አፍሪቃና የኦ.ኢ.ሲ.ዲ ዓመታዊ ዘገባ | ኤኮኖሚ | DW | 13.05.2009
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ኤኮኖሚ

አፍሪቃና የኦ.ኢ.ሲ.ዲ ዓመታዊ ዘገባ

ዓለምአቀፉ የኤኮኖሚ ቀውስ አፍሪቃን ከታሰበው ይልቅ ከባድ በሆነ የዕድገት ችግር ላይ ጥሎ ነው የሚገኘው። በጅምሩ

default

ክፍለ-ዓለሚቱ ከዓለምአቀፉ የፊናንስ ገበዮች ጋር በጥብቅ የተሳሰረች ባለመሆኗ ቀውሱ ከባድ ተጽዕኖ እንደማይኖረው ተሥፋ የጣሉት ጠበብትና ታዛቢዎች ጥቂቶች አልነበሩም። የሆነው ሆኖ አሁን በኢንዱስትሪ ልማት የበለጸጉት መንግሥታት የኤኮኖሚ ትብብርና ልማት ድርጅት ሰሞኑን ባወጣው ዘገባ እንዳመለከተው የአፍሪቃ ኤኮኖሚ በዚህ በያዝነው ዓመት ጠንከር ባለ መልክ ማቆልቆሉ የማይቀር ነው። እርግጥ ድርጅቱ ቀውሱን በፍጥነት ለማስወገድ ዕድል መኖሩንም መጥቀሱ አልቀረም።

ኦ.ኢ.ሲ.ዲ በሚል አሕጽሮት የሚጠራው በኢንዱስትሪ ልማት የበለጸጉ መንግሥታት የኤኮኖሚ ትብብርና ልማት ድርጅት በአፍሪቃ የምጣኔ-ሐብት ሂደት ላይ በያመቱ ዘገባ ያወጣል። ባለፉት ዓመታት የወጡት ዘገቦች የቀጣይ ዕድገትን ተሥፋ ያንጸባረቁ ነበሩ። የአፍሪቃ ኤኮኖሚ በነዚህ አምሥትና ስድሥት ዓመታት እርግጥ የእሢያን ያህል በከፍተኛ መጠን እመርታ አላሳየም። ሆኖም አንዳንድ የአፍሪቃ አገሮች ስኬታማ ዕርምጃ ማድረጋቸው በገሃድ የታየ ነው። የዚህ ዓመት ሁኔታ ግን ከቀድሞው ለየት ይላል። የዓለም ኤኮኖሚ ቀውስ ተጽዕኖ የጋረደው ሆኖ ነው የሚገኘው።

የኤኮኖሚው ትብብርና ልማት ድርጅት በወቅቱ ዘገባው እንደተነበየው የያዝነው 2009 ዓ.ም. የአፍሪቃ የምጣኔ-ሐብት ዕድገት በጣሙን ዝቅ ያለ ነው የሚሆነው። ዘገባው እንዳመለከተው ዕድገቱ 2,8 ከመቶ ቢሆን ነው። ችግሩ ድርጅቱ ቀደም ሲል እንዳሰበው ቀላል ነገር አልሆነም፤ የልማት ባለሙያው ዮሐነስ ዩቲንግ እንደሚሉት።

“ያሳዝናል እንደታሰበው አይደለም። የዘገባውም ጭብጥ ፍሬ-ነገር ከአምሥት በመቶ በላይ ከሆነ ጠንካራ የግማሽ አሠርተ-ዓመት ዕድገት በኋላ ሂደቱ ጨለም ያለ እንደሚሆን ነው”

ሁኔታው ከአሁኑ ይበልጥ ሊባባስም ይችላል። ምክንያቱም የኤኮኖሚ ትብብርና ልማት ድርጅቱ ዘገባ የተጠናቀረው በዓመቱ መጀመሪያ ገደማ፤ በትክክል ባለፈው የካቲት በቀረቡ ዳታዎች ላይ በመመሥረት ነው። ግን ከዚያን ወዲህ የዓለም ኤኮኖሚ በፍጥነት የማገገም ተሥፋ ይብስ እያቆለቆለ ነው የመጣው። የበለጸጉት መንግሥታት የኤኮኖሚ ትብብርና ልማት ድርጅት ባለሙያዎች ለዚሁ የዓለም ኤኮኖሚ ቀውስ ተጽዕኖ ላስከተለው የማቆልቆል ሂደት አራት ምክንያቶችን ደርድረዋል። አንደኛው በአጠቃላይ የዓለም ንግድ እየቀነሰ መሄድ ነው። ቀደም ያሉ መረጃዎች ይሄው ዘጠኝ ከመቶ ማቆልቆሉን ይጠቁማሉ።

የጥሬ ዕቃዎች ዋጋ መውደቅም ለምሳሌ አንጎላንና ናይጄሪያን የመሳሰሉ በነዳጅ ዘይት ሃብት የታደሉ አገሮችን ክፉኛ ነው የመታው። የአንጎላ ኤኮኖሚ ባለፈው 2008 ዓ.ም. 16 ከመቶ ዕድገት ሲያስመዘግብ ዘንድሮ ግን ወደ ሰባት ከመቶ እንደሚወርድ ይታመናል። ይህም ራሱ የተጋነነ ግምት ሊሆን የሚችል ነው። በአፍሪቃ ባለፉት ሶሥት አራትና አምሥት ዓመታት ያየነው ዕድገት በተለይም በውጭ ንግድ ላይ የተመሠረተ ዕድገት ነበር። ለንጽጽር ያህል በእሢያ እንዲያውም ይሄው ያለፉት ሃያ ዓመታት ሃቅ ነው።

በአጠቃላይ የበለጸጉት መንግሥታት በቀውሱ ሳቢያ ወደ አገር የሚያስገቡት ጥሬ ዕቃና የእርሻ ምርት መቀነስ የታዳጊውን ዓለም ንግድ ክፉኛ የሚጫን ነው የሚሆነው። የአንዳንዶቹ ምርቶች ዋጋ ባለፉት አሥር ወራት ገደማ 50 ከመቶ ያህል ቀንሷል። ይህ ደግሞ በተለይ በጥሬ ዕቃ ንግድ ላይ ጥገኛ ለሆኑት አገሮች አደገኛ ነገር ነው። አፍሪቃ ውስጥ ዛሬ ከሃምሣ አገሮች ኤኮኖሚ የ 25ቱ ከአንድ እስከ ሶሥት በሚሆኑ ምርቶች ላይ ጥገኛ ነው። እና የዋጋው ማቆልቆል በዚህ መጠን ከቀጠለ ሊያስከትል የሚችለውን ኤኮኖሚያዊና ማሕበራዊ አደጋ ማሰብ ብዙም አያዳግትም። የሕብረተሰብ ነውጽን ሊያፈነዳም የሚችል ነው።
ሶሥተኛው የአፍሪቃ ኤኮኖሚ ድቀት ምክንያት ከአውሮፓና ከአሜሪካ መዋዕለ-ነዋይ ሊያስገቡ የሚችሉ ባለሃብቶች የፊናንሱ ቀውስ ባስከተለው ስጋት ሳቢያ ንብረታቸውን ጠበቅ አድርገው መያዛቸው ነው። በዚሁ የተነሣ በተለይ ቀጥተኛው የመዋዕለ-ነዋይ አቅርቦት በሰፊው እየቀነሰ ይገኛል። ይህ ደግሞ ለአፍሪቃ ዕድገት ተጎታችነት ተጨማሪ ምክንያት በመሆን ላይ ነው። እናም ወዳለፉት ዓመታት ስኬታማ ዕርምጃ መመለሱ ቀላል የሚሆን አይመስልም።

አራተኛው ችግር ፈልሰው በውጭ የሚኖሩ አፍሪቃውያን ወገን ለመደገፍም ሆነ ለመነገድ ወደ አገር የሚልኩት ገንዘብ መቀነስ ነው። እነዚሁ በምዕራቡ ዓለም በአብዛኛው በቂ ማሕበራዊ ዋስትና በሌላቸው ሥራዎች የተሰማሩ ሲሆኑ የፊናንሱ ቀውስ ተጽዕኖ የመጀመሪያዎቹ ሰለቦችም ናቸው። የዚህ ግዙፍ ገንዘብ መቀነስ እጅግ ከባድ ተጽዕኖ ይኖረዋል። ጥናቶች እንደሚያመለክቱት በውጭ የሚኖሩ ሠራተኞች በዚህ መልክ ወደ ታዳጊዎቹ አገሮች የሚልኩት ገንዘብ በአማካይ 300 ሚሊያርድ ዶላር ገደማ ይጠጋል። ይህም ከዓለምአቀፉ ይፋ የልማት ዕርዳታ ሲነጻጸር በሶሥት ዕጅ የሚበልጥ ነው።

ለግንዛቤ ያህል ለምሳሌ በማዕከላዊው አሜሪካ ሆንዱራስን ወይም ጉዋቴማላን ብንመለከት በውጭ ከሚኖሩ፤ በተለይም በአሜሪካ ከሚሠሩ ተወላጆቻቸው የሚላከው ገንዘብ ከአርባ እስከ ሃምሣ በመቶውን የውጭ ምንዛሪ ገቢ ይሽፍናል። በኤኮኖሚያቸው ላይ በጣም ወሣኝነት አለው ማለት ነው። ይህ ሁሉ ተጠቃሎ ሲታይ ታዲያ የዕድገቱ ብዙ ሳይቆይ መልሶ ማንሰራራት አጠያያቂ ነው የሚሆነው። አፍሪቃንና ኤኮኖሚዋን በተመለከተ አንዳንድ የኤኮኖሚ ጠበብት የወደፊቱ ሂደት የደበዘዘ ሊሆን እንደሚችል ደጋግመው አስገንዝበዋል። ቢሆንም በሌላ በኩል የተሥፋ ጭላንጭል የሚታያቸውም አልታጡም። በጀርመን የላይፕዚግ ዩኒቨርሲቲ የአፍሪቃ ኤኮኖሚ አዋቂና ፕሮፌሰር የሆኑት ሄልሙት አሸም ከነዚሁ አንዱ ናቸው።

“በመዋዕለ-ነዋይ አቅርቦትና በንግድ ዘርፎች ጽኑ ዕርምጃ ብቻ አልነበረም የታየው። አፍሪቃ ውስጥ እስካለፈው 2008 ዓ.ም. ከመጀመሪያው የነዳጅ ዘይት ቀውስ ,ወዲህ የታዘብነው ረጅሙና ጠንካራው የዕድገት ዘመንም ታይቶ ነበር። ሶሥኛውና የመጨረሻው ነጥብ ደግሞ በፊናንሱ ዘርፍም በቀድሞዋ የቀውስ አገር በናይጄሪያ ሳይቀር የተረጋጋ ደረጃ ላይ ተደርሷል። ይህ ቀድሞ ልናልመው እንኳ የሚቻል አልነበረም”

እርግጥ አንድም የአፍሪቃ ባንክ በዓለምአቀፉ የፊናንስ ቀውስ ሳቢያ ተንኮታኩቶ አልወደቀም። በአሜሪካ የፊናንስ ገበያ ላይ ትርፍ ለማጋበስ ሲል የረባ ገንዘብ የከሰረም የለም። አፍሪቃ፤ ሄልሙት አሸ የደረሱበት ድምዳሜ እንደሚለው ቀውሱ ውስጥ የገባችው በጥሩ ዝግጅት ነው። እርግጥ ቀውሱ እስከቀጠለ ድረስ ክፍለ-ዓለሚቱ በችግሩ መጎዳቷ አይቀርም። ግን ዓለምዓቀፉ ኤኮኖሚ መልሶ ሲያገግም አፍሪቃም በፍጥነት ወዳለፉት ዓመታት የዕድገት መጠን ትመለሳለች የሚል ተሥፋ አለ። በዚህ በኩል ቻይናና ሕንድ ይበልጥ በአፍሪቃ ማተኮራቸው እየጨመረ መሄዱ የአፍሪቃ አገሮች በአውሮፓ ላይ ያላቸውን ጥገኝነት መቀነሱም አስተዋጽኦ ይኖረዋል። የላይፕዚጉ ፕሮፌሰር እንደሚሉት ቻይና ምንም እንኳ ራሷ የዕድገት ማዘቅዘቅ ቢገጥማትም አፍሪቃ ውስጥ በአብዛኞቹ ፕሮዤዎቿ እንደጸናች ነው። ይህም ተገቢው አመለካከት ነው።

“ከሕዝባዊት ቻይናና ከአብዛኞቹ ተሳታፊዎች፤ የቻይናን የግል ኤኮኖሚ ዘርፍ ጨምሮ ከሁሉም በኩል በአጠቃላይ ተሥፋ የተመላው የገበያ ዕይታ ነው ያለው”

የጀርመን ኩባንያዎች በአንጻሩ ወደ አፍሪቃ መዋዕለ-ነዋይ ማስገባቱን ዛሬም በአጠቃላይ አደገኛ አድርገው ነው የሚመለከቱት። ለነገሩ ግን በቀውስ ጊዜም ቢሆን የቴሌኮሙኒኬሺን ገበያን በመሳሰሉ በአንዳንድ ዘርፎች ያለ አስተማማኝ ዕድገትን መሠረት ለማድረግ በተቻለ ነበር። ለምሳሌ ከሳሃራ በስተደቡብ ያለውን የአፍሪቃ ክፍል ያህል በዓለም ላይ በየትኛውም አካባቢ አዳዲስ ሞባይል ስልኮችን መሸጡ በፍጥነት ሲያድግ የሚታይበት ቦታ የለም።

በአጠቃላይ ከትናንት በስቲያ በርሊን ላይ የቀረበው የበለጸጉት መንግሥታት የኤኮኖሚ ትብብርና ልማት ድርጅት ዓመታዊ ዘገባ መረጃዎች የሚጠቁሙት የአፍሪቃ አገሮች ሁኔታ ከረጅም ጊዜ አንጻር የከፋ እንደማይሆን ነው። እርግጥ ለሁሉም ነገር የዓለም ኤኮኖሚ ይዞታ ወሳኝነት ይኖረዋል። አፍሪቃ በአንድ በኩል በውጭው ገበያ፤ በሌላም በዓለምአቀፉ የልማት ዕርዳታ ላይ ጥገኛ ናት። የጥሬ ዕቃዎች ዋጋ በዓለም ገበዮች ላይ ማቆልቆል ብርቱ ጉዳት አለው። በወቅቱ በራሳቸው ቀውስ የተወጠሩት ምዕራባውያን አገሮች ኤኮኖሚያችውን ለማነቃቃትና የሥራ አጦችን መብዛት ገትቶ ለመያዝ ትግል በያዙበት ሰዓት ሰፊ የልማት ዕርዳታ መገኘቱ ያጠራጥራል።

እንደ ዕውነቱ ከሆነ የነገውን መተንበዩ ዛሬ በጣሙን የሚያዳግት ነገር ነው የሚሆነው። የበለጸጉት መንግሥታት የኤኮኖሚ ትብብርና ልማት ድርጅት አሁን የአፍሪቃን የኤኮኖሚ ዕድገት ለዚህ ዓመት በ 2,8 ከመቶ ሲያሰቀምጥ በቅርቡ ታንዛኒያ ውስጥ ተካሂዶ በነበረው የአፍሪቃና የዓለምአቀፉ ምንዛሪ ድርጅት የ IMF ጉባዔ ላይ ከዚህ ያነሰ ግምት ነበር የቀረበው። በያዝነው 2009 ዓ.ም. ጨርሶ ዕድገት ላይኖርም እንደሚችል መጠቀሱም የሚዘነጋ አይደለም። አሁን ደግሞ የዓለም ኤኮኖሚ ይዞታ በአጠቃላይ ተባባሰ እንጂ አልተሻሻለም።

MM/DW/RTR/AA