አፍሪቃና የዕድገት ችግሯ | ኤኮኖሚ | DW | 11.03.2009
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ኤኮኖሚ

አፍሪቃና የዕድገት ችግሯ

በብዙ ሚሊዮን የሚቆጠሩ ተጨማሪ አፍሪቃውያን ዛሬ በዓለምአቀፉ የፊናንስ ቀውስ ሳቢያ የከፋ ድህነት ላይ እንዳይወድቁ እያሰጋ ነው የሚገኘው።

ኮፊ አናን

ኮፊ አናን

የዓለምአቀፉ ምንዛሪ ተቁዋም የ IMF አስተዳዳሪ ዶሚኒክ-ሽትራውስ-ካህን ትናንት ታንዛኒያ ርዕሰ-ከተማ ዳር-ኤስ-ሣላም ላይ በተከፈተው የድርጅታቸውና የአፍሪቃ የሁለት ቀናት ጉባዔ መክፈቻ ላይ ባሰሙት ንግግር “የተሰበሰብነው በአፍሪቃ ታሪክ ውስጥ አስቸጋሪ በሆነ ወቅት ላይ ነው” ብለዋል። ሁኔታው እጅግ አሳሳቢ ሲሆን በአንድ በኩል የበለጸገው ዓለም የፊናንስ ቀውሱን ለማሸነፍ የሚያደርገው ጥረት የተፋጠነ ዕርምጃ አለማሣየቱና በሌላ በኩልም በጥሬ ዕቃ ዋጋ ማቆልቆል የተነሣ የብዙዎች አፍሪቃውያን መንግሥታት የውጭ ገቢ መቀነስ ለዚህ ዓመት ተደርጎ የነበረውን የኤኮኖሚ ዕድገት ትንበያ ዝቅ አድርጎ ማረሙን ግድ እያደረገው ነው።

ባለፈው አንድ አሠርተ-ዓመት ለመጀመሪያ ጊዜ ቀታይነት ያለው የኤኮኖሚ ዕድገት የታየባት አፍሪቃ በወቅቱ በዓለምአቀፉ የፊናንሰ ቀውስ ሳቢያ ለፖለቲካና ለማሕበራዊ ነውጽ መንስዔ ሊሆን የሚችል ብርቱ ችግር ተደቅኖባት ነው የሚገኘው። ታዲያ የአፍሪቃ ኤኮኖሚ ከውድቀት ሊድን የሚችለው እንዴት ነው” ምክንያቶቹስ ምንድናቸው? የጀርመን የልማት ፖሊሲ ኢንስቲቲቱት የምጣኔ-ሐብት ባለሙያ ታቲያና ቻሁድ በተለይ ሶሥት ነጥቦችን ዓቢይ መንስዔ አድርገው ይጠቅሳሉ።

“አፍሪቃ በቀውሱ በጣሙን ነው የተነካችው። ክፍለ-ዓለሚቱ፤ በተለይም በጥሬ ሃብት የታደሉት አገሮች ባለፉት ዓመታት ታላቅ ስኬት ነበራቸው። አሁን ግን ከ 80ዓመታት ወዲህ ከባዱ ወደሆነው የኤኮኖሚ አዘቅት በተሻገረው ዓለምአቀፍ የፊናንስ ቀውስ በተለይ እነዚሁ ጥሬ ዕቃ ወደ ውጭ የሚሸጡት አገሮች እየተጎዱ ናቸው። ምክንያቱም የገበያው ዋጋ እንደ ችግሩ መጠን እያቆለቆለ ሄዷል። ከዚሁ ባሻገር የመዋዕለ-ነዋይ አቅርቦትና ምናልባት የልማት ዕርዳታውም እየቀነሰ ነው”

የዓለምአቀፉ ምንዛሪ ተቁዋም አስተዳዳሪ ዶሚኒክ-ሽትራውስ-ካህን ዳር-ኤስ-ሣላም ላይ እንዳስረዱት ችግሩ የኤኮኖሚ ዕድገትን ቀጣይ በማድረግና የቤተሰብ ገቢን በመንከባከብ ብቻ የተወሰነ አይደለም። ባለሥልጣኑ የንግድ ድከመትንና በውጭ የሚኖሩ አፍሪቃውያን ቤተሰብን ለመደገፍ የሚልኩት ገንዘብ መቀነስም የውጭው መዋዕለ-ነዋይ ፍሰት መለዘብ ታክሎበት በአፍሪቃ ኤኮኖሚ ላይ ግፊቱን እንዳጠናከረም ያምናሉ። ካህን እነዚህን ነጥቦች በማገናዘብ ለያዝነው 2009 ዓ.ም. ያቀረቡትን የአፍሪቃ ዕድገት ትንበያቸውን በሶሥት ከመቶ ገድበውታል።
ለዚያውም ቀውሱ ሥር መስደዱን ከቀጠለ ይህም የተጋነነ ግምት ነው የሚሆነው። በመሆኑም ችግሩን መታገሉ በተቀዳሚ የአፍሪቃውያን የራሳቸው መሆኑን ቢያምኑም የበለጸጉት መንግሥታት ያለባቸውን ክፍለ-ዓለሚቱን የመገደፍ ታሪካዊ ግዴታ አስረግጠዋል።

“ዕርዳታችን እንደ መሰል የዓለም ነዋሪዎች ቀውሱ በአፍሪቃ የፖለቲካና የማሕበራዊ ኑሮ ላይ ባሳደረው ስጋት ሳቢያ የምናደርገው የሞራል ግዴታ ብቻ አይደለም። የቅኝ አገዛዙ ዘመን ሲታሰብ ታሪካዊ ግዴታችንም ጭምር ነው። ሆኖም ዕርዳታው ፈተናው የተደቀነባት የአፍሪቃ የራስ ጥረት ሳይታከልበት አንዳች ጥቅም አይኖረውም። ስለዚህም ቀውሱን በመወጣቱ ረገድ በአካባቢው ስኬት የማግኘቱና የአፍሪቃን የረጅም ጊዜ ዕርምጃ የማረጋገጡ ተግባር በራሷ በአፍሪቃ ትከሻ ላይ ነው ያለው”

ሆኖም አፍሪቃ ውስጥ ሸክሙን በራስ አቅም ለማቃለል መቻሉ ብዙ የሚያጠያይቅ ነው። በሌላ በኩል በራሱ ችግር የተጠመደው የበለጸገው ዓለም ሁነኛ ድጋፍ ለመስጠት ቁርጠኛ ሆኖ መነሣቱም አስተማማኝ ነገር አይደለም። ሶሥት መቶ ገደማ ከሚጠጉት የዳር-ኤስ-ሣላም ጉባዔ ተሳታፊዎች አብዛኞቹ በምዕራቡ ዓለም አንድን የግል ኩባንያ ከውድቀት ለማዳን የፈሰሰው መደጎሚያ እንኳ ለመላው አፍሪቃ ከቀረበው የገንዘብ ድጋፍ እንደሚበልጥ በማስገንዘብ ምሬታቸውን ገልጸዋል። የ IMF አስተዳዳሪ ሽትራውስ-ካህን ራሳቸው “ዓለምአቀፉ ሕብረተሰብ ቀውሱን ለመፍታት በሊዮኖች ማውጣት በቻለበት ጊዜ ዝቅተኛ ገቢ ላላቸው አገሮች በመቶ ሚሊዮኖች የሚቆጠር ገንዘብ ማግኘት አለመቻሉን ልቀበለው አልችልም” ነው ያሉት።

የቀድሞው የተባበሩት መንግሥታት ዋና ጸሐፊ ኮፊ አናን ደግሞ በአፍሪቃ ላይ በማተኮር በዓይነቱ የመጀመሪያው በሆነው ጉባዔ አደጋውን ከኤኮኖሚ ማዕበል፤ ትሱናሚ ጋር አመሳስለውታል። እርግጥ በዓለምአቀፉ የፊናንስ ገበዮች ላይ ብዙም ተሳትፎ ባሌላት በአፍሪቃ ላይ ቀውሱ በመጀመሪያ ደረጃ ብዙም ተጽዕኖ አልነበረውም። ግን አሁን ኮፊ አናን እንዳሉት በቀጥታ ተጋፍጣዋለች።

“ዓለምአቀፉ ቀውስ በተቀዳሚ የፊናንስ ቀውስ ሆኖ ሲታይ ብዙዎች ያሰቡት ችግሩ አፍሪቃን አልነካም ብለው ነበር። ይሁንና እነዚህ የዓለም ኤኮኖሚ አድናፋዊነት ምን ማለት እንደሆነ፤ ኤኮኖሚያችንና ዕጣችን የተሳሰሩ መሆናቸውን በሚገባ አልለዩትም። አፍሪቃ አሁን ፊት መስመር ላይ ቆማ ነው የምትገኘው። ዓለምአቀፉ የምንዛሪ ተቁዋም በወቅቱ አፍሪቃ ሶሥት በመቶ ዕድገት እንደምታደርግ ይተነብያል። ግን ይህም ምናልባት ወደታች ሊታረም የሚችል ነው”

እርግጥም ከወቅቱ ተጨባጭ ሁኔታ አንጻር ይህ ማቆልቆል ሊገጥም እንደሚችል በምንዛሪው ተቁዋምም የሚጠበቅ ነው። የዓለም ኤኮኖሚ በአጠቃላይ በዚህ ዓመት ቀደም ሲል ከተባለው 0,5 ከመቶ ዕድገት በማቆልቆል ከዜሮ በታች እንደሚሆንም ግምት አለ። ከዚህ አንጻር በቅርቡ ለንደን ላይ የሚካሄደው የቡድን-ሃያ መንግሥታት የዓለም የፊናንስ ጉባዔ የሚወስዳቸው ዕርምጃዎች ለሂደቱ መሻሻል አለመሻሻል ወሣኝ ናቸው።

የኤኮኖሚው ቀውስ ሃብታም መንግሥታት ለድሆች አገሮች የሚያቀርቡትን ዕርዳታ በመቁረጥ ድህነትን እስከ 2015 ዓ.ም. በግማሽ ለመቀነስ የተጣለውን የተባበሩት መንግሥታትን የሚሌኒየም ግብ ተሥፋ ከንቱ እንዳያደርጉ ስጋት መፈጠሩም አልቀረም። የዋና ጸሐፊ ባን-ኪ-ሙን አማካሪ ጄፍሪይ ሣክስ ትናንት እንደገለጹት የቀውሱ ዕድሜ ከረዘመ የተቀመጠውን የጊዜ ገደብ ማራዘሙ ምናልባት አስፈላጊ ሆኖ ሊገኝም ይችላል። ሆኖም የተባበሩት መንግሥታት የልማት ዕቅድ ተጠሪ አድ ሜልከርት በቅርቡ እንዳስገነዘቡት ከሚሌኒየሙ ግቦች በመድረሱ ዓላማ ላይ መጽናት ግድ ነው።

“ዓለምአቀፉ ቀውስ በተቀዳሚ የፊናንስ ቀውስ ሆኖ ሲታይ ብዙዎች ያሰቡት ችግሩ አፍሪቃን አልነካም ብለው ነበር። ይሁንና እነዚህ የዓለም ኤኮኖሚ አድናፋዊነት ምን ማለት እንደሆነ፤ ኤኮኖሚያችንና ዕጣችን የተሳሰሩ መሆናቸውን በሚገባ አልለዩትም። አፍሪቃ አሁን ፊት መስመር ላይ ቆማ ነው የምትገኘው። ዓለምአቀፉ የምንዛሪ ተቁዋም በወቅቱ አፍሪቃ ሶሥት በመቶ ዕድገት እንደምታደርግ ይተነብያል። ግን ይህም ምናልባት ወደታች ሊታረም የሚችል ነው”

የሆነው ሆኖ ከወቅቱ የቀውስ አያያዝ አንጻር የሚሌኒየሙ ግብ የሩቅ ተሥፋ ሆኖ እንዳይቀር ያሰጋል። የዓለም የምግብና የእርሻ ድርጅት ፋኦ ቀደም ሲል ባቀረበው መረጃ መሠረት የምድራችን ረሃብተኛ ሕዝብ ቁጥር እስከ 2007 ዓ.ም. መጨረሻ ከ 854 ወደ 923 ሚሊዮን ከፍ ብሎ ነበር። ይህም ከዓለምአቀፉ የፊናንስ ቀውስ በፊት መሆኑ ነው። አሁን ደግሞ ይበልጥ ለመጨመሩ አንድና ሁለት የለውም። ከኤኮኖሚው ቀውስ የመላቀቁ ጥረት እየተጎተተ መሄዱ እስከቀጠለ ድረስ ደግሞ የድህነቱም ሁኔታ የሚከፋ ነው የሚሆነው። በአፍሪቃ ባለፉት ዓመታት ዕድገት ታየ ቢባልም በሌላ በኩል በከፋ ድህነት ላይ የሚገኘው የሕብረተሰብ ክፍል 50 ከመቶ ከሚጠጋ ድርሻው ንቅንቅ አላለም። የተባበሩት መንግሥታት ባለሥልጣን አድ ሜልከርት የሚፈሩት እንዲያውም መባባሱን እንዳይቀጥል ነው።

“እዚህ ላይ በእርግጥ ቁርጠኛ መሆንና የድህነትን ችግር አጥብቀን መመልከት ይኖርብናል። በዚህ የፊናንስ ቀውስ ካለፉት ዓመታት የበለጠ ብዙ ሰዎች ወደ ድህነት እንደሚገፉ ግልጽ ነው። እና ይህን ሂደት መቀልበስ አለብን። ለዚህ ሌላ አማራጭ የለም”

በጄፍሪይ ሣክስ ዕምነት በወቅቱ ዓለምን ከዚህ ቀውስ ልታወጣ የምትችለው ጤናማ የውጭ ምንዛሪ ክምችት ያላት፣ ግዙፍ የንግድ ትርፍ የምታስገባውና በዓለም ዙሪያ ሰፊ መዋዕለ-ነዋይ በሥራ ላይ የምታውለው ቻይና ናት። ሣክስ እንደሚሉት ቻይና እስካሁን ቀውሱን ከአሜሪካና ከአውሮፓ በተሻለ ሁኔታ ተቁዋቁማለች። ምንም እንኳ በነዚሁ ክፍለ-ዓለማት የምታደርገው የውጭ ንግድ በቀዉሱ ሳቢያ በማቆልቆሉ ብትጎዳና ብዙ ፋብሪካዎችን መዝጋት ብትገደድም! ይሁንና በኤኮኖሚ ጥንካሬዋ በዓለም ላይ ሶሥተኛዋ የሆነችው ቻይና በወቅቱ ሁለት ትሪሊዮን ዶላር የውጭ ምንዛሪ ክምችት አላት። ይህም ግዙፍ ገንዘብ ነው። በቤይጂንግ መንግሥት መረጃ መሠረት የአገሪቱ የበጀት ትርፍም ባለፈው 2008 ዓ.ም. 440 ቢሊዮን ዶላር ይደርስ ነበር። ይህም ቀደም ካለው ዓመት ሲነጻጸር ሃያ በመቶ ከፍ ያለ መሆኑ ነው።

ቻይና ከዚህ አንጻር የዓለምን ኤኮኖሚ ጤናማ በማድረጉ ረገድ በቡድን-ሃያ ውስጥም ታላቅ ሚና ይኖራታል። በዚህም መልክ ነው በወቅቱ በበለጸጉት መንግሥታት ዘንድ የምትታየው። የሆነው ሆኖ የቡድን-ሃያ ጉባዔ ዓለምአቀፉን የፊናንስ ስርዓት ፍትሃዊ አድርጎ ለመጠገን የሚያበቃ ጥርጊያ ካልከፈተና ለታዳጊውን ዓለም ጥቅምም ተገቢውን ትኩረት ካልሰጠ ችግሩን መፍታቱ ከባድ ነው የሚሆነው። ምናልባት በተወሰኑ ዕርምጃዎች በበለጸጉት አገሮች የተፈጠረውን የፊናንስ ውዥምብር ለጊዜው በረድ ማድረግ ይቻል ይሆናል። ዓለምአቀፉ የኤኮኖሚ ቀውስና የታዳጊ አገሮች ዘላቂ የዕድገት ዕጣ ግን መሠረታዊ ለውጦችን የሚጠይቅ ነው የሚሆነው። በተለይ አፍሪቃን ከድህነት ማጥ ለማውጣት የበለጸገው ዓለም የገባውን ቃል ዕውን ማድረግ ይጠበቅበታል። የዳር-ኤስ-ሣላም የ IMF ና የአፍሪቃ መንግሥታት የሁለት ቀናት ጉባዔ መልዕክት ይህ ነው።

Mesfin Mekonnen