አፍሪቃ በጀርመን አጠቃላይ ምርጫ ዘመቻ | አፍሪቃ | DW | 19.09.2017
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

አፍሪቃ

አፍሪቃ በጀርመን አጠቃላይ ምርጫ ዘመቻ

ጎርጎሪዮሳዊው 2017 ዓም፣ በጀርመን ፖለቲካ ውስጥ ከአፍሪቃ ጋር ሊኖር ስለሚገባው ግንኙነት ብዙ የተባለበት ዓመት ነው። ጀርመን በያዘችው የቡድን 20 ፕሬዚደንትነት ስልጣን ወቅት ከተነሱት ሀሳቦች ኮምፓክት ዊዝ ከአፍሪቃ ጋር፣ የማርሻል እቅድ የተሰኙት ይጠቀሳሉ።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 05:43
አሁን በቀጥታ እየተሰራጨ ያለ
05:43 ደቂቃ

ሁሉም ፓርቲዎች አፍሪቃን ለኢንቬስትመንት አመቺ አድርገው ይመለከታሉ።

በጀርመን ከሁለት ሳምንት በኋላ በሚካሄደው ምክር ቤታዊ ምርጫስ ዘመቻ ላይ ግን አፍሪቃ  በፓርቲዎች መርሀግብር ያን ያህል ትኩረት አላገኘችም ነው የሚባለው። አፍሪቃ በዘንድሮው የምርጫ ዘመቻ ላይ በፓርቲዎች የምረጡኝ መቀስቀሻ ሰሌዳዎች ላይ የመውጣት  እድል አላገኘችም። በምርጫ ዘመቻው ላይ ትኩረት የሚያገኙት ማህበራዊ ፍትሕ፣ የፀጥታ ጥበቃ ወይም ተገቢው ትክክለኛ  ደሞዝን የመሳሰሉ የሀገር ውስጥ ጉዳዮች ናቸው። ያም ሆኖ ግን፣ ተፎካካሪ ፓርቲዎች አፍሪቃን ሳይነሱ ያለፉበት ጊዜ የለም፣ ስደተኞች አይመጡብህም በሚል የመራጩን ድምፅ ለማግኘት ያደረጉት ሊሆን እንደሚችል መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች የተጠቃለሉበት ህብረት ፣ ፌንሮ ባልደረባ ቤርንት ቦርንሆርስት ገልጸዋል።


« የሁሉንም ፓርቲዎች መርሀግብር ብትመለከቱ አፍሪቃ  በሚያስገርም ሁኔታ ከሞላ ጎደል ትልቅ ምዕራፍ ተሰጥቶታል።  በክርስትያን ዴሞክራቶች ህብረት መርሀግብር ላይ የስደተኞችን ቁጥር በዘላቂነት ዝቅተኛ ማድረግ ወይም ፓርቲዎች  መርሀግብር ላይ  አረንጓዴዎቹ ደግሞ ለስደተኞች ደህና የወደፊት እድል በመፍጠር የስደትን መንስዔ መታገል የሚሉ ተመሳሳይ ሀሳቦች  በሁሉም ፓርቲዎች ፕሮግራም ላይ ይታያል። ስደት የሚለው ርዕስ ከአፍሪቃ ጋር በተያያዘ ቀርቧል። ጥያቄው ግን ሀሳቡ ስለአፍሪቃ በማሰብ የተነሳ ወይስ የስደትን መንስዔ ተቆጣጥረናል በሚል የመራጩን ሕዝብ ስሜት ለመያዝ የታሰበ ነው ወይ ነው። » 
የአፍሪቃውያን ስደተኞች ቁጥር በጨመረበት ሁኔታ የተነሳ የበርሊን ፖለቲከኞች እንደዘንድሮ ስለአፍሪቃ አንስተው አያውቁም። መራሒተ መንግሥት አንጌላ ሜርክል በጀርመን የቡድን 20 ፕሬዚደንትነት ስልጣን ዘመን አፍሪቃን ዋና የትኩረት አጀንዳ አድርገዋል፣ ሶስት ሚንስትሮቻቸውም አዲስ የልማት መርሆችን ነድፈዋል። ይሁንና፣ የቡድን 20 ጥረት ከአምስት አፍሪቃውያት ሀገራት ጋር ከፈጠረው ወረት የማሰራት አጋርነት ባለፈ ይህ ነው የሚባል ውጤት እንዳላስገኘ ታዛቢዎች ተችተዋል።
እንዲያም ቢሆን የክርስቲያን ዴሞክራቶች ፓርቲ ሲዲዩ ሜርክል ኮምፓክት ዊዝ አፍሪካ በሚል ለቡድን 20 ያዘጋጁትን እቅድ ይዘው መቀጠሉን መርጧል። እንደ ኤፍዲፒ ሲዲዩም ከተለመደው የልማት ርዳታ ጎን የግል ወረትን በማሰራት በአፍሪቃ የኑሮውን ደረጃ ለማሻሻል እንደሚቻል ያምናል። ይህ አባባል ግን በሀያስያን አስተያየት የሚጠቅመው የጀርመን ተቋማትን ነው፣ ቢሆንም ሲዲዩ ይህንኑ መንገድ መምረጡን  በፌዴራዊው ምክር ቤት ቡንድስታግ የዚሁ ፓርቲ አንጃ የአፍሪቃ ጉዳይ ተመልካች ቡድን ሊቀመንበር አንድሪያስ ሌምል አስረድተዋል።
« ድህነት ካለተጨማሪ የግል ወረት መፍትሔ አያገኝም የሚል የግል አስተያየት አለኝ። መንግሥትም ለዚህ ችግር  መፍትሔ አያስገኝም። ይህን ከብዙ ዓመት ወዲህ ለልማቱ ትብብር ያቀረብነው ብዙ ርዳታ በልማቱ ላይ የተጠበቀውን ሁነኛ ለውጥ ባላስስገኘበት ድርጊት ለማወቅ ይቻላል። በዚህም የተነሳ፣  እንደኔ አስተሳሰብ፣ ድህነትን በመታገሉ ረገድ ወደፊት ለመራመድ በአፍሪቃ ተጨማሪ የግል ወረት ያስፈልጋል። »

ስደተኞችን የሚመለከተውን ፖለቲካ በተመለከተ ሲዲዩ ከአፍሪቃ ሀገራት ጋር የአውሮጳ ህብረት ከቱርክ ጋር የደረሰው ዓይነት የፍልሰት ውል እንዲደረስ ጠይቋል። የሶሻል ዴሞክራቶቹ ፓርቲ ተጨማሪ የግል ወረት ያስፈልጋል መባሉን ቢደግፍም ገንዘባቸውን ለሚያሰሩ ተቋማት ማበረታቻ ወይም ዋስትና  ሊሰጥ እንደሚገባ በምክር ቤት የየኤስፔዴ አንጃ የልማት ፖሊሲ ቃል አቀባይ ወይዘሮ ጋብሪየላ ሀይንሪኽ አመልክቷል።
«  በአፍሪቃ ተጨማሪ ወረት ለማሰራት ብዙ እድል አለ ብለን እናምናለን። ይህ ጥሩ ነው ብለን የምናስበው እድል እውን በሚሆንበት ጊዜ በአፍሪቃ ብዙ የስራ ቦታ ሊፈጠር እና ብዙ ሰዎችም ኑሯቸውን ለመምራት የሚያስችላቸውን አማራጭ ሊያገኙ ይችላሉ።   »
ኤስፔዴ እስካሁን የጀርመን መንግሥት የቡድን 20 ንመስመር ሲከተል ቢቆይም እና የኤኮኖሚ ሚንስትር  ሶሻል ዴሞክራቷ ብሪጊተ ሲፕሪስ በግል ወረት ላይ ጥገኛ የሆነውን ፕሮ አፍሪካ የተሰኘውን ፕሮዤ ቢያነቃቁም ፣ ፓርቲያቸው አሁን ከዚሁ መስመር ራሱን በማራቅ ከተቋማት፣ ከአብያተ ክርስትያን፣ ከሙያ ማህበራት እና ከግል የልማት ድርጅቶች ጋር አብሮ ለመስራት በመሞከር ላይ ነው። በአውሮጳ ህብረት እና በአፍሪቃ ሀገራት መካከል የተደረሰው አከራካሪው የኤኮኖሚ አጋርነት ውል በጥንቃቄ ሊመረመር እንደሚገባም ኤስፔዴ አስታውቋል።  
የአረንጓዴዎቹ ፓርቲ ከምጫው በኋላ በሚቋቋመው መንግሥት ውስጥ የመሳተፍ እድል ካገኙ የኤኮኖሚ አጋርነት ውልን ለማስቆም እና በአዲስ ውል ላይ ለመደራደር አስበዋል።

ከዚህ ባለፈም ፍትሓዊ የአውሮጳ ንግድ እና የግብርና ፖሊስ እንዲኖር ጠይቀዋል። በነሱ አስተያየት ሁኔታዎችን እያዩ በምግብ ላይ የሚደረገውን የዋጋ ውጣ ውረድ ለማስቀረት በዓለም አቀፍ የፊናንስ ገበያ ላይ ጠንካራ ቁጥጥር ማድረግ አስፈላጊ ነው።  
የዓለም ንግድ ድርጅትም ተሀድሶ እንዲደረግበት ተጠይቋል። ይሁንና ስደተኞችን መልሶ ከመቀበሉ ቅድመ ግዴታ ጋር የተያያዘ የልማት ርዳታን እንደማይደግፊ አስታወቀዋል። የልማቱ ትብብር ዘዴ ፍቱን መሆን አለበት። የሰብዓዊ መብት መመሪያዎችን የማያከብሩ የፍልሰት ውልን አይቀበሉም። የግራ ፓርቲም እንደ አረንጓዴዎቹ ፓርቲ  የተዛባ የንግድ ግንኙነት ፖሊሲን ከመቀጠል ዓለም አቀፍ ማህበራዊ መሰረተልማት እንዲቋቋም ጥረት እንዲያደርግ በመርሀግብሩ ጠይቋል። የልማት ፖሊሲውም እንደአዲስ መሰራት አለበት። በንግድ ወደውጭ ለሚላክ የግብርና ምርት እና ምግብ ድጎማ መስጠት እንዲቆምም ይፈልጋል፣ ምክንያቱም ይህ የአዳጊዎቹን ሀገራት የግብርና መዋቅርን አብዝቶ እየጎዳ ነው። 
የነፃ ዴሞክራቶቹ ፓርቲ አፍሪቃን፣ ወረት ለማሰራት ጥሩ እድል ያለባት አህጉር አድርጎ ሲመለከት፣የልማቱ ትብብር መቀጠልም እንዳለበት ያምናል። ከአፍሪቃ ግዙፍ ፍልሰት አስግቷል የሚለው አማራጭ ለጀርመን ግን የልማቱ ትብብር የጀርመን ንግድን እና ፀጥታ ጥበቃ ጥቅሞችን ያገናዘበ እንዲሆን፣ እንዲሁም፣  የጀርመን ገበያ ለአዳጊ ሀገራት ምርቶች ይበልጥ ክፍት እንዲሆንም ይፈልጋል።  
ይሁን እንጂ፣ ከምርጫው በኋላ አፍሪቃ በጀርመን ፖለቲካ ውስጥ እንደ 2017 የመጀመሪያዎቹ ስድስት ወራት ትኩረት ማግኘቷን እንደሚጠራጠሩ ገልጸዋል። 

አርያም ተክሌ

ኂሩት መለሰ

Audios and videos on the topic