አፍሪቃውያኑ እና የፓናማ ሰነዶች | አፍሪቃ | DW | 11.04.2016
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

አፍሪቃ

አፍሪቃውያኑ እና የፓናማ ሰነዶች

በፓናማ ሰነዶች እስካሁን አንድም የኢትዮጵያዊ ፖለቲከኛ አሊያም ኩባንያ ስም አልተገኘም። ይሁንና በሰነዱ ስማቸው ከሰፈሩ የውጭ አገራት ኩባንያዎች መካከል በኢትዮጵያ በስራ ላይ የተሰማሩ አሊያም ከኢትዮጵያውያን ጋር ለመገበያየት የሞከሩ አልጠፉም።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 12:36
አሁን በቀጥታ እየተሰራጨ ያለ
12:36 ደቂቃ

የፓናማ ሰነዶች

በጎርጎሮሳዊው 2010 ዓ.ም. በነዳጅ ዘይት እና ጋዝ ፍለጋ ላይ የተሰማራ ሔሪቴጅ የተሰኘ ኩባንያ የዩጋንዳ መንግሥት የሚጠብቅበትን 400 ሚሊዮን ዶላር (280 ሚሊዮን ፓውንድ) የገቢ ግብር ላለመክፈል መላ ይፈልጋል።

ሔሪቴጅ የሚጠበቅበትን ግብር ለመሸሽ ቢሮውን ከሞሪሽየስ ወደ ባሃማስ ቀየረ። ሁለቱ አገሮች በጣም አነስተኛ ግብር የሚያስከፍሉ በመሆናቸው የፋይናንስ ባለሙያዎች Tax haven ወይም በግርድፍ ትርጉሙ 'የግብር ገነት' ይሏቸዋል። የሔሪቴጅ ኩባንያ እና ኩባንያውን ወክሎ የሚንቀሳቀስ የሒሳብ ባለሙያ የተለዋወጧቿው የኤሌክትሮኒክ መልዕክቶች በዓለም አቀፉ የምርመራ ጋዜጠኞች ጥምረት ይፋ ከተደረጉ በርካታ መረጃዎች መካከል ይገኙበታል።

በመልዕክት ልውውጦቹ መሠረት የኩባንያው አመራሮች ከተወካዮቻቸው ጋር ሸርበው ለዩጋንዳ መክፈል የነበረባቸውን የገቢ ግብር ለመሸሽ ቢሯቸውን ከሞሪሽየስ ወደ ባሃማስ አዛውረዋል።የሔሪቴጅ ኩባንያን በውክልና የሚያንቀሳቅሰው ደግሞ ሞዛክ-ፎንሴካ የተሰኘ የባሃማስ የጥብቅናና ሐብት አስተዳደር ተቋም ነበር።

በባህማስ የተመዘገበው ኩባንያ ለመንግሥት ባለስልጣናት፣ ለቤተሰቦቻቸው፤ የምሥጢር አጋሮቻቸው ድብቅ ድርጅቶች በመመሥረት ገንዘብ ለማዘዋወር፤ ሕጋዊም ይሁን ሕገ-ወጥ ግብይት ያካሂድላቸዋል።ከደንበኞቹ መካከል ስልጣናቸውን የለቀቁ ፖለቲከኞች፤ የጦርመሳሪያ ነጋዴዎች፤ የአደንዛዥ እጽ አዘዋዋሪዎች ጭምር አሉበት።ስልጣን እና ገንዘብ ያላቸው እጅግ ጥቂቶች የአገሮቻቸውን ሕግጋት ለመጣስ እና ገንዘብ ለማሸሽ ሞዛክ-ፎንሴካ የዓመታት ታማኝ ወኪላቸው ሆኖ ቆይቷል። የመረጃው አይነት፤ ብዛት እና በውስጡ የያዛቸው ግለሰቦች ማንነት እስካሁን በመገናኛ ብዙሃን ይፋ ከተደረጉ የምሥጢር ሰነዶች ሁሉ የተለየ አድርጎታል። ጄራርድ ራይል የዓለም አቀፉ የምርመራ ጋዜጠኞች ጥምረት ፕሬዝዳንት ናቸው።

«ለሁላችንም አስገራሚ የሆነብን ነገር በውጭ አገራት ኩባንያዎች የማንቀሳቀስ አሠራር ስልጣን ላይ ባሉ ሰዎች ምን ያክል እየተጠቀሙበት መሆኑን መገንዘባችን ነው። በሰነዱ ላይ አስራ ሁለት የቀድሞ እና አሁንም በስልጣን ላይ የሚገኙ የአገር መሪዎች፤ በመቶዎች የሚቆጠሩ ፖለቲከኞች አግኝተናል። አንዳንዶቹ በአደባባይ ምሥጢራዊነትን የሚወቅሱ ጭምር ናቸው።»

ከአንድ ዓመት በፊት ከሞዛክ-ፎንሴካ አፈትልከው ለጀርመኑ ዙድ ዶይቸ ሳይቱንግ የደረሱት ከ11.5 ሚሊዮን በላይ ሰነዶች የቭላድሚር ፑቲንን ምሥጢሮች፤ የዩክሬኑ ፕሬዝዳንት ፔትሮ ፔሬሼንኮ እና የሳዑዲ አረቢያው ንጉሥ ድብቅ መረጃዎች አፍረጥርጠውታል። የቻይናው ፕሬዝዳንት በሚስታቸው ወንድም፤ የሶርያው አምባገነን በሺር አል-አሳድ በዘመድ አዝማዶቻቸው፤ የእንግሊዙ ጠቅላይ ሚኒስትር ዴቪድ ካሜሮን በአባታቸው ስም በተከፈቱ ድብቅ ኩባንያዎች ከአገራቸው እና ከህዝባቸው ከፍተኛ መጠን ያለው ገንዘብ ሳያሸሹ እንዳልቀረ የሚጠቁሙ ሰነዶችም ይገኙበታል።

ፖለቲካዊ ኃይል፤ ገንዘብ እና ጥቅሞቻቸውን የሚያስጠብቅ ወዳጅነት ያላቸው ሰዎች ምሥጢራዊ ኩባንያዎች መሥርተው ገንዘባቸውን ከመንግሥት ተቋማት ዕይታ ማራቅ ያስቻሏቸው እንደ ሞዛክ-ፎንሴካ አይነት ድርጅቶች አሠራር እና ስፋት ጥልቀት ከተገመተው በላይ አስከፊ ተብሏል።

የአፍሪቃ መንግሥታት ባለስልጣናትም ስሞቻቸው ከፓናማ ሰነዶች መካከል ይገኙበታል። በዓለም አቀፉ የምርመራ ጋዜጠኞች ጥምረት እና በጀርመኑ ዙድ ዶይቸ ሳይቱንግ ጋዜጣ ለአንድ ዓመት ያክል የተመረመሩት የፓናማ ሰነዶችን ይፋ ሲደረጉ በቀዳሚነት ከተጠቀሱት አፍሪቃውያን መካከል አንዱ የደቡብ አፍሪቃ ፕሬዝዳንት ጃኮብ ዙማ ናቸው። በሰነዶቹ መሠረት ፕሬዝዳንቱ መቀመጫውን በብሪቲሽ ቨርጂን አይላንድ ካደረገው ካፕሪካት የተሰኘ የነዳጅ ዘይት እና ጋዝ ኩባንያ እና ከዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ፕሬዝዳንት ጆሴፍ ካቢላ ጋር ተያይዟል። የጃኮብ ዙማ የወንድም ልጅ ክሊቭ ኹሉቡስ ዙማ በሞዛክ-ፎንሴካ በኩል በተከፈተ ካፕሪካት ሊሚትድ የተሰኘ ኩባንያ በኩል ከዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ የነዳጅ ዘይት የሚገኝበት መሬት ገዝቷል።

ቦትስዋና

ቦትስዋናዊው ጋዜጠኛ አልቪን ንቲቢነያዬ የፓናማን ሰነዶች ከሚመረምሩት መካከል አንዱ ነው። በምርመራው ካገኛቸው ግለሰቦች መካከል የቦትስዋና ይግባኝ ሰሚ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት ኢያን ኪርቢ ይገኙበታል። ፍትህ የማስፈን ኃፊነት የተጣለባቸው ኢያን ኪርቢ በውጭ አገራት በሚገኙ አምስት ድብቅ ኩባንያዎች ውስጥ ባለ ድርሻ መሆናቸውን የፓናማ ሰነዶች አጋልጠዋል። «አሁን ጉዳዩ በአገሪቱ የመነጋገሪያ አጀንዳ ሆኗል» የሚለው ጋዜጠኛ አልቪን፤ ኢያን ኪርቢ ስልጣናቸውን እንዲለቁ የጠየቁ መኖራቸውንም ተናግሯል።

ኢትዮጵያ?

በፓናማ ሰነዶች እስካሁን አንድም የኢትዮጵያዊ ፖለቲከኛ አሊያም ኩባንያ ስም አልተገኘም። ይሁንና በሰነዱ ስማቸው ከሰፈሩ የውጭ አገራት ኩባንያዎች መካከል በኢትዮጵያ በሥራ ላይ የተሠማሩ አሊያም ከኢትዮጵያውያን ጋር ለመገበያየት የሞከሩ አልጠፉም። የእስራኤሉ ሐሬትዝ የተሰኘዉ ጋዜጣ እንደዘገበው በኢትዮጵያ የማዕድን ሥራ ላይ የተሠማራው አይሪስጊያንማን ኩባንያ ይጠቀሳል። ኤንግል ኢንቨስት በተባለ ኩባንያ ሥር በአንጉይላ ደሴት የተመዘገበው ኩባንያ ባለቤቶች ኢርስ ሌቪንስታይን፤ ዋይ የተባሉ ሁለት እስራኤላውያን እና ነዋሪነቱን በአዲስ አበባ አድርጓል የተባለው ቫሎና ጊያንካርሎ የተባለ ጣልያናዊ ይገኙበታል።

አሁንም በምርመራ ላይ በሚገኙት ሰነዶች ስማቸው ከተጠቀሰ አፍሪቃውያን መካከል በገንዘብ ማሸሽ ተከሰው በብሪታኒያ በእስር ላይ የሚገኙት ናይጄሪያዊ ጄምስ ኢቦሪ አንዱ ናቸው። የቀድሞው የዴልታ ግዛት አስተዳዳሪ ጄምስ ኢቦሪ በጎርጎሮሳዊው 2012 ዓ.ም 75 ሚሊዮን ዶላር ከአገራቸው መመዝበራቸውን አምነው ጥፋተኛ ነኝ ይበሉ እንጂ የአገራቸው ፖለቲከኞች ከዛ የበለጠ ሳያሸሹ አልቀሩም ብለው ያምናሉ። ከጄምስ ኢቦሪ በተጨማሪ የአገሪቱ ምክር ቤት ፕሬዝዳንት ቡኮላ ሳራኪ፤ የአሊኮ ዳንጎቴ ወንድም ሳዩ ዳንታታ ይገኙበታል። በአፍሪቃ ቀዳሚ ቱጃር የሆኑት አሊኮ ዳንጎቴ እና ወንድማቸው በሲሸልስ 13 ኩባንያዎችን በተደጋጋሚ እየገዙ መሸጣቸውን ከሞዛክ-ፎንሴካ የወጡት ሰነዶች ይጠቁማሉ። የናይጄሪያ ሲቪል ዴሞክራሲ መብት አራማጆች ዳይሬክተር ሳኒ አልዩ የአገራቸውን ፖለቲከኞች ምሥጢር አሳፋሪ ይሉታል።

Unabhängigkeitstag in Nigeria 2015

የናይጄሪያ ምክር ቤት ፕሬዝዳንት ቡኮላ ሳራኪ እና የአገሪቱ ፕሬዝዳንት ሙሃማዱ ቡሐሪ

«ይህ አስገራሚ እና አሳፋሪ ነው። የምክር ቤቱ ፕሬዝዳንት በእንዲህ አይነት አሳፋሪ ቅሌት ውስጥ መገኘታቸው ማፈሪያ ነው። ጄምሲ ኢቦሪ እስር ቤት ናቸው። እንዳለመታደል ሆኖ ድርጊቱ አሳፋሪ ቢሆንም ይፋ መውጣቱ ምንም አይነት ምሥጢር የትም ሊደበቅ የማይችል መሆኑን በማሳየቱ ጥሩ ነገር ነው። ይህ ለሁሉም ናይጄሪያውያን ፖለቲከኞች ማስጠንቀቂያ ነው። ቡኮላ ሳካሪ በሠሩት ጥፋት ከተከሰሱ ከዚህ በኋላ በምንም አይነት ስልጣን ላይ ሊቀመጡ አይችሉም። ፕሬዝዳንቱ እንኳ ይቅርታ ሊያደርጉላቸው አይችሉም።»

የኬንያ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ምክትል ፕሬዝዳንት ካልፓና ራዋል በብሪቲሽ ቨርጅን አይስላንድ ከተመዘገቡ አስራ አንድ ኩባንያዎች ጋር ስማቸው ተያይዟል። ዳኛዋ የአራት ኩባንያዎች ባለድርሻዎች ዳይሬክተር እንደነበሩም የፓናማ ሰነዶች ጠቁመዋል።

የአንጎላ የነዳጅ ዘይት ሚኒሥቴርን ሁለት ጊዜ በኃላፊነት የመሩት ጆሴ ማሪያ ቦቴልሆ እና የዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ፕሬዝዳንት መንትያ እህት ጃኔት ዲዚሬ ካቢላም ትንሽ ግብርበሚያስከፍሉት አገራት በድብቅ የሚያንቀሳቅሷቸው ኩባንያዎች እንዳሏቸው ሰነዶቹ አጋልጠዋል።

የፓናማዎቹ ሰነዶች ሙስና የአፍሪቃውያን ችግር ብቻ ላለመሆኑ ማረጋገጫ ቢሰጡም እንደ ዶ/ር ሌኒ ካሶጋ ያሉ የአህጉሪቱ የኢኮኖሚ ባለሙያዎች እና የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች ይህ ለአፍሪቃ ውርደት ነው ይላሉ።

«ይህ ለአፍሪቃ ውርደት ነው። የአፍሪቃ መሪዎች አሳፋሪ ተግባርም ነው። አፍሪቃ የምትፈልገው ከግል ጥቅማቸው ይልቅ አገራቸውን የሚያስቀድሙ መሪዎችን ነው። እንዳለመታደል ሆኖ አብዛኞቹ የአፍሪቃ መሪዎች የግል ጥቅማቸውን የሚያስቀድሙ እና ገንዘብ የሚያከማቹ ናቸው። አፍሪቃ ያሏት በራሳቸው አገር ሥራ ላይ መዋል የሚገባውን ገንዘብ ወደ ውጭ አገራት የሚያሸሹ እና በውጭ አገራት ባንኮች የሚያከማቹ መሪዎች ነው።»

የፓናማ ሰነዶች ይፋ ሲሆኑ ከአገራቸው ጋዜጠኞች የቀረቡላቸውን ፈታኝ ጥያቄዎች መቋቋም ያቃታቸው የአይስላንድ ጠቅላይ ሚኒስትር ዴቪድ ጉንላውጉሶን ባለፈው ሳምንት ስልጣናቸውን ለቀዋል። ሩሲያ የፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲንን ሰብዕና ለማጥፋት ምዕራባውያን የጠነሰሱት ሴራ ብላዋለች። የእንግሊዙ ጠቅላይ ሚኒስትር ዴቪድ ካሜሮን ትችት ሲበዛባቸው ግብር የከፈሉባቸውን ደረሰኞች ይፋ አድርገዋል። አፍሪቃ ዉስጥ ከፓናማ ሰነዶች ጋር ስማቸው የተያያዙ ግለሰቦችን እመረምራለሁ ያለችው እስካሁን ደቡብ አፍሪቃ ብቻ ነች። የዓለም አቀፉ የምርመራ ጋዜጠኞች ጥምረት ፕሬዝዳንት ጄራርድ ራይል የሰነዶቹ ይፋ መሆን ለመሠረታዊ የአሠራር ለውጥ መነሾ እንደሚሆን ያምናሉ።

አፍሪቃ ገንዘብ ያሸሹም ሆነ ግብር የደበቁ ፖለቲከኞቿን፤ ነጋዴዎቿን እና የውጭ ኩባንያዎችን የምትዳኝበት ጠንካራ ተቋማት ያሏት አይመስልም። ፖለቲካዊ ስልጣንን እና ሐብትን አጣምረው የያዙት የአፍሪቃ መሪዎች እና ቤተሰቦቻቸው መረጃዎች አሁንም ከፓናማ ዶሴዎች ውስጥ ብቅ ማለታቸው እንደማይቀር ይጠበቃል።

እሸቴ በቀለ

ሸዋዬ ለገሰ

Audios and videos on the topic