አፍሪቃውያን እና የትራምፕ አሜሪካ | አፍሪቃ | DW | 12.11.2016
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

አፍሪቃ

አፍሪቃውያን እና የትራምፕ አሜሪካ

በርካታ አፍሪቃውያን ዩናይትድ ስቴትስ በአፍሪቃ ላይ የምትከተለው ፖሊሲ ትረምፕ ስልጣን ሲረከቡ ሊቀየር ይችላል የሚል ሥጋት አላቸው። ለሌሎች አሜሪካ በአፍሪቃ ስታደርገው የቆየችውን ጣልቃ ገብነት ስለሚቀንስ መልካም ዜና አድርገው ወስደውታል። 

አውዲዮውን ያዳምጡ። 05:51
አሁን በቀጥታ እየተሰራጨ ያለ
05:51 ደቂቃ

የትራምፕ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ እና አፍሪቃ  

ለዶናልድ ትራምፕ ፤ ፕሬዝዳንት ባራክ ኦቦማ እና ሔላሪ ክሊንተን ችላ ያሉት ዓለም በመጥፎ ሰዎች የተሞላ አደገኛ ሥፍራ ነው ይላሉ ተንታኞች። ትራምፕ በምረጡኝ ዘመቻቸው የእስልምና እምነት ተከታዮችን ማገድ፤ ስደተኞችን ማባረርን ጨምሮ በርካታ እርምጃዎች ሊወስዱ ቃል-ቢገቡም 45 ኛው የአገሪቱ ፕሬዝዳንት ሆነው ከመመረጥ አላገዳቸውም። ከፖሊሲዎቻቸው ይልቅ በአወዛጋቢነታቸው የዓለምን ትኩረት የሳቡት ትረምፕ መመረጥ ካስገረማቸው መካከል አንዱ በደቡብ አፍሪቃው የቪዝ ዩኒቨርሲቲ የዓለም አቀፍ ግንኙነት ፕሮፌሰር የሆኑት ጆን ስትራም ላው ናቸው።

«የአሜሪካውያኑ ስነ-ልቦና በአሁኑ ወቅት ቅሬታ እና ፍርሐት የነገሰበት ይመስላል። ለምን እድላችንን በዶናልድ ትራምፕ አንሞክርም ብለው ድምፅ የሰጡ ይመስላል።»
የአዲስበባ ዩኒቨርሲቲው መምህር  ዶ/ር ያዕቆብ አርሳኖ የዶናልድ ትረምፕ መመረጥ አሜሪካ በአፍሪቃ የምትከተለው ፖሊሲ ላይ አንዳች ለውጥ ስለማምጣቱ እርግጠኛ አይደሉም። 
«የአሜሪካ ፖለቲካ ሥርዓት ጠንካራ መሰረት ያለው በመሆኑ ለአንድ ግለሰብ የሚያሸረግድ አይደለም። ቢሆንም ፕሬዝዳንቱ ከፍተኛ ስልጣን ያለው እና ተፅዕኖ ፈጣሪ ነው። በሕዝቡ እና አገሪቱ ላይ በሚያምነው እና በሚያስበው ተፅዕኖ ለማሳረፍ መሞከሩ አይቀርም። ነገር ግን በሌሎች እንደ ኮንግረስ ባሉ ተዋናዮች ቁጥጥር ይደረግበታል።»

እንደ ያዕቆብ አርሳኖ ሁሉ በዓለም አቀፍ የፖለቲካ እና የኤኮኖሚ መድረክ የአሜሪካንን ጥቅም አስቀድማለሁ ሲሉ የቀሰቀሱት ዶናልድ ትራምፕ መመረጥ በርካታ ፍሪቃውያንን አስገርሟል። የምረጡኝ ዘመቻቸውን የተከታተሉ ተንታኞች አፍሪቃ በዶናልድ ትራምፕ የውጭ ፖሊሲ ቸል ልትባል እንደምትችል ከወዲሁ ስጋታቸውን እየገለጡ ነው። ሰውየው በምረጡኝ ዘመቻቸው አፍሪቃን አሊያም በአህጉሪቱ የሚገኙ አገሮች አሳሳቢ ጉዳዮች እምብዛም ሲጠቅሱ አልተደመጡም። የውጭ ጉዳይ ፖሊሲያቸው ጠብ ጫሪነት የሚስተዋልበት ከትብብር ይልቅ ማግለል የሚጫነው እንዳይሆነ የሰጉም ጥቂት አይደሉም። ሰውየው ለሰብዓዊ እርዳታ ቸልተኛ መሆናቸው ለአፍሪቃ እና አፍሪቃውያን መልካም ዜና አይደለም።

ባራክ ኦባማ በሥልጣን በቆዩባቸው አመታት አፍሪቃ በሽብር ላይ ለተከፈተው ዘመቻ ዋንኛ ግንባር ሆና አገልግላለች። አሜሪካ የአፍሪቃ ጦርን ለማሰልጠንና እና የራሷን ወታደራዊ የጦር ሰፈር ለመመስረት ከፍተኛ ገንዘብ ወጪ አድርጋለች። ዛሬም ድረስ የአሜሪካ ሰው አልባ የጦር አውሮፕላኖች በሶማሊያ እና ሊቢያ ድብደባ ይፈፅማሉ። በውጭ ጉዳይ ፖሊሲያቸው አብዝተው የሚተቹት ዶናልድ ትረምፕ ይኽን አቋም ለማስቀጠላቸው ለጊዜው የሚታወቅ ነገር የለም። ኬንያዊው የፖለቲካ ተንታኝ ናፍታሊ ማውራ ዶናልድ ትራምፕ አሜሪካንን ለይቶ የመጠበቅ ሥልት ለአፍሪቃ አዋጪ አይደለም ሲሉ ይተቻሉ።

«በግሌ ለአፍሪቃም ይሁን ለኬንያ የሚያናድድ ውጤት ነው። አፍሪቃ ለእርሳቸው ትኩረት የሚሰጣት አህጉር አይደለችም። በምረጡኝ ዘመቻቸው የአሜሪካን ኩባንያዎችን መጠበቅን ሲያቀነቅኑ የነበሩ ግለሰብ ናቸው።»

ዶናልድ ትረምፕ አፍሪቃን ስለማወቃቸው በርካቶች ጥርጣሬ አላቸው። በጎርጎሮሳዊው 2013 ዓ.ም. ከቀድሞው የደቡብ አፍሪቃ ፕሬዝዳንት ኔልሰን ማንዴላ ጋር ጥሩ ወዳጅነት እንደነበራቸው ተናግረው ነበር። ከአመት በኋላ ግን ደቡብ አፍሪቃ ዝርክርክ ነች ሲሉ ወርፈዋል። በጎርጎሮሳዊው 2014 እና 2015 በተከሰተው የኢቦላ ወረርሽኝ ትረምፕ ድሮም አፍሪቃ የበሽታ እና ሕመም አህጉር ነች ሲሉ ከሞገቱት መካከል አንዱ ነበሩ። ሰውየው በሶስት የምዕራብ አፍሪቃ አገራት የተከሰተውን ወረርሽኝ ለመግታት የተሰማሩ አሜሪካውያን ተመልሰው ወደ አገራቸው መግባት የለባቸውም እስከ ማለትም ደርሰዋል። 

በዶናልድ ትራምፕ መመረጥ በርካታ አፍሪቃውያን ሥጋት ቢገባቸውም ተስፋ የሰነቁ አልጠፉም። በናይጄሪያ የካዱና ስቴት ዩኒቨርሲቲ መምህር የሆኑት ዶ/ር ትኩር አብዱልቃድር ከእነዚህ መካከል አንዱ ናቸው።

«ላለፈው አንድ አመት ከስድስት ወር በናይጄሪያ በስልጣን ያለ አዲስ መንግስት አለን። በዩናይትድ ስቴትስም ለውጥን የሚያቀነቅን አዲስ መንግስት ይመሰረታል። በናይጄሪያ ሙስናን ለመዋጋት ቆርጦ የተነሳ መሪ አለ። በዓለም ልዕለ ኃያል አገርም በናይጄሪያ እና በሌሎች አገሮች የሚታየውን ሙስና እና ብልሹ አሰራር  በግልፅ የሚያወግዝ መሪ ሊመጣ ነው። አብረው ሊሰሩ ይገባል ብዬ አምናለሁ።» 

እሸቴ በቀለ

ነጋሽ መሐመድ

Audios and videos on the topic

ተዛማጅ ዘገባዎች