«አፍሪቃዊዉ የሩምባ ንጉስ» ፓፓ ዌምባ | ባህል | DW | 29.04.2016
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ባህል

«አፍሪቃዊዉ የሩምባ ንጉስ» ፓፓ ዌምባ

በዓለም እዉቅናን ያተረፈዉ ኮንጋዊዉ ከያኒ ፓፓ ዌምባ ባለፈዉ ሳምንት መጨረሻ መዲና አቢጃን አይቮሪኮስት የሙዚቃ ድግሱን ሲያሳይ ተዝልፍልፎ ከወደቀ በኋላ ከዚህ ዓለም በሞት መለየቱን በተለይ የሙዚቃ አፍቃሪዉን ዓለም አስደንግጦአል።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 16:25
አሁን በቀጥታ እየተሰራጨ ያለ
16:25 ደቂቃ

ፓፓ ዌምባ


የአፍሪቃ ሙዚቃን በተለይ ከምዕራባዉያኑ የፖፕ፤ ሮክና ራፕ የሙዚቃ ስልት ጋር በመቀላቀል ባቀረባቸዉ የሙዚቃ ሥራዎቹ የሩምባዉ ንጉስ የሚል ዝናንም ተጎናፅፎአል። ፓፓ ዌምባ የአፍሪቃ ኅብረት 50ኛ ዓመት የምስረታ በዓሉን ሲያከብር፤ መዲና አዲስ አበባ ላይ ለሁለት ቀናት ተገኝቶ በሚለኒየም አዳራሽ ሙዚቃዉን አሳይቶአል። በእለቱ ዝግጅታችን የታዋቂዉን አፍሪቃዊ አቀንቃኝ የፓፓ ዌንባን አድናቂዎቹን አስተያየት አካተን የሙዚቃ ሥራ ሕይወቱን እንቃኛለን።


ከያኒ ፓፓ ዌንባ አቢጃን አይቮሪኮስት ለሚገኙ አፍቃሪዎቹ ሙዚቃዉን እያሳየ ጩኸቱ እልታዉ ደምቋል፤ በዓለም ታዋቂዉ ኮንጎዊ ሙዚቀኛ በትዕይንቱ መኃል ድንገት ተዝለፍልፎ ወደቀ፤ በርግጥ ይህ የትርኢቱ አንድ አካል ሊሆን ይችላል ነዉ እንጂ ፓፓ ዌምባ ታሞ ተዝለፍልፎ ወደቀ ብሎ ያሰበ አልነበረም እዉቁ አፍሪቃዊ ሙዚቀኛ ግን ከወደቀበት ቀና አላለም። በርግጥ ሙዚቃ ድግሱ አካባቢ የቁሞ የቀይ መስቀል ድርጅት የድንገተኛ ጊዜ ደራሾች ከያኒዉን ሕይወት ለማትረፍ ከፍተኛ ፍጥነት ቦታዉ ላይ ተገኝተዉ ተደጋጋሚ ጥረት ቢያደርጉም የፓፓ ዌምባን ሕይወት ማዳን ግን አልቻሉም። የከያኒዉ ቃል-አቀባይ «ኦካፒ ለተሰኘ» ለአንድ የኮንጎ ራድዮ ጣብያ በሰጡት መግለጫ ይህንኑ ነዉ ያረጋገጡት። እንደ ቃል አቀባዩ፤ ዌምባ

Demokratische Republik Kongo Stadt Kinshasa Fluss Congo

ዴሞክራቲክ ኮንጎ ኪንሻሳ

ከሙዚቃ ድግሱ በፊት እጅግም ጤና እንዳማይሰማዉ ተናግሮ እንደነበርም ተናግረዋል። በአፍሪቃዉያን ሙዚቃ ቀዳሚና የታዋቂነትን ቦታ የያዘዉ የፓፓ ዌምባ አድናቄዎችና ወዳጆች በከያኒዉ ድንገተኛ ሞት እጅግ ተደናግጠዋል። ከአፍሪቃ ሙዚቃዎች እንደ ቀድሞዋ ዛየር ማለትም እንደ አሁንዋ ዴሞክራቲክ ሬፐብሊክ ኮንጎ ያህል በዓለም አቀፍ ደረጃ ከፍተኛ ዝናንና ተወዳጅነትን ያገኘ ሙዚቃና ሙዚቀኛ የለም ማለት ይቻላል። አፍሪቃዊ ኮከብ ሙዚቀኛ፤ ፓፓ ዌምባ በሙዚቃዉ ብቻ ሳይሆን ለየት የሚያደርጋቸዉ አልባሳቱም በአፍሪቃዉያኑ ዘንድ ዝናንና የልብስ ፋሽንን አሳይ እንዲሆን ተደርጎ እንዲታይም አድርጎታል።

ፓፓ ዌምባ በሚል የመድረክ ስሙ የሚታወቀዉ የሩምባዉ ንጉስ በጎርጎረሳዊዉ 1949 ዓ,ምወደዚህ ዓለም ሲመጣ የተሰጠዉ ስም ሹንጉ ዌምባዲዮ ፔኔ ኪኪምባ የሚል ነዉ። በጎርጎረሳዊ 1960 ዓ,ም የቀድሞዋ ዛየር ከቤልጂግ ቅኝ ግዛት ሥር ነፃ ስትሆን ፓፓ ዌምባ የዝያን ጊዜዉን ታዋቂ የኮንጎ ሩምባ ሙዚቃ ንጉስ ጆሴፍ ካባሴላስ ፈለግን ይዞ አደገ። ዌምባ የዝያን ጊዜዉን የዛየር ሩምባ ንጉሥ ፈለግ በተጨማሪ ሙዚቀኛዉ ኪንሻሳ ዉስጥ በተማሩበት ትምህርት ቤትም ነበር ትምህርቱን የተከታተለዉ።


በጎርጎረሳዉያኑ 1969 ዓ,ም ዛኮ ላንጋ ላንጋ በሚል ፓፓ ዌምባ የሚመራዉና ሌሎች ወጣቶች የተካተቱበት የሙዚቃ ቡድን ካቋቋሙ በኋላ ዌምባ የሙዚቃዉን መድረክ እየተዋወቀ ታዋቂነቱም እየገነነ ሄደ። ቡድኑ በሚጫወተዉ አዲስ በፈጠረዉ የኮንጎ የሩምባ ሙዚቃ ቅላጼ ማለት ከምዕራባዉያኑ ፖፕ ሮክና ራፕ ስልቶች በመቀየጥ በሚያቀርበዉ ሙዚቃ በተለይ በኪንሻሳ ከተማ በፍጥነት በርካታ አፍቃሪዎችን ማፍራት አስችሎታል። ቡድኑ ያቀርባቸዉ የነበረዉ ሙዚቃ ከአሜሪካዉያኑ የሶል ሙዚቃ ቅላጼ ጋራ የተቀላቀለ እንደነበርም ዘገባዎች ያሳያሉ። ፓፓ ዌምባ ከዶይቼ ቬለ ጋር ባደረገዉ ቃለ ምልልስ « እንደሚባለዉ ሙዚቃ ድንበር አያግደዉም » ይላል
« ከኮንጎ ሙዚቀኞች የተለየሁ ሆኜ ይሰማኛል። ሙዚቃ ምንም ዓይነት ድንበር አይገታዉም ። በርካታ የተለያዩ ሙዚቃዎችን አዳምጣለሁ።»


ፓፓ ዌምባ በጎርጎረሳዉያኑ 1970ና 1980 ዓ,ም በኮንጎ ለየት ያለ ቅላጼ ያለዉን ሙዚቃ በመጫወት ኮከብ ሙዚቀኛ ሆነ፤ አፍሪቃ ሁሉ የሱን ሙዚቃ ወደደ ደነሰበትም። በሌላዉም ዓለም ሙዚቃዉ የአፍሪቃ ሙዚቃ ተብሎ ጥቅል ስምን ለመያዝ በቃ ተወደደም ።
የኮንጎዉ ሙዚቀኛ ፓፓ ዌምባ ሲዘፍን በተለይ በአፍንጫዉ ቀጠን አድርጎ በሚያወጣት ቅላጼዉ ይታወቃል። » ዌምባ ለብቻዉ መድረክ ላይ ለመቅረብ ፣ «ዛይኮ ላንጋ ላንጋ የተሰኘዉን ከሌሎች ወጣቶች ጋር የሙዚቃ ቡድን ከአራት ዓመታት የጋራ መድረክ በኃላ በጎርጎረሳዉያኑ 1977 ዓ,ም ለቆ ወጣ።


በኢትዮጵያ የሙዚቃ አስተማሪ ቀማሪና ታዋቂ ጊታር ተጫዋች የሆነዉ ግሩም መዝሙር ፓፓ ዌምባ የአፍሪቃ ሙዚቃ በዓለም መድረክ እንዲተዋወቅ ትልቅ ሚናን የተጫወተ ሲል ይገልፀዋል።

Demokratische Republik Kongo Papa Wemba ist gestorben

«አፍሪቃዊዉ የሩምባ ንጉስ» ፓፓ ዌምባ


ፓፓ ዌምባ በአለባበሱም ቢሆን ከሌሎች የተለየ ከያኒ ነበር። ዌምባ ብቻ ሳይሆን አባቱም ፋሽን ተከታይ እንደነበሩ ዌምባ ተናግሮ ነበር።
«አባቴ ልብሱን በትዕዛዝ ያሰፋ የነበረዉ በብረስልስ እንደነበር አስታዉሳለሁ። በ1977 ለመጀመርያ ጊዜ ቤልጂግ በሄድኩበት ጊዜ ፤ አንድ ትልቅ ዘመናዊ የልብስ መስፊያና ና መሸጫ አኘሁ። ታድያ ያገኘሁት የአዉሮጳዉያን ዘመናዊ ልብስን ሳይሆን የጃፓን ዘመናዊ ልብስ ነበር»


ዌምባ ከብረስልስ ወደ ዛየር ከተመለስ በኋላ ከቤልጂግ የገዛቸውን የጃፓን ዘመናዊ ልብሶች አድርጎ በቴሌቭዥን ይቀርብ እንደነበር አለባበሱን በቴሌቭዥን የሚያዩ ወጣቶችም ያብድለት እንደነበር በወቅቱ ተናግሯል። በኮንጎ የኮኮቡን ሙዚቀኛ አለባበስ ያየ ልብስ ሰፊ ሁሉ እንደ ዌምባ አይነት ልብስን እየሰፋ ገበያዉያን ያሞቀዉ ነበር፤ ወጣቱም ቢሆን የኮከቡን ሙዚቀኛ ዌምባን አለባበስ ተከታይ ነዉ እንደ ዌንባ

Papa Wemba

«አፍሪቃዊዉ የሩምባ ንጉስ» ፓፓ ዌምባ


« ዘመናዊ ያልኩዋቸዉን አልባሳት ማድረግ ያስደስተኛል። ሁሉም ሰዉ የሚያደርገዉ ዓይነት ልብስ አይደለም ያለኝ። እንደ አንድ ሙዚቀኛ ለየት ያለ ነገርን ለብሼ በዝያ የመታወቅ መብት አለኝ። ግን የልብስ ሞድ አድርጎ የማሳየት ሰለባ አይደለሁም።»


ለታዋቂዉ ከያኒ ለዌምባ በዝያን ጊዜዋ ዛየር በተለይ በጎርጎረሳዊዉ 1980ዎቹ ዓመታት የአኗኗርና ሥራ ሁኔታዉ እጅግ ከባድ እየሆነ መጣ ። እንደሌሎች ከያንያን ሁሉ ፓፓ ዌምባ የሙዚቃ መድረኩን ወደ ፓሪስ እያዞረ መጣ ።
እነዚህ ዓመታት ደግሞ አፍሪቃዊ ከያንያን በዓለም የሙዚቃ መድረክ በርካታ እድምተኞችንና አፍቃሪዎችን እያገኙ የመጡበትም ወቅት ነበር። በዚሁ ወቅት ፓፓ ዌምባ ከታዋቂዉ እንጊሊዛዊ ሙዚቀኛ ከፒተር ጋብርኤል ጋር በመሆን ዓለም አቀፉን የሙዚቃ መድረክ ተቆናጠጠ።
« አንድ ከያኒ የአፍሪቃ ሙዚቃን ብቻ የሚሰራ ከሆነ ዉስን እደምተኛ ብቻ ነዉ ሊኖረዉ የሚችለዉ። የዓለም አቀፉን መድረክ ለመቆናጠጥና ለመቆጣጠር ከያኒዉ የሙዚቃ ትዕይንት ዓለም ሕግጋትን ሊያዉቅ ይገባል»
ሲል ዌምባ ከዚህ ቀደም ለዶይቼ ቬለ በሰጠዉ ቃለ ምልልስ ተናግሮ ነበር። ከዚህ ሌላ የኮንጎዉ ሙዚቀኛ ፓፓ ዌምባ ከዚህ ቀደም ከዶቼ ቬለ ጋር ባደረገዉ ቃለ-ምልልስ አንድ የኮንጎ ሙዚቃ ርዝመቱ ቢያንስ 7 ደቂቃ ነዉ፤ የሌላዉ ዓለም ግን ከዚህ በጣም ያጥራል ብሎም ነበር ። የማቀነቅነውም ሙዚቃ ብቻ ነዉ ብሎም ነበር ።


« የማቀነቅነዉ የኮንጎ ሙዚቃን አይደለም የአፍሪቃ ሙዚቃም አይባልም። ብቻ የማቀነቅነዉ ሙዚቃ ነዉ በቃ ይህ ነዉ። እኔ አፍሪቃዊ አልያም የዛየር ሙዚቀኛ ነኝ ብዬ አላስብም። እኔ አንድ ሙዚቀኛ ብቻ ነኝ ። የሙዚቃዉ ፍጥነት ዝማሪ ግን የዛየር ባህል ሆኖ ይዘልቃል፤ የሙዚቃዉ ቅላፄ ዋና መሰረት ግን ለየት ያለ ነዉ።»
የዌንባ አፍሪቃዊ አድናቂ በከያኒዉ ከዚህ ዓለም መለየትን ተከትሎ በሰጡት አስተያየት
«ፓፓ ዌንባ ለኛ አባታችን ነዉ። ሞቱ እጅግ አሳምሞናል። በጣም እናፍቀዋለን ፤ እናጣዋለንም። በጣም ያማል »
የአፍሪቃ ኅብረት በጎርጎረሳዉያኑ 2013 ዓ,ም የተመሰረተብትን 50ኛ ዓመት ባከበረበት ወቅት ፓፓ ዌምባ አዲስ አበባ በሚለኒየም አዳራሽ ተገኝቶ አዚሟል። ሙዚቀኛ ሙኒት መስፍን በአፍሪቃ አዳርሽ ከፓፓ ዌምባ ጋር በሕብረት ዝማሪ ተሳትፋለች
በዌንባ ሞት ያዘነ አንድ ሌላ የዌንባ አፍሪቃዊ አድናቂ
«ፓፓ ዊንባ ከዚህ ዓለም በሞት መለየቱን ሰምተን በጣም አዝነናል። ፓፓ ዌንባ በመጀመርያ የ 40 ዓመታት የሙዚቃ ቆንጮ ነበር። በሌላ በኩል ደግሞ ፓፓ ዌንባ ማለት ዘናጩ ማለት ነዉ። እኔን ኳ የለበስኩትን ታያላችሁ እንደ ፓፓ ዌንባ ነዉ። »

ፓፓ ዌምባ በአዲስ አበባ የአፍሪቃ ኅብረት በዓል ላይ በተገኘ በዓመቱ የኮንጎን የሩምባ ሙዚቃ ዳግም ያደሰበትን "Maître d'école", የተሰኘዉን መጨረሻዉን የሙዚቃ ዓልበሙን ማዉጣቱም ይታወሳል። የኮንጎ ሙዚቀና ፓፓ ዌምባ የተካነዉ በጥሩ ልዩ በሆነ የሙዚቃ አጨዋወቱ ብቻ አልነበረም። ዌምባ ጥሩ ራድዮን መርጦ መባድመጥ የታወቀም ነዉ።
«እኔ የጥሩ ሙዚቃ ደጋፊና ዶቼ ቬሌን አድማጭ ነኝ »

Demokratische Republik Kongo Papa Wemba ist gestorben

«አፍሪቃዊዉ የሩምባ ንጉስ» ፓፓ ዌምባ


በዓለም አቀፍ ደረጃ ታዋቂነትን ያተረፈዉ ፓፓ ዌምባ በድንገት ከዚህ ዓለም በሞት የተለየው
ሚያዝያ 16 , 2008 ዓ.ም ነበር ።


«የሩብምባዉ ንጉስ » በመባል የሚታወቀዉ የኮንጎ ተወላጁ ኮከብ ሙዚቀኛ የፓፓ ዌምባ አስክሬን ባለፈዉ ሳምንት መጨረሻ እሁድ የሙዚቃ ድግሱን ሲያሳይ ተዝልፍልፎ ከወደቀበት ከአቢጃን አይቮሪኮስት ወደ ትዉልድ ሃገሩ ኮንጎ ኪንሻሳ ዛሬ ተመልሶአል። ትናንት ለዛሬ አጥብያ ለሊቱን ሙሉ አቢጃን አይቮሪኮስት ላይ ከያኒዉን የሚዘክር ከፍተኛ የሙዚቃ ማስተወሻ ዝግጅትም ተካሂዶአል። የ66 ስድስት ዓመቱ ከያኒ አስክሬን ዛሬ ዴሞክራቲክ ኮንጎ ኪንሻሳ አዉሮፕላን ጣብያ ሲደርስ የሃገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር አዉጉስቲን ማታ ማታ ፖንዮና የሃገሪቱ ምክር ቤት አፈጉባዔ አዉቢን ሚናኩ መገኘታቸዉ ተገልፆአል። በዚሁ አቀባበል ሥነ-ስርዓት ላይ የከያኒዉ ቤተሰቦች የሃገሪቱ ታዋቂ የኪነ-ጥበብ ሰዎችንና በርካታ አድናቂዎቹ አዉሮፕላን ጣብያ ተገኝተዉ ነበር። ለ40 ዓመታት በኮከብ ሙዚቃ ተጫዋችነቱ የሚታወቀዉ የኮንጎ ተወላጅ ፓፓ ዌንባ ሙዚቃዎቹ በዓለም አቀፍ ደረጃ «የአፍሪቃ ሙዚቃ» የሚል መጠርያን ያስገኙ መሆናቸዉም ይታወቃል። የፊታችን ሰኞች የስድስት ልጆች አባቱ ከያኒ ለፓፓ ዌምባ በትዉልድ ሃገሩ የኃዘን ሥነ-ስርዓት ከተካሄደ በኃላ፤ ሥርዓተ ቀብሩ በሚቀጥለዉ ቀን ማክሰኞ ከኪንሻሳ ወጣ ብሎ በሚገኝ ቦታ እንደሚፈፀም ተዘግቦአል።

አዜብ ታደሰ


ኂሩት መለሰ

Audios and videos on the topic