አፍሪቃና የኢንተርኔት አገልግሎት | ሳይንስ እና ኅብረተሰብ | DW | 27.06.2012
 1. Inhalt
 2. Navigation
 3. Weitere Inhalte
 4. Metanavigation
 5. Suche
 6. Choose from 30 Languages

ሳይንስ እና ኅብረተሰብ

አፍሪቃና የኢንተርኔት አገልግሎት

ድሮ ፤ ከመካከለኛው ዘመን አንስቶ እስከ 19ኛው ክፍለ ዘመን ከውቅያኖስ በኩል የሚመጣውን ሁሉ ፣ አፍሪቃውያን ለእኩይ ዓላማ እንጂ ለሚበጅ ነገር ይሆናል የሚል እምነት አልነበራቸውም። ለዚህ ደግሞ በቂ ምክንያት እንደነበራቸው ፣ የአፍሪቃውያን

የቅኝ ግዛት ዘመን ታሪክ በሚገባ ያስረዳል። አገር ለማሰስ፣ ለመውረርም ሆነ ቅኝ ግዛት ለማድረግ፤ ባሪያ ለመፈንገል፤ ሁሉም የመጡት ፤በባህር  ማለት፣  ውቅያኖስ እያቋረጡ እንደነበረ የታወቀ ነው። አሁን ግን በ 21ኛው ክፍለ ዘመን፣ በውቅያኖስ ወለል እልፍ አእላፍ ኪሎሜትር አቋርጦ ፣ ጥቁር ዘንዶ መስሎ ወደ አፍሪቃው ክፍለ ዓለም ፣ የብስ በመሻገር፤ ፍርሃትን ሳይሆን ድፍረትን ፤ ኀዘንን ሳይሆን  ደስታን ነው ለህዝብ ይዞ መምጣቱ የሚነገርለት።  የመገናኛ መረብ የሚያስዘረጋው ፣ ለኢንተርኔት የሚበጀው የሽቦ ገመድ ! ወድ ከሆነው ሳቴላይት ይልቅ፤ ይበልጥ የሚመረጠው፤ ሰፊና ጠንካራ አገልግሎት የሚያበረክተውም ይኸው ዘመናዊው ሽቦ ነው።

 እርግጥ የክፍለ ዓለሙ ጥቂት ፈላጭ ቆራጭ ገዥዎች በዚህ፣ በዘመኑ የመገናኛና  ፣ የዕውቀት ማስፋፊያ መሣሪያ ደስተኞች አይደሉም።  አፋኞች የመኖራቸውን ያህል፣ ለትምህርት ፤ ለእውቀት፤ ለኤኮኖሚ ዕድገትም ያለውን ሰፊ አስተዋጽዖ  በመገንዘብ፤ እንዲስፋፋ ሰፊ ዕድል በመስጠት ላይ የሚገኙ  የአፍሪቃ አገሮች በርካታ ናቸው። ኢትዮጵያ በዚህ ረገድ በፍጹም በአወንታዊ መልኩ የምትጠቀስ አገር አለመሆኗን ፤ የጋዜጠኞችን ተግባር የሚከታተሉ፤ የሰብአዊ መብትን ይዞታም የሚያጤኑ ክፍሎች የሚናገሩት ጉዳይ ነው።  የኢንተርኔት መረብ  ከሚያበረክታቸው ግልጋሎቶች አንዱ የሆነውን  የድምፅ አገልግሎት፣  በተመለከተ  አዲስ የመሰለ ደንብ  ወጥቷል።  ህጉ ፣  በኢንተርኔት  አማካኝነት ለንግድ በቴሌኮሙዩኒኬሽን አገልግሎት የሚጠቀሙትን  15 ዓመት ድረስ ለእሥር ሊዳርግ እንደሚችልም  ነው የተነገረው። እስካይፕና መሰል የቀጥታ የኢንተርኔት የድምፅ ግንኙነቶችን ፤ ደንቡ  አይፈቅድም የሚሉ ዘገባዎች ቀርበዋል። መንግሥት አልከለከልኩም ማለቱም ተጠቅሷል። ስለአደናጋሪው ሁኔታ፤ ዋና ጽ/ቤቱ በኒውዮርክ የሚገኘው  ዓለም አቀፉ የጋዜጠኞች ደኅንነት ተመልካች ድርጅት፣ የምሥራቅ አፍሪቃ አማካሪ ቶም ሮድስ፣ እንዲህ ማለታቸው የሚታወስ ነው።

አፍሪቃ ውስጥ ኢንተርኔት ፤ በአፋጣኝ በመስፋፋት ላይ ሲሆን ፤ ኢትዮጵያን የመሳሰሉ አንዳንድ አገሮች ግን፣ አያያዛቸው እንደ ህዝባቸው ብዛትም ሆነ  የአገሩ ቆዳ ስፋት ከቶውንም የሚመጥን አይደለም። ለዚህ እጅግ ጠቃሚ የህዝብ መገናኛ አውታር  ተገቢውን ቦታ አልሰጡትም።ለምሳሌ ያህል ፣ ወደ 41 ሚሊዮን ገደማ የሚጠጋ ህዝብ ባላት ጎረቤት ኬንያ፣ ከ 8,5 ሚሊዮን በላይ ህዝብ የኢንተርኔት ተጠቃሚ ሲሆን ፣ ታንዛንያ ፤ ከ 4 ሚልዮን ስድስት መቶ  ሺ በላይ፤ ዩጋንዳም፣ ከ 4 ሚልዮን በላይ የኢንተርኔት ተጠቃሚዎች አሏት።  ጋና ፤ ከ 2 ሚሊዮን በላይ ፤ 85 ሚሊዮን ገደማ ህዝብ እንዳላት በሚነግርላት  ኢትዮጵያ ደግሞ፣  ቁጥራቸው ፣ ከ600ሺ  እስከ 700 ሺ  ገደማ የሚገመት  ሰዎች ብቻ ናቸው በኢንተርኔት የሚገለገሉት።

ከአፍሪቃ ፤ በአጠቃላይ ሞሮኮ፤ ቱኒሲያ፤ ግብጽ፣  እንዲሁም ፤ ደቡብ አፍሪቃ ዝምባብዌና  ናይጀሪያም ፣ በኢንተርኔት የሚገለገሉ በርከት ያሉ ዜጎች  ነው ያሏቸው። ስለኢንተርኔት አስፈላጊነት ፤ እ ጎ አ ከ 1980ኛዎቹ ዓመታት መግቢያ ገደማ አንስቶ ከመወትወት ያልቦዘኑት የሳይንስና ሥነ ቴክኒክ የፈጠራ ጉዳዮች ምሁር ፕሮፌሰር ማሞ ሙጬ ፤ በተለይ ለከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ስላለው ጠቀሜታ እንዲህ ማለታቸው ይታወሳል።  

ኢንተርኔት ፤ ለእውቀት ማስተላላፊያ ፤ ለሐሳብ መለዋወጫ ፤ በአጭሩ ለእድገት ዐቢይ ረዳት መሣሪያ  ከመሆኑም ሌላ፤ ከዚህ ጋር ተያይዞ የሚያበረክተው ሰፊ ድርሻም አለ። ምዕራቡንና  ምሥራቁን አፍሪቃ ያገናኘው በባህር የሚያልፍ የሽቦ መስመር፣ ለክፍለ ዓለሙ ልማት  አዲስ በር ነው የከፈተው። ይህ ብቻ አይደለም።  የአፍሪቃ ጉዳይ በሰፊው፣ ለመጀመሪያ ጊዜ ፤ በአሁኑ ዘመን  ነው፣ ከድንበር ባሻገር ፣ ድምጹ፣ የሚገኝበት ሁኔታ፣ ተስፋውና ትጽቢቱ በራሱ ልጆች አንደበት እንዲሰማ ዕድሉን ያገኘው።  ከአፍሪቃ በየዕለቱ  በ ኢ-ሜይልና  በመሳሰለው ከሌላው ዓለም ጋር በጽሑፍ በድምፅና ምስል ሐሳብ የሚለዋወጡ በመቶ ሺ የሚቆጠሩ ናቸው። ርቀትና ሌላም መሰናክል አያጋጥመውም። አፍሪቃውያን ስለአፍሪቃ ራሳቸው ይናገራሉ።

ቀደም ባሉት ባለፉት ምዕተ ዓመታት፤ ስለአፍሪቃ እንዳሻቸው ሲጽፉ ፣ ሲተርኩ የኖሩት፤

ሚሲዮናውያን፤ መንገደኛ ተመራማሪዎችና  የቅኝ ግዛት ባላሥልጣናት ነበሩ።

Antennen und Funk Anlage Schüssel Sonnenaufgang Sonnenuntergang Mond


 

በአሁኑ ጊዜ፤ ከሰሀራ ምድረበዳ በስተደቡብ የሚገኙ  አፍሪቃውያን አገሮች ምሁራን፤ ነጋዴዎች፣ የፓርላማ አባላትና ተመራማሪዎች፤ በቀላሉ የሚግባቡ ሲሆን፤ በዓለም ዙሪያ የክፍለ-ዓለማቸውን ራእይ፣ ብሩኅ ተስፋ፤ችግሮችና መፍትኄዎች በመግለጽ ፤  በዓለም ዙሪያ አድማጭና ተመላካች የሚያገኙበትን ዕድል ነው የፈጠረላቸው።  ለምሳሌ ያህል ዩጋንዳዊቷን የኢንተርኔት ባለድረገጽ፤ ሮዝቤል ካጉማይርን እንውሰድ። Jason Russel የተባለው የፊልም መሪ የሠራው «ኮኒ 2012 »የተሰኘው ፊልሙ እንዳበገናት በመግለጽ ነው አብጠልጥላ የተቸችው። አንድ ለአገሩ እንግዳ ለሰው ባዳ የሆነ ሰው አፍሪቃ ውስጥ ግብቶ፤ የአፍሪቃን ልጆች እንደሚያድን ተደርጎ ፣ ልክ እንደድሮዎቹ ዕብሪተኞች ቅኝ ገዥዎች፤ አፍሪቃውያን ራሳቸውን የማይችሉ፣ ፣ አሜሪካውያን  ብቻ ልጆቻቸውን እንደሚያድኑላቸው በማስመሰል  የተሠራው ፊልም፣ ሮዝቤልን  በእጅጉ አናዷል። እ ጎ አ፣  በ 2006 ወደ ኮንጎ የፈረጠጠውን ፣  የ LRA ውን የጦር አበጋዝ ጆሰፍ ኮኒን መያዝም ሆነ ማጥፋት የሚችሉ አሜሪካውያን ብቻ እንደሆኑ፣ ዩጋንዳውያኑ ተዋጊዎች ጭራሽ መረሳታቸው ፣ ዩጋንዳም ውስጥ ጦርነት ያለ አስመስሎ ፊልሙን ማቅረቡ እንዳናደዳቸው ነው ሮዝቤል ካጉማየር የገለጹት።

Vernetzung Internet Weltweit

ኢንተርኔት ፣ በአፍሪቃ ሐሳብን በነጻ ለማንሸራሸር፤ ትምህርትን በከፍተኛ ደረጃ ለማስፋፋት፣ የሰብአዊ መብት ጥበቃንና ዴሞክራሲን ለማጠናከር አገልግሎት መስጠት ይችላል። ኢንተርኔት በመሠረቱ ዕውቀትን ለማዳበር ፣ መረጃዎችን ለመለዋወጥ ሰፊ አስተዋጽዖ ማድረግ  የሚችል  እጅግ  ዘመናዊ የሥነ ቴክኒክ ውጤት ሲሆን፤ አጭበርባሪዎች፤ ጥላቻ አስፋፊዎችና የመሳሰሉትም እንደሚገለገሉበት የሚያጠራጥር አይደለም።  ይሁን እንጂ፣  ገና በየዘርፉ ሁለንተናዊ ዕድገት የሚያሻው አፍሪቃ፤ ይህን ዐቢይ የመገናኛ መሣሪያ በአግባቡ ሊጠቀምበት እንደሚገባ ነው የሚታሰበው።  

ተክሌ የኋላ

አርያም ተክሌ

Audios and videos on the topic

 • ቀን 27.06.2012
 • አዘጋጅ
 • ያትሙ ገፁን ያትሙ
 • Permalink https://p.dw.com/p/15MR6
 • ቀን 27.06.2012
 • አዘጋጅ
 • ያትሙ ገፁን ያትሙ
 • Permalink https://p.dw.com/p/15MR6