አፍሪቃን የሚያሰጋ አዲስ የውጭ እዳ ቀውስ | አፍሪቃ | DW | 17.03.2018
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

አፍሪቃ

አፍሪቃን የሚያሰጋ አዲስ የውጭ እዳ ቀውስ

በአውሮጳ በወቅቱ የብድር ወለድ ዝቅተኛ መሆኑ አፍሪቃን ለግል ባለሀብቶች አማላይ አድርጓታል። ወለድ ዝቅ ማለቱ ግን በአፍሪቃ ብድር ከፍ የሚልበትን ቀውስ ስጋት ይዞ እንደሚመጣ ለጎርጎሪዮሳዊው 2018 ዓም የወጣ የውጭ እዳን የተመለከተ አንድ ዘገባ አስጠንቅቋል።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 08:01

«በአፍሪቃ አዲስ የዕዳ ቀውስ እንደገና እየተከሰተ ነው።»

ሞዛምቢክ እስከ ሁለት ዓመት በፊት ድረስ በአፍሪቃ በአርአያነት የምትታይ ሀገር ነበረች። ይሁንና፣ ይኸው ሞዛምቢክ በተምሳሌነት ትታይበት የነበረችበት ሁኔታ የውጭ ሀገራት ባንኮች ለከፊል የመንግሥት ተቋማት ለባህር ጠረፍ ጥበቃ የሚውሉ ጀልባዎችን እና የአሳ ማስገሪያ መርከቦችን መግዣ የሚሆን ብዙ ቢልዮን ዶላር ብድር የሰጡበት ቅሌት ይፋ በሆነበት ጊዜ አክትሞለታል።  የሞዛምቢክ መንግሥት ዋስ ሆኖ የተሰጠው ብድር ግን የት እንደገባ ሳይታወቅ ጠፍቷል። ሞዛምቢክም ይህን እዳ መክፈል አልቻለችም፣ የሀገሪቱ ሸርፍ ወድቋል፣ የምግብ ዋጋም እጅግ ተወዷል።  

ይህ በሞዛምቢክ የተከሰተው ሁኔታ በጣም የተጋነነ ቢሆንም፣ በአህጉሩ እውን እየሆነ ያለውን አዲስ ብድር የመውሰድ አዝማሚያ አመላካች መሆኑን ድሆች ሀገራት የተሸከሙት የውጭ እዳ እንዲሰረዝ የሚሟገት ከሲቭል ማህበረሰብ፣ አብያተ ክርስትያን እና ከፖለቲካው ዘርፍ የተውጣጡ 600 የጀርመን ድርጅቶች የሚጠቃለሉበት ኤርላስያር ዴኤ የተባለው የድረ ገፅ ጥምረት አስተባባሪ ዩርገን ካይዘር ተናግረዋል።


« አዲስ የዕዳ ቀውስ እንደገና እየተከሰተ መምጣቱን ካለፉት ጥቂት ዓመታት ጀምረን በመመልከት ላይ ነን። ይህ፣  በተለያዩ የዕዳ ክምር ማሳያ ሰንጠረዞች ላይ ተጠቁሟል። ጥቆማው የእያንዳንዷን ሀገር የዕዳ መጠን እና የኤኮኖሚ እንቅስቃሴን፣ ማለትም፣ ወደውጭ በንግድ ከምትልከው ምርት የምታገኘውን ገቢ ወይም ጠቅላላ ብሔራዊ ገቢዋን ያገናዘበ ነው። »  

ጥምረቱ ያወጣው «የ2018 ዓም የውጭ እዳ ዘገባ» ጉዳዩ አሳሳቢ መሆኑን ያስጠነቅቃል። ዘገባው ከተመለከታቸው 141 ሀገራት መካከል 119 እጅግ ከፍተኛ የውጭ እዳ የተሸከሙ ናቸው። እነዚህ ሀገራት የተሸከሙት የውጭ እዳ የፊናንሱ ቀውስ ከተከሰተ ከጎርጎሪዮሳዊው 2008 ዓም ወዲህ በእጥፍ ያህል ጨምሮ ወደ ሰባት ቢልዮን ዶላር ደርሷል። ከ119 ሀገራት መካከልም የ87 ሁኔታ በወቅቱ ተበላሽቷል። በዘገባው መሰረት፣ የውጭ እዳን በተመለከተ በተለይ አስር የአፍሪቃ ሀገራት እጅግ ብዙ ብድር ያለባቸው ሲሆን ሁኔታቸው እጅግ አሳሳቢ ከመሆኑ ባሻገር፣ ይበልጡን እየተበላሸ የመሄድ አዝማሚያ ይታይባቸዋል። በአስሩ ሀገራት ውስጥ ቀውስ የሚታይባቸው ብቻ ሳይሆኑ ፣ ካሁን ቀደም በተምሳሌትነት ይጠቀሱ የነበሩ ጋናን ወይም በነዳጅ ዘይት ሀብት የታደሉ አንጎላን የመሳሰሉ ሀገራት ይገኙባቸዋል።  ሰባት ሀገራት፣ ሶማልያ እና ዚምባብዌ ጭምር እዳቸውን በከፊል ይከፍላሉ ወይም ከናካቴው አይከፍሉም። ለዚህም የኤርላስያር ዴኤ ጥምረት አስተባባሪ ዩርገን ካይዘር በርካታ ነጥቦችን እንደ ምክንያት ጠቅሰዋል። ብዙ አፍሪቃውያት ሀገራት የፊናንስ ይዞታቸውን እስካስተካከሉ ድረስ ከዓለም አቀፍ የካፒታል ገበያ ገንዘብ መበደር መቻላቸውም እየታየ ነው።  በኤርላስያር ዴኤ የአፍሪቃ አዋቂ ክሪስቲና ሬባይን እንደሚሉት፣ በብድር የሚገኘው ገንዘብ፣ ለምሳሌ በጣም አስፈላጊ ለሆኑ መንገድ፣ ወደብ ወይም የባቡር ሀዲዶች ስራ ለመሳሰሉ የመሰረተ ልማት ዘርፎች በትክክል እስከዋለ ድረስ አፍሪቃ ውስጥ ኢንቬስት ማድረግ ጥሩ ነው።

Jürgen Kaiser

ዩርገን ካይዘር


« በካፒታል ገበያው ላይ ትርፍ የሚያስገኝ አጋጣሚን በመጠባበቅ ላይ የሚገኝ ብዙ ወረት አለ። ባለሀብቶች፣ ይህን ትርፍ የሚያስገኝ አጋጣሚ የሚያገኙት በምዕራቡ ዓለም አይደለም፤ በጥሬ አላባ በበለፀጉ፣ ጥሩ ገቢ የማስገኘት ተስፋ ባላቸው አፍሪቃውያት ሀገራት ውስጥ ነው።»

ጉዳዩ ግን ይበልጥ አሳሳቢ የሚሆነው ከውጭ በተፈጠሩ ምክንያቶች እዳቸውን መክፈል በማይችሉበት ጊዜ ነው። ይህ ለምሳሌ በተፈጥሮ ሀብት የታደሉ ሀገራትን ይመለከታል፣ እንደ ክሪስቲና ሬባይን አስተሳሰብ። እነዚህ ሀገራት በዓለም ገበያ ላይ ለሚታየው የዋጋ መለዋወጥ ተጋላጭ ናቸው። የተፈጥሮ መቅሰፍት ወይም የአየር ንብረት ለውጥ መዘዝም ሀገራቱን ክስረት ውስጥ ሊጥላቸው ይችላል። ሙስናም የራሱ የሆነ ሚና ይጫወታል።

የኤርላስያር ዴኤ አስተባባሪ ዩርገን ካይዘር ቡድናቸው በተለይ በጀርመን የቡድን 20 ፕሬዚደንትነት ዘመን የተነቃቃውን ኮምፓክት ዊዝ አፍሪካ የተባለውን የልማት እቅድ በጥርጣሬ እንደሚመለከተው ገልጸዋል።እቅዱ የግል ኢንቬስትመንትን እንዲያጠናክር የታሰበ ነው። አንዱ መንገድ ብድር መስጠትም ሊሆን ይችላል። 
ይሁንና፣ በጀርመን የቡድን 20 ፕሬዚደንትነት ዘመን የውጭ እዳ የተሰኘው ጉዳይ አንድም ትኩረት አለማግኘቱ የ2018 የ

ውጭ እዳ ዘገባ አዘጋጆችን እንዳሳዘናቸው ክሪስቲን ሬባይን ተናግረዋል።
« ቡድን 20፣ በተለይም፣  ሀሳቡን ያነቃቃው የጀርመን መንግሥት በዚህ አኳያ፣ ማለትም፣ ባንድ በኩል ሀገራቱ ሀብታቸውን እንዲያንቀሳቅሱ ቢያበረታቱም፣ ይህ የውጭ እዳን ሊያገዝፍ እና ቀውስ ሊያስከትል የሚችልበትን ስጋት ይዞ እንደሚመጣ አለመገንዘባቸው ነው። ይህ ገሀድ ሙሉ ለሙሉ ችላ ተብሏል። በኛ አመለካከት፣ ክርክሩ በትክክል ተካሂዶ ቢሆን ኖሮ አዲስ የእዳ ቀውስ ቢፈጠር ሊዘጋጅ ስለሚገባው ዋስትናም በተመከረ ነበር። »

በአንድ ሀገር ውስጥ ይህ ዓይነት የክስረት ሁኔታ በሚፈጠርበት ጊዜ ይበልጡን የሚጎዱት ድሆቹ ዜጎች ናቸው። ምክንያቱም የነዚህ ሀገራት መንግሥታት የውጭ እዳቸውን መክፈል ይችሉ ዘንድ ሰፊው ሕዝብ ተጠቃሚ ለሆነባቸው የትምህርት ወይም የጤና ጥበቃ ዘርፍ የሚመድቡትን ወጪ በጉልህ መቀነስ ይገደዳሉ። ይህ እንዳይሆን ታድያ ድሆቹ ሀገራት ክስረት ሲያጋጥማቸው ይህን ሁኔታ ሊያስተካክሉ የሚቻሉበት አሰራር እንዲዘጋጅ እና ተግባራዊ እንዲሆን ካይዘር እና ባልደረቦቻቸው ያወጡት ዘገባ ጠይቋል። 

« ከሰማንያኛዎቹ ዓመታት ወዲህ ፣  በዓለም አቀፉ የገንዘብ መርህ እና በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ውስጥ አንድ መንግሥት ክስረት ቢደርስበት ሁነኛ የእዳ አከፋፈል ዘዴ ሊዘጋጅ ይገባል የሚል ክርክር ይሰማል። ልክ በኛ የሕግ አውታር ውስጥ እንደሚደረገው፣ አበዳሪዎች ሊከፋፈል ከሚችለው የተበዳሪ ንብረት መካከል የተወሰነ የሚያገኙበትን እና እዳ ተሸካሚውንም ከእዳ ተሸካሚነት የሚያላቀቅበትን ሁኔታ ሊያመቻች ይገባል። »

ዳንየል ፔልስ/አርያም ተክሌ

ማንተጋፍቶት ስለሺ
 

Audios and videos on the topic

ተዛማጅ ዘገባዎች