አዳጋቹ የጦር መሣሪያ ቁጥጥር ዉል | ዓለም | DW | 29.03.2013
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ዓለም

አዳጋቹ የጦር መሣሪያ ቁጥጥር ዉል

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት አጠቃላይ ጉባዔ፣ የጦር መሣሪያዎች ቁጥጥር በውል እልባት ያገኝ ዘንድ ትናንት እንደገና ለሁለተኛ ጊዜ ጥረት ቢያደርግም ባልታሰቡ አገሮች ተቃውሞ ሊከሽፍ ችሏል።

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ጸሐፊ ባን ኪ ሙን ፣ በዓለም ዙሪያ፣ የ «ቲ ሸርት» ቲማቲምና አሻንጉሊት ንግድ ደንብ ወጥቶለት በሥርዓት ይካሄዳል፤ የጦር መሣሪያ ንግድ ግን አንዳች ቁጥጥር ሳይደረግበት መካሄዱን ቀጥሏል በማለት በጥብቅ ነው የነቀፉት።
የጦር መሣሪያ ንግድ ቁጥጥር በውል እንዲታሠር የሚፈለገው፤ የሚሸጠው ጦር መሳሪያ፣ ሰብአዊ መብትን ለመደፍጠጥ ውሎ እንደሁ ለማጣራት ነው። ከዚህም ሌላ ጦር መሳሪያ ከአሸባሪዎችና ከተደራጁ ወንጀለኞች እጅ እንዳይገባ ለመቆጣጠር እንደሚያመች ታምኖበት ነው። ውዝግብ ባለባቸውና ውጊያ በሚካሄድባቸው የዓለማችን ክፍሎች፤ በያመቱ ከ 500,000 በላይ ሰዎች ይገደላሉ ። የጦር መሳሪያ ንግድ ደንብ እንዲወጣለት ከሚሹትና በዚህም ረገድ ለመተባበር ዝግጁ ከሆኑት አገሮች አንዷ ጀርመን ናት። አንድ የጀርመን የውጭ ጉዳይ ሚንስቴር ቃል አቀባይ እንዳሉት፤ ህጋዊነት ያለው የጦር መሣሪያ ንግድ ፣ ለሰላምና ለአካባቢ መረጋጋት ጠቀሚ ድርሻ ይኖረዋል።


የሰብአዊ መብት ተሟጋቾች፤ እንደሚያስረዱት፤ በድርድር እልባት ያልተደረገለት የጦር መሣሪያ ንግድ፣ በተለያዩ መንገዶች፤ አደገኛ ከሆኑ ሰዎች እጅ መግባቱ አይቀሬ ነው። የ OXFAM ባልደረባ፣ ሮበርት ሊንድነር እንደሚሉት፤ በህግ ሊያስጠይቅ የሚችል ውል ሊኖር ይገባል። ትናንት ኒው ዮርክ ውስጥ፣ የተካሄደውን ድርድር የተከታተሉት ሊንድነር፣ ለዶቸ ቨለ በሰጡት ቃል፤ ጅምላ ጭፍጨፋ፤ የጦር ወንጀል፤ በሰብአዊነት ላይ ግፍ ፣ እንዲሁም ሆን ተብሎ ሰብአዊ መብት ጥሰት እንዲፈጸም በሚደረግባቸው አካባቢዎች ጦር መሳሪያ እንዳይቀርብ ፈጽሞ መታገድ አለበት ነው ያሉት። የተባበሩት መንግሥታት፣ በዓለም ዙሪያ በጦር መሣሪያ ንግድ ላይ ቁጥጥር ማድረግ የሚቻልበት ውል ይፈረም ዘንድ ጥረት ማድረግ ከጀመረ 7 ዓመት ሆኖታል። የመጀመሪያው የውል ረቂቅ ሰነድ፣ ባለፈው ዓመት በሐምሌ ወር ተቀባይነት ሳያገኝ የቀረው፤ ዩናይትድ እስቴትስ፤ ሩሲያና ቻይና በመቃወማቸው ነው። ዘንድሮ ግን፤ እነርሱ ሳይሆኑ ፤ ያልተጠበቁት፣ ኢራን፤ ሰሜን ኮሪያና ሶሪያ ሆነዋል፣ ረቂቁን ህግ መቅኖ ያሳጡት። ረቂቁ ውል እንዲጸድቅ፤193 ቱ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት አባል ሃገራት ሁሉ መስማማት ነበረባቸው። አሁን ረቂቁን ውል ያከሸፉት ሀገራት ፤ ምዕራቡ ዓለም በእኩይ ሥርዓት የሚመሩ ናቸው በማለት እንደሚተቻቸው የታወቀ ነው። ሰሜን ኮሪያና ኢራን የጦር መሳሪያ እገዳ የተጣለባቸው አገሮች ሲሆኑ፣ ሦሪያ፤ በአርስ-በርስ ጦርነት ከተጠመድች፣ አሁን 3ኛ ዓመቷን ይዛለች።


ትናንት ኒው ዮርክ ውስጥ በተባበሩት መንግሥታት ድምፅ እንዲሰጥበት የቀረበው ረቂቁ ውል፤ የጦር መሣሪያና የጥይት ዓይነት በሚሰኘው ነጥብ ላይ ከበድ ያሉ አሻሚ ሁኔታዎች መከሠታቸውን የኦክስፋሙ ባለሙያ ሊንድነር የጠቆሙ ሲሆን፤ የጥይት ዓይነቶችን የመመርመሩ ሁኔታም እልባት አልተደረገለትም። የጦር መሳሪያ ክፍሎችና መለዋወጫዎችም በቂ ትኩረት አልተደረገባቸውም። ቅድሚያ ሊሰጥ የተፈለገው፤ ለታላላቆቹ የጦር መሳሪያዎች--ታንኮች፤ የጦር አኤሮፕላኖችና የጦር መርከቦች ነው።
ትናንሽ የጦር መሳሪያዎች ችላ የተባሉ ነው የሚመስለው። ሊንድነር እንደገለጹት ደግሞ የብዙ ሰዎች ህይወት የሚቀጠፈውና የመቁሰል አደጋ የሚያጋጥማቸውም ፣ በእነዚሁ ትናንሽ የጦር መሳሪያዎች ነው። በዓለም ዙሪያ 900 ሚሊዮን ያህል ጠብመንጃዎች በመዘዋወር ላይ ናቸው፤ ዓለም አቀፉ የሰብአዊ መብት ተሟጋች ድርጅት AI እንዳስታወቀው፤ በየደቂቃው፤ አንድ ሰው በሽጉጥ ተኩስ ሳቢያ ህይወቱ ታልፋለች። በያመቱ በጦር መሣሪያ ሽያጭ 60 ቢሊዮን ዩውሮ ገቢ ይገኛል።


የጦር መሳሪያ ውል እንዳይኖር የሚያከልክል መንግሥት የለም። እርግጥ በዛ ያሉ መንግሥታት፣ በዚህ ረገድ የኤኮኖሚ ጥቅማቸው እንዳይካ በመሻት አንዳንድ አንቀጾች እንዲለወጡ ይፈልጋሉ። በጥይት ዓይነቶችና በጦር መሣሪያ መለዋወጫዎች ሳቢያ የሚያንገራግሩ፤ ሩሲያ ፤ ዩናይትድ እስቴትና ቻይና ናቸው። ህንድ፤ ብራዚልና ደቡብ አፍሪቃም የራሳቸውን የጦር መሣሪያ ፋብሪካ መገንባት ይፈልጋሉ። ጥብቅ ቁጥጥር ሲደረግ፤ ለጦር መሳሪያ የሚያስፈልጉ ቁሳቁሶች ይጓደሉብናል የሚል ሥጋት በማንጸባረቅም ነው የተጠቀሱት አገሮች፤ ቁጥጥሩን የሚቃወሙት።
እነዚህ አገሮች፣ አቋማቸው የሚያናድድ መሆኑንም ነው ሊንድነር የገለጹት። በዚህ አያያዛቸው ውል እንኳ ቢፈረም ፣ ውሉን የሚያከብሩ ስለመሆናቸው የሚያስተማምን ሁኔታ አይኖርም።

ሚርያም ጌርከ

ተክሌ የኋላ

ነጋሽ መሐመድ

Audios and videos on the topic