1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

አፍሪቃና አልደረስበት ያለው የልማት ግቧ

ረቡዕ፣ የካቲት 7 1999

በአፍሪቃ የልማት ሂደት ላይ ታላቅ ትኩረት ተሰጥቶት የሚገኘው በክፍለ-ዓለሚቱ ድህነትን ለመቀነስ የተባበሩት መንግሥታትን የሚሌኒየም ዕቅድ ከግቡ የማድረሱ ጉዳይ ነው።

https://p.dw.com/p/E0dA

እርግጥ በዚህ አቅጣጫ ብዙ ጥረት መደረጉ፤ አልፎ አልፎም ዕርምጃ መታየቱ አይቅር እንጂ አብዛኞቹ የአፍሪቃ መንግሥታት ዕቅዱን ገቢር ለማድረግ እስከ 2015 ዓ.ም. ድረስ በተጣለው የጊዜ ገደብ ተፈላጊውን ስኬት ማግኘታቸው አሁንም አጠያያቂ ሆኖ እንደቀጠለ ነው። ምናልባት ታንዛኒያን የመሳሰሉ አንዳንድ አገሮች ዕቅዱን፤ ለዚያውም በከፊል ከግብ ማድረስ ቢችሉ ነው። በቅርቡ አዲስ አበባ ላይ ተሰብስበው የነበሩት የአፍሪቃ ሕብረት መንግሥታት መሪዎች ዘመኑ በክፍለ-ዓለሚቱ ላይ የጣለውን ብርቱ የልማት ፈተና ለመቋቋም የዕውቀትን መዳበርና ራስ መቻልን አስለላጊ መሣሪያ አድርገው መጠቆማቸው አልቀረም። ጥያቄው እንዴት? የሚል ይሆናል።

አፍሪቃን ወድቃ ከምትገኝበት የኤኮኖሚ አዘቅት ለማውጣትና የልማት ዕጦትን ለማስወገድ ድህነትንና ኋላ ቀርነትን፤ ረሃብና በሽታን ያለፈ ታሪክ ማድረግ ግድ ነው። የተባበሩት መንግሥታት ለዚሁ ዓላማ በ 2000 ዓ.ም. የሚሌኒየም የልማት ዕቅድ አውጥተው ተግባራዊ ለማድረግ ቢጥሩም ባለፉት ሰባት ዓመታት ውስጥ የታየው ዕርምጃ ውጥኑ ከግቡ ለመድረሱ ብዙም ተሥፋ የሚሰጥ አይደለም። በከፊል እንኳ ስኬታማ ዕርምጃ ይዘዋል ሊባሉ የሚችሉት የአፍሪቃ አገሮች ጥቂቶች ናቸው።

በሚሌኒየሙ ዕቅድ መሠረት፤ ድህነትን በግማሽ መቀነስ፣ መሠረታዊ ትምሕርት ለሁሉ እንዲዳረስ ማድረግ፤ የሕጻናትን በአጭር ዕድሜ መቀጨት መግታትና የጾታ እኩልነትን ማስፈን፤ HIV-AIDS-ን መቋቋምና ተፈጥሮን መንከባከብን የመሳሰሉት ዋነኞቹ ግቦች ናቸው። ዕቅዱ ሰፊ ነው፤ በውል የተሰላ ዕርምጃንም ይጠይቃል።

የችግሩ መንስዔ ብዙ ገጽታ ያለው ሲሆን በአፍሪቃ በተለይ የተፈጥሮ ጸጋን ለልማት እንዲበጅ አድርጎ በአግባብ መጠቀም አለመቻል፣ ሙስናና የፍትሃዊ አስተዳደር መጓደል ብርቱ የዕድገት መሰናክል ሆነው ነው የሚገኙት። አፍሪቃ ከተመጽዋችነት ተላቃ ወደ አዲስ ምዕራፍ እንድትሸጋገር አስፈላጊውን ሁኔታ ለማመቻቸት አልተቻለም። ለዚህም ነበር የአፍሪቃ ሕብረት ኮሚሢዮን ሊቀ-መንበር አልፋ ኦማር ኮናሬ ከተመጽዋችነት ስንብት ያደረገች፤ ለራሷ ሃላፊነት የምትወስድና ከጥገኝነት የተላቀቀች አፍሪቃ ዕውን ትሆን ዘንድ ጥሪ ያደረጉት።

“ለራሷ ሃላፊነት የምትወስድ አፍሪቃ በልማት አቅጣጫ ልታመራ ትችላለች። አፍሪቃ ብዙ የተፈጥሮ ጸጋ ያላት ሃብታም ክፍለ-ዓለም ናት። በደቡብ አፍሪቃ አፓርታይድን እንደታገልነው ሁሉ በዚያው ስሜት፣ ቁርጠኝነትና ትብብር አሁን ደግሞ ራስን ለመቻል መታገል ይኖርብናል። ይህ ከሆነ ከልማት ግባችን እንደርሳለን” ነበር ያሉት አልፋ ኦማር ኮናሬ! ዕውነት አላቸው። ጥያቄው ይህ ቁርጠኝነትና የተግባር አንድነት ይገኛል ወይ ነው።

ለነገሩ አፍሪቃ መሠረታዊ ማሕበራዊና ፖለቲካዊ ሁኔታዎች ቢሟሉ ለዕድገት ተሥፋ የሚሰጡ ብዙ ምክንያቶች አሏት። ክፍለ-ዓለሚቱ ከነዳጅ ዘይት አንስቶ እስከተለያዩ ንጥረ-ነገሮች በተፈጥሮ ሐብት የታደለች ናት። 900 ሚሊዮን ገደማ ከሚጠጋ ሕዝቧ ከግማሽ የሚበልጠው ወጣት መሆኑም ለወደፊት ዕድገቷ አስተማማኝ የሰው ጉልበት እንዳላት ያመለክታል። እርግጥ ይህ ወጣት ትውልድ ገንቢ ሃይል የሚሆነው በዕውቀት ሲታነጽ፤ ጤናማ ዕድገት የሚያገኝበት ሁኔታ ከወዲሁ መመቻቸት ሲችል ነው። አፍሪቃ የዘመኑ ቴክኖሎጂና ሣይንስ ተቋዳሽ ለመሆን መብቃት ይኖርባታል።

የተባበሩት መንግሥታትን የሚሌኒየም ዕቅድ በጊዜው ገቢር በማድረጉ ረገድ ስኬታማ ዕርምጃ እያደረጉ መሆናቸው ከሚነገርላቸው ጥቂት የአፍሪቃ አገሮች መካከል አንዷ ታንዛኒያ ናት። በናይሮቢ የተባበሩት መንግሥታት የሚሌኒየም ዕቅድ ማዕከል የጤና ባለሙያ በርናርድ ኦላያ ለታንዛኒያ ዕርምጃ ከዓመት በፊት የተመረጡት ፕሬዚደንት የጃካያ ኪክዌቴ አስተዋጽኦ ታላቅ እንደሆነ ይናገራሉ። በነገራችን ላይ የሚሌኒየሙ ማዕከል የተቋቋመው ከተለያዩት ሃገራት ጋር በመተባበር ውጥኑ ከግብ የሚደርስበትን የፊናንስ ዕቅድ ለማውጣት ነበር።

ኦላያ ከተባበሩት መንግሥታት የሚሌኒየም ፕሮዤ ዋና ተጠሪ ከጄፍሪይ ሣክስ ጋር በመሆን ባለፈው ጥር ወር ታንዛኒያን ጎብኝተው ነበር። በርናርድ ኦላያ በዚሁ አጋጣሚ የታንዛኒያ መንግሥት ለመላው የአገሪቱ ሕጻናት ነጻ የአንደኛ ደረጃ ትምሕርት ለመስጠት የሚያራምደውን ፕሮግራም አንስተው አወድሰዋል። ታንዛኒያ ውስጥ ለአንደኛ ደረጃ ትምሕርት የሚመዘገቡት ሕጻናት ቁጥር ባለፉት ሰባት ዓመታት በእጥፍ፤ ማለት ከአራት ወደ ሥምንት ሚሊዮን ከፍ ማለቱ ነው የሚነገረው።

አፍሪቃ በመሠረቱ አብዛኞቹ ሕጻናት የትምሕርት ክፍያ እጦትና የመማሪያ ቦታዎች እጥረትን በመሳሰሉ ምክንያቶች በአንደኛ ደረጃ የሚወሰኑባት ክፍለ-ዓለም ናት። አሁን ግን ታንዛኒያ ውስጥ መንግሥት ሕብረተሰቡ በአገሪቱ ዙሪያ ሁለተኛ ደረጃ ትምሕርት ቤቶችን እንዲያንጽ በሚደግፈው ፕሮዤ በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ ወጣቶች በአጭር ዕውቀት ተወሰነው እንዳይቀሩ እያበረታታ ነው። ኦላያ እንደሚሉት አንድን አገር ለማሳደግ የትምሕር ሥርዓቱን ከማሻሻል የበለጠ ጠቃሚ መንገድ የለም። በዓለም ገበዮች ላይ ተገቢውን ድርሻ ለማግኘት የሚቻለውም ይህ ሲሟላ ነው።

ታንዛኒያ የተባበሩት መንግሥታትን የሚሌኒየም ግብ ዕውን እንድታደርግ የሚረዳት ብዙ ሃብት አላት። አገሪቱ ሰፊ የንጥረ-ነገር ሃብት፤ ታንዛኒት፣ ወርቅና መዳብ ሲኖሯት በእርሻው ዘርፍም የታወቀች የጥጥ፣ የቡናና የሻይ አምራች ናት። ብዙዎች ኩባንያዎችም በወቅቱ ነዳጅ ዘይት በመፈለግ ላይ ይገኛሉ። ምሥራቅ አፍሪቃይቱ አገር ወደ አገር ምሮቶችና ካፒታል ለሚያስገቡ ነጋዴዎች ዝቅተኛ ግብርና ታክስ በመጠየቅም የውጭ ባለሃብቶችን ለመሳብ ትሞክራለች። ማንኛውም መዋዕለ ነዋይ በመንግሥት እንዳይያዝም ሆነ እንዳይወረስ ዋስትና አለ።

የታንዛኒያ መንግሥት ከዚሁ ሌላ በኪስዋሂሊ መጠሪያው “እምኩኩታ” በመባል የሚታወቅ ስልታዊ የሆነ የብሄራዊ ዕድገትና የድህነት ቅነሣ መርሁን በ 2005 አጠናቆ ያራምዳል። በዓለምአቀፉ የምንዛሪ ተቋም IMF ና ዓለምአቀፍ የልማት ድርጅት International Development Association ዘገባ መሠረት ታንዛኒያ ከተባበሩት መንግሥታት የሚሌኒየም ዕቅድ ግቦች መካከል በድህነት ቅነሣ፣ በምግብ ይዞታ መሻሻል፣ በጾታ እኩልነት፣ በአንደኛ ደረጃ ትምሕርትና የሕጻናትን ሞት በመቀነስ ጠቃሚ ዕርምጃ አድርጋለች።

ለዚህም ምክንያቱ የአገሪቱ ኤኮኖሚ ዕድገት ማሣየቱ ነው። የአገሪቱ አጠቃላይ ብሄራዊ ምርት በ 2005 ቀደም ካለው ዓመት ሲነጻጸር ከ 6,7 ወደ 6,8 ከፍ ብሏል። የቀላል ኢንዱስትሪው ምርትም በተመሳሳይ ጊዜ ከ 8,6 ወደ 9 ከመቶ በማደግ ለዕርምጃው ድርሻ ነበረው። በአንጻሩ በዚያው ጊዜ የእርሻው ዘርፍ መለስተኛ የ 0,6 በመቶ ማቆልቆል ታይቶበታል። ይህም የሚያመለክተው በገጠሩ አካባቢ ድህነት የቀጠለ ጉዳይ መሆኑን ነው። በተለይ አነስተኛ ገበሬዎች ኑሯቸውን አሁንም በከባድ ሁኔታ ከመግፋት አልተላቀቁም።

ከታንዛኒያ ሕዝብ 80 በመቶው በግብርና የሚተዳደር ወይም በዚያ ላይ ጥገኛ ሲሆን ችግሩን ማሰቡ ብዙም አያዳግትም። በመሆኑም በመንግሥቱ መርህ ጤና ጥበቃ፣ ትምሕርትና የዕርሻ ልማት ምንም እንኳ ከፍተኛ ትኩረት ቢሰጣችውም ለገበሬዎች የበለጠ ዕርዳታ ማስፈለጉ የተሰወረ ነገር አይደለም። እንግዲህ መንግሥት በዚህ ዘርፍ ብሄራዊ ድጎማ አስፈላጊ በሆነባቸው ቦታዎች ሁሉ ይበልጥ ማተኮር ይጠበቅበታል። ለምሳሌ ማዳበሪያ፣ የእህል ዘርና የተባይ መከላከያ መድሃኒቶች አብዛኛውን ጊዜ ውድ በመሆናቸው ገበሬዎች ብዙ ይቸገራሉ።

በሌላ በኩል የፕሬዚደንት ኪክዌቲ ወደ ሥልጣን መምጣት በዘጠኝ ዓመታት ውስጥ እርሻን የበለጠ ለማሳደግግ የልማት ዕቅድ በተግባር ላይ በማዋላቸው በዚህ ዘርፍ የተሥፋ ጮራ መፈንጠቁ አልቀረም። ፕሮግራሙ ገበሬዎችን መደጎሙን ጭምር የሚጠቀልል ነው። ይህንንም ዓለምአቀፍ አበዳሪዎችና መንግሥታት ደግፈውታል። ብሪታኒያ በቅርቡ ታንዛኒያ ድህነትን ለመታገል ለምታደርገው ጥረት 105 ሚሊዮን ፓውንድ መለገሷ ለዚሁ እንደ አብነት የሚጠቀስ ነው። በያዝነው ዓመት መጀመሪያ ደግሞ በርከት ያሉ ሃገራትና ተቋማት ለታንዛኒያ በጋራ ዕርዳታ በሚያቀርቡበት አንድ ስልት ተስማምተዋል። ስብስብ የአውሮፓን ኮሚሢዮን፣ ቤልጂግን፣ ካናዳን፣ ዴንማርክን፣ ፊንላንድንና ፈረንሣይን፤ ስዊድንን፣ ስዊስን፣ ብሪታኒያንና አሜሪካን፤ እንዲሁም የዓለም ባንክንና የአፍሪቃን የልማት ባንክ የሚጠቀልል ነው።

የሆነው ሆኖ ታንዛኒያም በሚሌኒየሙ ግብ አቅጣጫ የምታድገው ዕርምጃ በዓለምአቀፉ ዕርዳታ ላይ ጥገኛ መሆኑ ነው ችግሩ። በአፍሪቃ መንግሥታት የመሪዎች ጉባዔ ራስን መቻል የሚለው ቃል ጎላ ብሎ ተሰምቷል። ችግሩ ቀደም ያለው ልምድ የሚያሣየው በመሪዎች ጉባዔ ላይ የተባለው ነገር በአብዛኛው በተግባር ትርጉም እንደማያገኝ ነው። የአፍሪቃ መሪዎች ከሁለት ዓመታት በፊት ናይጄሪያ-አቡጃ ላይ ከየብሄራዊ በጀታቸው 15 በመቶ የሚሆነውን ድርሻ በጤና ጥበቃ ተግባር ላይ ለማዋል ቃል ገብተው ነበር። ግን እስካሁን ቃላቸውን ያከበሩት ከሁለት አገሮች አይበልጡም። ሊቢያ ውስጥ ከዓመት ተኩል ገደማ በፊት አሥር በመቶውን በጀት በእርሻ ልማት ላይ ለመዋል የተደረገው ስምምነትም እንዲሁ በሰፊው ነው ችላ የተባለው። አፍሪቃን ከኤኮኖሚ አዘቅት ማውጣት፤ ራስ ማስቻሉ እንግዲህ ሕልም ብቻ ሆኖ እንዳይቀር ከተፈለገ ቃልና ተግባር መጣጣማቸው ግድ ነው። የሕብረቱም ፍቱንነት የሚለካው በዚሁ ይሆናል።