አፄ ቴዮድሮስ ሲታወሱ | ባህል | DW | 19.01.2018
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

ባህል

አፄ ቴዮድሮስ ሲታወሱ

«አየሽልኝ እናት ዓለም፤ ጉዴን ጉድሽን ሰማሽልኝ ኢትዮጵያዬ፤ ይሄ ጊዜ የሰጠዉ ቅል እጅህን ስጥ ነዉ እኮ የሚለኝ። ተይ ስቲ አንቺ መስክሪብኝ። የአደራ ቃልሽን በትኖማ እጅ መስጠት የት አዉቄ። ሐገሪ ዛሬም እመኝኝ ከቶም አትጠርጥሪኝ። ምን ፈተናዬን ብታበዥዉ ኢትዮጵያዬ እወድሻለሁ»

አውዲዮውን ያዳምጡ። 15:16

የአፄ ቴዮድሮስ 199ኛ የትዉልድ ቀን ክብረ በዓል

«አንሱ ካላችሁ እናንሳ ወንድ፤ የቋራዉ ካሳ አባ ሞገድ፤ መቼ ሞተና መቼ ተነሳ፤ መቅደላ  ያለዉ የቋራዉ ካሳ።»

የአፄ ቴዎድሮስ ስም ሲነሳ፤ ሽንፈቱን አውቆ በጠላት እጅ ከመዉደቅ የገዛ ሕይወቱን በራሱ እጅ ያጠፋ ኩሩ የኢትዮጵያ ንጉሠ ነገሥት መሆናቸውን አብዛኞች ይናገራሉ። እኝህ ንጉሰ ነገስት ፣ የዘመናዊት ኢትዮጵያ መስራች በመሆናቸውና ዘመነ መሳፍንት በመገርሰስ ኢትዮጵያን እንደ አንድ ለመግዛት መሰረት መጣላቸው ከሚጠቀሱላቸው ሥራዎቻቸዉ ቀዳሚውን ቦታ መያዙም የታሪክ መዛግብት ያሳያሉ። ። ባሳለፍነዉ ሳምንት መጠናቀቅያ ጥር ስድስት ቀን ኢትዮጵያዉያን የአፄ ቴዎድሮስን የ199ኛ የልደት ቀን መታሰብያ በተለያዩ ዝግጅቶች አክብረዉ ዉለዋል። 

አልደፈር ብሎ ራሱን ገደለ፤

ጀግና ሰዉ ሰዉቶ ካሳ መች ከፈለ፤

በመቅደላ በኩል ጩኸት በረከተ፤

የሴቱን አናዉቅም ወንድ አንድ ሰዉ ሞተ።

አባት እናናቱ ከአላንድ አልወለዱ

አባታጠቅ ካሳ ያዉ አንዱ ያዉ ወንዱ።

እጅ አልሰጥም ብሎ ለፈረንጅ ካቴና

ወድቆ ተሰበረ ሽጉጡን ጠጣና።

በ1811 ዓ.ም ጥር ስድስት ቀን  ከጎንደር ከተማ  አስራ ሁለት ኪሎ ሜትር  እርቃ በምትገኘው ዳዋ በተባለች መንደር ከአባታቸው ከአቶ ኃይሉ ወልደ ጊዮዎርጊስ እና ከእናታቸው ከወ/ሮ አትጠገብ በወንድወሰን  የተወለዱት ካሳ፤  በመሳፍንት ተከፋፍላ የወደቀች ሃገራቸውን ለማንሳት የተነሱ ታላቅ ሐገር ወዳድ እንደነበሩ የታሪክ አዋቂዎች ይናገራሉ። 

አባ ታጠቅ ካሳ፤  አርባ ሽህ የጦር ወታደር፤ስምንት ሽህ ባለ ጠመንጃ አራት ሽህ፤ ፈረሱኞች ያላቸውን፤ አማቻቸውን ደጃች ውቤ ኃይለማሪያምን፤ ድል ካደረጉ በዃላ፤ በየካቲት ወር፤ 1845 ዓ.ምአፄ ቴውድሮስ፤ ተብለው በደራስጌማርያም ፤ ቤተክርስቲያን፤ በጳጳስ አቡነ ሰላማ እጅ እንደነገሱ የታሪክ መጻሕፍት ያሳያሉ።

ባለፈዉ ሳምንት እሁድ 199ኛ የልደት ቀናቸዉ በሃገር ዉስጥ እና ከኢትዮጵያ ዉጭ በሚኖሩ ኢትዮጵያዉያን ዘንድ ታስቦ ዉሎአል። በተለይ በአፄ ቴዎድሮስ የትዉልድ ቦታ በሆነችዉ በጎንደር የትዉልድ ቀናቸዉ በተለያዩ ዝግጅቶች ደምቆ ነዉ የዋለዉ። በቴዎድሮስ ስንብትና በቴዎድሮስ ራዕይ ትያትሮች ላይ ከታዋቂዉ ተዋናይ ፈቃዱ ተክለማርያም ጋር የተወነዉ የጎንደር ሲኒማ ካፈራቻቸዉ ታዋቂ አርቲስቶች መካከል ሱራፊል ተካ በጎንደር ከተማ በተካሄደዉ ክብረበዓል ላይ በክብር እንግድነት ተገኝቶአል። የአፄ ቴዎድሮስ ገጸ ባህሪንም ተላብሶ በሥነ ስርዓቱ ላይ ለተገኘዉ ታዳሚ አቅርቦአል። አርቲስት ሱራፊል ተካ የአፄ ቴዮድሮስ ዘንድሮ ጥር 6 ቀን 199 ዓመት ይሆናቸዉ ነበር ሲል በመግለፅ ይጀምራል።  

« በጣም ልዩ ቀን ነዉ፤ መነሻዉ ላይ ትንሽ የቁጥር ስህተት ታይቶ ነበር። ዘንድሮ 199 ኛ ዓመት ነዉ የሚሆነዉ። የኢትዮጵያ አንድነት የተሰበከበት ቀን ነዉ። የኢትዮጵያ አንድነት የታየበት እለት ነዉ። ምክንያቱም አፄ ቴዮድሮስ የኢትዮጵያ ጀግና ናቸዉ። ብዙ ጊዜ አፄ ቴዮድሮስ የሚታወቁት በኢትዮጵያ አንድነት ነዉ ። እናም ይህ የልደት በዓል ያ አንድነት የታየበት ነዉ። »

በጎንደር ከተማ በተካሄደዉ የአፄ ቴዮድሮስ የትዉልድ ቀን መታሰብያ ዝግጅት ላይ አርቲስት ሱራፊል ተካ አፄ ቴዮድሮስን በመሆን ተዉኖአል።

« ይህ በዓል ላይ የክብር እንግዳ ሆኜ፤ በ199ኛ የልደት በዓላቸዉን ሻማ ለኩሻለሁ። የምኖረዉ አዲስ አበባ ነዉ፤ በዚህ በዓል ላይ እንድታደም ታጋብዤ ነዉ ወደ ጎንደር የመጣሁት። ይህ የእሳቸዉ የልደት በዓል የእኔም ነዉ ማለት እችላለሁ። ምክንያቱም አፄ ቴዮድሮስ በተወለዱበት ሃገር ነዉ የተወለድኩት። ከአባቴም ከአያቴም ሆነ ከማኅበረሰቡ ስለሳቸዉ ታሪክ ስሰማ ነዉ ያደኩት። እናም በዝግጅቱ ላይ የቴዮድሮስን አልባሳት ለብሼ የመቅደላዉን መነባንብ ምሽት ላይ አቅርቤያለሁ። እጅግ ደስ የሚል ድባብ ነበረዉ። አዳራሹ ዉስጥ የነበሩ ታዳሚዎች ደስታ እንባ በተቀላቀለበት ስሜት ነበር ሲከታተሉ የነበረዉ። ደስ የሚል የኢትዮጵያ አንድነት የታየበት ምሽት ነበር። »

 

አርቲስት ሱራፊል ለዶይቼ ቬለ ተከታታዮች በመድረክ ካቀረበዉ መነባንብ በከፊል አቅርቦአል። 

«በርግጥ መነባንቡ ከትጥቅና ከአልባሱታ ጋር ታጅቦ ቢሆን ጥሩ ነበር። ለቅምሻ ያኽል፤ አፄ ቴዮድሮስ በመጨረሻዉ ሰዓት መቅደላ ላይ ራሳቸዉን እንዳጠፉ ይታወቃል። በዚህ የመጨረሻ ጦርነት ላይ በጣም ታማኝ የጦር አዝማቻቸዉ ገብርዬ፤ ሮዴ ላይ ከእንጊሊዞች ጋር ሲዋጋ ሕይወቱን ሰዉቶአል። ይህ መርዶ ለአፄ ቴዮድሮስ መቅደላ ላይ ይነገራቸዋል። ከዚህ በኋላ በጦርነቱ የማሸነፍ ተስፋቸዉ ይሟጠጣል። ምክንያቱም በጣም ጀግና አገልጋያቸዉ ጦር አዝማች ገብርዬ በማለፉ ብዙ ተስፋ የሚያስቆርጥ ስሜት ተሰምቶአቸዋል። ገብርዬን ከገደሉ በኋላ እንጊሊዞቹ በቀጥታ አፄ ቴዮድሮስን መግደል ስላልፈለጉ በክብር እጆትን ይስጡ ሲል በዝያን ወቅት የታላቅዋ ብሪታንያ የጦር አዝማች የነበረዉ ጀነራል ሮበርት ናፔር እጃቸዉን በክብር እንዲሰጡ በጦርነቱ ሲነግራቸዉ ያንን ስሜት የሚገልፁበትን መንገድ ነዉ ለመተረክ የፈለኩት። እናም በክብር እጆትን ይስጡ ሲባሉ በጣም ገርሞአቸዉ ይስቃሉ። « በክብር በክብር ! በስልጣኔ ተራቆ እንዲህ በሰማያት ሰማያት ሲነካ፤ ክብር ምን እንደሆን ገና የማያዉቅ እንግሊዝ ደንቆሮ ነዉ ለካ። ይገርማል ዘመን ቁጭ ብለዉ ከጠበቁት ጉድ ወልዶ ያሳያል። ይሄዉ ይሄ ጊዜ የሰጠዉ ቅል፤ ይሄ ጅል የእንጊሊዝ ጀነራል፤ የአንድ የኢትዮጵያን ንጉሰ ነገስት እጅን መጨበጥ ይመኛል። እኮ እጄን! የእኔን! ይሄን! እጄን! ስንት ጀግና እንደቆሎ በእፍኝ ይዞ የኖረዉ እጄን ምን ሊያርገዉ፤ ስሜን እንጂ እንግሊዝ እጄን በሩቁ አያዉቀዉ። እዉነት አለዉ።  እንኳን እንደኔ ልዑል እግዚአብሄር የመረጠዉ፤ የአገር ፍቅር ፀጋና አደራ ቀብቶ የሰጠዉ እንደ ዳዊት ከትብያ አንስቶ፤ ከወርቅ ዙፋን ያስቀመጠዉ ለነካሌብ ክብርና ለዘዉድ ያበቃዉ አንድ ንጉስ ይቅርና ከአበሻ ሐገር መጠጋቱ ደመነፍሱ ለምትነግረዉ ገና ለአንድ ፍሪ ጨቅላ እንኳ እጅ መስጠት ማለት ሞት ነዉ። አየሽልኝ እናት ዓለም፤ ጉዴን ጉድሽን ሰማሽልኝ ኢትዮጵያዬ፤ ይሄ ጊዜ የሰጠዉ ቅል እጅህን ስጥ ነዉ እኮ የሚለኝ፤ ተይ ስቲ አንቺ መስክሪብኝ፤ ተይ እስቲ አንቺ ፍረጂኝ፤ ነፍስ ከአወቅሁ ጀምሮ ከአንቺ ማህፀን ተፈልቅቄ፤ ላንቺ ክብር ማኖርና ዝና ክብርሽን ጠብቄ፤ የአደራ ቃልሽን በትኖማ እጅ መስጠት የት አዉቄ። ሐገሪ ዛሬም እመኝኝ አሁንም ቃልሽን ጨብጫለሁ፤ ስጥ በተባልኩት እጄ የአንቺ  የአንቺ ክብር እዳለ አዉቃለሁ። ስላንቺ ስለፋ እንደኖርኩ ዛሬም ስለአንቺ አልፋለሁ። ሞቶ በክብር መኖርን፤ ለእንጊሊዝ አሳየዋለሁ፤ ከቶም አትጠርጥሪኝ ምን ፈተናዬን ብታበዥዉ ኢትዮጵያዬ እወድሻለሁ»        

አርቲስት ሱራፊል ተካ የስንብት ጽሑፍ በሚል ካቀረበዉ የተዉኔት ክፍል በተጨማሪ አቦል ጥበብ በተሰኘ የሚታወቁት የጎንደር ጥበብ ወጣቶች የሥነ -ጽሑፍ ዝግጅት አቅርበዋል። የዝግጅቱ አስተባባሪ የሆነዉ የአቦል ጥበብ  የሥነ ጽሁፍ ቡድን አዘጋጅ ወጣት የሕግ አማካሪና ጠበቃ  መክት ካሳሁን ስለዝግጅቱ የገለጸዉ አለ።

« በዝግጅቱ ላይ የአፄ ቴዮድሮስ የስልጣኔ ትልቅ ፈር ቀዳጅ መሆናቸዉን የሚያሳዩ ሥራዎችና ንግግሮች ታይተዉበታል። ከዝግጅቱ አቅራቢ ዉስጥ እኔ አንዱ ነበርኩ። ከጀብዱ ሕይወታቸዉም በዘለለ የፍቅር ሕይወታቸዉን የዳሰስንበት የጥናት ፅሁፍ ነበር። ለአብነት ያህል እኔ ካቀረብኩት ሥራ እቴጌ ተዋበች ወይም ተዋቡ ዓሊ የራስ ዓሊ ልጅ ፤ ከአፄ ቴዮድሮስ ጋር የነበራቸዉን የፍቅር ታሪክ የሚያሳይ ለሴት ልጅ ያላቸዉን ክብር ለሚስት ያላቸዉን ክብር የሚያሳይ ነዉ። ጥሩ ጥሩ ይዘት ያላቸዉ የሥነ-ጽሑፍ ሥራዎች ቀርበዋል። አሁን በዚህ ዘመን ላይ ሊነሳ የሚችልና በነበሩ የሚያሰኝ ትልቁ ነገራቸዉ ሐገራዊ አንድነት ነዉ። ከምንም በላይ ሐገራዊ አንድነት ከምንም በላይ ለአንድ ኢትዮጵያ ትልቅ ጭንቀት ነበራቸዉ። የሚናፍቀን የኢትዮጵያ ቅርስ እሳቸዉ ጋር ነበረች። ከዚህ አንፃር አፄ ቴዮድሮስ ከሌሎች መሪዎች ይለያሉ»

    

በጎንደር ከተማ ጎዳና ላይ በተካሄደዉ ትዕይንት በተዋንያኑ የሴባስቶፖል መድፍ ቀርቦ ነበር ።የዝግጅቱ አስተባባሪ መክት ካሳሁን እንደሚለዉ በከተማዋ ላይ የሚካሄዉ ዝግጅቱ ይቀጥላል። 

« ከፊስቲቫሉም ጋር ተያይዞ እስከ ጥምቀት በዓል ድረስ የሚቀጥል ነዉ የሚሆነዉ። ልዩ ልዩ የጎዳና ላይ ትሪኢቶች ታይተዋል። የጎዳና ላይ ትርኢቱ ሁሉ አፄ ቴዮድሮስን የሚያስታዉስ ነዉ። ለምሳሌ የሴቫስቶፖልን መድፍ መጎተቱ መሃል ጎንደር ከተማ የሚገኘዉን የአፄ ቴዮድሮስን ሃዉልት ጃኖ አልብሶ የማክበር፤ በዙርያዉ ላይ የተለያዩ ዝግጅቶች ማድረጉ ሁሉ ጥር 6 ቀን በጠዋቱ ነበር የጀመረዉ። ሌላዉ የፋሲል ከነማ የእግር ኳስ ቡድን 50ኛ ዓመት ጋር ተያይዞ የክለቡ መለያ «ዓርማ» አፄ ቴዮድሮስ ከመሆናቸዉ አንፃር 50ኛ ዓመቱ ከአፄ ቴዮድሮስ ከዉልደት ቀናቸዉ ከጥር 6 ቀን ጀምሮ ንግስናቸዉን እስተቀበሉበት እስከሚያዝያ ወር ድረስ 50ኛ ዓመቱ በተለያዩ ዝግጅቶች እየተከበረ መቀጠሉ ነዉ»    

አፄ ቴዮድሮስ ለአካባቢዉ ነዋሪ ከንጉስም በላይ የማንነት መገለጫም ናቸዉ ያሉን በጎንደር ዩንቨርስቲ የሥነ ልቦና ባለሞያ መምህር ገበየሁ በጋሻዉ፤ ይህንን ለመረዳት ይላሉ በመቀጠል።

« ከንጉስም በላይ ናቸዉ። የአካባቢዉ የወጣቱ የማንነቱ አካል አድርጎ ያያቸዋል። እልፍ ጊዜ ለሐገራቸዉ የደሙ ፤ እልፍ ጊዜ ለወገናቸዉ የተጉ ናቸዉ። የዚያን ጊዜዉ ሊቀ-ንጉስ የዛሬዉ ሥረ-መሠረት ሁሌም እኛም ሆነ እናት አባቶቻችን ልብ ዉስጥ የሚኖሩ ሰዉ ናቸዉ።

ይሄን ለመረዳት በጣም ቀላሉ ኢትዮጵያ ዉስጥ በጣም ብዙ ሰዉ የቴድሮስን መጠርያ መያዙ ነዉ። ወደ ትዉልድ ቦታቸዉ ወደ ጎንደር ሲኬድ ደግሞ በጣም ብዙ ቴዮድሮስ የሚል ስያሜን እናገኛለን። በተለይ ደግሞ ወላጆች ልጆቻቸዉ እንዲይዙ የሚመኙት አፄ ቴድሮስ የነበራቸዉን ራዕይ ፤ ሐገርን አንድ የማድረግ ራዕይ ነዉ። አፄ ቴዎድሮስ ሩህሩህ ነበሩ ደግ ሰዉ ነበሩ። እንደንጉስም ተከበዉ የሚኖሩ ሰዉ አልነበሩም። በባዶ እግራቸዉ ከታች ከድኸ ማኅበረሰብ ጋር ሆነዉ የሕዝብን ችግር ለመፍታት የሚጥሩ የነበሩ ንጉስ ናቸዉ። በዝያ ላይ ለጥበብ ለቴክኖሎጂ፤ ለትምህርት፤ ለእዉቀት የነበራቸዉ ፍላጎት እጅግ ከፍተኛ ነበር። ከመድፍ መስራት ጀምሮ ጋፋት አካባቢ የብረት ማቅለጫ፤ ከዝያም በራሳቸዉ ጥረት በጣና ላይ የባሕር ሐይል ለመስራት የሞከሩ የራሳቸዉን ጀልባ ለመስራት የሞከሩ ሰዉ ናቸዉ። ሌላዉ በአካባቢዉ እጅግ እንዲወደድ የሚያደርጋቸዉ ጀግንነታቸዉ ነዉ። ለቱርኮች አልደፈር ብለዋል፤ ለእንጊሊዞች አልደፈር ብለዋል፤ በአላማቸዉ ጽኑ ነበሩ። አላማቸዉ ጽኑ እንደነበር ለማረጋገጥ እስከመሞት ድረስ መሄዳቸዉ ነዉ። ወደ ንግሥናዉ የመጡት ሐገር ለማዳን ነዉ ሲሞቱም ሕዝቡ ሐገሩ አንድ እንዲሆኑ ብለዉ ነዉ። ከሌሎቹ ንጉሶች ለየት የሚያደርጋቸዉ ደሐን ለመርዳት እታች ወርደዉ በባዶ እግራቸዉ ከኅብረተሰቡ ጋር ይኖሩ የነበሩ ስለነበር ነዉ። ከተማ ዉስጥ ለምሳሌ የነፋሲል ቤተ-መንግሥት ነበር። እዝያ ዉስጥ መኖር ይችሉ ነበር። ነገር ግን እዛያ ዉስጥ መታሸግ ስላልፈለጉ ገጠር አካባቢ ገበሪዉ ከደሐዉ ሕዝብ ጋር በመሆን ሐገራቸዉን ለመስራት ነበር ፍላጎታቸዉ»        

«ብቻዉ ሲሄድ ይመስላል ሃምሳ

አካሉ የሰዉ ድምጡ ያምበሳ።»

የአፄ ቴዮድሮስን የሥነ-ልቦና እና የአካል ጥንካሪ ለመግለፅ በትዉልድ አካባቢያቸዉ ላይ የሚደመጥ ሥነ- ቃል ነዉ። ጎንደር አካባቢ አሁንም በቴዎድሮስ ስም እንደሚማል መምህር ገበየሁ ተናግረዋል። 

« ይማላል! በተለይ ወደ ገጠሩ አካባቢ አሁንም ኸረ በቴዮድሮስ ይባላል። አካባቢዉ ላይ አሁንም ቴዮድሮስ ይሙት ነዉ የሚባለዉ። አፄ ቴዮድሮስ ቅጥፈት ሌብነት ማስመሰል አይወዱም ነበር። አሁንም ጎንደር አካባቢ የሚታየዉ ይሄ ነዉ። ሠዉ ቀጥተኛ ነዉ፤ መናገር የሚፈልገዉ ይናገራል። ቅጥፈት ስርቆት አይፈልግም። ለዚህ ነዉ የጎንደር ማተሙ የሚባለዉ። ይህ ሁሉ ከንጉሳዉያኑ የተወረሰ ነዉ።

«The Barefoot Emperor: An Ethiopian Tragedy» በተሰኘ ርዕስ የአፄ ቴዎድሮስን ታሪክ የፃፈዉ የታዋቂዉን የእንጊሊዛዊ የፊሊፕ ማርስደንን መጽሐፍ የተረጎሙትና ባለፈዉ ታኅሳስ ወር «ጫማ አልባዉ ንጉሰ ነገስት፤ አሳዛኙ የኢትዮጵያ ታሪክ» በሚል ርዕስ ተርጉመዉ ለአማርኛ አንባብያን ያቀረቡት አቶ ተክለማርያም መንግሥቱ በመጨረሻ   

« ስለ አፄ ቴዮድሮስ ብዙ ሰዉ ነዉ የሚያዉቀዉ። ስለ አፄ ቴዮድሮስ ታሪክ የፃፈዉ የእንጊሊዛዊዉ ፊሊፕ ማርስደን መፀሐፍ ከየምዕራፉ ለቀም ለቀም አድርጌ የተረጎምኩት እንጊሊዛዊዉ ደራሲ ስለ አፄ ቴዮድሮስ ታሪክ በርሕራሄ ሳያድበሰብስ በመፃፉ ነዉ። ስለ አፄ ቴዮድሮስ የፃፈዉ ወደ ኢትዮጵያም ሄዶ ዘመዶቻቸዉን ጠይቆ በትክክል በመፃፉ ነዉ። ለመፀሐፉ የሰጠሁት ትርጉም «ጫማ አልባዉ ንጉሰ ነገስት፤ አሳዛኙ የኢትዮጵያ ታሪክ» ብዬ ነዉ። መጽሐፉ ወደ 164 ገፅ አለዉ። »

የአፄ ቴዮድሮስን 199ኛ  የትዉልድ ዓመት ለማዉሳት የያዝነዉ ሙሉ ቅንብር የድንፅ ማድመጫ ማዕቀፉን በመጫን ይከታተሉ።     

አዜብ ታደሰ

ነጋሽ መሐመድ

Audios and videos on the topic