አፍሪቃና የኡንክታድ ዘገባ | ኤኮኖሚ | DW | 25.03.2004
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ኤኮኖሚ

አፍሪቃና የኡንክታድ ዘገባ

የተባ መ የንግድና የልማት ጉባኤ(ኡንክታድ) ባቀረበው አዲስ ዘገባ መሠረት፣ የአፍሪቃው አህጉር በዓለም-አቀፉ የውጭ ንግድ ድርሻ ረገድ እያደር በመጠርቃት ፈንታ ጭራሹን ወደ ኋላ እያሸረተተ ነው የተገኘው። ከቅርብ ጊዜ በፊት ብሩክሴል ውስጥ በይፋ የቀረበው ይኸው የኡንክታድ ጥናት እንደሚለው ከሆነ፣ ብዙ አፍሪቃውያት ሀገሮች ከውጭ ንግድ የሚያገኙት ገቢ አለቅጥ እያነሰ የተገኘበት ሁኔታ ያስከተለባቸው የንግዱ ወጥመድ ወደ ድህነቱ ወጥመድ ነው የመራቸው። አለቅ

ጥ ያጋደለው የንግድ ግንኙነቱ ሁኔታ እና የንግድ ድርሻው እጦት ለአህጉሩ የእዳ ድርርብ ዋነኛው ምክንያት ሆኖ ነው የሚታየው--እንክታድ እንደሚለው


በዚሁ በተባ መ የንግድና የልማት ጉባኤ(ኡንታድ) ጥናት መሠረት፣ የአፍሪቃ ሀገሮች ወጭ-ንግድ ነጥብ-፮ በመቶ ብቻ ነበር ዓመታዊ ዕድገት ያሳየው። የኡንክታድ ጥናት የመላውን አዳጊ ሀገሮች ዓመታዊ የኤክስፖርት ዕድገት ፫-ነጥብ-፫ በመቶ፣ የእስያን ደግሞ ፭ በመቶ ነው ያደረገው። አፍሪቃ ከጠቅላላው ወጭ-ንግድ ያላት ድርሻ ከ፮-ነጥብ-፫ ወደ ፪-ነጥብ-፭ የተቀነሰ ሆኖ ነው የተገኘው። ከዚህም የተነሳ፣ አፍሪቃ በዋጋው ውዥቀት ላይ ካለባት ጥገኝነት እንድትላቀቅና የረዥም ጊዜ መዋቅራዊ ማስተካከያ መርሐግብር እንዲዘረጋላት የሚያደርገው ርምጃ ቅድሚያን ማግኘት እንደሚገባው ጥናቱ ያስገነዝባል።

የኡንክታድ ጥናት እንደሚለው፣ አፍሪቃ የምትገኝበትን የንግድ ሁኔታ በተለይ የሚያቃውሰው፣ ሐብታሞቹ እንዱስትሪ-ሀገሮች የሚከታተሉት የንግድ ክለላው ርምጃ ነው። በእንዱስትሪ-ሀገሮች ውስጥ ለግብርናው ዘርፍ የሚሰጠው የድጎማው ክፍያ፣ እንዲሁም የጥጥ፣ የለውዝና የስኳር ዋጋ ድክመት በተለይ ድሆቹን አፍሪቃውያን ገበሬዎች ነው የሚጎዳው--የኡንክታድ ዘገባ እንደሚያስገነዝበው።

በእንዱስትሪ-ሀገሮች ውስጥ ለጥጥ አምራቾች የሚሰጠው የድጎማው ክፍያ ለምሳሌ በ፲፱፻፺፬ አፍሪቃውያኑ ጥጥ-አልሚዎች በ፫፻ ሚሊዮን ዩኤስ-ዶላር የሚታሰብ የገቢ ጉድለት እንዲደርስባቸው አድርጓል--የኡንክታድ ጥናት እንዲሚያስገነዝበው። በዚሁ ጥናት መሠረት፣ ይኸው የገበያ ጉድለት ፪፻፴ ሚሊዮን ዶላር ከሚደርሰው፣ በምዕራብና በማዕከላይ አፍሪቃ ላሉት ለዘጠኙ ጥጥ-ላኪ ሀገሮች ጠቀሜታ ከታወጀው የእዳ ምኅረት የበለጠ ነው።

ያው የተባ መ የንግድና የል’ማት ጉባኤ(ኡንክታድ) እንደሚለው ከሆነ፣ የአፍሪቃው አህጉር በሚደርስበት በዚሁ መዋቅራዊ መሰናክል በመጠቀም ትርፉን በተለይ የሚያካብቱት፣ ታላላቆቹ ዓለምአቀፍ ኩባንያዎች ናቸው። ዝቅተኛው የጥሬ አላባዎች ዋጋ ለእነዚሁ ታላላቅ ዓለምአቀፍ ኩባንያዎች እና ነጋዴዎች ግዙፉን ትርፍ ነው ያስገኘላቸው ይላል የኡንክታድ ዘገባ። ይኸው አለቅጥ ያጋደለ የንግድ ሁኔታ ድሆቹን አፍሪቃውያን ገበሬዎች ይብሱን የሚያዳክምና የመንግሥትንም ገቢ የሚያመናምን ነው የሚሆነው፥፥በዚህ ረገድ በተለይ የቡናው ገበያ ነው ዓይነተኛ ምሳሌ የሚሆነው። በዚህም መሠረት፣ በ፸ ሚሊያርድ ዶላር ከሚታሰበው የቡና ሽያጭ፣ ለቡና አምራቾቹ የሚዳረሰው ፭ነጥብ፭ ሚሊያርድ ዶላር ብቻ ነው። ከአሥር ዓመታት በፊት ግን የቡና አምራቾቹ ድርሻ አንድ-ሦሥተኛ የደረሰ ነበር ይላል የዓለሙ ድርጅት ዘገባ።

አፍሪቃውያኑ አምራቾች ከባድ የገቢ ጉድለት የሚደርስባቸው በውጭው ገበያ ላይ በሚቀርቡት የአሣ፣ የአበባና የአትክልት ምርቶችም ረገድም ነው የሚለው የተባ መ ዘገባ፣ የአጭር ጊዜውን የዋጋ ውዥቀትና የገቢ ጉድለት ለማካካስ፣ አንድ ደጋፊ የፊናንስ አውታር መፈጠር እንዳለበት ያስገነዝባል።

በየጊዜው እንደሚመለከተው፣ አፍሪቃውያንና ሌሎቹም አዳጊ ሀገሮች ለባሕር ማዶው ንግድ ብቻ ቀዳሚውን ትኩረት በመስጠት ፈንታ እርስበርሱን አካባቢያዊ ንግድና ትብብርም ለማነቃቃት ነው መጣር ያለባቸው። በአፍሪቃው አህጉር አሁን በያለበት ጅምሩ አለ፣ ይኸው ጅምር ነው መጠናከር ያለበት። በዚህ ረገድ አሁን አንድ አዲስ ምሳሌ የሚሆነን፣ ነባሩ የምሥራቅ አፍሪቃ ማኅበር ያካባቢውን ኤኮኖሚያዊ ዕድገት ለማነቃቃት እንደሚያስችል የሚታመንበት አንድ የጉምሩክ ኅብረት ለመፍጠር የደረሰው ስምምነት ነው። ሦሥቱ ማኅበርተኞች ኬንያ፣ ታንዛኒያና ኡጋንዳ በሰሜን ታንዛኒያ ከተማ አሩሻ ለጉምሩኩ ኅብረት የተፈራረሙት ሠነድ በመጭው ሐምሌ የሚፀና እንደሚሆን ነው የሚጠበቀው።

በ፫ቱ ሀገሮች መካከል የሚሸጋገሩት ሸቀጦች እንዴት መቀረጥ እንዳለባቸው የሚደቀነው ጥያቄ ፫ቱን ሀገሮች ለረዥም ጊዜ ሲያከራክር ነበር የቆየው። የሠነዱ ፍርርም ካሁን ቀደም አራት ጊዜ እንዲተጓጎል ያደረገው፣ በተለይም ታንዛኒያና ኡጋንዳ በአካባቢው የኤኮኖሚ አውራ ሆና ከምትታየው ኬንያ ጋር የገበያ ውድድር ለማድረግ አቅም እንደሌላቸው የሚያጎሉት ክርክር ነበር። ይኸውም፣ በምሥራቅ አፍሪቃው ማኅበር ዙሪያ በሚተላለፉት ሸቀጦች ላይ የጋራው ጉምሩክ ከተደነገገ፣ የንግዱ ሚዛን አለቅጥ የሚቃወስባቸው እንደንደሚሆን ታንዛኒያና ኡጋንዳ ከባድ ሥጋት ሲሰማቸው ነበር የቆዩት። በዚህም ምክንያት፣ አሁን የተፈረመው ሠነድ እንደሚያዋውለው፣ በምሥራቅ አፍሪቃው ማኅበር ዙሪያ ለገበያ የሚቀርቡት የታንዛኒያና የኡጋንዳ ዕቃዎች ከጉምሩኩ ቀረጥ ነፃ ሲሆኑ፣ ከኬንያ የሚላኩት ሸቀጦች ደግሞ እስከ አምስት ዓመታት ለሚዘልቅ ጊዜ ቀረጡ ይጫንባቸዋል።

በስምምነቱ መሠረት፣ ከጉምሩክ ኅብረቱ ውጭ ከሆኑት ሀገሮች የሚላኩት የገበያ እቃዎች በአንድ የጋራ ጉምሩክ ሥርዓት ሥር የሚቀረጡ ሲሆን፣ ይኸው የጋራ ጉምሩክ ሥርዓት ሸቀጦቹን በ፫ ይመድባቸዋል፥ ይኸውም፥ ጥሬ-አላባዎች በማኅበረሰቡ ገበያዎች ላይ ያለቀረጥ እንዲቀርቡ ሲፈቀድ፣ በከፊል የተደራጁትና በከፊል የተፈበረኩት ዕቃዎች ደግሞ ፲ በመቶ ቀረጥ ይጫንባቸዋል። በምልዓት የተፈበረኩት ዕቃዎች ፳፭ በመቶ ቀረጥ እንዲከፈልባቸው ስምምነቱ ያዋውላል።

አንድ የጉምሩክ ኅብረት ሰፊ የገበያ አድማስ እንደሚፈጥር፣ በነጋዴዎች መካከል ውድድርን እንደሚያጠናክር እና የምርትንም አያያዝ እንደሚያቀላጥፍ ይታመንበታል። ባሁኑ ጊዜ፣ የምሥራቅ አፍሪቃው ማኅበረሰብ ለዘጠና ሚሊዮን ያህል ሕዝብ ነው ገበያ የሚሰጠው። የማኅበሩ ጽ/ቤት በሚሰጠው መረጃ መሠረት፣ የማኅበረሰቡ ጠቅላላ ብሔራዊ ውጤት ተዳምሮ ሲታይ፣ በ፳፭ ሚሊያርድ ዶላር ነው የሚታሰበው።

ታዛቢዎች እንደሚሉት፣ ታንዛኒያና ኡጋንዳ ውስጥ የኬንያን ሸቀጦች መቅረጥ ብቻውን በቂ አይደለም፣ በዚያው በምሥራቅ አፍሪቃው አካባቢ ታንዛኒያና ኡጋንዳ እኩል ሚና የሚይዙ፣ ባለሐብቶችንም ለመሳብ ይበልጥ ውድድር የሚፈጥሩ እንዲሆኑ ያስፈልጋል። ሦሥቱን ሀገሮች የሚያስተሳስረው የጉምሩኩ ኅብረት የኋላ ኋላ የጋራውን ገበያ፣ የጋራውን ሸርፍ እና የፖለቲካውን ፈደራሲዮን ለመፍጠር የሚያስችል ሆኖ ነው የሚታየው።

በኬንያውያኑ አመለካከት መሠረት፣ ወደ መጨረሻው ግብ ለመቃረብ ይቻል ዘንድ፣ በማኅበረሰቡ አባል-ሀገሮች መካከል ሕዝቡ የነፃ ዝውውር መብት ማግኘት ይኖርበታል። ሦሥቱ ሀገሮች ዜጎቻቸው በአካባቢው በነፃ ሊዘዋወሩ እንዲችሉ ከሁለት ዓመታት በፊት አንድ ስምምነት ቢፈራረሙም፣ ያው የዝውውር ነፃነት በተግባር ተተርጉሞ አያውቅም።

የምሥራቅ አፍሪቃው ማኅበረሰብ በ፲፱፻፷ ነበር በመጀመሪያ የተመሠረተው፣ ግን በልይዩ ምክንያቶች ወዲያው ከሁለት ዓመታት በኋላ ፈረሰ። ከእነዚሁ ምክንያቶች አንዱ፣ ከበርቴአዊውንና ሶሻሊስቱን የኤኮኖሚ ሥርዓት ያመላከተው ክርክር ነበር። የሆነ ሆኖ፣ በ፲፱፻፺፩ እንደገና ለመመሥረት የበቃው ያው የምሥራቅ አፍሪቃው ማኅበረሕዝብ፣ የኋላ ኋላ በአባላቱ ሀገሮች መካከል ኤኮኖሚያዊውና ፖለቲካዊው ኅብረት የሚፈጠርበትን የውኅደቱን ጉልላት ነው ግብ የሚያደርገው።