አጶፊስና መላ ፈላጊዎቹ የኅዋ ተቋማት | ሳይንስ እና ኅብረተሰብ | DW | 10.02.2010
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ሳይንስ እና ኅብረተሰብ

አጶፊስና መላ ፈላጊዎቹ የኅዋ ተቋማት

በተፈጥሮ ህግጋት ወይም የስበት ኃይል፣ ፕላኔቶችና ከዋክብት ፣ ጨረቃዎችና ስብርባሪ ኮከቦች ሁሉም ምኅዋራቸውን ጠብቀው በሥፍራቸው እንደሚገኙ የታወቀ ነው።

አጶፊስና መላ-ፈላጊዎቹ 3 ዐበይት የኅዋ ተመራማሪ ድርጅቶች

የአውሮፓው የኅዋ ምርምር ድርጅና የ Don Quijote የመንኮራኩር ተልእኮ፣

ይሁን እንጂ በአያሌ ዘመናት ውስጥ ይህን የተፈጥሮ ህግ የሚጥስ ሁኔታ ሲያጋጥም እንደነበረና ወደፊትም እንደማይቀር ነው የኅዋ ተመራማሪዎች የሚናገሩት።

እንደሚባለው ከ 65 ሚሊዮን ዓመታት በፊት ምድራችንን ያነጎደ ስባሪ- ከከብ በየብስ በግዙፍነት ወደር ያልነበራቸውን ዳይኖሰርስ የተባሉትን ዐራዊት ከገጸ ምድር አጥፍቷል።

የተለያዩ ቀላልና ከባድ የሚሰኙ ጥፋቶችም፤ በተለያዩ የምድራችን ክፍሎች ሳያጋጥሙ አልቀሩም። አንዳንድ ስርጓዳ፣ ጉድጓድ መሰል ቦታዎች፣ በስባሪ ከዋክብት ሳቢያ ፣ አሁን የያዙትን ቅርፅ እንደያዙ ይገኛሉ። በግዙፍነት የበላይነቱን ይዘው የነበሩት የዳይኖሰር ዓይነቶች፣ አርጌንቲኖሶረስ የተባሉት፣ ከ 100 ሚሊዮን ዓመት በፊት በዛሬዋ አርጀንቲና ይኖሩ የነበሩ ዐራዊት ናቸው። ቁመታቸው 45 ሜትር ገደማ ፣ ክብደታቸውም፣ 80 ቶን ያህል እንደነበረ ነው የሚነገርላቸው እነዚሁ ዐራዊት የጠፉት እንደሚባለው በስባሪ ኮከብ ሳቢያ ነው።

እ ጎ አ በ 2004 በጎርጎሪዮሳውያኑ የገና በዓል ዋዜማ ለመጀመሪያ ጊዜ እንደታየ የሚነገርለት በጥንት ግብፃውያን ፣ የፀሐይ ግርጋ ጣዖት ስም የሚጠራው በግምት 350 ም ሆነ 250 ሜትር ወርድ ያለው ስባሪ ኮከብ ፣ «አጶፊስ»፣ በሳይንሳዊ መጠሪያው (2004 MN4) በዩናይትድ እስቴትስ፣ በሩሲያም ሆነ በአውሮፓ ዐበይት የኅዋ የምርምር ጣቢያዎችን የሚያነጋግር ጉዳይ ሆኗል። ማነጋገር ብቻ ሳይሆን ፣ መላ እንዲፈለግም እየገፋፋ ይመስላል። አጶፊስ፣ ከዚህ ቀደም እንደተተነበየው፣ እ ጎ አ ሚያዝያ 13 ቀን 2029 ፣ ከምድራችን ጋር ቢላተም፣ 1900 ሜጋቶን ( TNT )የፍንዳታ ኃይል እንደሚኖረውና የፈረንሳይን ያህል ሥፋት ያለውን ቦታ ምድረ-በዳ በማድረግ መጠነ ሰፊ ጥፋትና ዕልቂት ሊያስከትል እንደሚችል ነው የተገለጠው። አጶፊስ በተጠቀሰው ዕለት ለምድራችን 36,000 ኪሎሜትር ያህል ብቻ ራቅ ብሎ እንደሚሽከረከርና ፣ ይህ ርቀት ለቴሌቭዥን ፕሮግራሞች ሥርጭት የሚረዱ ሳቴላይቶች የሚገኙበት፣ በመሬትና በጨረቃ ካለው ርቀትም 1/10 በመሆኑ ጭምር ነው አደጋው በቀላል እንዳይታይ ያደረገው። የአሜሪካው የኅዋ ምርምር ድርጅት(NASA)፣ አፖፊስ ብቻ ሳይሆን፣ ወደ መሬት የተጠጉ ገዝፍ ያላቸው ነገሮች፣ Near Earth Objectes (NEOs)በሚሊዮን የሚቆጠሩ መሆናቸውን ይገልጻል። ይህም፤ ስባሪና ስብርባሪ ከዋክብትን የሚመለከት ነው። በ Harvard –Smithsonian የአስትሮፊዚክስ ማዕከል ባልደረባ ዶ/ር Irwin Shapiro አሁን የሚነገረው ሁሉ የሚያስደንቅ እንዳልሆነ ፣ ምድራችን ከዚህ ቀደም ብዙ ጊዜ በስብርባሪ ከዋክብት መመታቷን ጠቁመዋል።

06_03_31_pz_asteroid_03.jpg

«ያለፈው ምድራችንን ክፉኛ የመታት የስባሪ ከከብ አደጋ የደረሰው ከ 65 ሚሊዮን ዓመታት በፊት ነበር። ይህም መለስ ብለን በጥሞና ስንገመግመው ፣ በምድራችን እጅግ በዛ ያሉ ፍጥረታትን ማውደሙን እንገነዘባለን። እርግጥ ነው፣ ከስባሪ ከከብና ምድር መላተም በኋላ፣ ከገጸ-ምድር በመጥፋት እጅግ የታወቁት ዐራዊት ዳይኖሰርስ ናቸው። ዋናው ነጥብ እንዲህ ዓይነቱ መቼ እንደሚደርስ የማናውወቅ መሆናችን ነው»።

ዶ/ር ሻፒሮ በቅርቡ ለዩናይትድ እስቴትስ ም/ቤት፣ በጻፉት ደብዳቤ፣ ስብርባሪና ስባሪ ከዋክብትን መከታተል ይቻል ዘንድ የ NASA ዓመታዊ በጀት እንዲጨመር መጠየቃቸው ታውቋል። እርሳቸውና በብሔራዊው የምርምር ም/ቤት የሚገኙት ባልደረቦቻቸው በጀቱ በቂ ባለመሆኑ፣ እስከ 2020 ወደ መሬት ጠጋ ብለው ከሚገኙት ገዝፍ ያላቸው ነገሮች 90 ከመቶውን ለይቶ ለማወቅ አያስችልም ብለዋል። በዚህ ረገድ ጥናት ማድረጉም ሆነ ቅየሣ ማካሄዱ ከስብርባሪና ስባሪ ከዋክብት ሊደርስ የሚችልን የመላተም አደጋ ሥጋት ለመቀነስ ጠቃሚ እርምጃ ነው ብለዋል። አሁንም ፣ ዶ/ሻፒሮ፣---

«ለምድር ቀረብ ብለው የሚገኙ ግዝፍ ያላቸው የሰማይ አካላት የሚደቅኑት ሥጋት ፣ የተፈጥሮ አደጋን ስናስብ ማለት ነው፣ የተለመደ አይደለም። ምክንያቱም፣ የምድር ነውጥን መቼ እንደሚያጋጥም የምናውቅበት መላ የለንም። ስለባህር ማዕበል መተንበይ አንችልም። የሆነው ሆኖ፣ እዚህ ላይ ስጋት መደቀኑን ለመተነበይ የምንችልበት የተለየ ሁኔታ አጋጥሞናል። ከሰማይ የሚመጣ አንድ ገዝፍ ያለው አካል መቼ ከምድራችን ጋር ሊላተም እንደሚችል እናውቃለን፣ ስለዚህም የሚበጀውን እርምጃ ለመውሰድ ችሎታው አለን።»

ከዚህ ጠንቀኛ ሥብርባሪ ኮከብ አደጋ፣ ራስን እንዴት መከላከል ይቻላል? በሚለው ጥያቄ ዙሪያ፣ የተለያዩ አገሮች የሥነ-ፈለክ ጠበብትና ተቋማት መምከራቸው አልቀረም። የአጶፊስን አደጋኛነት አሳሳቢ አድረገው ከተመለከቱት የኅዋ ምርምር ተቋማት መካከል አንዱ የሩሲያው «ሮስኮስሞስ» ነው። የዚሁ ድርጅት ኀላፊ አናቶሊ ፐርሚኖቭ «በሰው ህይወት መጫዎት እንዳይሆን፣ ችላ ማለት አይገባንም » ነው ያሉት። እርሳቸው እንደተናገሩት ፣ የተቃጣውን አደጋ ለማክሸፍ የሩሲያን ፣ የአውሮፓን፣ የዩናይትድ እስቴትስንና የቻይናን ትብብር የግድ ይላል።

ተክሌ የኋላ

ሸዋዬ ለገሠ