ያጠናቀቁት። በአፍሪቃ ለትምህርቱ ስርዓት መዳከም ደቡብ አፍሪቃ አንዷ ምሳሌ ብትሆንም ብዙ ልጆች ትምህርት ቤት የማይሄዱባቸው አፍሪቃውያት ሀገራት ጥቂት የሚባሉ አይደሉም።

የተመድ የትምህርት፣ የሳይንስ እና የባህል ድርጅት፣ በምህፃሩ «UNESCO» ያወጣው መዘርዝር እንዳሳየው ፣ ናይጀሪያ እና ኮትዲቯር ውስጥ ዕድሜአቸው ለትምህርት ከደረሱት ልጆች መካከል ትምህርት ቤት የመሄድ ዕድል ያላገኙ 80% ናቸው።

እርግጥ፣ በአፍሪቃ ትምህርት ለመከታተል የሚመዘገበው ተማሪ ቁጥር በየጊዜው ከፍ እያለ መሄዱን መዘርዝሩ አረጋግጦዋል። ይሁንና፣ እጎአ በ2012 ዓም ትምህርት ቤት መግባት ከነበረባቸው ህፃናት መካከል ቢያንስ 30 ሚልዮኑ ይህን ዕድል አላገኙም። በአፍሪቃ ለትምህርቱ ዘርፍ የተሰጠው ትኩረት ከፍተኛ ቢሆንም፣ ዘርፉ እንደሚገባው አለማደጉን ነው ዶይቸ ቬለ ያነጋገራቸው የበርሊን የስነ ህዝብ እና ልማት ተቋም ዋና ስራ አስኪያጅ ጀርመናዊው ራይነር ክሊንግሆልስ ያስታወቁት።

«ካለፉት አሰርተ ዓመታት ወዲህ በአፍሪቃ ፣ በተለይም ባንዳንድ ሀገራት የትምህርቱን ዘርፍ ለማሻሻል ብዙ ገንዘብ ተመድቦዋል። ይሁንና፣ ይህ ላጭር ጊዜ እንጂ በቀጣይነት አልተሰራበትም። በዚህም የተነሳ አፍሪቃ አሁንም በዓለም በትምህርቱ ዘርፍ በሚገባ ያልሰለጠነ እና ወደኋላ እንደቀረ ይገኛል። ይህም አህጉሩ ይህንን ሁኔታ ለማሻሻል ብዙ መስራት እንዳለበት ያሳያል። ምክንያቱም፣ እጅግ እየተቀራረበ በመጣ ዓለም ውስጥ ተፎካካሪ መሆን ከተፈለገ ሰዎች ከጊዜው ጋር የሚስማማ እና አስፈላጊ የሚባል ችሎታ ሊኖራቸው ይገባል።»

በብዙ አፍሪቃ ሀገራት ማንበብ እና መጻፍ የማይችሉ ለአካለ መጠን የደረሱ ሰዎች ወይም ህፃናት ቁጥር እጅግ ከፍተኛ ነው። የሚሄዱትም ቢሆን የትምህርቱ ጥራት ዝቅተኛ በመሆኑ ጥሩ ትምህርት ስለማይገኙ፣ በሌሎች ሀገራት ካሉት እኩዮቻቸው ጋር መፎካከር የሚያስችላቸው እውቀት የላቸውም። እንደ ራይነር ክሊንግሆልስ አስተያየት፣ በብዙዎቹ አፍሪቃውያት ሀገራት በተለያዩ ምክንቶች የትምህርቱ ስርዓት ለ21ኛው ምዕተ ዓመት የሚመጥን አይደለም።

«ደካማ መምህራን፣ በሚገባ ያልተዘጋጀ የትምህርት ስርዓት፣ አስፈላጊው መሰረተ ልማት፣ ማለትም፣ የትምህርት ክፍሎች መጓደላቸው ባንድ በኩል ሂደቱን ሲያደናቅፍ ይታያል፣ ከዚህ ሌላም፣ የአስተማማሩ ዘዴ ተማሪዎች ከመምህራን ጋር በቅርብ ሀሳብ እንዲለዋወጡ፣ ጥያቄዎቻቸውን እንዲያቀርቡ የሚያደፋፍር አይደለም። ባጠቃላይ፣ የትምህርቱ ስርዓት ተማሪዎችን በአሁኑ ጊዜ ምርታማ ለመሆን ለሚያስፈልገው የትምህርት ዓይነት ዝግጁ አያደርጋቸውም።»

በዚህም የተነሳ ባንዳንድ የአፍሪቃ ሀገራት የሚገኙ ህፃናት በኢንዱስትሪ በበለጸጉት ሀገራት ያሉት እኩዮቻቸው በሁለት ዓመት የሚያገኙትን እውቀት ለማግኘት ከአራት እስከ አምስት ዓመት እንደሚያስፈልጋቸው ራይነር ክሊንግሆልስ ገልጸዋል። በዋሽንግተን የሚገኘው የብሔራዊ ዴሞክራሲያዊ ተቋም ባልደረባ ክርስቶፈር ፎሙንዮ እንዳስታወቁት፣ የትምህርት እጦት አፍሪቃውያኑን ህፃናቱን ለከፋ አደጋ ያጋልጣቸዋል።

«በአፍሪቃ ውዝግብ የሚካሄድባቸውን አካባቢዎች ስንመለከት ለውጊያ ተግባር የሚመለመሉት ህፃናት እና ወጣቶች ሲሆኑ፣ በተለይ ግን፣ ትምህርት የሌላቸው እና በታጠቁ ቡድኖች ውስጥ ተቀጥሮ መስራቱን ኑሮአቸውን ለመምራት እንደሚያስችላቸው አንድ አማራጭ አድርገው የሚመለከቱ ናቸው።»

በሰሜን ናይጀሪያ የሚንቀሳቀሰውን ፅንፈኛው ቡድን «ቦኮ ሀራም» በምሳሌነት የሚጠቅሱት ክርስቶፈር ፎሙንዮ በዚሁ አካባቢ መሰረታዊ የሚባል የትምህርት ዕድል የሌላቸው እና ትምህርት ቤት ያልሄዱ ብዙ ወጣቶች በህብረተ ሰቡ ውስጥ ተዋህደው መኖር ሲያዳግታቸው እንደሚታዩ፣ በዚህም የተነሳ አዘውትረው ለአክራሪ ቡድኖች የምልመላ ተግባር እንደሚጋለጡ ገልጸዋል።

ስለ አፍሪቃ የትምህርት ስርዓት ምርምር ያደረጉ አንዳንድ ምሁራን እንደሚሉት፣ ለትምህርቱ ስርዓት ደካማነት ቅኝ አገዛዝ የተጫወተው ሚና ከፍተኛ ነው። ቅኝ ገዢዎች አፍሪቃውያን በትምህርት እንዳይጎለብቱ በሚል ትምህርት ቤቶችን አልሰሩም፣ አፍሪቃውያቱ ሀገራት ነፃነታቸውን ካገኙ በኋላ የተቋቋሙት መንግሥታትም፣ አዘውትረው በአህጉሩ በተነሱ ውዝግቦች በመጠመዳቸው፣ ለትምህርቱ ዘርፍ እንደሚገባው አስፈላጊውን በጀት ሳይመድቡ የቀሩበት አሰራራቸው አሁን የሚታየው ሁኔታ ሊፈጠር ችሏል። ዓለም አቀፉ የገንዘብ መርህ ድርጅት ፣ «አይ ኤም ኤፍ» ም ባያቀረበው ጥጥሩ የቁጠባ መርሀግብr ትምህርቱ ስርዓት ማሻሻል የሚቻልበት አሰራር ችላ እንዲባል አድርጓል። ይሁንና፣ በደቡብ አፍሪቃ በሚገኘው የሽቴልንቦሽ ዩኒቨርሲቲ የትምህርት ስርዓት ሂደት ተመራማሪ ሴርቫስ ፋን ደር በርግ እንዳመለከቱት፣ ችግሩ የገንዘብ እጥረት ብቻ አይደለም።

«ብዙ አፍሪቃ መንግሥታት፣ አንዳንዴም ጥቂት የማይባሉ ለጋሽ ሀገራት፣ እንዲሁም ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርታቸውን የሚከታተሉትን ህፃናት ቁጥር ለማሳደግ ከፍተኛ ጥረት በማድረግ ላይ ናቸው፣ ሆኖም፣ ለልጆቹ ለሚቀርበው ትምህርት ጥራትም ሆነ ለአስተማማሩ ዘዴ አስፈላጊውን ትኩረት አልሰጡም። እና ብዙ ህፃናት ትምህርት ቤት መግባታቸው ብቻ፣ ማለትም፣ ተገቢውን ትምህርት የማያገኙበት ድርጊት ጥረቱን መና በማስቀረት፣ ትምህርት ለህፃናቱ እና ለህብረተሰብ ሊያበረክተው የሚገባውን ድርሻ እንዳያበረክት ያደርጋል።»

ይህን ለማስተካከል የመምህራን ስልጠናን ማሻሻል እና ለትምህርት አስፈላጊ የሆነውን ሁሉ ማቅረብ የግድ ይሆናል። በብዙ ሀገራት የሚሰራበትን እና አሁንም የቅኝ ጊዜ ዘመን አሻራ የሚታይበትን የትምህርት ስርዓት መቀየርም አስፈላጊ ነው። በአፍሪቃ ባጠቃላይ የትምህርቱ ዘርፍ፣ ማለትም፣ ስርዓቱ እና አቀራረቡ እንደገና ሊከለስ እንደሚገባ የጠቆሙት በዋሽንግተን የሚገኘው የብሔራዊ ዴሞክራሲያዊ ተቋም ባልደረባ ክርስቶፈር ፎሙንዮ በአሁኑ ጊዜ ብዙ ተማሪዎችን በማህበራዊ ሳይንስ ማስመረቅ ጥሩ ነገር ቢሆንም፣ አፍሪቃ ባጠቃላይ በተፈጥሮ ሳይንሱ ዘርፍ በቂ ምሁራንን በማውጣት ላይ መሆን አለመሆንዋ ሊጤንበት እንደሚገባ አሳስበዋል።

አርያም ተክሌ
ማንተጋፍቶት ስለሺ

Audios and videos on the topic