አፍሪቃውያን ስደተኞች በሞሮኮ | አፍሪቃ | DW | 02.05.2015
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

አፍሪቃ

አፍሪቃውያን ስደተኞች በሞሮኮ

በአስር ሺህ የሚቆጠሩ አፍሪቃውያን በሞሮኮ በኩል አድረገው አውሮጳ ህብረት አባል ሀገራት ለመግባት ይሞክራሉ። ይኸው ሙከራቸው ግን በዚችወ ሰሜን አፍሪቃዊት ሀገር በሚገኙት የስጳኝ ግዛቶች በተተከለው አጥር የተነሳ ሲከሽፍ ታይቷል። ሞሮኮ ሕጋዊ የመኖሪያ ፈቃድ እንዲያገኙ ለመርዳት ትፈልጋለች።

ይሁን እንጂ፣ በየቀኑ ብዙ እንቅፋቶች ናቸው የተደቀኑባቸው ፣ ለዚህም ብዙዎች የአውሮጳ ህብረት ተጠያቂ ያደርጋሉ። ወደ አውሮጳ ለመግባት የሚሞክሩ በወቅቱ በሞሮኮ የሚገኙ አፍሪቃውያን ስደተኞች ሁኔታ ምን ይመስላል? ከአፍሪቃ ቀንድ ሀገራት እና ከመካከለኛው ምሥራቅ የሚሰደዱ ስደተኞች አውሮጳ ህብረት አባል ሀገራት ለመግባት በተለይ በወቅቱ በቀውስ ወስጥ የምትገኘዋን ሊቢያ፣ ምንም እንኳን አደገኛ ቢሆንም፣ ዋነኛ መተላለፊያ አድርገዋታል። የመገናኛ ብዙኃን ዘገባዎች እንዳመለከቱት፣ የሜድትሬንያን ባህርን ለማቋረጥ በሚያደርጉት ሙከራ ሕይወታቸውን ያጡትን ስደተኞች ባህሩ ይቁጠራቸው። በሰሜን አፍሪቃቷ ሀገር ሞሮኮ በሚገኙት የስጳኝ ሴውታ እና ሜሊያ ከተተከለው ስድስት ሜትር ርዝመት ካለው የሽቦ አጥር ጀርባ የተሻለ ሕይወት መምራት እንደሚችሉ በአስር ሺህ የሚቆጠሩ አፍሪቃውያን፣ በተለይም ብዙ የካሜሩን፣ ሴኔጋል፣ የኮት ዲቯር፣ ማሊ፣ ኮንጎ ተወላጆች ተስፋ አድርገዋል። ከሞሮኮ ጋ የሚያዋስናቸው ድንበር ነው አፍሪቃን ከአውሮጳ ህብረት አባል ሀገራት ጋ የሚያገናኘው ብቸኛው መንገድ። በአውሮጳ የተሻለ ሕይወት ለመጀመር ከሚፈልጉት መካከል የጊኒ ተወላጅ ዦን ቤንዋት አንዱ ነው።

« በስጳኝ በአንድ የግንባታ ፕሮዤ የሚሰራ አንድ ጓደኛ አለኝ። ወደ ትውልድ ሀገራችን ተመልሶ በመጣበት አንድ ወቅት በስጳኝ ያለው የስራ ሁኔታ ከኛ ሀገር የተሻለ መሆኑን ነግሮኛል። እና እኔም ለምን አልሞክርም አልኩ። በዚያን ጊዜ ወደ ሞሮኮ መሄዱ ቀላል ነበር፣ እንዲህ እንዳሁኑ የሽቦ አጥር አልተተከለም ነበር። »

በተመድ የስደተኞች ጉዳይ ተመልካች መስሪያ ቤት ዘገባ መሠረት፣ ባለፈው ዓመት ከ5,000 የሚበልጡ አፍሪቃውያን በሕገ ወጥ መንገድ ሴውታ እና ሜሊላ ገብተዋል። ከ600 በላይ ስደተኞች ነበሩ ከሁለት ወራትም በፊት እአአ ሰኔ 2014 ዓም በአውሮጳ ህብረት ገንዘብ የተሰራውን እና በፍፁም አይበገርም ተብሎ የታሰበውን የሽቦ አጥር ዘለው ለማለፍ የሞከሩት። 35 ቱ ተሳክቶላቸዋል፣ ከነዚሁ ብዙዎቹም በዚሁ ሙከራ ወቅት የመቁሰል አደጋ ደርሶባቸዋል። 15 አፍሪቃውያን ከአንድ ዓመት በፊት ዋኝተው ወደ ሴውታ ለመሄድ ሲሞክሩ ሕይወታቸው አልፋለች። የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶች በዚያን ጊዜ ያወጡዋቸው ዘገባዎች እንዳሳዩት፣ ስደተኞቹ የሞቱት ድንበር ጠባቂ ዘቦች በተኮሱባቸው የጎማ ጥይት ተመተው ነው።

ሌሎች ብዙዎችም ከስንት አደገኛ ሙከራ በኋላ ሴውታ እና ሜሊላ ከደረሱ በኋላ በግዳጅ ወደ ሞሮኮ ተመልሰዋል፣ ይህ ርምጃ ዓለም አቀፍ ውሎችን የሚጥስ ቢሆንም የስጳኝ ምክር ቤት ርምጃውን አፀድቆታል። በዚህም የተነሳ በወቅቱ ብዙ ስደተኞች ሞሮኮ ውስጥ መቆየት ተገደዋል። ይህንን ተከትሎ እአአa ሰኔ 2014 ዓም ሞሮኮ እነዚህ ስደተኞች በሀገሯ በሕጋዊ መንገድ መኖር የሚችሉበት ልዩ ደንብ ያወጣች ብቸኛዋ ሰሜን አፍሪቃዊት ሀገር መሆንዋን የፍልሰት እና ስደት ጉዳይ ተመልካች መስሪያ ቤት ሚንስትር አኒስ ቢሩ ለዶይቸቬለ ገልጸዋል።

« ስደተኞቹ ከተመዘገቡ በሞሮኮ የአንድ ዓመት የመኖሪያ ፈቃድ ማግኘት የሚያስችላቸው ውሳኔ ተደርሶዋል። በዚሁ መሠረት፣ በመጀመሪያ ደረጃ፣ የመኖሪያ ፈቃዳቸው ሊራዘምላቸው ይችላል፣ በሁለተኛ ደረጃ ደግሞ ልክ እንደ ሞሮኮ ተወላጆች ከማህበራዊው አገልግሎት ተጠቃሚ ሊሆኑ ይችላሉ። »

እንደ ሚንስትር ቢሩ አባባል፣ ስደተኞቹ ስራ መስራት ባይችሉም፣ የጤና ጥበቃ እና መኖሪያ ቤት ማግኘትን የመሳሰሉ አገልግሎቶችን ሊያገኙ ይችላሉ።

በንድፈ ሀሳብ መሠረት፣ ይኸው ሕግ መልካም ዓላማ በመያዙ የሚሞገስ መሆኑን የጀርመናውያኑ ግብረ ሠናይ ድርጅት «ብሮት ፊውር ዲ ቬልት » ባልደረባ ሶፊያ ቪርሺንግ ገልጸዋል። ቪርሺንግ እንዳመለከቱት፣ በተለይ፣ በጤና ጥበቃው ዘርፍ አንዳንድ መሻሻል ተመዝጎቦዋል። ይሁንና፣ ሕጉ መኖሩ ለብዙዎቹ ስደተኞች እንግዳ ነው።

« እስካሁን ከተጓዳኞቻችን እና ችግሩ ከሚመለከታቸው ወገኖች እንደሰማነው፣ የዚሁ ሕግ ተጠቃሚ ሊሆኑ ይችላሉ የሚባሉት ችግር ላይ የሚገኙት ስደተኞች ስለሕጉ መውጣት የሚያውቁት ነገር እንደሌለ ነው። »

ሶፊያ ቪርሺንግ እንደሚገምቱት፣ በአሁኑ ጊዜ በሞሮኮ - 40,000 ስደተኞች የሚገኙ ሲሆን፣ ከነዚህም ብዙዎቹ ሕጋዊ የመኖሪያ ፈቃድ የሌላቸው ናቸው። ካለ ሕጋዊ መኖሪያ ፈቃድም መስራት ስለማይችሉ ብዙዎች ልመና እና አልሆነ ቦታ ውስጥ መግባት እንደሚገደዱ ነው ቪርሺንግ ያመለከቱት። በዚህም የተነሳ፣ የሞሮኮ ተወላጆች ስለስደተኞ ጥሩ አስተያየት ስለሌላቸው ብዙ ጊዜ በስደተኞቹ አኳያ ዘረኝነት እና አድልዎ ይታያል፣ ይህም አልፎ አልፎ ወደ ኃይሉ ተግባር ይቀየራል።

ብዙ ስደተኞች ዘረኝነትን እና የሞሮኮ መንግሥት መስሪያ ቤቶች ሕገ ወጥ ስደተኞች የሚያዋክቡበትን፣ በስደተኞች መጠላያ ጣቢያዎችም አሰሳ የሚያካሂዱበትን ድርጊት በመፍራት የመመዝገብ መብታቸውን አይጠቀሙበትም።

የአውሮጳ ህብረት በስደተኞች አኳያ የሚሰራበትን ግትር አቋም በማስፈፀሙ ረገድ ሞሮኮ ተባባሪ ናት፣ ይላሉ ሶፊያ ቪርሺንግ።

« አውሮጳውያኑ በጎረቤት ሀገራት አኳያ በሚከተሉት ፖሊሲ መሠረት፣ አድርግልኝ ላርድርግልህ ዓይነት አሰራር ነው የሚጠቀሙት፣ ማለትም፣ አንድ ሀገር ከአውሮጳ ህብረት ጋ ለመተባበር ከፍተኛ ዝግጁነት ካሳየች፣ ከህብረቱ ብዙ ልትጠብቅ እንደምትችል ነው የተረዳነው። »

የአውሮጳ ህብረት ተባባሪ ናት በምትባለዋ ሞሮኮ ውስጥ በስደተኞች ላይ ለሚፈፀመው የኃይል ተግባር በተዘዋዋሪ መንገድ በኃላፊነት የሚጠየቀው ህብረቱ በሚል በራባት ዩኒቨርሲቲ የማህበራዊ ጥናት መምህር፣ የፀረ ዘረኝነት እና ስደተኞች ደህንነት ተሟጋች ቡድን ሊቀ መንበር ሜህዲ አሊዋ ወቅሰዋል።

« የአውሮጳ ህብረት ምንም እንኳን ራሱ በመብት ረገጣው ላይ በቀጥታ ባይሳተፍም፣ ሌሎች የመብት ጥሰት እንዲፈፅሙ ያበረታታል። »

አውሮጳ ስደተኞችን በቀላሉ በግዳጅ ወደ ሞሮኮ መመለስ የሚያስችላት ስምምነት ከተዘጋጀ ብዙ ጊዜ ቢሆነውም ፣ ሞሮኮ እስካሁን አላፀደቀችውም።

አርያም ተክሌ/ሂልከ ፊሸር

አዜብ ታደሰ

Audios and videos on the topic