አፍሪቃና የዕድገት ችግሮቿ | ኤኮኖሚ | DW | 09.01.2013
 1. Inhalt
 2. Navigation
 3. Weitere Inhalte
 4. Metanavigation
 5. Suche
 6. Choose from 30 Languages

ኤኮኖሚ

አፍሪቃና የዕድገት ችግሮቿ

ጊዜው የአፍሪቃ ተነሳሽ ሃገራት የዓለም ኤኮኖሚ ዕድገት መንኮራኩር እየሆኑ መሄዳቸው የሚነገርበት ወቅት ነው።

default

ጊዜው የአፍሪቃ ተነሳሽ ሃገራት የዓለም ኤኮኖሚ ዕድገት መንኮራኩር እየሆኑ መሄዳቸው የሚነገርበት ወቅት ነው። ይሁንና የዓለምአቀፉ ምንዛሪ ተቋም የ IMF አስተዳዳሪ ክሪስቲን ላጋርድ እንደሚሉት የፖለቲካ ውዝግብና የትጥቅ ትግል በክፍለ-ዓለሚቱ የወደፊት ዕርምጃ ላይ ዋነኛውን አደጋ ደቅነው ይገኛሉ። ከዚሁ ሌላ በክፍለ-ዓለሚቱ የተስፋፋው ሙስናና የፊናንስ ምዝበራም ልማትን አንቆ የያዘ ብርቱ ጠንቅ መሆኑ በሰፊው የሚታወቅ ነገር ነው።

በተፈጥሮ ጸጋ የታደሉት የአፍሪቃ ሃገራት የአውሮፓ ኤኮኖሚ መሰናክል ገጥሞትና አሜሪካም ከበጀት ኪሣራዋ በውል ማገገም አቅቷት በምትገንበት በዛሬው ወቅት አስደናቂ ዕድገት በማስመዝገብ ቀጥለዋል። ዓለምአቀፉ የምንዛሪ ተቋም በአዲሱ 2013 ዓ-ም ከሣሃራ በስተደቡብ ለሚገኘው የአፍሪቃ ክፍል አማካይ 5,25 ከመቶ ዕድገት የሚተነብይ ሲሆን ይህም ክፍለ-ዓለሚቱን ከአባቢዎቹ የእሢያ ሃገራት ቀጥሎ ሁለተኛ የሚያርግ ነው። ተቋሙ ለዓለም ኤኮኖሚ ከተነበየው የ 3,6 ከመቶ ዕድገት ደግሞ በጣሙን ይበልጣል።

የምንዛሪው ተቋም አስተዳዳሪ ፈረንሣዊቱ ክሪስቲን ላጋርድ በዓለም ላይ ቀደምቷ ኮኮ አምራች በሆነችው በአይቮሪ ኮስት ለአገሪቱ እንደራሴዎች ባሰሙት ንግግር ዕርምጃ በማሳየት ላይ የሚገኙ ተነሳሽ የአፍሪቃ ሃገራት የዓለም ኤኮኖሚ ዕድገት መንኮራኩር መሆናቸውን አስረግጠዋል። በነገራችን ላይ ከከባድ የፖለቲካ ቀውስ የተላቀቀችው አይቮሪ ኮስት በተገባደደው 2012 ዓ-ም በዓለም ባንክና በዓለምአቀፉ ምንዛሪ ተቋም የአራት ቢሊዮን ዶላር የዕዳ ምሕረት ተደርጎላት እንደነበር የሚዘነጋ አይደለም። ላጋርድ በንግግራቸውአያይዘው እንዳስረዱት እርግጥ ክፍለ-ዓለሚቱ ከውዝግቦች መላቀቋ ቀጣይነት ላለው ልማት ቅድመ-ግዴታ ነው።

« ሰላም ከሌለ ነዋሪዎች እንደ ውጭ ዜጎች ሁሉ ለወደፊት የሚጠቅማቸውን መዋዕለ-ነዋይ ለማድረግ ዕምነቱም ሆነ ድፍረቱ አይኖራቸውም። ውዝግቦቹ በተዋጊዎቹ ወገኖች ላይ የሚያስከትሉት ጥፋት አስከፊ ነው። በጎረቤቶቻቸው ላይም እንዲሁ ተጽዕኖ አላቸው። ይህን ደግሞ በሚገባ ታውቃላችሁ። የኤኮኖሚ ዕድገት አንደኛ ጠላት ማን እንደሆነ መጥቀስ ካለብን ያ ለእኔ ጦርነት ነው»

ይህም ሆኖ ክሪስቲን ላጋርድ ለአፍሪቃ ዕድገት አድናቆት ከመግለጽ ወደ ኋላ አላሉም። የዓለም ኤኮኖሚ ከባድ ፈተና ገጥሞት በሚገኝበት በዛሬው ጊዜ ከመዳብ እስከ ብረት፤ ከአልማዝ እስከ ወርቅ ሁሉንም የሚለግሰው የአፍሪቃ የማዕድን ዘርፍ ንግድ በተለይም በቻይና ኢንዱስትሪ የጥሬ ዕቃ ጥም ሳቢያ በማበብ ላይ ይገኛል። የነዳጅ ዘይቱም ዘርፍ ሁኔታ ተመሳሳይ ሲሆን ብዙም ያልተነኩት የፍጆት ገበዮቿም የመዋይለ-ነዋይ ባለቤቶችን በሰፊው እየሳቡ ነው። ግን ይህ የቅርብ ግኝት በክፍለ-ዓለሚቱ ዙሪያ በሚነሱ ግጭቶች አደጋ ላይ መውደቁ ነው ችግሩ።

ከነጻነት ማግሥት፤ ማለትም ከግማሽ ምዕተ-ዓመት በፊት አንስቶ የፖለቲካ ቀውስ አዙሪትን ለማስወገድ ረጅም ትግል ባደረጉት በምዕራብና ማዕከላዊ አፍሪቃ ሃገራት ያለፈው 2012 ዓ-ም አካባቢው እንደገና ዓመጽ ላይ ወድቆ የታየበት ነበር። የናይጄሪያው እስላም አክራሪ ቡድን ቦኮ ሃራም የፖለቲካ ነውጽ በገጠመው በአገሪቱ ሰሜናዊ ክፍል ዕለታዊ ጥቃት ሲያደርስ ቆይቷል። የዴሞክራቲክ ሬፑብሊክ ኮንጎና የማዕከላዊት አፍሪቃ ሬፑብሊክ ዓማጺያንም በመጠናከር መንግሥታቱን ከመገልበጥ አደጋ ላይ እስከመጣል ነው የደረሱት።

ከአል-ቃኢዳ የተሳሰሩ እንደሆኑ የሚነገርላቸው የማሊ ተዋጊዎች ደግሞ በአገሪቱ የተካሄደ ወታደራዊ መፈንቅለ-መንግሥት የፈጠረውን ክፍተት በመጠቀም የአገሪቱን ግማሽ ክፍል ለመቆጣጠርና በአካባቢው የዓመጽ መዛመት ስጋት እስከመፍጠር ደርሰዋል። የዓለምአቀፉ ምንዛሪ ተቋም አስተዳዳሪ ክሪስቲን ላጋርድ በአይቮሪ ኮስት የሚያካሂዱትን የሶሥት ቀናት ጉብንት ነገ የሚያጠቃልሉ ሲሆን ከአሠርተ-ዓመት የፖለቲካ ቀውስና ግጭት ተላቃ ማገገም የያዘችው የምዕራብ አፍሪቃ አገር የክፍለ-ዓለሚቱን ዕድገት በማራመድ ረገድ ግንባር ቀደም ልትሆን እንደምትችል ዕምነታቸው ነው።

«አይቮሪ ኮስት ምናልባት የዚህ ለውጥ ግንባር ቀደም መሪ ልትሆን ተችላለች። እኔ ይህ ጽኑ ዕምነት አለኝ። ግን እናንተም እንደኔው ነው የምታስቡት። ለነገሩ አንዴ የአይቮሪ ኮስት የኤኮኖሚ ዕድገት ተዓመር ለአፍሪቃ ጥንካሬና ለአዳጊው ዓለም በአርአያነት የታየ ነበር። አሁን ደግሞ ለሁለተኛው የአይቮሮች ተዓመር ጊዜው መጥቷል። በጦርነት ተጽዕኖ የደረሰባችሁን ስቃይ ተቋቁማችሁ ውዝግብንና ክፍፍልን ለማስወገድ፤ ለኤኮኖሚ ስኬት አስፈላጊ የሆነውን ዕርቀ-ሰላምም ለማውረድ በቅታችኋል»

በእርግጥም የአይቮሪ ኮስት ሁኔታ ተሥፋ ሰጭ እየሆነ ነው የመጣው። ሆኖም አካባቢው ለዘለቄታው የዕድገት ጠንቅ ከሆነው ውዝግብና ግጭት ተላቆ መቀጠሉን በሙሉ ልብ መናገሩ በጣሙን ያዳግታል። ይህ የአፍሪቃ ሃቅ ነው።

አፍሪቃንና ዕድገቷን በተመለከተ የጦርነቱን ያህል መሰናክል ሆኖ የሚገኘው ሙስናና የፊናንስ ምዝበራ ነው። በጎ አስተዳደር በክፍለ-ዓለሚቱ ባዕድ ነገር እንደሆነ ቀጥሏል። «ግሎባል ፋይናንሺያል ኢንቴግሪቲይ» በአሕጽሮት GFI በመባል የሚታወቀው ዋሺንግተን ላይ ተቀማጭ የሆነ ዓለምአቀፍ አጥኚ አካል ባለፈው ወር አውጥቶት በነበረ አዲስ ዘገባው እንዳመለከተው አዳጊው ዓለም በአጠቃላይ በሙስና፣ በታክስ አፈናና ገንዘብን ወደ ውጭ በገፍ ማሾለክን በመሳሰሉ ሌሎች የፊናንስ ወንጀሎች ከሁለት ዓመት በፊት ያጣው ገንዘብ በአንድ ትሪሊየን ዶላር ይገመታል።

የገንዘብ በዚህ መልክ ከአገር እንዲፈስ መደረግ አዳጊ አገሮች በዚያው በዓለምአቀፉ የምንዛሪ ተቋምና በዓለም ባንክ የተጠናቀሩ የመጨረሻ የንግድና ሌሎች ዳታዎች በቀረቡበት በ 2010 ዓ-ም በጥቅሉ 859 ቢሊዮን ዶላር እንዲያጡ ያደረገ ነበር። ገንዘቡ በሌላ አነጋገር በዚያው ዓመት ለአዳጊ ሃገራት ከቀረበው ይፋ የልማት ዕርዳታ በአሥር ዕጅ ገደማ የሚበልጥም መሆኑ ነው። እንግዲህ ወደ ታዳጊው ዓለም በየገባቸው አንዲት ዶላር በአንጻሩ አሥር ዶላር ሾልኮ ወጥቷል ማለት ነው። በአጠቃላይ ከአዳጊ ሃገራት ወደ ውጭ የሚፈሰው ሃብት እንዲያውም ከዚያ እንደሚበልጥ አንዳንድ ባለሙያዎች ይናገራሉ።

80 ገጾችን ያቀፈው ዘገባ እንደሚያመለክተው አብዛኛውን ገንዝብ ያጣችው ቻይና ስትሆን ሜክሢኮ፣ ማሌይዚያ፣ ሳውዲት አረቢያና ሩሢያም ዋና ዋና ከሚባሉት መካከል የሚመደቡት ናቸው። ከመጀመሪያዎቹ አሥር ሃገራት መካከል አፍሪቃይቱ አገር ናይጄሪያም የምትገኝበት ሲሆን ከአገሪቱ ውጭ የፈሰሰው ገንዘብ 17 ቢሊዮን ዶላር ይጠጋል። እርግጥ ኤኮኖሚያቸው በዚህ መልክ በአብዛኛው የተመታው መካከለኛ ገቢና ካታርን ወይም የተባበሩት አረብ ኤሚሮችን የመሳሰሉ ባለ ከፍተኛ ገቢ ሃገራት ቢሆኑም ኢትዮጵያን የመሳሰሉ ድሃ ተብዬ ሃገራትም በዝርዝሩ ውስጥ መስፈራቸው አልቀረም።

በአፍሪቃ ከናይጄሪያ ቀጥሎ ሱዳን 8,58 ቢሊዮን ዶላር ስታጣ ከኢትዮጵያ የሸሸውም ከአምሥት ቢሊዮን ተኩል ይበልጣል። እንግዲህ ይህ ግዙፍ ገንዘብ በሕገ-ወጥ መንገድ ታክስ ወደማይጠይቁ ባሕር ማዶ አካባቢዎችና ወደበለጸጉ ሃገራት ባንኮች ተሻግሯል ጥናቱ እንዳመለከተው። ዘገባው የወጣው ሙስና ለልማት መሰናክል መሆኑ ይበልጥ ዓለምአቀፍ ትኩረት ባገኘበት ወቅት ነው። ሙስና በቅርቡ የቻይና ብሄራዊ ሸንጎ 18ኛ ጉባዔ ላይ ሳይቀር አፍጦ የወጣ አክርክሪ ርዕስ እንደነበር የሚዘነጋ አይደለም።

በሙስና፣ በታክስ አፈና ወይም በጉቦ መልክ ወዘተ-የሚሾልከው ገንዘብ እንግዲህ በቀላሉ የሚገመት አይደለም። ዘገባው እንዳመለከተው በያዝነው ሚሌኒየም የመጀመሪያ አሠርተ-ዓመት ማለት ከ 2001 እስከ 2010 ባለው ጊዜ አዳጊ ሃገራት በያመቱ በአማካይ 586 ቢሊዮን ዶላር ገደማ አጥተዋል። ይህም በመላው አሠርተ-ዓመት በጠቅላላው 5,86 ትሪሊየን ዶላር የሚደርስ መሆኑ ነው። ሊያሰሉት ያዳግታል። ሂደቱ እየጨመረ የሚሄድ ሲሆን ከሣሃራ በስተደቡብ ባለው የአፍሪቃ ክፍል እንኳ 24 በመቶ ገደማ ከፍ ብሏል። እናም ሁኔታው እጅግ የሚያሳስብ ሲሆን መገታት እንዳለበት ነው ባለሙያዎች የሚያሳስቡት።

ወደተነሳንበት ወደ አፍሪቃ ልማት ከተመለስን ዛሬ ብዙ መወደስ የያዘውን የኤኮኖሚ ዕድገት ዘላቂና በማሕበራዊ ልማት የሚንጸባረቅ እንዲሆን ለማድረግ የሙስና መቅሰፍት ሳይውል ሳያድር መወገድ ያለበት ነገር ነው። ምዝበራው ባለበት ከቀጠለ ግን ክድህነት መላቀቅ ምን ጊዜም የማይቻል ነው የሚሆነው። አፍሪቃ ከዕድገት ችግሮቿ፣ ከፖለቲካ ውዝግቦችና ከባለሥልጣናት የዕጅ ዓመል ከጸዳች ብቻ ነው የዓለምአቀፉ ምንዛሪ ተቋም አስተዳዳሪ ክሪስቲን ላጋርድ እንዳሉት የዓለም ኤኮኖሚ መንኮራኩር በመሆን መቀጠል የምትችለው። አለበለዚያ ዕድገቱ ወሬ ብቻ ሆኖ ይቀራል።

መሥፍን መኮንን

አርያም ተክሌ

Audios and videos on the topic

 • ቀን 09.01.2013
 • አዘጋጅ
 • ያትሙ ገፁን ያትሙ
 • Permalink https://p.dw.com/p/17G7r
 • ቀን 09.01.2013
 • አዘጋጅ
 • ያትሙ ገፁን ያትሙ
 • Permalink https://p.dw.com/p/17G7r