አፍሪቃውያን ወጣቶችና የዩኤስ አሜሪካው መርሃ-ግብር | ባህል | DW | 07.08.2015
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ባህል

አፍሪቃውያን ወጣቶችና የዩኤስ አሜሪካው መርሃ-ግብር

ፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማ ሰሞኑን ለአፍሪቃ ጠቃሚ ድርሻ ሊያበረክቱ ይችላሉ ተብለው ዘንድሮ ወደ ሀገራቸው ለተጋበዙ 500 ወጣት አፍሪቃውያን በኃይት ሀውስ ንግግር አድርገዋል። ልክ ከዓመት በፊት ደግሞ ሌሎች 500 ከተለያዩ የአፍሪቃ ሀገራት የተውጣጡ ወጣቶች የዚህ መርሃ ግብር አካል ነበሩ። ለመሆኑ እነዚህ ወጣቶች ዛሬ ምን እያደረጉ ይገኛሉ?

አውዲዮውን ያዳምጡ። 10:52

የኦባማ የወጣት አፍሪቃውያን መርሃ ግብር

የዩኤስ አሜሪካ ፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማ እጎአ 2010 ዓም የአፍሪቃውያን ወጣቶችን ለማበረታታት የጀመሩት መርሃግብር እንደቀጠለ ነው። ለአፍሪቃ እድገት እና ብልፅግና ትልቅ ሚና ይጫወታሉ በሚባለው መርሃግብር ስር ዘንድሮም ከተለያዩ የአፍሪቃ ሀገራት የተውጣጡ አፍሪቃውያን ለስድስት ሳምንታት በዮናይትድ ስቴትስ ቆይታ አድርገዋል። የዛሬ ዓመት በዚሁ መርሀ ግብር የተሳተፉ ስድስት ወጣቶችን በአነጋገርንበት ወቅት በአገኙት እድል ተደስተው እና ወደ ኢትዮጵያም ሲመለሱ በየተሰማሩበት የስራ መስክ የበለጠ መስራት እንደሚፈልጉ ገልፀውልን ነበር። ወጣቶቹ ከአንድ ዓመት በኋላ በርግጥ በምን ሁኔታ ላይ ይገኛሉ? አላማቸውን ምን ያህል ከግብ አድርሰዋል? ጥቂቱን በስልክ አግኝተን ጠይቀናቸዋል።
የህግ ባለሙያ የሆነው ደግነህ ወታንጎ በኦባማ፤ የወጣት አፍሪቃውያን የመሪዎች መርሃ ግብር ስር በ2006 ዓ ም ወደ ዩናይትድ ስቴትስ የመሄድ እድሉን ካገኙ 12 ኢትዮጵያውያን አንዱ ነው። አይነ ስውሩ ደግነህ በአሁኑ ወቅት ካምፓላ ዩጋንዳ ውስጥ እየሰራ ይገኛል። በአካል ጉዳተኞች ጉዳይ ላይ መስራት የበፊትም ፍላጎቱ ነበር። ደግነህ ከሁለት ወር በኋላ ወደ ኢትዮጵያ ይመለሳል። በአሁኑ ሰዓት ኢትዮጵያ የምትገኘው ኢዳ ዘካሪያስ ደግሞ አዲስ አበባ በሚገኘው የተባበሩት መንግስታት ቢሮ ውስጥ የነበራትን ስራ እንደቀጠለች ነው። ወጣቷ በሴቶች ጉዳይ ላይ የበለጠ ለመስራት እንደምትፈልግ ከዚህ ቀደም ነግራን ነበር። ኤዳ ወደ ኢትዮጵያ ከተመለሰች ከአንድ ዓመት በኋላም ይህን ምኞቷን ዕውን እያደረገች ትገኛለች።


እንደ ደግነህ የህግ ባለሙያ የሆነችው ሀሌታ ግደይ ፤ «ብዙም የተለየ ተዓምር የመፍጠር አላማ ይዤ አይደለም ወደ ኢትዮጵያ የምመለሰው» ብላን ነበር።ዘንድሮም በጀመረችው ዕቅድ ላይ ተጠናክራ እየሰራች ትገኛለች።
ዩናይትድ ስቴትስ እንደዚህ አይነት እድል ለአፍሪቃውያን የምትሰጠው የሀገሪቷን ጥቅም እና ፍላጎት ለማስጠበቅ ነው እያሉ አንዳንዶች ይተቻሉ። ይህ በርግጥ ምን ያህል እውነት ነው? ወጣቶቹስ በሚያደርጉት ስራ ምን ያህል ነፃ ናቸው? ለዚህ እና ሌሎች ጥያቄዎችም ወጣቶቹ ምላሽ ሰጥተውናል።
ፕሬዚዳንት ኦባማ ዘንድሮ ለ500 ወጣት አፍሪቃውያን ባሰሙት ንግግር አፍሪቃውያንን ወደ ዩናይትድ ስቴትስ መጋበዝ ብቻ ሳይሆን 80 ወጣት አሜሪካውያንንም በሚቀጥለው ዓመት ወደ አፍሪቃ እንደሚልኩ ተናግረዋል። የዩኤስ አሜሪካ የወጣት አፍሪቃውያን መርሃግብርን ፋይዳ በአጭሩ የቃኘንበት የወጣቶች ዓለም ዝግጅትን በድምፅም ያገኙታል።
ልደት አበበ
ነጋሽ መሐመድ

Audios and videos on the topic