አፍሪቃ እምቢ ያለችው የአውሮጳ ′ቆሻሻ ነዳጅ ዘይት′ | ኤኮኖሚ | DW | 03.05.2017
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

ኤኮኖሚ

አፍሪቃ እምቢ ያለችው የአውሮጳ 'ቆሻሻ ነዳጅ ዘይት'

ጋና እና ናይጄሪያ ከአውሮጳ ኩባንያዎች ሲሸምቱ የከረሙትን ዝቅተኛ የጥራት ደረጃ ያለው የነዳጅ ዘይት ከመጪው ሐምሌ ጀምሮ ላለመግዛት ወስነዋል። የአውሮጳ ኩባንያዎች ለምዕራብ አፍሪቃ ሐገራት ሲሸጡ የከረሙት የነዳጅ ዘይት ዝቅተኛ የጥራት ደረጃ ያለው ሲሆን የሚያስከትለው ብክለት ለሳንባ ነቀርሳ እና ለሰረሰር ሕመሞች ይዳርጋል። 

አውዲዮውን ያዳምጡ። 10:13

አፍሪቃ እምቢ ያለችው የአውሮጳ 'ቆሻሻ ነዳጅ ዘይት'

የምዕራብ አፍሪቃ ሃገራት ከፍተኛ የድኝ (ሰልፈር) እና ሌሎች መርዛማ ንጥረ ነገሮች ይዘት ያለውን የነዳጅ ዘይት ግብይትን አግደዋል። ፐብሊክ አይ የተባለው የስዊዘርላንድ መንግሥታዊ ያልሆነ ድርጅት ባለፈው ዓመት ይፋ ባደረገው ዘገባ ለአፍሪቃ ገበያ የሚቀርበው ዝቅተኛ ጥራት ያለው የነዳጅ ዘይት በአብዛኛው መነሻው ከአውሮጳ ሃገራት እንደሆነ ገልጦ ነበር። የድርጅቱ ዘገባ «ፍትኃዊ ያልሆነ» ባለው የንግድ ሥርዓት የአውሮጳ የነዳጅ ዘይት ኩባንያዎች እጅግ ዝቅተኛ የጥራት ደረጃ ያለን የነዳጅ ዘይት ለአፍሪቃ ሃገራት እንደሚሸጡ አጋልጧል።

ኩባንያዎቹ በአውሮጳ ገበያ የሚሸጡት የነዳጅ ዘይት ከ0.01 በመቶ በላይ  የድኝ (ሰልፈር) ይዘት እንዲኖረው አይፈቀድላቸውም። በአፍሪቃ አገራት ግን ጉዳዩ ሌላ ነው። የምዕራብ አፍሪቃ አገራት የነዳጅ ዘይት ከውጭ አገራት ሲሸምቱ ያስቀመጡት መሥፈርት ዜጎቻቸውን ለውስብስብ ሕመሞች የሚዳርግ እንደሆነ ባለሙያዎች ይናገራሉ።  በነዳጅ ዘይት የበለጸገችውን ናይጄሪያን ጨምሮ በአይቮሪ ኮስት፤ ማሊ እና እና ጋናን በመሰሉ አገራት ለገበያ የሚቀርበው የነዳጅ ዘይት በውስጡ እስከ 0.3 የድኝ አሊያም ሰልፈር ይዘት እንዲኖረው ይፈቀዳል። 

እንዲህ ዝቅተኛ የጥራት ደረጃ ያለው የነዳጅ ዘይት ሲሸምቱ ከከረሙ የአፍሪቃ አገሮች መካከል ጋና እና ናይጄሪያ ቁርጥ ውሳኔ አሳልፈዋል። በጎርጎሮሳዊው የዘመን አቆጣጠር መሠረት ከመጪው ሐምሌ 1 ቀን ጀምሮ በጋና እና ናይጄሪያ ገበያ የሚቀርበው የነዳጅ ዘይት በአገሪቱ መንግሥታት የተቀመጠውን የጥራት ደረጃ ማሟላት ይጠበቅበታል። በጋና እና ናይጄሪያ እርምጃ ደስተኛ መሆናቸውን የሚናገሩት የፐብሊክ አይ ዋና ሥራ አስፈፃሚ ኦሊቨር ክላሰን ሌሎች አገሮችም የምዕራብ አፍሪቃውያኑን መንገድ እንዲከተሉ ይሻሉ።

«በሁለት ቁልፍ አገሮች የነደጅ ዘይት የጥራት ደረጃ 50ppm ሆኗል። እንደ አይቮሪ ኮስት፤ ቤኒን፤ ቶጎ አሊያም ማሊን የመሳሰሉ ሌሎች የምዕራብ አፍሪቃ አገሮችም ይኸንኑ ይከተላሉ ብለን ተስፋ እናደርጋለን። ለዚህም ምልክቶች አሉ። ይኸኛው ግን በአውሮጳ አሊያም በአሜሪካ ከተቀመጠው የጥራት ደረጃ አኳያ አምስት እጥፍ ብልጫ ያለው ነው። ነገር ግን ቀድሞ ከነበረው 60 እጥፍ የሚቀንስ በመሆኑ ደስተኞች ነን። ነገር ግን በፍጹም በቂ አይደለም። በመሆኑም ትግሉ እና ተፅዕኖ ማሳደሩ ይቀጥላል። ምን አልባት የጋና እና የናይጄሪያን ተምሳሌታዊ እርምጃ ሌሎች አገሮች ይከተሉ ይሆናል። ከዚህ የተሻለ የጥራት መስፈርትም ሥራ ላይ ይውል ይሆናል።»

ፐብሊክ አይ የተባለው መንግሥታዊ ያልሆነ ድርጅት በስምንት የአፍሪቃ አገሮች የሚሸጠውን ነዳጅ ዘይት ለሦስት ዓመታት ባደረገው ምርመራ ፈትሿል። ከስምንቱ አገሮች አምስቱ በምዕራብ አፍሪቃ የሚገኙ ናቸው። ድርጅቱ በናሙና ከፈተሸው የነዳጅ ዘይት ውስጥ ከሁለት ሦስተኛው በላይ የሚሆነው ከአውሮጳ ገበያ ከሚሸጠው 150 እጥፍ የድኝ (ሰልፈር) ይዞታ ያለው ነበር። ይኸ ለአፍሪቃ ከተሞች እጅጉን አሳሳቢ የጤና ሥጋት ነው።

የአፍሪቃ ከተሞች በፍጥነት እያደጉ ነው። የናይጄሪያዋ ሌጎስ 21 ሚሊዮን ነዋሪዎች አሏት የከተማይቱ የሕዝብ ቁጥር በጎርጎሮሳዊው 2050 ዓ.ም. በእጥፍ ይጨምራል ተብሎ ይጠበቃል። የምዕራብ አፍሪቃዎቹ ከተሞች ፈጣን እድገት እና በቀጣናው እየተበራከተ የመጣው አሮጌ መኪኖች አጠቃቀም ለከተሞቹ የአየር ብክለት ተጠቃሽ ምክንያቶች ናቸው። ዝቅተኛ የጥራት ደረጃ ያለው የነዳጅ ዘይት አስተዋፅዖም ቀላል አይደለም። 

የነዳጅ ዘይት ብክለት ለአስም፤ የሳንባ ነቀርሳ እና የሰርሰር ሕመሞች ያጋልጣል። የፐብሊክ አይ ዘገባ የአፍሪቃ ሃገራት ዝቅተኛ የድኝ (ሰልፈር) መጠን ያለው ነዳጅ ዘይት ቢጠቀሙ፤ እንዲሁም የተሻሻሉ የበካይ ጋዝ መቆጣጠሪያ የተገጠመላቸው ተሽከርካሪዎች ለተገልጋዮች ቢያስተዋውቁ በጎርጎሮሳዊው 2030 ዓ.ም. 25,000 በ2050 ዓ.ም. ደግሞ 100,000 ድንገተኛ ሞት መቀነስ ይችላሉ ብሎ ነበር። ኦሊቨር ክላሰን ድርጅታቸው በነዳጅ ዘይት ግብይት ኢንደስትሪው ውስጥ መሠረታዊ ለውጥ እንዲመጣ ጥረት ሲያደርግ መቆየቱን ያስታውሳሉ። በአውሮጳ በተለይም በአገራቸው የማይሸጡትን ወደ አፍሪቃ የሚልኩት የስዊዘርላንድ ኩባንያዎች የንግድ ሥልት ሕገ-ወጥ ነው ሲሉ ሥራ አስፈፃሚው ይወቅሳሉ። 

«ባለፈው መስከረም ይፋ ያደረግንው ዘገባ የስዊዘርላንድ የሸቀጥ ነጋዴዎች የሚከተሉትን ሕገ-ወጥ የንግድ ሥልት አጋልጧል። ኩባንያዎቹ ለአፍሪቃ የሚሸጡትን በአገራቸው ገበያ አያቀርቡትም። ለዓመታት ሲሸጡ ነበር። አሁንም እየሸጡ ነው። የሚሸጡት የነዳጅ ዘይት በውስጥ ከፍተኛ መጠን ያለው ሰልፈር ስለያዘ በጃፓን፤አውሮጳ አሊያም በዩናይትድ ስቴትስ ለመሸጥ የተከለከለ ነው። ኩባንያዎቹ የተከተሉት በሌሎች አገሮች የተከለከለውን ዝቅተኛ ጥራት ያለው ነዳጅ ዘይት ለአፍሪቃ በመሸጥ ላይ የተመሠረተ የንግድ ሥርዓት ነው የተከተሉት። ይኸን ጥናት ስናከናውን የንግድ ሥርዓቱን በጥልቀት ፈትሸን በቀዳሚዎቹ የስዊዘርላንድ ኩባንያዎች ላይ ተፅዕኖ ለማሳረፍ ሞክረናል። በአፍሪቃ የሚገኙ አጋር ድርጅቶቻችን በመንግሥቶቻቸው ላይ ጫና እንዲያደርጉ አድርገናል። ምክንያቱም ይኸ የንግድ አካሔድ ፍትኃዊ አይሁን እንጂ ሕገወጥ አይደለም። በምዕራብ አፍሪቃ ገበያዎች የሚሸጠው የነዳጅ ዘይት መርምረን ያገኘነው አስደንጋጭ ውጤት ነው። መንግሥታት የሕዝባቸውን ጤና ለመንከባከብ ቸልተኛ ናቸው። ስለዚህ መንታ ዘመቻ ነበር ስናካሒድ የነበረው።በአንድ በኩል  በስዊዘርላንድ ያለሐፍረት በትጋት እና በሥልታዊ አካሔድ ጥራቱ የተጓደለ የነዳጅ ዘይት የሚሸጡ ኩባንያዎችን ስንሟገት ነበር። በሌላ በኩል በምዕራብ አፍሪቃ የሚገኙ አጋሮቻችን  በዚህ የነዳጅ ዘይት የጤና እክል የገጠማቸው ዜጎች ዋይታ በመንግሥቶቻቸው እንዲደመጥ ግፊት ያደርጉ ነበር።» 

ዘገባው በተለይ ጥራቱ የተጠበቀ የነዳጅ ዘይት እጅግ ከተበከለው ጋር በመቀላቀል በአፍሪቃ ገበያ የሚነግዱት ላይ ትኩረት አድርጓል። ሙሉ በሙሉ ጥራቱን ያልጠበቀው ቅልቅል ነዳጅ ዘይት በገበያው ''የአፍሪቃ የጥራት ደረጃ'' ተብሎ ይታወቃል። ይኸ የነዳጅ ዘይት የፐብሊክ አይ የሦስት ዓመት ምርምር ዘገባ 'ደካማው' የሚለውን የአፍሪቃ ሃገራት የቁጥጥር ሥርዓት ይለፍ እንጂ ለአውሮጳ ገበያ ግን መብቃት አይችልም። ኩባንያዎቹ ጥራቱ የተጓደለውን የነዳጅ ዘይት ከደሕናው ጋር የሚቀላቅሉት በአውሮጳ ወደቦች አሊያም ወደ አፍሪቃ በጉዞ ላይ ሳሉ መሆኑ ደግሞ ጉዳዩን የበለጠ ያወሳስበዋል። ከተለያዩ የነዳጅ ዘይት አቅራቢዎች የመጣው ሁሉ በአንድ የምርት አይነት ሊቀላቀል ይችላል።  

እንደ ፐብሊክ አይ ዘገባ ከሆነ የስዊዘርላንዶቹ ኩባንያዎች በመቀላቀሉ ብቻ ሳይሆን በነዳጅ ዘይት ማመላለሻዎች፤ አከፋፋዮች እና ማከማቻዎች ውስጥም ባለድርሻ ናቸው። እነዚህ ኩባንያዎች በአፍሪቃውያን ላይ የከፋ የጤና እክል ስለሚያስከትለው የነዳጅ ዘይት የሚያወሳው ዘገባ ይፋ ሲሆን ምላሽ ለመስጠት ፈቃደኛ አይደሉም።

«ምንም ምላሽ አልሰጡም። በዚህ በስዊዘርላንድ ይህ ጎጂ የነዳጅ ዘይት ግብይት እንዲቆም የሚጠይቅ በ20,000 ሰዎች የተሰበሰበ ፊርማ አቅርበን ነበር። የተሰበሰበውን ፊርማ በዚህ በጄኔቫ ትራፊጉራ ለተባለው ኩባንያ ስናቀርብ ምንም የለወጠ ነገር የለም። ሌላው ግዙፍ የስዊዘርላንድ የሸቀጥ ነጋዴ ቪቶ የተባለው ነው። እነርሱም ምንም እርምጃ ለመውሰድ ፈቃደኛ አይደሉም። እናም ከኩባንያዎቹ በኩል ምንም የተፈጠረ ነገር የለም።»
ሁለቱም ኩባንያዎች ለዶይቼ ቬለ በፅሁፍ በሰጡት ምላሽ የጥራት ደረጃውን ያልጠበቀ የነዳጅ ዘይት ሊያስከትል ስለሚችለው እክል ቢስማሙም በግብይት ወቅት የመቆጣጠሩን ኃላፊነት በአፍሪቃ መንግሥታት ትከሻ ላይ ጥለውታል። ​​​​​​​

ጥራቱ የተጓደለ የነዳጅ ዘይት የሚሸምቱት የምዕራብ አፍሪቃ ሃገራት ከፍተኛ የተፈጥሮ ዘይት ሐብት ክምችት ቢኖራቸውም ለማምረት አቅማቸው አይፈቅድም። ኦሊቨር ክላሰን እንደሚሉት እጅ ያጠራቸው ሃገራት ርካሽ ግን ደግሞ ለጤና አስጊ የሆነውን የነዳጅ ዘይት ለመሸመት ተገደዋል። ቪቶል የተባለው ኩባንያ አሁን ባለው የግብይት ሥርዓት ለአንድ አገር ያቀረቡት ምርት በዚያው አገር ለመሸጡ የአውሮጳ ኩባንያዎች እርግጠኛ መሆን አይችሉም ሲል አክሏል። «ቪቶልም ይሁን ሌላ ኩባንያ በአውሮጳ የጥራት ደረጃ ተመጣጣኝ የሆነ ምርት (በኪሳራም ቢሆን) ለአንድ የአፍሪቃ አስመጪ ቢሸጥ፦አስመጪው ጥራቱ ከፍ ያለውን ለሌላ ሸጦ ሌላ የተጓደለ ጥራት ያለው ምርት ለአገር ውስጥ ፍጆታ ሊያቀርብ ይችላል።» ብሏል። 

ዘገባው ይፋ ከሆነ በኋላ የምዕራብ አፍሪቃ ሃገራት መንግሥታት የነዳጅ ዘይት ግብይታቸውን ከመሠረቱ ለመቀየር ቃል ገብተው ነበር። ጋና እና ናይጄሪያ ቃላቸውን ጠብቀው ለሚሸምቱት የነዳጅ ዘይት የነበራቸውን የጥራት መሥፈርት አሻሽለዋል። 
«ዘገባውን ይፋ ስናደርግ ትልቅ የአደባባይ ክርክር ተቀስቅሷል። ለነገሩ ጉዳዩ ከዚህ ቀደምም በሌሎች ድርጅቶች ተነስቶ ነበር። መሠረታዊ ለውጥ ግን አልመጣም። ነገር ግን በምዕራብ አፍሪቃ መንግሥታት እና ባለስልጣናት ዘንድ በተወሰነ ደረጃ የችግሩን አሳሳቢነት እንዲገነዘቡ አድርጓል። ለከባቢ አየር ብክለት ያለውን አስተዋፅዖ እና የሚያስከትለውን የጤና እክል ሁሉም እንዲነጋገርበት አድርጓል። የችግሩ ምንጭ እነዚህ ኩባንያዎች በአውሮጳ የማያደርጉትን በዚያ መሸጣቸው ነው። መንግሥታቱ ለችግሩ በፍጥነት እልባት እንሰጠዋለን ሲሉ ለሕዝባቸው ተናግረው ነበር። የጥራት መስፈርታቸውን ለማሻሻል እና ከአውሮጳ ጋር

ለማስተካከል ፍላጎት እንዳላቸውም አሳይተዋል። በተለይ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች በጉዳዩ እጅግ ተቆጥተው ተከታታይ ክርክሮች እና ውይይቶች ተደርገዋል። በአፍሪቃ መንግሥታት ላይ ከፍ ያለ ጫና የተፈጠረ ሲሆን ጋና እና ናይጄሪያ ለሚገዙት የነዳጅ ዘይት የጥራት መስፈርቱን በማስተካከል ቀዳሚ ሆነዋል። ይኸን የፖሊሲ ለውጥ  በማየታችን ደስተኞች ነን። ድርጅታችን ካሳካቸው ትልቅ ጉዳዮች ምን አልባትም ትልቁ ይኸ ነው።» አፍሪቃ ከአውሮጳ ከምትሸምተው የነዳጅ ዘይት 50 በመቶው የሚያልፈው በአንትዎርፕ፤ ሮተርዳም እና አምስተርዳም ወደቦች በኩል ነው። ፐብሊክ አይ የተባለው ድርጅት እነዚህ ወደቦች የአውሮጳ የጥራት መሥፈርት የማያሟላውን የነዳጅ ዘይት ወደ አፍሪቃ ከማሻገር እንዲያግዱ ጥሪ አቅርቧል። ኦሊቨር ክላሰን በሆላንድ እና ቤልጅየም የሚደረገው ክርክር በኩባንያዎቹ ላይ ጫና ያድራል የሚል ተስፋ አላቸው።«የአፍሪቃ የጥራት ደረጃ የሚባለውን በሚያመርቱት በሆላንድ እና በቤልጅየም ሰፊ ሕዝባዊ ውይይት እየተደረገ ነው። ይኸ የጥራት ደረጃ በገበያው ቆሻሻ ነዳጅ ዘይት ተብሎ ይታወቃል። በምክር ቤቶች በጉዳዩ ላይ የውሳኔ ሐሳቦች ቀርበዋል። በርካታ የመገናኛ ብዙኃን በጉዳዩ ላይ ዘገባ ሰርተዋል። በመንግሥታቱ ላይ ተከታታይ ጫና አለ። እናም የስዊዘርላንድ የሸቀጥ ነጋዴ ኩባንያዎች ላይ ጫና የሚያሳድር ለውጥ ይኖራል ብለን ተስፋ እናደርጋለን። »
የጋናው ምክትል ፕሬዝዳንት ማሐሙዱ ባዉሚያ አገራቸው ገቢራዊ ያደረገችው አዲሱ የጥራት መሥፈርት ከምዕባውያኑ አሊያም ከምሥራቅ አፍሪቃ ሃገራት ጎራ እንደሚያሰልፋት ተናግረዋል። ምክትል ፕሬዝዳንቱ የሰረሰር ሕመሞች እና ከፍተኛ ድኝ (ሰልፈር) ካለው የነዳጅ ዘይት የሚፈጠሩ የጤና እክሎችም ይቀንሳሉ ብለው ተስፋ አድርገዋል። ናይጄሪያ ከውጭ የምትሸምተው ብቻ ሳይሆን በአገር ውስጥ የሚመረተው ጭምር አዲሱን የጥራት መስፈርት ማሟላት አለበት ብላለች።  
ራቼል ስቴዋርት/እሸቴ በቀለ
ሸዋዬ ለገሠ

Audios and videos on the topic

ተዛማጅ ዘገባዎች