አፍሪቃዊ ጥንተ-መሰረት | አፍሪቃ | DW | 05.09.2017
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

አፍሪቃ

አፍሪቃዊ ጥንተ-መሰረት

በኢትዮጵያ ሰምጥ ሸለቆ አፋር «ሐዳር» በተባለ ቦታ የተገኘችዉ «ድንቅነሽ» ወይም «ሉሲ» ቅሪተ-አካል ላለፉት አርባ ዓመታት የሰዉ ልጆችን አመጣጥ ለማወቅ የሚደረገዉን ምርምር በማገዝ ረገድ እስካሁን ወደር አልተገኝለትም። 3.2 ሚሊዮን ዓመት እድሜ ያስቆጠረዉ ይህ ቅሬተ አካል የሰዉ ልጆችን አፍሪቃዊ መሰረት ያጠናክራል ሲሉም ተመራማሪወች ይገልጻሉ።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 04:29

«የሰዉ ልጆች አፍሪቃዊ መሰረት አላቸዉ»ዶክተር ብሉመንሻይን

በጎሮሳዊዉ የዘመን ቀመር 1974 ዓ.ም. በኢትዮጵያ፤  በአቧራማዉ ሰምጥ ሸለቆ  አፋር ምድር ዶናልድ ጆንሰንና ቶም ግሬይ የተባሉ አሜሪካዉያን ሳይንቲስቶች ከሰዉ ልጆች ዝርያ ጋር የሚመሳሰል ቅሬተ አካል ያገኙበት ጊዜ ነበር። አሜሪካዉያኑ ተመራማሪወች በዚያዉ ዕለት ምሽት ላይ ታዲያ ይኽ አዲስ ግኝት የፈጠረባቸዉን ደስታ በድንኳናቸዉ ዉስጥ ሆነዉ አክብረዉት ነ ነበር። በዚህ የፌሽታ ወቅት በሳይንቲስቶቹ ቴፕ ይንቆረቆር የነበረዉ ሙዚቃ በዚያ ዘመን ገነዉ የነበሩት ዘ ቢትልስ  የተባሉ አሜሪካዉያን ሙዚቀኞች ያቀነቀኑት «Lucy in the Sky with Diamonds»የተሰኜዉ  ሙዚቃ ነበር።  እናም « ሉሲ» የዚህች አዲስ ቅሬተ አካል መጠሪያ ሆነ።

ከሁለት ሳምንት ቁፋሮ በኋላ በሞቃታማዉ የኢትዮጵያ ምድር የምርምር ቡድኑ ተጨማሪ በመቶወች የሚቆጠሩና የተበታተኑ ቅሬተ አጽሞችን በቁፋሮ አወጣ። ይህ ሉሲን በዚያ ዘመን ከተገኙት ቅሬተ አካላት የበለጠ የተሟላች አደረጋት። እንደ ታዋቂው ኢትዮጵያዊ ቅሪተ-አካ ተመራማሪ ፕሮፌሰር ፕሮፌሰር ብርሃኔ አስፋዉ ሉሲ በምርምር ዘርፉ ያደረገችዉ አስተዋጽኦ ቀላል አይደለም።

«የሉሲ ቅሬተ አካል  በዉስጡ 40 ከመቶ የሚሆነዉ  የአካል ክፍል ተጠብቆ  የቆየ በመሆኑ፣ ቢያንስ  ስነህይወታዊ  ሁኔታዋን በዚያን ዘመን ከነበሩ  ሌሎች  ቅሬተ አካላት በተሻለ መንገድ ለመረዳት ችለናል። በዚህ የተነሳም  ሉሲ   በሰዉ ልጆች  ዝግመተ ለዉጥ  ሂደት  ላይ ለረጅም ጊዜ ትኩረት ስባ ቆይታለች።» 

ቡድኑ በዚህ ቁፋሮ የሉሲን ሁለት አምስተኛ የሰዉነት ክፍል አግኝቶ የነበረ ቢሆንም  ይህን በማግኜቱ ብቻ ስራዉን አላቆመም።የሰዉ ልጆችን አመጣጥ የበለጠ ለመረዳት ካለዉ ጉጉት የተነሳ  በድንቅነሽ ቅሬተ አካል ላይ ምርምሩን ቀጥለ።  እናም ድንቅነሽ በጎልማሳነት እድሜ  የነበረች ከዘመናዊዉ ሰዉ ጋር በእጅጉ ተቀራራቢና መራመድ ትችል እንደነበረም ጥናቶቹ  ማሳየት ችለዋል። በደቡብ አፍሪቃ  የቅሬተ አካል ተመራማሪ ዋና ሳይንቲስት ዶክተር ሮበርት ብሉመንሻይ እንደሚሉት ከድንቅነሽ  ቅሬተ አካል በመነሳት  ስለሰዉ ልጆች እንቅስቃሴ መናገር እንደተቻለ ያብራራሉ።።


«በቅሬተ አካሏ የተገኙት ቀሪዎቹ የራስ ቅልና ጥርስ ከፊሎች ስለ ሉሲ አመጋገብ እና ስለ አንጎሏ መጠን ለማወቅ ያስቻሉን በጣም አስፈላጊ ነገሮች ናቸው። ቀሪ የአጥንት ክፍሎቿም ሉሲ በሁለት እግሮቿ ትራመድ እንደነበር ወሳኝ መረጃ የሰጡ ናቸው። "

ሉሲ እነደ ሰዉ ልጆች ትራመድ ነበር የሚል ግምት ቢኖርም ከጦጣዎች የምትጋራዉ ገጽታ፣ የእጆቿ መጉበጥና ከእግሮቿ ረዝሞ መገኘት ጊዜዋን ከዛፍ ዛፍ እየተንጠላጠለች ታሳልፍ ነበር የሚል እሳቤ እንዲያዝ አድርጓል።እንደ ተመራማሪወቹ ደፍጣጣ አፍንጫዋ ሰፋ ያለዉ አገጭዋ ሉሲን መሰረታቸዉ አፊሪቃ ከሆኑት ከችንፓዚ ከተባሉ የዝንጀሮ ዝርያወች ጋር ያመሳስላታል።ዶክተር ብሉመንሻይ ሉሲ ከሌሎች ቀደምት የሰዉ ዘር ግኝቶች በበለጠ አፍሪቃ የሰዉ ዘር መሰረት መሆኗን ያሳያል ሲሉ ያብራራሉ።

«የተጠቀሱት ባህሪያት በሙሉ  እኛን በዚህ አህጉር ከተገኙት «ችንፓንዚ» በመባል ከሚታወቁት የዝንጀሮ ዝርያዎች እና በቅርብ ከሚዛመዱን ሌሎች  ህይወት ካላቸዉ  ነገሮች ይለዩናል። በራስ ከመተዳደር ወደ ቴክኖሎጅ ጥገኝነት ፣  ዕዉቀታችን ፣ ምዕናባዊ የአስተሳሰብ  ችሎታችን፣ እንዲሁም ተምሳሌታዊዎቹ ባህሪያት  ከትልቁ  አዕምሮአችን ጋር የተሳሰሩ ናቸዉ ። እነዚህ አፍሪቃዊ ፈጠራዎች በጠቅላላ በዓለም የሚኖረውን ማንኛውንም  ግለሰብ በመሰረቱ አፍሪቃዊ የሚያደርጉ ናቸዉ።» 

የሉሲን እድሜ ያህል ባይሆንም በአፍሪቃ ፤ በሞሮኮና በደቡብ አፍሪቃ ቅሬተ አካላት ተገኝተዋል።በዓለም ላይም  የተለያዩ ቅሬተ አካሎች በምርምር ሲገኙ ቆይቷል ያም ሆኖ ግን አንዳቸዉም የሉሲን ያህል ዕዉቅናና ዝና ያገኙ አልነበሩም። ምክንያቱ ደግሞ ለሰዉ ልጆች ጥንታዊ አመጣጥ ከሉሲ የተሻለ ፍንጭ የሰጠ ባለመኖሩ ነዉ። ። 3 ነጥብ ሁለት ሚሊዮን አመታንን ተሻግሮ የሰዉ ልጆችን አኗኗር፣ተፈጥrሯዊ ሁኔታና አስተሳሰብ  ለማሳየት ከሉሲ የቀደመም አልተገኜም።ከዚህ ሁሉ ዓመታት በሁዋላ ከ40 በመቶ የሚሆነዉ የሰዉነት ክፍሏ  በተሟላ ሁኔታ መገኔቱም  የተለዬ አድርጓታል። ላለፉት 4 አስርተ ዓመታትም በሰዉ ልጆች አመጣጥ ላይ የሚደረገዉን ምርምር እያገዘ ቀጥሏል። ኢትዮጵያ ብሎም አፍሪቃ የሰዉ ዘር መሰረት መሆናቸዉም እንዲሁ። እዉነትም ድንቅነሽ።

ይህ ዘገባ አፍሪካዊ ሥረ-መሠረት በሚል ከጌርዳ ሔንክል ተቋም ጋር በመተባበር የሚቀርብ ልዩ ዝግጅት አንድ አካል ነው።

This report is part of African Roots, a project realized in cooperation with the Gerda Henkel foundation.

ማንተጋፍቶት ስለሺ/ ፀሀይ ጫኔ

አርያም ተክሌ

Audios and videos on the topic