አፍሪቃ ላይ የሚበረታው ሥራ አጥነት | ኤኮኖሚ | DW | 02.08.2017
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

ኤኮኖሚ

አፍሪቃ ላይ የሚበረታው ሥራ አጥነት

የአፍሪቃ ሃገራት ገበያን ያማከለ ልማትን ካልመረጡ የሥራ አጥ ቀውስ እንደሚያሰጋቸው የቶኒ ብሌር ማዕከል ይፋ ያደረገው ጥናት አስጠንቅቋል። ጥናቱ በተወሰኑ የአፍሪቃ ሃገራት በጎርጎሮሳዊው 2040 ዓ.ም. ይከሰታል ያለው ይኸው የስራ አጥነት ቀውስ ለዓለም ኤኮኖሚ ዳፋው ይተርፋል ተብሏል።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 10:05

አፍሪቃ ላይ የሚበረታው ሥራ አጥነት

በጎርጎሮሳዊው 2040 ዓ.ም. አፍሪቃ 50 ሚሊዮን ሥራ አጦች ይኖሯታል። ይኸን የሚለው የዓለም ባንክን መረጃዎች እያጣቀሰ የአፍሪቃ አገሮችን ኤኮኖሚያዊ ፈተና የሚዳስሰው የቶኒ ብሌር ኢንስቲቲዩት ነው። 
ዘገባው እንደ ጋና፤ ኬንያ ፤ ላይቤሪያ ፤ ማላዊ ፤ ናይጄሪያ እና ሴራሊዮንን የመሳሰሉ የአፍሪቃ ሃገራት ትልቅ የኤኮኖሚ እምቅ አቅም ቢኖራቸውም ሁሉንም ዜጎቻቸውን የሚያካትት እድገት ማምጣት ተስኗቸዋል ሲል አትቷል።እንደ ዘገባው በተለይ ዝቅተኛ ገቢ ያላቸው ከሰሐራ በታች የሚገኙ የአፍሪቃ ሃገራት ገበያን ያማከለ ልማት ያሻቸዋል። ዶ/ር ጌትነት ኃይሌ ኢትዮጵያን ጨምሮ አብዛኛው የአፍሪቃ ሕዝብ ሥራ ፈላጊ ብቻ ሳይሆን ገበያ ጭምር እንደሆነ ይናገራሉ። ዶ/ሩ በኖቲንግሐም ዩኒቨርሲቲ የኢንዱስትሪያል ኤኮኖሚክስ ረዳት ፕሮፌሰር ናቸው። በእርሳቸው አባባል የአፍሪቃ ሃገራት ወጣት የሰው ኃይላቸውን "እንዴት ይጠቀሙበታል?" የሚለው ጥያቄ አንገብጋቢ ነው።

"አሁን ያለው የኢትዮጵያም ሆነ በአጠቃላይ የአፍሪቃ አብዛኛው ህዝብ ወጣት ነው። ይኸ ሁኔታ ደግሞ ይቀጥላል። አገሮች ይኸንን እንዴት ይጠቀሙበታል የሚለው ነገር በጣም አስፈላጊ ጥያቄ ነው። ጥሩ ፖሊሲ አስቀምጠህ ይኸንን በከፍተኛ ሁኔታ እየመጣ ያለ የሰው ኃይል መጠቀም ከቻልክ ብዙ ጉልበት እየመጣ ነው ማለት ነው። ብዙ ተመጋቢ እየመጣ ነው ማለት ነው። እነዚህ ነገሮች የኤኮኖሚ እድገት ያመጣሉ። በትክክል ከተጠቀምክበት ትልቅ ተስፋ ነው። በአሁኑ ጊዜ በአፍሪቃ እና በኢትዮጵያ እስከ 45% የሚደርሰው ሕዝብ ከ14 አመት በታች ነው። ከ25 አመት በታች ያለው ወደ 60% ይደርሳል። ግን ያንን እምቅ አቅም ለመጠቀም የሚያስፈልግ ዝግጅት አለ ወይ የሚለው ሌላ ነገር ነው።"

የአፍሪቃ ሃገራት በተከተሏቸው ኤኮኖሚያዊ እና ፖለቲካዊ ፖሊሲዎች በፍጥነት እያደገ ለመጣው ሕዝባቸው ሥራ የሚፈጥር ገበያ ተኮር ልማት ማሳካት እንደተሳናቸው የቶኒ ብሌር ተቋም ዘገባ ያትታል። ለዚህም  መንግሥታቱ ከዘመናዊ የኢንዱስትሪ ፖሊሲ ይልቅ ጠቅለል ያሉ መንገዶችን መምረጣቸውን ይተቻል። መንግሥታቱ እና የልማት አጋሮቻቸው ለፖለቲካዊ ኤኮኖሚ ፈተናዎቻቸው በተናጠል መፍትሔ አለመሻታቸው፣ እንዲሁም፣ እቅዶቻቸውን መተግበር መቸገራቸው ከተጠቀሱት መካከል ይገኛሉ። በተለይ ከሰሐራ በታች ለሚገኙ ሃገራት የክህሎት እና የገበያ ፍላጎት አለመጣጣም ሁነኛው ፈተናዎቻቸው ናቸው። ሃገራቱ የትምህርት ተቋሞቻቸውን ቁጥር ማሳደጋቸው በቂ አለመሆኑን የሚተቹት ዶ/ር ጌትነት ኃይሌ ወጣቶች የስራ ላይ ስልጠና እንደሚያስፈልጋቸው ይናገራሉ።

"አሁን በብዛት የሚነሳው የኢትዮጵያም የአፍሪቃም ችግር ምንድነው የክኅሎት አለመጣጣም የሚባል ነገር አለ። የክኅሎት አለመጣጣም ማለት ገበያ ላይ ፋብሪካዎች የሚፈልጉት የሰው ኃይል አለ። ትምህርት ቤቶች የሚያወጡት ደግሞ አለ። የሁለቱ አለመጣጣም ማለት ነው። ይህ አንዱ ትልቅ ችግር ነው። እሱን መለወጥ መቻል ጊዜ የሚወስድ ነገር ነው። ግን ሊታሰብበት የሚገባ ነገር ነው።"

ዶ/ር ጌትነት ኢትዮጵያን የመሰሉ የአፍሪቃ ሃገራት ከፊታቸው የሚጠብቃቸው ፈተና ለወጣቶቻቸው ሥራ የመፍጠር ጉዳይ ብቻ እንዳልሆነ ይናገራሉ። ለወጣቶች ገንዘብ የሚያቀርቡ ተቋማት ተደራሽነት እና ለወጣቶቹ ክኅሎት የሚመጥን ክፍያ መኖር ተጨማሪ ጉዳዮች ናቸው። 
እሸቴ በቀለ
አርያም ተክሌ 

Audios and videos on the topic