አፍሪቃውያን አፍሪቃዊነትን እንዴት ይገልፁታል? | ወጣቶች | DW | 12.07.2019
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

ወጣቶች

አፍሪቃውያን አፍሪቃዊነትን እንዴት ይገልፁታል?

አብዛኛውን ጊዜ አፍሪቃ ከአህጉሯ ሰዎች ይልቅ በምዕብራባዊያን እይታ ወይም እነሱ በጻፉት እና በተናገሩት ስትገለፅ ይዘወተራል። የጥቁሮች አህጉር፣ የ 3ኛው ዓለም፣ በማደግ ላይ ያሉ ሃገራት፣ እየተባለ ለአፍሪቃ ማኅበረሰብ የተለያዩ ስሞች ወጥተዋል። አፍሪቃውያንስ ስለ ራሳቸው ምን ይላሉ?

አውዲዮውን ያዳምጡ። 10:00

አፍሪቃውያን አፍሪቃዊነትን እንዴት ይገልፁታል?

DW ደቡብ አፍሪቃ ውስጥ ካነጋገራቸው ወጣቶች አፍሪቃዊነትን እንዲህ ይገልፁታል።
«አፍሪቃዊነት እንደ አንድ በተለይም በርካታ ባህል እንዳለባት እንደ ጥቁር ደቡብ አፍሪቃዊት የምለው ከተለያየው ባህል ጋር ተያያዥ የሆኑ ብዙ ነገሮች አሉ። ይህ ደግሞ ከምዕራቡ ዓለም እጅጉን የተለየ ነው። አፍሪቃ ውስጥ የምንጋራቸው በርካታ ነገሮች አሉ። ወደ ሌላ የአፍሪቃ ሀገር ብሄድ በቀላሉ ከባህላቸው ጋር መዛመድ እችላለሁ። »
«ስለአፍሪቃዊነት ስናወራ በእኛው በአፍሪቃውያኖች መካከል የበዛ ጥላቻ ያለ ይመስለኛል።  ስለ አፍሪቃዊነት የበለጠ ማወቅ አለብን።»
« አፍሪቃዊነት ማለት ስለ ራስ ማንነት ማወቅ ፣ የመጡበትን ታሪክን እና ባህልን መረዳት ነው።  አሁን በምንኖርበት የሰለጠነ ዓለም አንዳንዴች የተለዩ መሆንን ይመርጣሉ ነገር ግን አብዛኛው ወጣት በመጨረሻ በአፍሪቃዊነቱ መኩራት ጀምሯል። ሁሉም ባህል ጥሩ ነው። በመጀመሪያ ነገር ግን አፍሪቃዊ በመሆኔ እኮራለሁ። አንዳንድ ሰዎች አፍሪቃዊ መሆንሽን በፀጉርሽ ፣ በምትቀጥይው ዊግ ምክንያት ልትጠይው ትችያለሽ ሊሉ ይችላሉ። ነገር ግን እውነት ለመናገር አፍሪቃዊ መሆን ክብር ነው። በማንኛውም ሰዓት ቢሆን አፍሪቃዊነቴን መቀየር አልፈልግም።» 


በተለይ የባርነት ንግድ ከተካሄደባቸው የአፍሪቃ ሃገራት የመጡ ሰዎች ወይም ለረዥም ጊዜ በቅኝ ግዛት የተያዙ ሃገራት ዜጎች የማንነት ጥያቄ ሲረብሻቸው ይስተዋላል። እኢአ በ2012 ለዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዚደንታዊ እጩነት የተወዳደሩት ሄርማን ኬን ለምሳሌ አፍሮ አሜሪካዊ ከመባል ይልቅ ጥቁር አሜሪካዊ መባሉን እንደሚመርጡ ተናግረዋል። 
ኢትዮጵያውያን ወጣቶችስ አፍሪቃዊነትን እንዴት ይገልፁታል? ራሳቸውንስ ምን ያህል አፍሪቃዊ አድርገው ያያሉ?
«አፍሪቃዊነትን አይደለም ሰው ኢትዮጵያዊነቱን ለመቀበል የተቸገረበት ወቅት ላይ ነው ያለነው።» « ያለንን ትልቅ ዘጋ የማንጠቀምበት ስፍራ ናት።« ዝቅጠኝነት ነው የሚሰማኝ። መንፈሳችንን የሚያቀጠቅዙ ድርጊቶች እየተከናወኑ ስለሆነ እንዴት ብለን እንኩራ። »

ካሜሮናዊው ማቦሎ ዩፋንዪ በርሊን ከተማ የሚገኝ የጥቁር አፍሪቃውያን ማኅበረሰብ ስብስብ መሥራች ናቸው።« የአፍሪቃውያን ማንነት በአውሮጳውያን ቀኝ ገዢዎች ተከፋፍለን ስለነበር ራሳችንንም ነጣጥለን ነው የምናየው። ራሴን እንደ አፍሪቃዊ ነው የማየው። ነገር ግን በአፍሪቃ ግዛቶች ራሴን የምገልፅበት ሌላ መጠሪያ ቢኖረኝ እመርጥ ነበር። »

አንዳንድ በቅኝ ግዛት ስር የነበሩ አፍሪቃውያን የአፍሪቃዊ ማንነታችንን እናስመልሳለን ሲሉ ይደመጣል። በርግጥ ይህን እውን ማድረግ ይችሉ ይሆን? የፖለቲካው ተንታኝ ዩፋንዪ ይቻላል ባይ ናቸው።«ማንነታችንን የምናስመልስበት በርካታ መንገዶች አሉ። አንዱ መንገድ ውጭው ዓለም የሚኖረው ተመልሶ ወደ አፍሪቃ አህጉር የመጣው ወገን ነው። ለዚህም ነው በውጭ ሃገራት የሚኖረው አፍሪቃዊ ትልቅ ሚና የሚጫወተው። ይህ አንዱ መንገድ ነው። ራሳችንን እንደ አፍሪቃዊ ሳይሆን የምናየው እንደ ሙስሊም ወይም ክርስትያን ነው። አሁን የምናወራው  በእንግሊዘኛ ቋንቋ ነው። እነዚህ ናቸው የማንነታችን ገፅታዎች። የምንናገረው ቋንቋ የማንነታችን መገለጫ ነው። ይህንን ማንነታችን ሸጠን አሁን ከነጮች እያስመለስን ነው። »
ሳምሶን ተስፋይ በጀርመን ሽቱትጋርት ከተማ የቤተ ክርስትያን አገልጋይ እና የመጽሐፍ ቅዱስ መምህር ናቸው። እሳቸው ደግሞ አፍሪቃዊነትን እንዲህ ይገልፁታል።  « አፍሪቃዊነት ከአስተሳሰብ የሚመጣ ነው።  ከቀዬ የሚጀምረው ስሜት ሰው እያደገ ሲመጣ አካባቢያዊ ወይም ብሔራዊ ስሜትን ይፈጥራል ከዛ ደግሞ የዘመኑ ቴክኖሎጂ ምድራችንን ጠባብ ስላደረጋት የሰው አስተሳሰብም አህጉራዊ ይሆንና የአፍሪቃዊነትን ስሜት ይፈጥራል።»

ሳምሶን አፍሪቃዊ ነኝ ብለዋል። ይሁንና አንዳንድ ኢትዮጵያውያን ራሳቸውን ለይተው ወይም ከሌሎች አፍሪቃውያን አብልጠው ሲያዩ ይስተዋላል።  እንዲህ አይነት አስተሳሰብ ሳምሶንንም ገጥሟቸው ያውቃል። « ይሄ የአስተሳሰብ ችግር ነው። እኔ እራሴን በልዩ አይነት ሁኔታ ከለካሁ ወይም ሰው ከሚባለው መለኪያ ውጪ ራሴን ካየሁ ከሌላ ሰው ጋር ያለውን ግንኙነት ያበላሸዋል።»ሸጋው ማሬ ቢሻው ደግሞ ከደብረ-ማርቆስ አፍሪቃዊነትን የሚረዳው እንዲህ ነው።« በምድር ስኖር እንደ አፍሪቃዊነቴ የሚመሥጠኝ የለም። ራሴን የአፍሪቃ ልጅ፣ የምድሯ ፍጡር፣ የእናታለም ልጅ አድርጌ ነው የማየው። በርግጥ ከኬንያ ውጭ ሌሎች አፍሪቃውያንን አላውቃቸውም።  ግን ኢትዮጵያ ቁጭ ብዬ ወደ ዚምባቡዌ ብንደረደር፤ ወደ ሱዳን ባገድም ወደ ምዕራብ አፍሪቃውያን ብቀላቀል ደሞቼ፣ ዘሮቼ፣ ሰዎቼ ነው የሚመሥሉኝ። 

«የተስፋችን ምድር አፍሪቃ ከሰሜን እስከ ደቡብ፤ ከምዕራብ እስከ ምሥራቅ የተዘረጋ የተፈጥሮ ሐብት ቢኖራትም ልጆቿ በአሜሪካና

በአውሮጳ የተሰደዱት ራሳቸውን እንደ «አፍሪቃዊ» ባለማየት አይመሥለኝም። የቴክኖሎጂው ድክመት፤ የሥራ ዕድሉ ጥበት፤ 

የአስተዳደሩ ልሽቀት ነው የሚያስወጣቸውእንጂ አንድ ሱዳናዊ አፍሪቃዊነቱን፤ አንድ ኢትዮጵያዊ አፍሪቃዊነቱን፤ ደቡብ አፍሪቃዊው

 የእምዬ ልጅነቱን የሚያስበውን ያኽል የምዕራብ አውሮጳ ዜጎች ባንድ ሕብረት ተጠቃልለው አይተያዩም። 

እኔ ኢትዮጵያዊ ነኝ። ሱዳናዊው የእኔ ነው። ምድር ትጠብበኛለች። የምዕራብ አፍሪቃ ጫካዎች ይናፍቁኛል፤ ካካዎ ምርቱ

 ይታወሰኛል። የደቡብ አፍሪቃ የባሕር ዳርቻዎች ይናፍቁኛል። ወጣት ነኝ። ሥሜቴ ድንበር፣ ወሰን የለውም።

 ልሻገር፣ ልሔድ የምሻው አፍሪቃ ውስጥ ነው። እኔ አፍሪቃዊ ነኝ።»

«እንደኔ አመለካከት አፍሪቃዊቴ በጣም ያስደስተኛል ምክንያቱም ጠንካራ ነን እናም ዝንጉርጉር ነን ብዙ ቋንቋዎችም አሉን።» መምህር ሀቢብ «እኔ አፍሪካዊነቴን እኮራበታለሁ እንደውም ከሌሎች ሀገራት ይልቅ ደግሞ እኔነቴን  ኢትዮጵያዊነቴን  ጥቁር አንበሳ ስል እኮራበታለሁ እንደ አጠቃላይ ግን  በአፍሪቃ የተንሰራፋውን ሱሰኝነት ከእኔ ጀምሬ እቃወማለሁ

ሱስ ማንነትን ዝቅ ያደርጋል !! ሲሉ ኢትዮጵያውያኑ አፍሪቃዊነትን ይገልፃሉ። የኬንያውያን ወጣቶች ደግሞ አፍሪቃዊነትን እንዲህ ይገልፁታል።« ለረዥም ዓመታት አልነበርንም ማለት ይቻላል። ብዙ ነገር ከተከናወኑበት የጥቁር ታሪክ በኋላ አሁን ተመልሰናል። የዚህች አህጉር የወደፊት ጊዜ የተሻለ እንዲሆን ማንነታችንን መፈለግ አለብን። ይህ ደግሞ ትምህርት ቤት ካሉ ልጆች ይጀምራል። አብሮ ያድጋል። ትኖሪዋለሽ፣ ትተነፍሺዋለሽ።»
«ጥቁር የሚለው በሰው ልጆች ምድብ ጨርሶ የለም። አፍሪቃ የሚለው የለም። ሰው ለመባል ወይ ነጭ መሆን ወይም ከነጭ መጠጋት ይጠይቃል። ስለዚህ አፍሪቃን ለማካተት ስንል ሰው የሚለውን አመለካከት እያሰፋን ነው ያለውን።» ይላሉ አፍሪቃውያን አፍሪቃዊነትን ሲገልፁ።

ልደት አበበ

ሸዋዬ ለገሠ
 
 

Audios and videos on the topic