አጠቃላዩ የታንዛንያ ምርጫ | አፍሪቃ | DW | 24.10.2015
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

አፍሪቃ

አጠቃላዩ የታንዛንያ ምርጫ

24 ሚልዮን የታንዛንያ ሕዝብ እሁድ ጥቅምት 14 ቀን፣ 2008 ዓ. ም. አጠቃላይ ምርጫ ላይ ድምፁን ሰጥቷል። በርካታ መራጮች ለምርጫ ተሰልፈው የምርጫ ሰአት ማብቃቱ ተነግሯቸዋል። ከወዲሁ ግልጽ የሆነው ከምርጫው በኋላ ታንዛንያ አዲስ ፕሬዚደንት እንደሚኖራት ነው።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 10:20
አሁን በቀጥታ እየተሰራጨ ያለ
10:20 ደቂቃ

ታንዛንያ

በአፍሪቃ ባሉት ብዙዎቹ ፕሬዚደንቶች አንፃር ፕሬዚደንት ጃካያ ኪክዌቴ የሃገሪቱን ሕገ መንግሥት በማክበር ለሶስተኛ የስልጣን ዘመን አይወዳደሩም። በታንዛንያ የመድብለ ፓርቲ ሥርዓት እአአ በ1995 ዓም ከተዋወቀ ወዲህ ከተካሄዱት ምርጫዎች ሁሉ በነገው ዕለት የሚደረገው ፕሬዚደንታዊው ምርጫ በምህፃሩ «ሲ ሲ ኤም» በሚል መጠሪያ ለሚታወቀው እአአ ከ1977 ዓም ወዲህ በስልጣን ላይ ለሚገኘው ለገዢው « ቻማ ቻ ማፒንዱዚ» ወይም በዘረፋ ትርጉሙ ለዓብዮታዊው ፓርቲ አዳጋቹ እንደሚሆን ይጠበቃል። ምክንያቱም፣ በገዢው ፓርቲ ውስጥ ባለፉት ወራት የተፈጠረው ውዝግብ ቁጥራቸው ትንሽ የማይባል ከፍተኛ የፓርቲው አባላት ፓርቲውን ለቀው የወጡ ሲሆን፣ የተቃዋሚ ቡድኖች በዚሁ አጋጣሚ በመጠቀም ቅር የተሰኙትን ፖለቲከኞች ወደ ጎራቸው ተቀብለዋል።

በዚሁ ምርጫ ላይ ስምንት እጩዎች በተወዳዳሪነት ቀርበዋል፣ ከእጩዎቹ መካከልም በሃገሪቱ ታሪክም ውስጥ ለመጀመሪያ ጊዜ አንዲት ሴት ተወዳዳሪ ይገኙበታል። ያም ቢሆን ግን፣ ከሁለት ወር የምርጫ ዘመቻ በኋላ፣ ብዙ የፖለቲካ ታዛቢዎች እንደሚገምቱት፣ ፕሬዚደንት ጃካያ ኪክዌቴን ለመተካት ጠንካራው ፉክክር የሚካሄደው በሁለት እጩዎች መካከል ብቻ ይሆናል፥ የመጀመሪያው የገዢው « ቻማ ቻ ማፒንዱዚ ፣ «ሲ ሲ ኤም» ፓርቲ እጩ ጆን ማጉፉሊ ናቸው። ማጉፉሊ የቀጣዩ መንግሥት ፕሬዚደንት ሆነው ቢመረጡ እንደሚያከናውኑዋቸው ከገለጹዋቸው ተግባራት መካከል በተለይ በሃገሪቱ በሚታየው ሙስና አንፃር ቁርጠኛ ርምጃ የሚወስዱበት ድርጊት አንዱ እንደሚሆን በምርጫ ዘመቻው ወቅት ቃል ገብተዋል።

« በሃገሪቱ መንግሥት ውስጥ ገንዘብ የሚሰርቁ ጥቂት ሙሰኛ ባለስልጣናት አሉ። ለነዚህ ባለስልጣናት ልነግራቸው የምፈልገው ሕግን ተከትለው መስራት እንዳለባቸው እና ቃለ መሀላ እንደፈፀምኩም አንድ የሙሰኞችን ጉዳይ የሚመለከት እና ወዲያውኑ ወደ ወህኒ የሚልክ አንድ ልዩ ፍርድ ቤት እንደማቋቁም ነው። »

ያለፉት 20 ዓመታትን የካቢኔ ሚንስትር ያገለገሉት ማጉፉሊ፣ ምንም እንኳን ታታሪ እና ጠንካራ በመሆናቸው ቢታወቁም፣ በፓርቲው ውስጥ ተሰሚነታቸው ያን ያህል ባለመሆኑ አሁን የገዢው «ቻማ ቻ ማፒንዱዚ» ፓርቲ ፕሬዚደንታዊ እጩ ሆነው መመረጣቸው ብዙዎችን አስገርሟል። የማጉፉሊ እጩነት ፖለቲካዊ ስህተት ነው ያሉ አንዳንድ የፓርቲው አባላት ፣ ይኸው ሁኔታ ምናልባት የ«ሲ ሲ ኤም»ን በስልጣን ላይ የመቆየት ዕድሉን አደጋ ላይ ሊጥለው እንደሚችል ሰግተዋል።

ጉቦኝነትን ፣ ድህነትን እና ስራ አጥነትን መታገል፣ እንዲሁም፣ በመሬት ሰበብ ለቀጠሉት ንትርኮች መፍትሔ ማስገኘት የተሰኙት ጉዳዮች የተቃዋሚ ቡድኖች በምርጫ ዘመቻው ወቅት ያነሱዋቸው ዋነኛ ነጥቦች ናቸው። የተቃዋሚ ቡድኖች ለመጀመሪያ ጊዜ በአንድ ፕሬዚደንታዊ እጩ ላይ፣ ማለትም፣ በኤድዋርድ ሎዋሳ እጩነት ላይ በመስማማት ህብረት ፈጥረዋል። ሎዋሳ እአአ ከ2005 እስከ 2008 ዓም ድረስ የሃገሪቱ ጠቅላይ ሚንስትር ነበሩ። ሎዋሳ ይህንኑ የሙስና ወቀሳ በቀረበባቸው ጊዜ ወቀሳውን በጥብቅ በማስተባበል፣ የጠቅላይ ሚንስትርነቱን ስልጣን ለቀዋል። ይህን ተከትሎም፣ የገዢው «ቻማ ቻ ማፒንዱዚ» ፓርቲ አባል የነበሩት ሎዋሳ ለፕሬዚደንታዊው ምርጫ የፓርቲያቸው እጩ ሆነው ለመቅረብ ባለፈው ሀምሌ ወር ባደረጉት ፉክክር በጆን ማፉጉሊ በተሸነፉበት ጊዜ ከፓርቲው በመውጣት የተቃዋሚውን ጎራ ተቀላቅለዋል። ሎዋሳ አሁን አራት ዋነኛ የታንዛንያ ተቃዋሚ ፓርቲዎች፣ ብሎም፣ « ቻዴማ፣ ኤን ሲ ሲአር-ማግዊዚ፣ የተባበረው የሲቪክ ግንባር፣ (ሲ ዩ ኤፍ) እና የሕዝብ ሕገ መንግሥታዊ ህብረት (ኤን ኤል ዲ) የተጠቃለሉበትን ህብረት ይመራሉ። ሎዋሳ በምርጫው ዘመቻ ወቅት ትልቅ ትኩረት ካሳረፉባቸው ጉዳዮች መካከል ለሁሉም የሃገሪቱ ህዝብ የተሻለ የትምህርት ዕድል መስጠት የተሰኘው ርዕስ ነበር።

« በመጀመሪያ፣ መንግሥት ከአንደኛ ደረጃ እስከ ዩኒቨርሲቲ ድረስ ትምህርት በነፃ የሚሰጥበትን አሰራር ማረጋገጥ አለበት። ማንም መጥቶ ይህንን ማድረግ አንችልም ብሎ ሊነግረኝ አይገባም፣ ይህን ማድረግ እንችላለንና። ጥቅም ለሌላቸው ነገሮች ብዙ ገንዘብ ነው የምናጠፋው። ስለዚህ ለልጆቻችን ስንል ገንዘቡን በትክክለኛ መንገድ ጥቅም ላይ እናውለው። »

ምንም እንኳን ታንዛንያ ጉልህ የኤኮኖሚ እድገት ብታስመዘግብም፣ ብዙዎቹ የሃገሪቱ ዜጎች ከዚሁ እደገት ተጠቃሚ አልሆኑም፣ በብዙዎቹ ድሆች እና በጥቂቶቹ ሀብታሞች መካከል ልዩነቱ በየጊዜው እየሰፋ ነው የሄደው። የኮሬንቲ አቅርቦት አሁንም የተወሰነ ነው፣ የጤናውን፣ ትምህርት፣ ግብርና እና የመጓጓዣውን ዘርፎች ለማሻሻል ግን ተጨማሪ አቅርቦች አስፈላጊ እንደሆን ይገኛል።

በአፍሪቃ ዴሞክራሲያዊውን ሥርዓት ከተከሉት አፍሪቃውያት ሃገራት መካከል ቀዳሚ የምትባለዋ መረጋጋት በሰፈነባት ታንዛንያ ውስጥ በምርጫው ዋዜማ ውጥረት ይታያል። በተጭበረበረ የምርጫ ሂደት የሚገኝ ውጤት በሃገሪቱ ሁከት እንዳይቀሰቅስ ብዙዎች ሰግተዋል። ከዚህ በተጨማሪም፣ አንዳንድ የፖለቲካ ፓርቲዎች የወጣቶች ቡድኖቻቸውን ወደ ሚሊሺያ ክንፍ ለመቀየር ሳያቅዱ አልቀሩም የሚል መረጃ እንደደረሰው ብሔራዊው አስመራጭ ኮሚሽን ሰሞኑን የገለጸበት ድርጊት የሕዝቡን ስጋት ማጠናከሩ አልቀረም። እርግጥ፣ ፓርቲዎቹ ይህንን አስተባብለዋል። ይሁን እንጂ፣ የፖለቲካ ተንታኙ እና ደራሲው አቲሎ ታጋሊሌ ማስተባበያውን ይጠራጠረዋል።

« እንዲህ ዓይነቶቹን የሚሊሺያ ቡድኖችን በመጀመሪያ ያቋቋመው አረንጓዴ ዎቹ ዘቦች ያላቸውን ሚሊሺያዎች ያደራጀው ራሱ « ሲ ሲ ኤም » ነው። ሌሎች ፓርቲዎችም ይህን በመከተል፣ የተባበረው ሲቪክ ግንባር ሰማያዊ ዘቦች፣ ቻዴማ ደግሞ ቀዮቹ ዘቦች የተባሉትን ቡድኖች አቋቁመዋል። ባጭሩ ፣ እነዚህ ቡድኖች አደገኞች ናቸው፣ ምክንያቱም፣ ፓርቲዎቹ ቡድናቱን በምርጫው ዕለት ሁከትን ለመቀስቀስ ተግባር ሊጠቀሙባቸው ይችላሉ፣ ከዚህ በተጨማሪ ደግሞ ግልጽ መሆን ያለበት ጉዳይ ፣ የሚሊሺያዎቹ ቡድኖች ሕጋዊ እውቅና ያላገኙ መሆናቸው ነው። »

ንዑሱ የፀጥታ ስጋት በታየበት በአሁኑ ጊዜ የሃገሪቱ ፕሬዚደንት ኪክዌቴ እና የሀይማኖት መሪዎች ምርጫው በሰላማዊ ሁኔታ እንዲካሄድ ጥሪ አሰምተዋል።

ታንዛንያውያን በነገው ዕለት ከፕሬዚደንታዊው ምርጫ ጎን ለጎን ብሔራዊውን ምክር ቤታ እና ያካባቢ መስተዳድሮችንም ይመርጣሉ። ከዚህ በተጨማሪም፣ የከፊል ራስ ገዝዋ የዛንዚባር ደሴት ነዋሪዎች ከአጠቃላዩ የታንዛንያ ምርጫ ጎን፣ አዲስ የዛንዚባር ፕሬዚደንት እና ምክር ቤት ይመርጣሉ።

በታንዛንያ ባጠቃላይ ለውጥ እንዲኖር ከፍተኛ ፍላጎት ይታያል። ይሁንና፣ ጥያቄው፣ የተቃዋሚ ፓርቲዎች ህብረት ገዢውን የቻማ ቻ ማፒንዱዚን ፓርቲ ከስልጣን ኮርቻ ላይ ማንሳቱ ይሳካለታል ወይ የሚለው ነው። ይህ እውን ከሆነ የቻማ ቻ ማፒንዱዚ ፓርቲ በምርጫ ሳጥን ከስልጣን የተወገዱትን ፣ በዛምቢያ የዶክተር ኬኔት ካውንዳ የተባበረው ብሔራዊ የነፃነት ፓርቲ፣ በማላዊ የዶክተር ሄስቲንግ ካሙዙ ባንዳ የማላዊ ኮንግረስ ፓርቲ፣ እንዲሁም፣ የኬንያ አፍሪቃውያን ብሔራዊ ህብረት ፓርቲን የመሳሰሉትን የነፃነት ፓርቲዎችን ጎራ ይቀላቀላል።

የታንዛንያ ሕገ መንግሥት ሁለት የስልጣን ዘመናቸውን በሚፈቅደው መሠረት ያጠናቀቁት ፕሬዚደንት ጃካያ ኪክዌቴ ፣ የሕዝብን ተቃውሞ በመርገጥ ለሶስተኛ የስልጣን ዘመን በተመረጡት በቡሩንዲው አቻቸው ፒየር ንኩሩንዚዛ አንጻር፣ ወይም ለሶስተኛ ጊዜ ለመወዳደር እየተዘጋጁ ነው በሚባሉት የርዋንዳ እና የኮንጎ ሬፓብሊክ አቻዎቻቸው አንፃር አዲሱ ፕሬዚደንት ቃለ መሀላ እንደፈፀመ ስልጣናቸውን ይለቃሉ።

መሀመድ አብዱራህማን

አርያም ተክሌ

ልደት አበበ

Audios and videos on the topic