‘አገራዊ ንግግር’ ወይስ ‘ፖለቲካዊ ዕርቅ’? | ኢትዮጵያ | DW | 25.06.2021
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

ኢትዮጵያ

‘አገራዊ ንግግር’ ወይስ ‘ፖለቲካዊ ዕርቅ’?

የሰኔ 14ቱ ምርጫ የተሰጋውን ያክል ነውጥ ሳይገጥመው ተጠናቋል፤ ነገር ግን የምርጫዎች ዋና ዓላማ በሰላም መጠናቀቃቸው ሳይሆን የብዙኃንን ይሁንታ ለመንግሥት ማስገኘት መቻላቸው ነው። በአሁኑ ሁኔታ ምርጫው ፍትሐዊ ፉክክር የታየበት ባለመሆኑ ምክንያት የብዙኃን ይሁንታ "በሰላም ማለፉ" ላይ ብቻ አተኩሯል።

‘አገራዊ ንግግር’ ወይስ ‘ፖለቲካዊ ዕርቅ’?

በፍቃዱ ኃይሉ

የሰኔ 14ቱ ምርጫ የተሰጋውን ያክል ነውጥ ሳይገጥመው ተጠናቋል፤ ነገር ግን የምርጫዎች ዋና ዓላማ በሰላም መጠናቀቃቸው ሳይሆን የብዙኃንን ይሁንታ ለመንግሥት ማስገኘት መቻላቸው ነው። በአሁኑ ሁኔታ ምርጫው ፍትሐዊ ፉክክር የታየበት ባለመሆኑ ምክንያት የብዙኃን ይሁንታ "በሰላም ማለፉ" ላይ ብቻ አተኩሯል። ይህ ግን ለኢትዮጵያ ፖለቲካዊ ቀውስ ዘላቂ መፍትሔ አያመጣም።

በድኅረ ምርጫው ጊዜ በሒደቱ ያልተሳተፉትን እንዲሁም ተሳትፈው በኃይልና ሀብት አለመመጣጠን ሳቢያ የተሸነፉትን አካላት ያቀፈ ፖለቲካዊ ዕርቅ በማድረግ ለቀጣዩ ፍትሐዊ ምርጫ እንዲኖር መደራደሪያ ጊዜ ነው። ምክንያቱም የአንድ ፓርቲ በትልቅ ድምፅ ማሸነፍ ዴሞክራሲንም፣ ዘላቂ ሰላምንም አያመጣም። ምርጫ 2007 በኢሕአዴግና አጋሮቹ መቶ በመቶ አሸናፊነት በተጠናቀቀ በ6 ወር ውስጥ የማያባራ ሕዝባዊ አመፅ ተቀስቅሶ ነበር።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ “የመጀመሪያው የነጻ እና ፍትሐዊ ምርጫ ሙከራ” ያሉት ምርጫ 2013፣ በብዙ መሥፈርቶች ከምርጫ 97 ያነሰ፣ ነገር ግን ካለፉት ሁለት አገር ዐቀፍ ምርጫዎች የተሻለ ምርጫ ሆኖ እያለፈ ቢሆንም፥ ነጻ እና ፍትሐዊ ግን አልነበረም። ለዚህም ይመስላል የምርጫ ቦርድ መሪዎች “ነጻ እና ፍትሐዊ ምርጫ” በሚለው ምትክ “ተዓማኒነት ያለው” የሚለውን ገለጻ ሲጠቀሙ የከረሙት። ቀጣዩ ጥያቄ በመጪዎቹ አምስት ዓመታት ምን ይሠራበት የሚለው ነው። በዚህ ጽሑፍ በቀጣዮቹ በርካታ ወራት የሚያስፈልገው ብዙ የተባለለት “ብሔራዊ ንግግር” ሳይሆን “ፖለቲካዊ ዕርቅ” ነው ብዬ እከራከራለሁ።

“ፍትሐዊ” ያልተባለው ምርጫ

እንደቀደሙት አገር ዐቀፍ ምርጫዎች ሁሉ ምርጫ 2013ም የአቻዎች ውድድር አልነበረም። በገዢው ፓርቲ እና በተቀናቃኞቹ መካከል የነበረው የሥልጣንና ኢኮኖሚ አቅም የትየለሌ ነው። በዚያ ላይ በገዢው ፓርቲ እና በመንግሥት ያለው ጋብቻ ለገዢው ፓርቲ ድጋፍ ማሰባሰቢያነት የመንግሥትን መዋቅር ለመጠቀም አስችሎታል። ይህም ምርጫውን “ፍትሐዊ” እንዳይሆን አድርጎታል። የምርጫ ቦርድ ኃላፊዎች በገለጻዎቻቸው ላይ “ነጻ እና ፍትሐዊ” የሚሉ ቃላቶችን ሲጠቀሙ አልተስተዋሉም። ጭንቀታቸው ሒደቱን እና ውጤቱን ተዓማኒ ማድረግ ላይ ብቻ ያተኮረ ይመስላል።

ይህንን ኢፍትሐዊነት ያስተዋሉት የፖለቲካ ድርጅቶች ራሳቸውን ከሒደቱ አውጥተዋል። ይህንን ኢፍትሐዊነት ተረድተው ነገር ግን የተገኘውን ውጤት ለማግኘት ውድድሩ ውስጥ የገቡት የፖለቲካ ድርጅቶችም አብላጫ ድምፅ እንደማያገኙ፣ ነገር ግን የተወሰነ ውክልና ካገኙ ያንን ይዘው ለመንደርደር በማሰብና "ዋናው ግባችን ቀጣዩ ምርጫ ነው" በማለት ውድድሩ ውስጥ በየጊዜው አቤቱታቸውን እያሰሙ አጋጣሚውን መለማመጃ አድርገውታል።

እንዲያም ሆኖ የመጀመሪያው ዙር እና ቀጣዩን መንግሥት ማንነት የመወሰን ዕድል ያለውን የሰኔ 14ቱ ምርጫ በተካሔደ ማግስት ከየምርጫ ጣቢያው የተሰበሰቡት ውጤቶች ግን ብዙዎችን አስደንግጠዋል። በመጪው አምስት ዓመታት ተቃዋሚዎች፣ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በርከት ያሉ መቀመጫዎችን ያገኛሉ ተብሎ ተስፋ የተጣለውን ያክል ሳይሆን ቀርቶ፣ ብልፅግና ፓርቲ እንዳለፉት ሁለት ምርጫዎች “ስታሊናዊ” የሚሰኝ ድል እንደተቀናጀ ከወዲሁ መታወቅ ጀመረ። ፓርቲዎቹ በምርጫው ቀን በርካታ ቅሬታዎች አስመዝግበዋል፤ ሆኖም ቅሬታዎቹ ቢታረሙም መሠረታዊ ለውጥ አይመጣም። ውጤቱ የተወሰነው በገዢው ፓርቲ እና በተቃዋሚዎቹ መካከል ባለው የኃይልና ኢኮኖሚ አቅም የገዘፈ መበላለጥ ሳቢያ ነው። ስለሆነም በምርጫ 2013 ፍትሐዊ ምርጫ ማድረግ ከናካቴው የሚታሰብ አልነበረም።

ምርጫው ከተከናወነ በኋላ "በአንድም በሌላም መንገድ ሕዝቡ ተናግሯል" የሚሉ አባባሎች በተደጋጋሚ እየተደመጡ ነው። በምርጫ ለውጥ የሚመጣበት ጊዜ ደርሷል ብለው ያሰቡ ሰዎች "ሆ" ብለው ወጥተው መርጠዋል። በተለይ እንዳዲሳባ ባሉ ባመዛኙ በነፃ ፈቃድ የተወጣባቸው አካባቢዎች እዚህ ይመደባሉ። ለውጥ አይመጣም ብለው ያሰቡትም ከቤት ተቀምጠው የሚሆነውን ለመቀበል ወስነዋል። በርግጥ በክልሎች ውስጥ፣ በተለይም በኦሮሚያ ውስጥ፣ በከፍተኛ ግፊት የተሳተፉ ዜጎች እንዳሉ ተሰምቷል። ያም ሆነ ይህ "በአመፅ ጊዜ ዜጎች ሰላምን ይመርጣሉ" የሚባለው ሆኗል። ለኢትዮጵያውያን ለውጥ ሰላም የሚበጠብጥ ጉዳይ ሊሆን ስለሚችል የቅርብ ጊዜ ትዝታቸው በመሆኑ፣ በዝምታም ይሁን በተሳትፎ ከለውጥ ይልቅ በሰላም ውሎ ማደርን መርጠዋል ማለት ይቻላል፤ ይህ የሚያሳየው ዜጎች በለውጥ ሰላማዊነት ላይ ያላቸውን እምነት ማጣታቸውን እንጂ ለውጥ አለመፈለጋቸውን አያሳይም። ስለሆነም ነውጥ አልባ ለውጥ የሚያገኙበት ዕድል ይገባቸዋል።

አገራዊ ንግግር ወይስ ፖለቲካዊ ዕርቅ?

በአሁኒቷ ኢትዮጵያ፣ በአንድ በኩል በምርጫ ለውጥ አይመጣም የሚሉ አካላት አገራዊ ንግግር ይደረግ የሚል መፍትሔ ይጠቁማሉ፤ ሌሎች ደግሞ በሌላ በኩል በሕዝብ ምርጫ የሚደረግ ውክልና በሌላቸው ሰዎች መካከል የሚደረግ ምክክር ሕዝባዊ ተቀባይነት አይኖረውም ይላሉ። ምርጫው ደግሞ በተበላለጠ የኃይል እና የኢኮኖሚ አቅም ያላቸው አካላት መካከል የሚደረግ ኢፍትሐዊ ምርጫ ስለሆነ የእውነተኛ ሕዝባዊ ውክልና ማግኘት ይቸግራል። እዚህ መሐል ነው የፖለቲካዊ ዕርቅ አማካይ መንገድ ሆኖ መምጣት የሚኖርበት።

አገራዊ ንግግር በጣም ውስብስብ የሆነ፣ በርካታ የማኅበረሰብ ክፍሎችን በየእርከኑ የሚያሳትፍ፣ በይነብሔራዊ፣ በይነሃይማኖታዊ፣ እንዲሁም በይነመደባዊ ንግግር ነው። የሚደረገውም ለአጭር ጊዜ ሳይሆን ረዘም ላለ ጊዜ በተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች ዘንድ ጤናማ መስተጋብርን ለማዳበር እና እርስበርስ መገነዛዘብን ለመፍጠር ነው። በኢትዮጵያ ፖለቲካዊ ተዋስኦ አገራዊ ንግግር ሲባል የሚደመጠው፣ የተለያየ ፖለቲካዊ አመለካከትና ደጋፊ ያላቸው መሪዎች በጠረንጴዛ ዙሪያ ቁጭ ብለው እና የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤትን ተክተው የሚደራደሩበት፣ ሥልጣን የሚከፋፈሉበትና መፃዒ የኢትዮጵያ እና የኢትዮጵያውያንን ዕጣ ፈንታ የሚወስኑበት የሽግግር መንግሥት ባሕሪ ያለው መድረክ ነው። ይህ ዓይነቱ አካሔድ በኢትዮጵያ ውስብስብ ነባራዊ ሁኔታ ውስጥ ዘላቂ ሰላም ያመጣል ብሎ ማሰብ የዋህነት ይመስለኛል። ምክንያቱም ከመጀመሪያው የብዙኃንን ይሁንታ የለውም።

ይልቁንም የፖለቲካ መሪዎቹ በአገራዊ ንግግር ሥም ተቀራርቦ መነጋገር እና መግባባት የሚያስፈልጋቸውን  የዜጎች ማኅበረሰባዊ ቅራኔዎች በማራገብ እና ድጋፍ በማንቀሳቀስ ወደለየለት ብጥብጥና ግጭት ሊያመሩ ስለሚችሉ፣ በገለልተኛ ወገኖች ሊመቻች የሚገባው የፖለቲካዊ ዕርቅ መድረክ ነው። ይኸውም በፖለቲከኞቹ መካከል ያለውን ቅራኔ የሚፈታ እና የተመቻቸ ምኅዳር ፈጥሮ በእኩል ወይም ተቀራራቢ ኃይል እና የኢኮኖሚ አቅም ወደ ምርጫ ገብተው ሕዝባዊ ይሁንታ የሚጠይቁበት መንገድ እንዲመቻች ማድረግ ነው።

የፖለቲካ ዕርቅ መድረኩ፣ ተሳታፊዎቹን የመንግሥት የዴሞክራሲ ተቋማትን መሪዎች በጋራ ዕጩ አድርገው የሚሾሙበት፣ ምርጫና ምርጫ ነክ የሆኑ ጉዳዮችን የሚመለከቱ ሕግጋት ክለሳ ጉዳይ ላይ በጋራ የሚደራደሩበት እና የሚወስኑበት፣ የዴሞክራሲ ተቋማት መልሶ መዋቀር ላይ በጋራ የሚወስኑበት ሥልጣን እንዲኖረው በማድረግ በቀጣይ ፍትሐዊ ምርጫ እንዲዘጋጅ እና ገዢው ፓርቲ ሥልጣኑን ለማስጠበቅ፣ ተቃዋሚዎቹ ሥልጣን ለመቀማት የሚደረጉ ኃይል አዘል ንቅናቄዎችን በሙሉ ለማስቆም የሚስማሙበት መድረክ ሆኖ መዘጋጀት ማድረግ ይቻላል።

ፖለቲካዊ ዕርቆች በአንድ በኩል፣ አገራዊ ንግግሮች ደግሞ በሌላ በኩል ሊካሔዱ ይችላሉ። ነገር ግን ፖለቲካዊ ዕርቅ የሚያስፈልጋቸውን ጉዳዮች በአገራዊ ንግግር ማዕቀፍ ለማስኬድ መሞከር ውጤቱ ማኅበራዊ ቀውሶች ከድጡ ወደ ማጡ መስደድ ሊሆን ይችላል።

 

በዚህ አምድ የቀረበው አስተያየት የጸሐፊውን እንጂ የዶይቸ ቬለን አቋም አያንጸባርቅም።

ተዛማጅ ዘገባዎች