አፍሪቃ በጀርመን ጋዜጦች፧ | የጋዜጦች አምድ | DW | 07.05.2004
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

የጋዜጦች አምድ

አፍሪቃ በጀርመን ጋዜጦች፧

የጀርመን ጋዜጦችና የተለያዩ ወቅታዊ ኅትመቶች በዓለም ዙሪያ፧ በተለያዩ ክፍለ-ዓለማት ስለሚከናወኑ ድርጊቶች፧ ዘገባ፧ ግምገማም ሆነ ሐተታ እንደሚያቀርቡ የታወቀ ነው። በዛሬው አፍሪቃ በጀርመን ጋዜጦች፧ ስለአፍሪቃ አሳሳቢ መጻዔ-ዕድል ከተጻፈው በአጭሩ እንጠቅሳለን።ARD በሚል ማህጻር ለታወቀው፧ ለጀርመን ራዲዮና ቴሌቭዥን ድርጅት እንዲሁም ለአገር አቀፍ ጋዜጦች፧ ናይሮቢ ከሚገኘው ከመደበና የሥራ ቦታውና አልፎ-አልፎም ወደ ሌሎች አጎራባች አገሮች ጎራ በማለት ፭ ዓመት ዘገባ፧ ሐተታና የመሳሰለውን ሲያጠናቅር የነበረው Ralph Sina በሌላ አፍሪቃ ወዳድ ባልደረባው Wim Dohrenbusch ተተክቷል። ራልፍ ሲና፧ ስለአፍሪቃው ቀንድ አካባቢ ከዚህ ቀደም ያጠናቀራቸውን ዘገባዎች በዚህ ራዲዮ ጣቢያም በኩል ማሠራጨታችን ይታወስ ይሆናል። አፍሪቃ፧ ለንፅፅራዊ ዘገባ አመቺ ክፍለ-ዓለም ነው። ምሥራቁ አፍሪቃ በተለይ፧ የተፈጥሮ ውበት የታደለ፧ በበረዶ የተሸፈኑ ትልልቅ ማራኪ ተራሮች፧ የዱር እንስሳትና ዐራዊት መፈንጫ ክልሎች፧ የተንጣለሉ አነስተኛና መለስተኛ ሀይቆች፧ እንዲሁም ስምጥ ሸለቆዎች ይገኙበታል።
አፍሪቃ፧ ውዝግብ የሚንጠው፧ የተፈጥሮ መቅሠፍት በየጊዜው የሚዳስሰው ብቻ አይደለም። ብሩኅ ተስፋን ያነገበ፧ ሕይወትን የሚያጣጥም፧ የሚፍለቀለቅ፧ ብሩኅ ፈገግታ የማይለየው ህዝብ የሚኖርበትም ነው። WDR በሚል ምህፃር የታወቀው የምዕራባዊው ጀርመን የራዲዮና ቴሌቭዥን ድርጅት፧ ለ ARD ራዲዮ ፕሮግራሞች፧ የተለያዩ ዝግጅቶችን የሚያጠናቅሩ ጋዜጠኞች፧ በ ፳ የአፍሪቃ አገሮች ያሠማራ ሲሆን፧ በያመቱ በተጠቀሱትና በተለያዩ አጎራባች አገሮች የሚጠናቀሩ ከ፩ሺ የማያንሱ ዝግጅቶች ይቀርባሉ። ጋዜጠኞቹ፧ ለኅትመት ክፍልም እንደአስፈላጊነቱ ይጽፋሉ። የጀርመን የራዲዮ ዝግጅት አድማጮችና የተለያዩ ጋዜጦች አንባብያን የሆኑ ጀርመናውያን ወቅታዊ፧ አስተማማኝና በይዘትም ለየት ያለ ዘገባ ይቀርብላቸዋል። ለምሳሌ ያህል፧ ሩዋንዳ፧ ፲ ዓመት ከዘግናኙ የህዝብ ጭፍጨፋ በኋላ፧ በዕርቀ-ሰላም ወደፊት ለመራመድ፧ ስለምታደርገው ጥረት፧ የኬንያው ሰላማዊ የመንግሥት ለውጥ፧ እንዲሁም አዲሱ መንግሥት፧ ሙስናን ለማስወገድና የኤኮኖሚ ማሽቆልቆልን ለመግታት፧ ስለሚያሳየው ጥረት አወንታዊ ዘገባዎች ናቸው የተሠራጩት። በአንፃሩ ስለአስከፊው አሸባሪነት፧ የጀርመን ርእሰ-ብሔር ዮሐንስ ራው፧ በዚህ ሳቢያ፧ የአፍሪቃውን ጉብኝታቸውን እስከማሣጠር መድረሳቸውን ጋዜጠኞቹ በወቅቱ ዘግበዋል። እ ጎ አ በ 1980ኛዎቹ ዓመታት የጋዜጣ ዘጋቢ የነበረው ቪም ዶረንቡሽ፧ ራልፍ ሲናን አሳምሮ መተካት የሚችልመሆኑ ተመሥክሮለታል። ለሥራ ቅይይር፧ ስምምነት ላይ የተደረሰው፧ ባለፈው መጸው ነው። ራልፍ ሲና፧ ስለአፍሪቃ፧ ተስፋ አስጨባጩንናአንገት አስደፊውን ጉዳይ እያነጻጸረ ሲዘግብ የቆዬ ሲሆን፧ Stephen Smith የተሰኘው ጋዜጠኛ የአፍሪቃውን ክፍለ-ዓለም ዕድል ፍጹም አጨፍግጎ በመመልከት፧ Wenn Afrika Stirbt (አፍሪቃ ስትሞት ወይም የአፍሪቃ አሟሟት) በሚል ርእስ፧ አንድ መጽሐፍ ጽፏል። ከራይን ወንዝ ማዶ፧ ፈረንሳይ ውስጥ አፍሪቃን በተመለከተ፧ ማለፊያ ስም ያተረፈ ጋዜጠኛ መሆኑ የሚነገርለት Stephen Smith ከአፍሪቃው ክፍለ-ዓለም፧ ግማሹ፧ በጦርነትና የኃይል እርምጃ እንዳልነበረ ይሆናል። ሌላው ከፊል፧ በውዝግብ፧ በሙስና፧ በጎሣኛነትና በሥርዓት-አልበኛነት ይማቅቃል። በዚህ ላይ፧ የተማሩ ሰዎች አግ ለቀው በመውጣት ወደ አውሮፓና አሜሪካ መጓዝ፧ ሁኔታውን ይበልጥ ያመሠቃቅለዋል። በብዙዎቹ የአፍሪቃ አገሮች፧ የመንግሥት ሠራኞች፧ ወራት ሙሉ፧ ያለደመወዝ ሥራ ገበታ ውሎ መመለስ፧ ዕጣ-ፈንታቸው ይሆናል። ይህ አዝማሚያ፧ ባለፉት ዓመታት መከሠቱ የሚታበል አይደለም። ሀኪም ቤቶች፧ ፍርስርሳቸው ይወጣል፧ ትምህርት ቤቶች ይዘጋሉ። መንግሥት በማማረር፧ ራሱን እስከመርገም ይደርሳል። ከዳር እስከዳር፧ HIV/AIDS ይዛመታል። በብዙ ቦታዎች፧ የህዝቡን ዕድሜ፧ በ ፲፭ እና በ ፳ ዓመት ያሳጥረዋል ሲል ነው Stephen Smith የጻፈው። ለብዙ ዓመታት፧ Liberation(ነጻነት) ከዚያም፧ Le Monde(ዓለም) ለተሰኘው ጋዜጣ ይጽፍ የነበረው ይኸው ጋዜጠኛ፧ በአጭሩ፧ «አፍሪቃ፧ ራሱን፧ በራሱ ነው የሚገድለው« ባይ ነው።አፍሪቃ በይበልጥ በሰው ሠራሽ፧ በከፊልም ተፈጥሮ ባስከተለው መቅሠፍት፧ ዕድገቱ፧ ብዙ መሰናክል የገጠመው መሆኑ አይካድም። Stephen Smith የሚለው፧ በአመዛኙ ሟርት ባይሆንም፧ ሁኔታዎችን ለመለወጥ፧ አፍሪቃውያን በሁለንተናዊ የተኀድሶ ለውጥ ላይ ማትኮር ይጠበቅባቸዋል።

ተዛማጅ ዘገባዎች