አፍሪቃ፣ ኤኮኖሚዋና ማለቂያ ያጣ የውዝግቦች መዘዝ | ኤኮኖሚ | DW | 10.01.2007
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ኤኮኖሚ

አፍሪቃ፣ ኤኮኖሚዋና ማለቂያ ያጣ የውዝግቦች መዘዝ

አፍሪቃ ብዙዎቹን ታዳጊ ሃገራት ያቀፈች ክፍለዓለም የመሆኗን ያህል የተለያዩ ውዝግቦች ልማትን አንቀው ይዘው የሚገኙትም በዚህችው አህጉር ነው። ከጦርነት መዘዝ ተላቆ በልማት ላይ ማተኮር የሚቻለው እንዴት ነው?

የጦርነት ገጽታ

የጦርነት ገጽታ

ኡጋንዳ፣ ሩዋንዳ፣ ቡሩንዲ፣ ኮንጎና ሱዳን፤ ወይም ላይቤሪያ፣ አይቮሪ ኮስትና ቻድ፤ በነዚህ አገሮች ባለፉት አሠርተ-ዓመታት የታየው መዓት፤ የደረሰው ጥፋት መዘዝ ለሌላ ትውልድ ጭምር የሚተርፍ መሆኑ ብዙም አያጠያይቅም። አሁን ደግሞ በአፍሪቃ ቀንድ ትርምስ የሚታየው አዝማሚያ የአካባቢውን ልማት ቀርቶ የሕዝቡን መሠረታዊ ሕልውና እንዳያሳጣ ለስጋት መንስዔ የሚሆን ነው። በአፍሪቃ ቀንድ ላይ የተፈጠረው አዲስ የሃይል አሰላለፍ፣ የኢትዮጵያ ጦር የሶማሊያ ወረራና ለብዙ ዓመታት ሥርዓተ-ዓልባ ሆና የቆየችው አገር አለመረጋጋት በአካባቢው የኤኮኖሚ ዕድገት ላይ የሚኖረው ተጽዕኖ ምን ያህል ነው? ጉዳቱ ቀላል እንደማይሆን ከወዲሁ ለመናገር ብዙም አያዳግትም።

የአፍሪቃ የዕድገት ችግሮች በመሠረቱ ብዙና ውስብስቦች ናቸው። ሆኖም ከ 60ኛዎቹ ዓመታት የነጻነት ማግሥት ወዲህ ያለማቋረጥ በየቦታው የተከሰቱትና ዛሬም አልሸኝ ያሉት ውዝግቦች፤ የእርስበርስ ጦርነቶች ዋነኞቹ ልማትን አንቀው የያዙ መዘዞች ናቸው። አፍሪቃ በነዚህ አራት አሠርተ-ዓመታት ቅኝ ገዢዎች ተብትበውት ከሄዱት የጎሣ፣ የሃይማኖት ልዩነትና የወሰን ምስቅልቅል በመላቀቅ በኤኮኖሚ ዕድገት ላይ በሚገባ ለማተኮር አልቻለችም። ዛሬም ዓለም በ 21ኛው ክፍለ-ዘመን የብልጽግና ዕርምጃ ላይ በሚገኝበት ጊዜ አብዛኞቹ የአፍሪቃ አገሮች ተመጽዋቾች እንደሆኑ ነው ያሉት።

ከአውሮፓውያኑ የቅኝ አገዛዝ ዘመን በኋላ አሁን በዳርፉርና በሶማሊያ ምስቅልቅል እንደገና እንደሚታየው በአፍሪቃ ቀንድ አካባቢ ቀሪው ቅርስ በቀሰቀሰው ውዝግብ ያልተጠመደ አንድም አገር አይገኝም። ከሁለት አሠርተ-ዓመታት በላይ በአገሪቱ ደቡባዊ ክፍል በእርስበርስ ጦርነት ተወጥራ የቆየችውን ሱዳንን እንደ ምሳሌ መውሰድ ይቻላል። እርግጥ ሱዳን ዛሬ በቻይና እርዳታ በምታወጣው የነዳጅ ዘይት ሃብት የዓለም ባንክ በቅርቡ እንዳመለከተው የተፋጠነ ዕድገት እያደረገች ነው ቢባልም የዚህ የተፈጥሮ ጸጋ ተቋዳሾች በእጣት የሚቆጠሩ በመሆናቸው ሃብቱ ብዙሃኑን አላዳረሰም። ከካርቱም ወጣ ሲባል ያው ከጥንት አንስቶ የተለመደው ድህነት ነው የሕዝቡ ዕለታዊ ኑሮ መለያ ሆኖ የሚገኘው። የዳርፉርም ቀውስ አለ።

በአፍሪቃ ቀንድ አካባቢ አሁን ላሰጋው ጦርነት ከመንግሥታቱ የጠላት ወዳጅ ግንኙነት የሃይል አሰላለፍና የውስጥ ችግሮች ባሻገር አሜሪካ ለራሷ ጥቅም የምትከተለው ፖሊሲም ዓቢይ አስተዋጽኦ እንዳለው አሁን በሶማሊያ የአየር ድብደባ በማካሄድ በቀጥታ ጣልቃ ከገባች ወዲህ ይበልጥ ግልጽ ጉዳይ ሆኗል። ከሰባ ሺህ ያላነሰ ሕዝብ እንዳለቀበት የተነገረለት የኢትዮ-ኤርትራ የድንበር ጦርነት ቢያበቃም ችግሩ ገና ማሰሪያ አላገኘም። በሶማሊያ ወረራ ሁለቱ መንግሥታት ጦርነታቸውን በሰው አገር በርቀት ሊቀጥሉበት ተነሳስተዋል ሲል ተቀስቅሶ የነበረው ስጋት ለጊዜው ዕውን ባይሆንም ቢቀር ልዩነቱ እንዳለ ነው። ኬንያና ኡጋንዳም በአፍሪቃው ቀንድ የሃይል አሰላለፍ ስሌት የየራሳቸው ሚና አላችው።

አሜሪካ በሶማሊያው ጦርነት ለምን በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ጣልቃ መግባት አስፈለጋት? በይፋ የተነገረው በሶማሊያ የሻሪያን ፍርድቤቶች ሕብረት የማስወገዱ ዕርምጃ የዓለምአቀፉ ጸረ-ሽብር ትግል ዕርምጃ አንድ አካል እንደሆነ ነው። እርግጥ የቡሽ አስተዳደር በኢራቅ የገጠመውን ችግር ለማዘናጋት አዲስ ግንባር መፍጠሩ ነው የሚሉ ተቺዎችም አልታጡም። በሌላ በኩል የበርሊኑ የትራንስ-አትላንቲክ መረጃ ማዕከል ባልደረባ ኦትፍሪድ ናሳወር እንደሚሉት የአሜሪካ የውጭ ፖሊሲ ስልታዊ ግብም አለው።

“የአሜሪካ የውጭ ፖሊሲ ሁልጊዜ መልክዓ-ምድራዊ ስሌትን የጠቀለለ ነው። ለአሜሪካ እንደ ሃያል መንግሥት ለብሄራዊ ጥቅሟ እንደሚያመች ዓለምአቀፉን ስርዓት፣ ፊናንሱንም ሆነ የንግዱን ስርዓት መቆጣጠሩ መብቷ ሆኖ ነው የሚሰማት። ለዚህ ደግሞ የተለያዩ ዘዴዎችን የምትጠቀም ሲሆን ዓለምአቀፉን ስርዓት በወታደራዊ ሃይል ማቀናጀቱም በማያሻማ ሁኔታ አንዱ አማራጭ ነው”

የአሜሪካ ስሌት ያም ሆነ ይህ በአፍሪቃ ቀንድ ላይ በወቅቱ በርካታ አገሮችን ማጣቀስ የያዘው ውዝግብ በአስቸኳይ መፍትሄ ካላገኘ ለልማት ጠንቅ መሆኑ ነው። ውጥረቱና አለመረጋጋቱ፤ በቀጥታ በጦርነቱ በሚሳተፉት ወገኖችም ለጦርነት የሚፈሰው ገንዘብ ለዚያውም ኋላ ቀር የሆነው ኤኮኖሚ ሊሽከመው የሚችል አይሆንም። የዓለም ባንክ በቅርብ የ 2006 ዓ.ም. የአፍሪቃ ልማት ዘገባው ባለፈው አሠርተ-ዓመታት በክፍለ-ዓለሚቱ ለታየው አበረታች የኤኮኖሚ ዕድገት ምክንያት አድርጎ ከጠቀሳችው ነጥቦች አንዱ የአካባቢ ጦርነቶችን መቀነስ ነበር። ከዚህ አንጻር በአንዱ ቦታ ያከተመው ጦርነት አሁን ገና ማለቂያው ባልታወቀው በአፍሪቃ ቀንድ ውዝግብ መተካቱ በጦርነቱ በቀጥታና በተዘዋዋሪ የተነከሩትን አገሮች የልማት ዕርምጃ ክፉኛ የሚፈታተን ነው የሚሆነው። በመሆኑም የሶማሊያ ሕዝብ ችግሩን በራሱ እንዲፈታና የራሱ ዕጣ ወሣኝ እንዲሆን ማድረጉ ይመረጣል።

አፍሪቃውያን መንግሥታት ከአሜሪካም ሆነ ከሌሎች ወገኖች ካለባቸው ተጽዕኖ ተላቀው ድህነትን በመቋቋም የልማት ጥረታችው ወደፊት እንዲገፉ ዕጣቸውን በአንድ ማስተሳሰርና ዓለምአቀፉ ሁኔታ የፈጠረውን አማራጭ መጠቀም ይጠበቅባቸዋል። ከደቡብ ደቡቡ የንግድ ትስስር ሌላ በየቦታው ያሉ ውዝግቦቻቸውን በኤኮኖሚ ትብብር ለመወጣት መነሣታቸው ገንቢ ነው የሚሆነው። በአፍሪቃ የአካባቢ መንግሥታት የኤኮኖሚ መረብ፤ Inerregional Economic Network የተሰኘው ድርጅት ባልደረባ ጀምስ ሺክዋቲ ይህን መሰሉ የጥቅም ትስስር ነጻ የሚያወጣ ሃይል አለው ይላሉ።

“የአፍሪቃ የወደፊት ተሥፋ የኤኮኖሚ ትብብር ማስፈኗ ነው። አንድ አገር በውስጡ ባለው ጥቂት ሃብት ላይ በማተኮርና በመባዘን ብቻ ከመወሰን ይልቅ የሌላውን ማየት መቻል ይኖርበታል። ይህም በሰፊው ማተኮር፤ ለተሻለ ውጤት መጣር ማለት ነው። ለዚህ ደግሞ የኤኮኖሚው ትስስር ጠቃሚ አስተዋጽኦ ይኖረዋል። እርግጥ አፍሪቃውያን ዛሬ ጎረቤቶቻቸው ምን እንደሚያደርጉ ማስተዋልና የተሻለ ሆነው መገኘት እንዳለባቸውም እየተገነዘቡ ነው”

በዚህ በኩል ምናልባት የአውሮፓን ሕብረት አርአያ የተከተለ የኤኮኖሚ ትስስር ማስፈኑ እንደ መፍትሄ የሚታይ ጉዳይ ከሆነ ሰንብቷል። በሌላ በኩል የደቡብ ደቡቡ የንግድ ትስስር መጠናከር በሰሜኑ ዓለም ላይ ካለው ጥገኝነት መላቀቂያ መንገድ ሆኖ መታየት የያዘ ጉዳይ ነው። በተፋጠነ ዕድገትና ሽግግር ላይ የሚገኙት ቻይና፣ ሕንድ፣ ብራዚልና ደቡብ አፍሪቃም ዛሬ በ 132 ታዳጊ አገሮች የንግድ ልውውጡ እንዲዳብርና መዋዕለ-ነዋይም በሰፊው በሥራ ላይ እንዲውል ታላቅ አስተዋጽኦ እያደረጉ ነው።

ደቡቡ ዓለም በጥቅሉ ሃብታም መሆን ብቻ ሣይሆን የተሳሰረ የኤኮኖሚ ሃይሉ በዓለም ኤኮኖሚ አንጻር በሰፊው ነው የጨመረው። የደቡብ ደቡቡ የንግድ ልውውጥ ከማንኛውም በላቀ መጠን በዓመት 11 ከመቶ እያደገ ሲሆን የደቡብ አፍሪቃ ንግድ እንኳ ባለፈው አንድ አሠርተ-ዓመት በሶሥት ዕጅ ከፍ ብሏል። በቅርቡ ተካሂዶ የነበረው የላቲን አሜሪካና የአረብ መንግሥታት ስብሰባ፤ እንዲሁም የቤይጂንጉ የቻይናና የአፍሪቃ መሪዎች ጉባዔ ታዳጊ አገሮች በትብብራቸው ለመግፋት መቁረጣቸውን የሚያመለክቱ ነበሩ።

ለማንኛውም የአፍሪቃ መንግሥታት፤ የአፍሪቃን ቀንድ ጨምሮ ከጥገኝነት እንዲላቀቁና የአካባቢ ሕብረታቸውን በማጠናከር ለኤኮኖሚ ዕድገታችው እንዲጥሩ ከጦርነት መዘዝ ስንብት ማድረግ ይኖርባቸዋል። ውስጣዊም ሆነ የአካባቢ ሰላም ከሌለ በልማት አቅጣጫ ተገቢውን ዕርምጃ ማድረጉ የሚከብድ ነው የሚሆነው። እርግጥ የልማት ሃይል የሆነው ሕዝብ ለዚህ ዕድገት እንዲነሣሣ፤ የውጤቱም ባለድርሻ እንዲሆን አስፈላጊው ማሕበራዊ ፍትህ መስፈኑ ግድ ነው። በጎ አስተዳደርና የሰብዓዊ መብቶች ከበሬታ ከመንግሥታቱ ይጠበቃል፤ ለሁሉም ቁልፉ ያለውም እዚህ ላይ ነው።