አፍሪቃና የነጻ ንግድ ራዕይዋ | ኤኮኖሚ | DW | 15.06.2011
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ኤኮኖሚ

አፍሪቃና የነጻ ንግድ ራዕይዋ

ጆሃንስበርግ ላይ የተሰበሰቡ የአፍሪቃ መንግሥታት መሪዎች ባለፈው ዕሑድ የአህጉሪቱን ግዙፍ ነጻ የገበያ ክልል ለመፍጠር ተስማምተዋል።

default

26 አገሮችን እንዲያዳርስ የታለመለት ግዙፍ የነጻ ገበያ ክልል ከኬፕ እስከ ካይሮ፤ ማለት አፍሪቃን ከደቡብ እስከ ሰሜን የሚያቋርጥ ሲሆን ዕውን ቢሆን ጥቅሙ ለ 700 ሚሊዮን ሕዝብ የሚተርፍ ነው። የደቡብ አፍሪቃ ፕሬዚደንት ጄኮብ ዙማ በመክፈቻ ንግግራቸው የተሰበሰብነው አንድ-ወጥ የኤኮኖሚ ጠቀሜታ ያለው አህጉራዊ ገበያ ለመፍጠር በአፍሪቃ መስራች አባቶች ፊት ያለብንን የጋራ ሃላፊነት በመገንዘብ ነው ብለዋል። ትልቅ አነጋገር ነው። ግን ይህን ራዕይ ገቢር ማድረጉ በቀላሉ የሚሳካ መሆኑ በጣሙን ያጠራጥራል። አፍሪቃ ዛሬ ካለችበት ኋላ ቀር የልማት ሁኔታና የፖለቲካ ይዞታ አንጻር መንገዱ በእርግጥም ውጣ-ውረድ የሚበዛው ኮረኮንች ነው። ታዲያ ሃሣቡ እንዲያው ባዶ ተሥፋ፤ ወይስ ተጨባጭ ሃቅ! በኬፕታውን የጀርመን የንግድ ጋዜጣ የሃንደልስ-ብላት ወኪል ቮልዕጋንግ ድሬክስለር ጉዳዩን ለማሳካት በቅድሚያ መሠረታዊ ችግሮች መወገድ እንዳለባቸው ነው የሚያስገነዝቡት።

“ነጻ ገበያ ማስፈኑ ቢሳካ ግሩምና ጠቃሚም በሆነ ነበር። አፍሪቃ መዋዕለ-ነዋይ ለሚያደርጉ ባለገንዘቦች አንድ ሚሊያርድ ሕዝብ፣ አንድ ሚሊያርድ ደምበኛ ያላት ናት። ግን እነዚህ አንድ ሚሊያርድ ሰዎች የሚኖሩት የተለያየ የሕግ ይዞታ፣ የተለያየ የመዋዕለ-ነዋይ ሁኔታ፤ እንዲሁም የተለያየ ምንዛሪ ባላቸው 53 የተለያዩ አገሮች ውስጥ ነው። ይህም ባለሃብቶች በአፍሪቃ መዋዕለ-ነዋይ የሚያደርጉበትን ሁኔታ በጣሙን ያከብደዋል። ችግሩ ከታወቀው የአፍሪቃ ቢሮክራሲ ጋር ተዳምሮ ብዙ ግፊት ያለበት ሲሆን በያንዳንዱ አገር ዝርዝሩ የበዛ አስቸጋሪ የመዋዕለ-ነዋይ ደምብም አለ። ታዲያ ይህን ችግር በነጻ የገበያ ክልል ማጣጣምና ማለዘብ ቢቻል ግሩም በሆነ ነበር። እርግጥ ጉዳዩ ያልታወቀ ነገር አይደለም። ነጻ ገበያውን ለማስፈን ገና በ 2001 ዓ.ም. በደቡባዊውና በምዕራባዊው አፍሪቃ ክልሎች መካከል ጥረት ተደርጎ ነበር። ከዚያም በ 2009 ኡጋንዳ ውስጥ የሶሥቱ የንግድ ክልሎች የመሪዎች ጉባዔ ተካሂዷል። ግን ፖሊሲን በማስተካከሉ በኩል፤ ለምሳሌ ቀረጥን በማጣጣሙና የድንበር ተሻጋሪ ድምቦችን በማለዘቡ ረገድ የታየው ዕርምጃ ጥቂት ነው። ሃሣቡ ግሩም፤ ገቢር ማድረጉ ግን የሚያሳዝን ሆኖ ውሱን ሆኖ ነው የቀረው”

የደቡብና ምሥራቅ አፍሪቃ የጋራ ገበያን ኮሜሣን፣ የምሥራቅ አፍሪቃን AEC-ና የደቡባዊውን አፍሪቃ የልማት ማሕበረሰብ SADC-ን የሚጠቀልለው የ 26 ሃገራት አጠቃላይ ብሄራዊ ምርት በሁለት ዓመታት ውስጥ አንድ ትሪሊየን ዶላር ሊደርስ እንደሚችል ነው የሚነገረው። ይሁንና አፍሪቃን በንግድ በማስተሳሰሩ ላይ በተለይም በያገሩ ጎልቶ የሚታየው የመዋቅራዊ ይዞታ ድክመት ትልቁ ችግር ሆኖ ይገኛል። ይህን እንዴት ማስወገድ ይቻላል፤ የደቡብ አፍሪቃስ ሚና ምንድነው ሊሆን የሚችለው?

“በመሠረቱ ከሁሉም በላይ የሚጎለው እንደተጠቀሰው መዋቅራዊው ይዞታ ነው። የየሃገራቱ የኤኮኖሚ አቅም መለያየትም ሁኔታውን አያቀለውም። ደቡብ አፍሪቃ ለምሳሌ ከሌሎቹ ርቃ የተራመደች ናት። አርባ በመቶውን የአፍሪቃን አጠቃላይ ብሄራዊ ምርት ድርሻ ትይዛለች። ይህ ደግሞ በአርግጥም ልዕልና የሚሰጣት ነው። አሁን በወቅቱ በአውሮፓ እንደሚታየው ትንሿ ግሪክ በዚህ መሰሉ ልዩነት የተነሣ ከባድ ፈተና ላይ መሆኗን እናያለን። በቀላሉ ለፉክክር ብቁ ለመሆን አልቻለችም። ይህ የሚሆነው ለዚያውም ጠንካራና ስር የሰደደ ነጻ የገበያ ክልል ባለባት በአውሮፓ ነው”

ቮልፍጋንግ ድሬክስለር እንደሚሉት መዋቅራዊው ይዞታ እርግጥ ለንግዱ ትስስር ቁልፍ ጉዳይ ሆኖ ይቀጥላል።

“መዋቅርን በተመለከተ እርግጥ ነው ለንግድ መንገዶችና የባቡር ሃዲዶች መስፋታቸው ብቻ አይደለም የሚፈለገው። ለዚያውም ያሳዝናል የታለና! ንግድን፣ ኮምፒዩተሮችን ወይም ኢንዱስትሪን ለማንቀሳቀስ ለምሳሌ ኤሌክትሪክም ያስፈልጋል። ግን አስበው፤ በአፍሪቃ ከታላላቆቹ ባለኤኮኖሚዎች አንዷ የሆነችው ናይጄሪያ በዓመት የምትፈጀው የኤሌክትሪክ ሃይል ከአንድ ትንሽ የጀርመን ከተማ ቢነጻጸር እንኳ ያነሰ ነው። ናይጄሪያ ለ 150 ሚሊዮን ሕዝብ የምታመርተው መሆኑ ነው። ይሄ ደግሞ በአፍሪቃ ነጻ የገበያ ክልል ለመፍጠር በሚደረገው ጥረት ቀላል ፈተና አይሆንም”

በሌላ በኩል አንዳንድ የዓለም ባንክ ወይም የዓለምአቀፉ ምንዛሪ ተቋም ባለሙያዎች በሚቀጥሉት ዓመታት በዓለም ላይ የተፋጠነ ዕድገት ከሚያደርጉት አሥር ሃገራት መካከል ስድሥቱ የአፍሪቃ እንደሚሆኑ በየጊዜው ይናገራሉ። ግን ያለ ፖለቲካ መሻሻል የሚደረግ የኤኮኖሚ ዕድገት ፍሬያማ ሊሆን መቻሉ ሲበዛ የሚያጠያይቅ ሲሆን ቮልፍጋንግ ድሬክስለር እንደሚሉት በዚህ ረገድ ተሃድሶ መኖሩ ቁልፍ ቅድመ-ግዴታ ነው።

“ቁስሉን በትክክል ነው ያመለከትከው። ችግሩ የፖለቲካ ስርዓታቱ ጊዜ ያለፈባቸው መሆናቸው ነው። እና ለውጦችን እንዳስፈላጊነታቸው ገቢር አለማድረጉ እንቅፋት ሆኖ ይቀጥላል። መሪዎቹ በአብዛኛው በሙስና የተዘፈቁና አምባገነን ሲሆኑ ትንሽ የልማት ዕርዳታ እስካገኙ ድረስ ያን ያህል ግድ የላቸውም። ታዲያ ቅድመ-ግዴታ ስለሚበዛ የመዋዕለ-ነዋይ ባለቤቶች ወዳገር በሰፊው አይገቡም። ይህን ሁሉ ማስተካከሉ እንግዲህ እነዚህ ገዢዎች የማይፈቅዱት ነገር ነው። ተሃድሶንም ሆነ የግሉን የኤኮኖሚ ዘርፍ መክፈቱን ግፊትን በመፍራት አይፈልጉትም”

የአፍሪቃን የኤኮኖሚ ዕድገት አስመልክተው የሚቀርቡት አሃዞች ደግሞ ብዙ ማጠያየቃቸው አልቀረም።

“አንድ ነገር ልጨምር። ስድሥት በኤኮኖሚ በፍጥነት የሚያድጉ አገሮች የሚለውን አሃዝ በጥንቃቄ መመልከቱ ይመረጣል። እንደምታውቀው የአፍሪቃ ልማት በዝቅተኛ ደረጃ የተወሰነ ነው። አፍሪቃ ዛሬ በዓለም ኤኮኖሚና የውጭ ንግድ ላይ ያላትን ዝቅተኛ ድርሻ ማስተዋል ያስፈልጋል። ምሥራቅ እሲያ ከ 1980 ወዲህ ከ 3,3 በመቶ ተነስታ ዛሬ የዓለም ንግድ ድርሻዋን ወደ 14 በመቶ ለማሳደግ ችላለች። አፍሪቃ በአንጻሩ አሁንም በ 1,5 ከመቶ እንደተወሰነች ነው። እንግዲህ 53 አገሮች በ 1,5 ከመቶ የተወሰኑ ከሆኑ ይሄው ከ 1980 እስከ 85 ከነበረው ያነሰ መሆኑ ነው። እናም አሁን የኤኮኖሚ ዕድገት አሃዝ በሚጠቀስበት ጊዜ ከምን ጋር እየተነጻጸረ እንደሚቀርብ በትክክል ማስተዋል ይኖርብናል። በአንድ አገር በታየ ትልቅ የመዋዕለ-ነዋይ ፍሰት ለምሳሌ ለአሉሚኒየም ማቅለጥ ተግባር በሞዛምቢክ፤ ይህ አፍሪቃ የሚያስፈልጋትን ልማት በትክክል የሚያንቀባርቅ ሊሆን አይችልም”

የአፍሪቃን የአካባቢ የንግድ ድርጅቶች በአንድ ማስተሳሰሩ ለአፍሪቃ ኤኮኖሚ እንደሚበጅና ውስጣዊውን ንግድ ለማዳብር እንደሚረዳም አንድና ሁለት የለውም። ግን በአጭር ጊዜ የሚሳካ እንደማይሆን ግልጽ ነው። ከዚህ በተረፈ በየጊዜው የሚታየው የአውሮፓን ወይም የአውሮፓን ሕብረት ፈለግ የተከተለ የለውጥ ዘይቤ ተስማሚ መሆን አለመሆኑ ማጠያየቁ አልቀረም። በሌላ አነጋገር አውሮፓን መኮረጁ መጥቀሙ ያጠራጥራል።

“ትክክል ነው። ሌላ ቦታ ያለውን የመገልበጥ ጠንካራ ልምድ አለ። የአካባቢን ተጨባጭ ሁኔታ ማገናዘቡ ተገቢው ትኩረት አልተሰጠውም። አፍሪቃ በአውሮፓም ሆነ በእሢያ ሌላ ባሕልና ልምድ መኖሩን በማጤን ከራሷ ተጨባጭ ሁኔታ የሚስማማ ፈለግን መከተል ይኖርባታል። ይሄ ነው የመፍትሄው ምስጢር! ሃብታሙ ይበልጥ ሃብታም፤ ድሃውም ይበልጥ ድሃ እየሆነ የሚሄድበትን ሁኔታ ማስወገድ የሚቻለው እንዲህ ነው። የድሃው መብዛት አንዳንድ አገሮችን ብቻ የሚመለከት፤ በአንዳንድ አገሮች ብቻ የተወሰነ ነገር አይደለም። እንደ ምሳሌ ለመጥቀስ በአይቮሪ ኮስት ከ 10 እስከ 15 ዓመታት በፊት ከሁለት ዶላር በታች የቀን ገቢ ያላቸው ዜጎች 19/20 በመቶ ቢሆኑ ነበር። ዛሬ ከድህነት መስፈርት በታች የሚኖሩት 50 በመቶ ደርሰዋል። ይህ የሚያሳየው የሚያሳዝን ሆኖ ድህነት በአፍሪቃ እየጨመረ መሆኑን፤ ጥቂቶችም እየካበቱ መቀጠላቸውን ነው። ሁኔታው ለዘላቂ ልማት መሠረት አይሆንም”

አንድ-ወጥ የአፍሪቃ ነጻ ገበያን ገሃድ ለማድረግ የተነሳሱት የአህጉሪቱ መንግሥታት ሃሣቡ በእርግጥ ዕውን እንዲሆን ከፈለጉ ሁል-ገብ የፖለቲካ፣ የኤኮኖሚና ማሕበራዊ ለውጥ፤ ተሃድሶ ለማድረግ ቁርጠኛ መሆናቸው ግድ ነው። አለበለዚያ የጆሃንስበርጉ ስምምነት ከወረቀት የሚያልፍ ሊሆን አይችልም።

መሥፍን መኮንን

አርያም ተክሌ

Audios and videos on the topic