አፍሪቃና ጥሬ ሃብቷ | ኤኮኖሚ | DW | 05.12.2012
 1. Inhalt
 2. Navigation
 3. Weitere Inhalte
 4. Metanavigation
 5. Suche
 6. Choose from 30 Languages

ኤኮኖሚ

አፍሪቃና ጥሬ ሃብቷ

አፍሪቃ በጥሬ ሃብት በጣሙን የታደለች መሆኗ የሚታወቅ ሲሆን የብዙዎች የክፍለ-ዓለሚቱ ሃገራት ልማት መሠረትም በተለይ ከዚሁ የውጭ ንግድ የሚገኘው ገቢ ነው።

አፍሪቃ በጥሬ ሃብት በጣሙን የታደለች መሆኗ የሚታወቅ ሲሆን የብዙዎች የክፍለ-ዓለሚቱ ሃገራት ልማት መሠረትም በተለይ ከዚሁ የውጭ ንግድ የሚገኘው ገቢ ነው። የአፍሪቃ የተፋጠነ የኤኮኖሚ ዕድገት የሚራመደው መዳብን፣ ኒኬልን ወርቅን፣ አልማዝን ወይም ነዳጅ ዘይትንና ጋዝን በመሳሰሉት ምርቶች ሲሆን በነዳጅ ዘይት ሃብት በታደለችው በአንጎላ ለምሳሌ ዓመታዊው የኤኮኖሚ ዕድገት ከ 20 በመቶ በልጦ የታየበት ጊዜ አለ።

ሌሎች ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ማዕድን ሃብት ማውጣት የጀመሩ ሃገራትም ጠቃሚ ዕርምጃ በማድረግ ላይ ናቸው። ለምሳሌ ያህል ሞዛምቢክ በዓለም ላይ ታላቋ የማዕድን ከሰልና የጋዝ ሃብት አምራች ለመሆን በሚያበቃ በጥሩ ጎዳና እያመራቸ ነው የምትገኘው። በአጠቃላይ የዓለም ኤኮኖሚ በተፈጥሮ ጸጋ እጥረት ተወጥሮ በሚገኝበት በዛሬው ጊዜ አፍሪቃ በአንጻሩ እያበበች ነው።

እርግጥ በሌላ በኩል የጥሬው ሃብት ምርት ማበብ በአፍሪቃውያኑ ሃገራት የኤኮኖሚ ስርዓታት ላይ ተጽዕኖ ማስከተሉም አልቀረም። በጥሬ ሃብት የታደሉት ሃገራት በዓለም ገበዮች፣ በዋጋና በፍላጎት ውዥቀት ላይ ጥገኞች ናቸው። ከዚሁ ሌላ የተፈጥሮ አካባቢ ጉዳት፣ ሙስናና በጥሬ ሃብቱ ክፍፍል ረገድ የሚፈጠሩ ውዝግቦችም የራሳቸው ድርሻ አላቸው። እንግዲህ ይህ ሁሉ አዲሱን ጸጋ አጅቦ በመጓዝ ላይ የሚገኘው መዘዝ ነው።

ታዲያ የጥሬው ሃብት ጸጋ ለአፍሪቃ መቅሰፍት ወይስ ቡራኬ? ለመሆኑ መንግሥታቱና ሕዝቡ ከዚህ ሃብት ምን ያተረፉት ነገር አለ? ሃብቱን ለዘለቄታው ጠቃሚ አድርጎ መጠቀም የሚቻለውስ እንዴት ነው? ጠበብት እነዚህንና ከነዚሁ የተሳሰሩ በርካታ ጥያቄዎችን በተለይ ባለፉት ጥቂት ዓመታት በተደጋጋሚ ሲያነሱ ቆይተዋል።

መዳብን፣ ክሮም፣ ኮባልትና ቲታንን የመሳሰሉ ሚነራሎች ወይም የማዕድን ሃብቶች ዛሬ በዓለም ገበዮች ትልቅ ገቢ የሚያስገኙ ውድ ምርቶች ናቸው። እንዚህ እጅግ ተፈላጊ የሆኑ ጸጎች ተከማችተው የሚገኙት ደግሞ በታዳጊ ሃገራት፤ በተለይም በአፍሪቃ ክፍለ-ዓለም ነው። ይሁንና እነዚህን ከማዕድን በማውጣት የሚገኘው ገንዘብ አብዛኛውን ጊዜ በሙስና በተዘፈቁ መንግሥታት ዕጅ በመግባት የጦርነት ማራመጃ እስከመሆን መድረሱ አልቀረም። ንግዱን ግልጽ ለማድረግና ለማቀናጀት እስካሁን የተደረገው ሙከራም ያስገኘው ፍሬ በጣሙን ትንሽ ነው።

በዚያ ላይ ማዕድኑን ለማውጣት በጥቂት የላብ ዋጋ ደፋ ቀና የሚሉት ሠራተኞች መከራ በቀላሉ የሚገመት አይደለም። በጉድጓዶች ውስጥ ቆሻሻ ለብሰው፣ በገደል ላይ ተነጥልጥለው፣ በባዶ ዕጅና በደነዙ መጥረቢያ መሰል መሣሪያዎች ሲቆፍሩ፤ ሲፍቁ ይውላሉ። ለምሳሌ በኮንጎ ምሥራቃዊ ክፍል ወርቅ፣ መዳብ፣ አልማዝና ኮልታን ከከርሰ-ምድር የሚያወጡት የማዕድን ሠራተኞች የሚዳክሩት ጤንነታቸውና ደህንነታቸው፤ የአካባቢያቸው ተፈጥሮም ጨርሶ በማይጠበቅበት ሁኔታ ነው።

ስለዚህም ምዕራባውያን ተጠቃሚዎች የሃብቱ አያያዝ ወይም አስተዳደር ሁኔታና ግልጽነት እንዲሰፍን ነው የሚያሳስቡት። በዛሬው ጊዜ በተፈጥሮው ጸጋ የሚጠቀሙት ከማዕድኑ የሚያወጡት ሣይሆን ሌሎች ሆነው ይገኛሉ። የጀርመን የከርሰ-ምድር ሣይንስና የጥሬ ሃብት ጉዳይ ፌደራል ተቋም ፕሬዚደንት ሃንስ-ዮአሂም-ኩምፕል እንደሚያስረዱት የማዕድን ማውጣቱን ተግባር በዚያ የሚቆጣጠሩት ዓማጺያን ናቸው።

«ስለ ሚነራሎች ውዝግብ ስናወራ የዴሞክራቲክ ሬፑብሊክ ኮንጎን ሁኔታ ማንሳታችን ነው። እዚያ ከማዕድን በሚገኘው ገቢ ጦርነት እንዲካሄድና እንዲጠነሰስ ይደረጋል»

የእንዚህ የውዝግብ አካባቢ ሚነራሎች ንግድ በዓለምአቀፍ ደረጃ የተወገዘ ሲሆን ነገር ግን ሻጮቹ በዚህም በዚያም ተቀባይ አያጡም። ለምሳሌ ይህ ኮልታን የተሰኘውን የማዕድን ሃብትም ይመለከታል ። ኮልታን ታንታል የተሰኘ ይዘት ያለው ንጥረ-ነገር ሲሆን በባሕርዩ ከብረት የጠነከረና የበለጠ ዕድሜም ያለው ነው። ከዚሁ ሌላ ሙቀትን የበለጠ ለመቋቋም የሚችልና ለማጠፍ፤ ለማጉበጥም የሚቀል መሆኑ ጠቃሚነቱን ከፍ ያደርገዋል። ታንታል ከብረት ተቀይጦ በተለይም በሞባይል ስልኮች፣ ተንቀሳቃሽ ኮምፒዮተሮች ላፕቶፕ እንዲሁም ለጠፍጣፋ ቴሌቪዥኖች ስራ ጥቅም ላይ ይውላል።

ለነገሩ የኮልታን ሃብት እርግጥ በአውስትራሊያና በብራዚልም ይገኛል። ይሁን እንጂ የአውሮፓ ሕብረት ኮሚሢዮን እንደሚገምተው በዓለምአቀፍ ደረጃ ከማዕድን ከሚወጣው ኮልታን 18 በመቶው የሚመነጨው ከዴሞክራቲክ ሬፑብሊክ ኮንጎ ነው። ይህ ደግሞ የማዕቀብ ጥሪ ሳይበግረው እንዴት በዚህ መጠን መሸጥ እንደቻለ የጀርመንን ብረታ ብረት ነጋዴዎች ማሕበር ስራ አስኪያጅ ራልፍ ሽሚትስን ሳይቀር ማስገረሙ አልቀረም።

«ነጋዴዎቻችን ታንታል ከየት እንደሚያመጡ በምንጠይቃቸው ጊዜ ኮንጎ የሚል ምላሽ የሚሰማው ከስንት አንዴ ነው። እንግዲህ መንገዱ እንዲህ ነው። ብረቱ ከኮንኮ ወደ ቻይና ወይም ወደ ሌላ አገር ተልኮ እንዲከማች ይደረጋል። ከዚያም ታንታል ምርት እንደ ብረት ዓለም ገበያ ላይ ይቀርባል። በዚህ ሁኔታ እንግዲህ ፊንገር-ፕሪንት የተሰኘው ምንጭ መለያ አሻራም አይጠቅምም። ምክንያቱም መለያው የሚረዳው በጥሬ ሃብትነት ደረጃ ብቻ ነው። ይህ ነው ትልቁ ችግር»

ኤሌክትሮኒኩ ፊንገር-ፕሪንት ወይም መለያ አሻራ የጀርመን የከርሰ ምድር ሣይንስና ጥሬ ሃብት ፌደራል ተቋም አዲስ ፈጠራ ሲሆን ገና በወጣትነት ዕድሜ ላይ ያለ መቆጣጠሪያ ዘዴ ነው። የተቋሙ ፕሬዚደንት ሃንስ-ዮአሂም ኩምፕል እንደሚያስረዱት ቁጥጥሩ የተለያዩ ዘዴዎች ሊኖሩት ይችላል።

«ብረቱ የሚመጣው በተጣራ መልክ አይደለም። የአንድ መከማቻ ቦታን ባህርይ የሚጠቁሙ ይዘቶች ይኖሩታል። እናም በመለያው ዘዴ ፊንገር-ፕሪንት አማካይነት የተቀረ ይዘቱን በሚገባ መመርመር ይቻላል። ለዚህ ደግሞ የተለያዩ መንገዶች አሉ። ማለት የንጥረ-ነገር ይዘቱንና ዕድሜውን እንዲህ ብሎ ለመወሰን! ከዚህ በኋላ እያንዳንዱ ማከማቻ ስፍራ የራሱ ባሕርይ ያለው በመሆኑ አሻራውን ግልጽ ማድረግና ማስቀመጥ ይቻላል ማለት ነው»

እርግጥ ይህ ዘዴ የአውሮፓ ኮሚሢዮን የጥሬ ሃብት አቅራቢዎቹን መረብ ለመለየትና ግልጽነትን ለማስፈን ከሚጠቀምባቸው ዘዴዎች አንዱ ነው። ዩ ኤስ አሜሪካ ውስጥ ይሄው ተግባር «ዶድ-ፍራንክ-አክት» በተሰኘ ሕግ አማካይነት ይከናወናል። በደምቡ መሠረት በምንዛሪ ገበዮች ላይ የተመዘገቡ ኩባንያዎች ለምሳሌ ሚነራሉን ከየት እንደሚወስዱ በማያሻማ ሁኔታ በመረጃ ማሰመስከር ግዴታቸው ነው። ነገር ግን በዚህ በጀርመን በኤኮኖሚው ትብብር ፌደራላዊ የሚኒስትር መሥሪያ ቤት የም/ቤት ስራ አስኪያጅ የሆኑት ጉድሩን ኮፕ እንደሚሉት ይህ ብቻውን በቂ የማይሆንበት ጊዜም አለ።

«በወቅቱ ይዞታ ዓለምአቀፍ ደምብን ለማስፈን የብዙሃን ድጋፍ ይገኛል ብዬ አላምንም። ይህም ነው ጉዳዩን የሚያከብደው። እናም እኛም ሆንን የአውሮፓ ሕብረት፤ ምናልባትም አሜሪካና ሌሎች ታላላቅ የበለጸጉ መንግሥታት ቀድመን ልንራመድ እንችላለን። በፈቃደኝነት ጥሩ አርአያ ለመሆን ከፈለግን ማለት ነው»

የጀርመን ኢንዱስትሪ በበኩሉ በዚህ አስተሳሰብ ደስተኛ አይደለም። በዓለምአቀፍ ደረጃ አንድ ወጥ መርህ ከሌለ፣ የተወሰኑ ሃገራት ብቻ ደምቡን ሲያከብሩ ሌሎች የማይከተሉት ከሆነ ይህ በግልጽ የፉክክር እኩልነትን የሚጻረር ነው የሚሆነው። በ BMW አውቶሞቢል ኩባንያ የጥሬ ዕቃ ይዞታ ሃላፊ የሆኑት ክሪስቲያን ካርዱክ በኢንዱስትሪው ላይ ማነቆው ጠበቅ እንዳይል ያስጠነቅቃሉ።

«የዶድ-ፍራንክ-ሕግ የሚጠይቀው ለምርት በሚውለው ጥሬ ሃብት ምንጭ ላይ መረጃ እንዲቀርብ ብቻ አይደለም። ምርቱን ለማውጣት አስፈላጊ የሆኑትን ጭምር ይጠቀልላል። ይህም እንግዲህ ምርቱን የሚያወጡት መኪናዎችና መሣሪያዎች ውስጥ ያለውንም ጥሬ ዕቃ ያቅፋል ማለት ነው። በዛሬው ጊዜ ደግሞ በያንዳንዱ የምርት መኪናና መሣሪያ ውስጥ የውዝግቡ ሚነራል ይዘት በመኖሩ ይህ እንዴት ሊሆን እንደሚችል ለመለየት በዕውነቱ ጥበቡ ይሳነኛል»

በአውቶሞቢሉ ኩባንያ ውስጥ በወቅቱ አጠቃላዩ የምርት ተግባር ዘላቂ ሊሆን በሚገባው ባሕርይ የሚራመድ ነው። በካርዱክ አባባል የጥሬ ዕቃው አቅራቢ የሰብዓዊ መብት ከበሬታንና ማሕበራዊ መስፈርትን የሚጠይቅ የግዢ ቅድመ-ግዴታ የሚከተል ሆኖ መገኘት ይኖርበታል። ሁኔታውን ለመከታተል የሚያስችሉ የቁጥጥር ዘዴዎችን ማስፈኑም እንዲሁ በዕቅዱ የተጠቃለለ ጉዳይ ነው። ለአውቶሞቢሉ ኩባንያ BMW ይሄው የዝናው ዕድገት መለኪያ ሆኖ ነው የሚታየው።

ይህ አስተሳሰብ የኤኮኖሚው ትብብር ተቋም ባለሥልጣን ጉድሩን ኮፕም የሚደግፉት ሲሆን በርሳቸው አመለካከት ምናልባትም ሊሳካ ከማይችል ቁጥጥር ይልቅ ዕርምጃን የሚያስከትል ማስታወቂያ የሚበጅ ነው። ኮፕ በዚሁ ጥረት ጥሬ ሃብት አቅራቢ ሃገራትንም ለማሳተፍ የሚፈልጉ ሲሆን በልማት ፖሊሲ ረገድ ሁኔታዎችን የማሻሻል እያደገ የሚሄድ ዝግጁነት ከአሁኑ መኖሩን ነው የሚናገሩት።

«በራስ ግዴታ ውስጥ ለመግባቱ ሃላፊነት ነው ይበልጡን ክብደት የምሰጠው። ደምቡን የሚጥሱ በሚገባ ተለይተው መውጣት ይኖርባቸዋል። በዚህም በስፍራው የሚገኙ መንግሥታት በአገራቸው የሚሆነውን በተሻለ ሁኔታ ስለሚያውቁና ማወቅም ስላለባቸው ማገዝ የሚጠበቅባቸው ነገር ነው። የማዕድኖቻቸውን ሁኔታ ያውቃሉ። የማዕድን ሚኒስትሮቹ ይህን ግልጽነትን የመፍጠር ጥረት መቀላለቀል አለባቸው። እነርሱም ቢሆን ለአገራቸው በጎ ዝናን ማጎናጸፍ እንደሚሹና የተገኘውን ገንዘብም ለአገር ልማት ማዋል እንደሚፈልጉ ማረጋገጣቸው ግድ ነው»

ይህ በጎ አስተሳሰብ እርግጥ የጥሬ ሃብት ባለቤት የሆኑትን ሃገራት ቀናና ቁርጠኛ ፍላጎት ይጠይቃል። ከምዕራቡ ዓለም አንጻር እንደ ፖለቲከኛ በሙስና ከተዘፈቁ መንግሥታት ጋር መጋተሩ ቀላል እንዳልሆ ነው ኮፕ የሚናገሩት።

በአጠቃላይ የአፍሪቃ ሕዝብ በነዳጅ ዘይት ከታደለችው ከናይጄሪያ አንስቶ በተለያየ የተፈጥሮ ጸጋ እስከካበተችው እስክ ኮንጎ፤ ከርሰ-ምድራቸው በብዙ ሚነራሎች እስከተሞላው ሌሎች በርካታ የክፍለ-ዓለሚቱ ሃገራት፤ የትም ይሁን የት እስካሁን የጸጋው ተቋዳሽ ለመሆን አልበቃም። አብዛኛው ሕዝብ ዛሬም የበይ ተመልካች እንደሆነ ነው።

እናም ግልጽነት መስፈን ካለበት በተለይም ሙስና መወገዱና ሕዝቡ የገዛ ሃብቱ ተጠቃሚ መሆን የሚችልበት ሁኔታ በቅድሚያ መመቻቸቱ አማራጭ አይኖረውም። አፍሪቃ የተፈጥሮ ሃብቷን ዘላቂ በሆነ መንገድ ማስተዳደርና መገልገል፤ የውጭ ተጠቃሚውንም ፍላጎት ማሟላት ካለባት ይህ ግድ ነው የሚሆነው። ድርሻው የተነፈገው ሕዝብ ለዘለቄታው የውጭውን ዓለም የጥሬ ሃብት ፍላጎት ለማሟላት አቅሙም አይኖረውም።

መሥፍን መኮንን

ሸዋዬ ለገሠ

Audios and videos on the topic

 • ቀን 05.12.2012
 • አዘጋጅ
 • ያትሙ ገፁን ያትሙ
 • Permalink https://p.dw.com/p/16vib
 • ቀን 05.12.2012
 • አዘጋጅ
 • ያትሙ ገፁን ያትሙ
 • Permalink https://p.dw.com/p/16vib