አፍሪቃ እና ትልቅ ነፃ የንግድ ቀጣና ስምምነት | ኤኮኖሚ | DW | 11.06.2015
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ኤኮኖሚ

አፍሪቃ እና ትልቅ ነፃ የንግድ ቀጣና ስምምነት

26 የምሥራቅ እና የደቡባዊ አፍሪቃ ሀገራት በአህጉሩ ትልቁን ነፃ የንግድ ቀጣና ለመፍጠር የሚያስችላችውን የዕቅድ ሰነድ ተፈራረሙ። ሶስት የአህጉሩን የንግድ ማህበራት የሚያስተሳስረው በምህፃሩ «ቲ ኤፍ ቲ ኤ» በመባል

አውዲዮውን ያዳምጡ። 03:55

አፍሪቃ እና ትልቅ ነፃ የንግድ ቀጣና ስምምነት

የሚጠራው የንግድ ቀጣና ወደ 600 ሚልዮን የሚጠጋው የምሥራቅ እና የደቡባዊ አፍሪቃ ሀገራትን ሕዝብ ተጠቃሚ የማድረግ እና የዕቃ እና ኢንቬስትመንት ዝውውር የሚያጠናክር የጋራ ገበያ የማቋቋም ዓላማ አለው።

በግብፅ የሻርም ኤል ሼኽ ከተማ ትናንት የ26 የአፍሪቃ ሀገራት መሪዎች በምህፃሩ «ቲ ኤፍ ቲ ኤ» በመባል የሚጠራ አንድ ነፃ የንግድ ቀጣና ለማቋቋም የተፈራረሙት ስምምነት ከካይሮ እስከ ኬፕታውን ያሉ ሀገራትን ያጠቃልላል። የምሥራቅ አፍሪቃ የንግድ ማህበረሰብ፣ የደቡባዊ አፍሪቃ የልማት ትብብር ድርጅት ፣ በምህፃሩ ሳዴክ እና የምሥራቅ እና የደቡብ አፍሪቃ የጋራ ገበያ፣ በምህፃሩ ኮሜሳ በጋራ ሊያቋቁሙት ያሰቡት ይኸው ነፃ የንግድ ቀጠና በያመቱ ከአህጉሩ ጠቅላላ ገቢ መካከል 51%፣ ማለትም ወደ 884 ቢልዮን ዶላር ይሸፍናል።

በለንደን ብሪታንያ የሚገኘው የስታንዳርድ ቻርተርድ ባንክ የአፍሪቃ ኤኮኖሚ ምርምር ክፍል ኃላፊ ሬዛ ካን እንደታዘቡት፣ አዲሱ ስምምነት በአፍሪቃ ያካባቢ ማህበራት መካከል ያን ያህል ያልዳበረውን የንግዱ ግንኙነትለ ያጠናክራል።

« አፍሪቃ ከሌሎች በመልማት ላይ ካሉት አካባቢዎች ጋር ስትነፃፀር በተለያዩት ያህጉሩ ያካባቢ ማህበራት መካከል ንዑሱ የንግድ ግንኙነት ያለባት ቦታ ናት። በመጨረሻ የወጡ መዘርዝሮች እንዳሳዩት በዚሁ ረገድ በጣም አነስተኛ መሻሻል ነው ያሳየው፣ ብሎም ከ12% ወደ 14% ዕድገት ብቻ ነው የተመዘገበው። ተፈራራሚዎቹ የንግድ ማህበራት አባል ሀገራት ከአምስት ዓመት ድርድር ትናንት የደረሱትን አንድ ትልቅ የንግድ ቀጠና የማቋቋሙን ስምምነት ተግባራዊ በሚያደርጉበት ጊዜ ምናልባት ፉክክር ሳያሳስባቸው የንግድ ግንኙነት ማካሄድ ይችሉ ይሆናል በሚል ተስፋ ተደርጓል። »

ለአፍሪቃ ዕድገት እንደ ትልቅ ርምጃ የታየው ስምምነት እአአ በ2017 ዓም በተግባር ይተረጎም ዘንድ ግን የተፈራራሚ ሀገራት ምክር ቤቶች በቀጣዮቹ ጊዚያት የዕቅዱን ሰነድ ማፅደቅ ይኖርባቸዋል። ይህ ግን ቀደም ካሉ ተሞክሮዎች ሲታዩ ቀላል እንደማይሆን ነው በለንደን ብሪታንያ የሚገኘው የስታንዳርድ ቻርተርድ ባንክ የአፍሪቃ ኤኮኖሚ ምርምር ክፍል ኃላፊ ሬዛ ካን የሚገምቱት። « ቁልፉ ጉዳይ የስምምነቱ ተግባራዊ መሆን አለመሆን ነው። እርግጥ፣ብዙ አፍሪቃውያት ሀገራት ቀደም ሲል የተለያዩ ሀገራት አቀፍ ስምምነቶችን ቢፈራረሙም ተግባራዊ ባለማድረጋቸው አዘውትረው ይወቀሳሉ፣ እና ስራ ላይ እስኪውል ድረስ ጥቂት ዓመታት መውሰዱ አይቀርም። ያም ቢሆን ግን፣ ጥሩ ጅምር ነው፣ እና ወደፊት የመራመዱ ሂደት ስምምነቱ ተግባራዊ በሚሆንበት ደረጃ ላይ ጥገኛ ይሆናል። »

ሶስቱ ያካባቢ የንግድ ማህበራት በዙር በሊቀመንበርነት ከሚመሩት የነፃው የንግድ ቀጠና መቋቋም ደብብ አፍሪቃን እና ግብፅን የመሳሰሉ ትልቆቹ ኤኮኖሚያዊ ኃይላት፣ እንዲሁም፣ የምርታ ኢንዱስትሪ ያን ያህል ያልተስፋፋባቸው ንዑሱ ኤኮኖሚ የሚታይባቸው ሀገራት ተጠቃሚ ይሆናሉ።

የትናንቱ ስምምነት በምዕራብ አፍሪቃ መንግሥታት የኤኮኖሚ ማህበረሰብ፣ በምህፃሩ ኤኮዋስ የሚጠቃለሉ አባል ሀገራትን ፣ 177ሚልዮን ነዋሪ እና ወደ 600 ቢልዮን ዶላር የሚጠጋ ጠቅላላ ብሔራዊ ገቢ ያላትን ናይጀሪያን አያጠቃልም። ይሁንና፣ አንድ አህጉሩን ሁሉ የሚያጠቃልል ነፃ የንግድ ቀጣና ለሚቋቋምበት ድርጊት እንደ ጥሩ ጅምር ታይቶዋል። አፍሪቃውያን መሪዎች የፊታችን ሰኞ እና ማክሰኞ በጆሀንስበርግ ደቡብ አፍሪቃ በሚያካሂዱት የአፍሪቃ ህብረት ዓቢይ ጉባዔ ላይ ወደ አንድ አህጉር አቀፍ ነፃ የንግድ ስምምነት የሚያመራ የሁለት ዓመት ድርድር መጀመር እንደሚሆን ተገልጾዋል።

አርያም ተክሌ

ነጋሽ መሀመድ

Audios and videos on the topic