አፍሪቃና የፓሪሱ ጉባዔ | ጤና እና አካባቢ | DW | 03.12.2015
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ጤና እና አካባቢ

አፍሪቃና የፓሪሱ ጉባዔ

የፓሪስ የተ. መ.ድ. የአየር ንብረት ለውጥ ተመልካች ጉባዔ ዛሬ አራተኛ ቀኑን ይዟል። በጉባኤዉ ላይ በመሳተፍ ላይ የሚገኙ አገሮች ተደራዳሪዎች ሁሉን ከሚያግባባ ሕጋዊ የስምምነት ማዕቀፍ እንዲደርሱ ጥሪ እያቀረቡ ነው። ለከባቢ አየር ብክለት አነስተኛ አስተዋጽዖ የሚያበረክቱት አፍሪቃውያን በዚህ መዘዝ የተከተለዉ የአየር ንብረት ለውጥ ተጠቂ ናቸው።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 04:25
አሁን በቀጥታ እየተሰራጨ ያለ
04:25 ደቂቃ

አፍሪቃና የፓሪሱ ጉባዔ

በፓሪስ የአየር ንብረት ለውጥን ለመግታት የሚደረገዉ ድርድር ለሁለት ጥያቄዎች መልስ ያስገኛል ተብሎ ይጠበቃል። የጉባዔው ተሳታፊዎች የከባቢ አየር በካይ ጋዞችን መጠን ለመቀነስ የሚደርሱት ስምምነት ቀዳሚው ነው። ሁለተኛው ደግሞ የበካይ ጋዝ ቅነሳው በራሱ በቂ የመሆኑ ጉዳይ። የአየር ንብረት ለውጥ አስከፊ ጉዳት ካደረሰባቸው አገራት መካከል አንዷ የሆነችው ኢትዮጵያ በጠቅላይ ሚኒስትር ሐይለማርያም ደሳለኝ ተወክላ በጉባዔው ተገኝታለች። ጠቅላይ ሚኒስትሩ የአየር ንብረት ለውጥ፤ የአየር ጠባይ መቀያየርና ተዛማጅ ክስተቶች በኢትዮጵያውያን ኑሮ ላይ አደጋ አስከትለዋል ሲሉ ተናግረዋል። «በኤል ኒኖ ምክንያት ተከሰተው ድርቅ በሚሊዮኖች በሚቆጠሩ የአገሬ ሰዎች ላይ ተጽዕኖ አሳድሯል።» ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ «የአየር ንብረት ለውጥን እኛ አልፈጠርነውም። እኛም መፍትሄ አናበጅለትም።» በማለት ከሌሎች የአፍሪቃ መሪዎች ጋር የሚስማማ ድምጽ አሰምተዋል። የጠቅላይ ሚኒስትሩና ሌሎች አፍሪቃውያን ተመሳሳይ ሮሮዎች ምን አይነት ምላሽ እንደሚያገኙ ለማወቅ የድርድሩን መጠናቀቅ መጠበቅ ግድ ይላል። የአፍሪቃ ህብረት ኮሚሽነሯ ንኮሳንዛና ድላሚኒ ዙማ ግን «በዚህ ጉባዔ ሁሉንም ወገኖች የሚያካትት፤ የበካይ ጋዝ ልቀትን ለመቀነስ፤ ለማሻሻልና በገንዘብ ለመደገፍ ከሚያስችል አጠቃላይና አስገዳጅ ስምምነት እንዲደረስ በተባበረ የአፍሪቃ ድምጽ ጥሪ እናቀርባለን።»ሲሉ ተናግረዋል።

11.2015 DW Blog Faces Climate Change

የአየር ንብረት ተሟጋቾች የድርድሩ ተሳታፊዎች ከቁርጠኛ ስምምነት እንዲደርሱ እየወተወቱ ነው።

ከዓለም ህዝብ መካከል 10 በመቶ ብቻ የሆኑት ባለጠጎች ግማሽ የከባቢ አየር በካይ ጋዞችን ከቅሪተ-አካል እንደሚያመርቱ የብሪታንያው ኦክስፋም የእርዳታ ድርጅት ይፋ ያደረገው አዲስ ጥናት ጠቁሟል። በተቃራኒዉ በአየር ንብረት ለዉጥ ምክንያት ለድርቅና ኃይለኛ ማዕበሎች የተጋለጡት ወገኖች ለብክለቱ የሚያደርጉት አስተዋፅኦ አስር በመቶ ብቻ ነዉ። እናም በዚህ ጉባኤ የከባቢ አየር በካይ ጋዝ ልቀትን የመቀነሱም ሆነ በአየር ንብረት ለውጥ አስከፊ ጉዳት የደረሰባቸውን አገራት ለመርዳት የሚዉለዉን ገንዘብ የማግኘቱ ጉዳይ ከፍተኛ ድርድር ይጠብቀዋል። የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ዋና ጸሃፊ ባንኪ ሙን የከባቢ አየር ለውጥ ለአፍሪቃውያን የደቀነውን አደጋ ጠቁመዋል።

«በአየር ንብረት ለውጥ ምክንያት በምግብና የውሃ አቅርቦት ላይ የሚፈጠረው ችግር የሚጎዳዉ ኢኮኖሚያችሁን ብቻ ሳይሆን ፖለቲካዊ መረጋጋትን ጭምር ነው።»

የዓለም የምግብ እና የእርሻ ድርጅት በበኩሉ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት በዘላቂ የልማት ግብነት እንደታቀደዉ እስከ ጎርጎሪዮሳዊዉ 2030 ዓ.ም. ረሃብን ከዓለማችን የማጥፋቱ ዓላማ ተግባራዊ ሊሆን የሚችለዉ የተከሰተዉን የአየር ንብረት ለዉጥ የሚያስተካክል ቁርጠኛ ርምጃ መዉሰድ ሲቻል ብቻ መሆኑን አመልክቷል። ድርጅቱ አያይዞም የአየር ንብረት ለዉጡ ጉዳት ላደረሰባቸዉ ሃገራት ተገቢዉ ርዳታ እና ለዉጡ ለሚያስከትላቸዉ መዘዞች የተጋለጡ ወገኖች ከለዉጡ ጋር ተላምደዉ እንዲኖሩ በቂ የገንዘብ ድጋፍ እንደሚያስፈልግም ጠቁሟል።

በፓሪሱ ጉባኤ ላይ ፈረንሳይ በሚቀጥሉት አምስት አመታት ለአፍሪቃ 2 ቢሊዮን ዩሮ ለመስጠት ቃል ገብታለች። ገንዘቡ የታዳሽ ኃይል ማመንጫዎችን ለመገንባት እና ለአየር ሙቀት መጨመር ምክንያት ናቸው የተባሉትን የቅሪተ-አካል የኃይል ምንጮች ለመተካት ያለመ ነው። በጉባዔው ንግግር ያደረጉት የፈረንሳዩ ፕሬዝዳንት ፍራንሷ ኦሎንድ አገራቸው አፍሪቃ ዉስጥ የኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦትን ለማሳደግ ትኩረት መስጠቷን ተናግረዋል።

Estonian Wind

ታዳሽ የኃይል ምንጭ የመጪው ዘመን ተስፋ

«አፍሪቃ ሥራ ላይ ያልዋለ ከፍተኛ አቅም አላት። ይህን በተመለከተ የአፍሪቃ መሪዎችና መንግሥታት የአየር ንብረት ለውጥ ተመልካች ኮሚቴን በሊቀመንበርነት የሚመሩት የግብጹ ፕሬዝዳንት የመወያያ ሃሳብ ያቀርቡልናል። የአፍሪቃ ህብረትና የአፍሪቃ ልማት ባንክም የየራሳቸውን ፕሮጀክቶች ያቀርቡልናል። ምክንያቱም ለእኛ፤ ታዳሽ የኃይል ምንጭ የማግኘት ዕድል ማለት፤ እያንዳንዱ ቤተሰብ በኤሌክትሪክ ኃይል ምግቡን እንዲያበስል እና ሙቀት እንዲያገኝ ማለት ብቻ ሳይሆን በቀጥታ በኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴዎች ተሳትፎ ማድረግም ነዉ። ፈረንሳይ የኤሌክትሪክ ኃይል ለማግኘት ዕድል ቅድሚያ መስጠት ትፈልጋለች። ለዚህም በርካታ መፍትሄዎች አዘጋጅተናል።»

የፈረንሳይ የገንዘብ ድጋፍ በዋናነት ለምዕራብ አፍሪቃ አገራት የታለመ ነው። ፕሬዝዳንቱ አፍሪቃ በረሐማነትንና ሌሎች የአየር ንብረት ለውጥ ጫናዎችን መቋቋም እንድትችል፤ አገራቸው የምታደርገውን የገንዘብ ድጋፍ በጎርጎሮሳዊው 2020 ዓ.ም. ወደ 1 ቢሊዮን ዩሮ እንደምታሳድግም ቃል ገብተዋል። የአፍሪቃ አገራት መሪዎች ከፍተኛ በካይ ጋዝ ወደከባቢ አየር የሚለቁ አገሮች ከፍ ያለ ገንዘብ እንዲያዋጡ ይፈልጋሉ።

እሸቴ በቀለ

ሸዋዬ ለገሰ

Audios and videos on the topic

ተዛማጅ ዘገባዎች