አዳጋቹ የርዳታ አቅርቦት ለዳርፉር | የጋዜጦች አምድ | DW | 14.02.2005
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

የጋዜጦች አምድ

አዳጋቹ የርዳታ አቅርቦት ለዳርፉር

የተመድ የፀጥታ ጥበቃ ምክር ቤት አባላት በሱዳን የዳርፉር ግዛት በሚኖረው ጥቁሩ ሕዝብን በመጨፍጨፍ የስብዕና ወንጀል የፈፀሙትን ወገኖች በጥብቅ አውግዘዋል።

ተጠያቂዎቹን ለፍርድ ለማቅረብ ቆርጠው መነሣታቸውንም ምክር ቤቱን በሊቀ መንበርነት የሚመሩት የቤኒን አምባሳደር ዦዌል አደቺ አስታውቀዋል፤ ይሁንና፡ ስለሱዳን ጉዳይ የመከሩት የምክር ቤቱ አባል ሀገሮች ተጠያቂዎቹ በምን ዓይነት ፍርድ ቤት ፊት መቅረብ አለባቸው በሚለው ጥያቄ ላይ እስካሁን አንድ ስምምነት ላይ አልደረሱም። ብዙዎቹ የምክር ቤቱ አባል መንግሥታት ተጠያቂዎቹን ዴን ኻግ ኔዘርላንድስ በሚገኘው ዓለም አቀፍ የወንጀል ጉዳይ ተመልካች ፍርድ ቤት ፊት እንዲቀርቡ ፍላጎታቸውን ቢገልፁም፡ የፍርድ ቤቱን ኅልውና አጥብቃ የምትቃወመው ዩኤስ አሜሪካ የወንጀለኞቹን ጉዳይ የተመድ እና የአፍሪቃ ኅብረት ያቋቋሙት መንበሩ አሩሻ ታንዛንያ የሚገኘው ፍርድ ቤት እንዲመለከተው ሀሳብ አቅርባለች። በሌላ በኩል ደግሞ ሱዳን ተጠያቂዎቹ ዜጎችዋ ከሀገርዋ ውጭ በሚካሄድ ችሎት እንዲፈረዱ የቀረበውን ሀሳብ በፍፁም እንደማትቀበለው ያስታወቀቸት መግለጫ የፀጥታ ጥበቃ ምክር ቤቱን ክርክር ይበልጡን ውስብስብ አድርጎታል። በፀጥታ ጥበቃ ምክር ቤቱ ውይይት ላይ እንዲካፈሉ የተጋበዙት የሱዳን የመጀመሪያው ምክትል ጠቅላይ ሚንስትር አሊ ኦስማን ታሀ በዳርፉር የስብዕና ወንጀል ፈፅመዋል የሚባሉትን ተጠያቂዎችን ጉዳይ ባለሙሉ ችሎታ ነው የሚሉት የሱዳን የፍትሕ አውታር የመመልከት አቅምና ፍላጎት እንዳለው በማስረዳት የምክር ቤቱን አባል መንግሥታት ድጋፍ ለማግኘት ሞክረዋል። ችሎቱን ከሱዳን ውጭ ማካሄዱ የግዛቱ ሕዝብ ዕርቀ ሰላም እንዲፈጥር በመርዳት ፈንታ ሁኔታዎችን ይበልጡን አዳጋች ያደርጋል ሲሉ ታሀ አስጠንቅቀዋል። ካለፉት በርካታ ወራት ወዲህ ስለ ዳርፉር ጊዚያዊ ሁኔታ ለተመድ የቀረቡት ዘገባዎች በጠቅላላ የሱዳን መንግሥት በዳርፉር ግዛት በሱዳን ቶር ይረዳሉ የሚባሉት ዣንዣዌድ በሚል መጠሪያ የሚታወቁት ዐረባውያኑ ሚሊሲያዎጭ በግዛቱ ጥቁር ሕዝብ ላይ የቀጠሉት የኃይል ተግባርን ለማስቆም አንዳችም ሙከራ አለማድረጉን አሳይተዋል። በዳርፉር ለሚታየው የስብዕና ወንጀል በኃላፊነት የሚጠየቁትን ወገኖች በየትኛው ፍርድ ቤት ይታይ የሚለው ጉዳይ የፀጥታ ጥበቃ ምክር ቤቱን አባላት በከፋፈለበት ባሁኑ ጊዜ፡ በዳርፉር የሚገኙት የርዳታ ድርጅቶች አብዝቶ ያሳሳባቸው ለግዛቱ ተፈናቃይ ሕዝብ ርዳታ ለማቅረብ በሚያደርጉት ጥረታቸው ላይ በየቀኑ የገጠማቸው ችግር ነው። የፀጥታው ሁኔታ አስተማማኝ ያልሆነበት ድርጊት የርዳታ አቅርቦቱን አዳጋች እያደረገው አሉታዊ ተፅዕኖ እንዳሰረፈ በሱዳን የተመ የሕፃናት መርጃ ድርጅት ዩኒሴፍ ተጠሪ ሮሻን ካዲቪ አስታውቀዋል። ባካባቢው በቀጠለው የኃይል ተግባር የተነሣ አንዳንድ የርዳት ድርጅቶች ግዛቱን ለቀው በመውጣታቸው በወቅቱ በሰሜንና በምዕራብ ዳርፉር በተተከሉ የስደተኞች መጠለያ ጣቢያዎች ላሉት ሁለት ሚልዮን ተፈናቃዮች የሰብዓዊ ርዳታ የሚቀርብበት ሂደት ይበልጡን አዳጋች አድርጎታል። መንበሩ ብሪታንያ የሚገኘው ግብረ ሠናይ ድርጅት ሴቭ ዘ ችልድረን ባለፈው አውሮጳዊ ዓመት መጨረሻ ገደማ አራት ሠራተኙ ከተገደሉበት በኋላ ዳርፉርን ለቆ ወትቶዋል።
በምዕራብ ሱዳን የሚንቀሳቀሱት የሱዳን ነፃ አውጪ ጦርና የፍትሕና የዴሞክራሲ እንቅስቃሴ ዓማፅያን የካርቱም ማዕከላይ መንግሥት አካባቢያቸውን ከፖለቲካው፡ ከኤኮኖሚያዊው እና ከልማቱ ተግባር አግልሎዋል በሚል ከሁለት ዓመት በፊት ነበር በመንግሥቱ አንፃር ትግላቸውን የጀመሩት። የሱዳን መንግሥት በዚሁ ጊዜ ለውዝግቡ መፍትሔ በማፈላለግ ፈንታ፡ ዓማፅያኑን መንቀሳቀሻ ለማሳጣት ሲል በዳርፉር ባሉት የፉር፡ የማሳሊትና የዛግዋ ነገዶች አንፃር በጦሩ አማካይነት ትግሉን አጠናከረ። ከዚህ በተጨማሪም፡ ውኃና የግጦሽ መሬት ፍለጋ ከደረቁ ሰሜን ሱዳን ወደ ምዕራቡ በመሄድ በዚያ ከሚገኘው ነዋሪ ጋር በተደጋጋሚ ሲጋጩ የነበሩት በሱዳን ጦር ይረዳሉ የሚባሉት የዣንዣዌድ ዐረባውያን ሚሊሺያዎች የጥቃት፡ የዝርፊያና የክብረ ንፅሕና መድፈር ተግባራቸውን ሲያካሂዱ መንግሥት እንዳላየ ማየቱን ቀጠለ።
በተመድ ዘገባ መሠረት፡ በውዝግቡ እስከዛሬ ወደ ሰባ ሺህ ሰው ሲሞት እስከ ሁለት ሚልዮን ደግሞ ከቤት ንብረቱ ተፈናቅሎዋል። የተመድ ሁከቱን ለማስቆም በተደጋጋሚ ያደረገው ጥረቱ እእስካሁን ፍሬ አላስገኘለትም። ለዚህም ተቀናቃኞቹ ወገኖች የጦርና የፖለቲካ አቋማቸውን ለማጠናከር እያሉ የተደረሱትን የተኩስ አቁም ደምቦች በመጣሳቸው ሰበብ በመካከላቸው መተማመን የጠፋበት ድርጊት፡ እንዲሁም የሱዳን መንግሥትም ሚሊሺያዎቹን የጦር መሣሪያ ጥጥቅ እንዲያስፈታ የፀጥታ ጥበቃ ምክር ቤቱ ያቀረበለትን ቅድመ ግዴታ አለማክበሩ ተጠያቂ ናቸው። ዩኤስ አሜሪካና አንዳንድ ሀገሮች የዳርፉር ውዝግብ ከርዋንዳ የጎሣ ጭፍጨፋ ጋር የሚነፃፀር ነው በሚል ክስ ካሰሙ በኋላ የተመድ ክሱን እንዲመረምር ያቋቋመው ኮሚሽን፡ የኃይሉ ተግባር አስከፊ መሆኑን ቢያመለክትም የጎሣ ጭፍጨፋ ነው ከማለት ተቆጥቦዋል። የአፍሪቃ ኅብረትም ለዳርፉር የተደረሰውን የተኩስ አቁም የሚቆጣጠር በጥቂት መቶ የሚቆጠሩ ወታደሮች ያሉት አንድ ጓድ ልኮዋል፤ ይሁንና፡ ይኸው ጓድ አሁን ባለው አቅም ተልዕኮውን መወጣቱ ስለሚያዳግተው ብዙዎች የሚጠናከርበት ርዳታ ለአፍሪቃ ኅብረት እንዲቀርብ ጠይቀዋል። የአፍሪቃ ኅብረት ወቅታዊ ሊቀ መንበርነትን የያዘችው ናይጀሪያ በአቡጃ ለዳርፉር ውዝግብ መፍትሔ ያፈላለገችበት ትረትዋ ባለመሳካቱ፡ በዚህ ወር መጨረሻ ሌልብሰባ በግብፅ ካይሮ በመጥራት ሙከራው እንዲቀጥል ጠይቃለች። አውሮጳዊው ዓመት 2005 ሳያበቃ በፊት ለዳርፉር ሰላም እንዲወርድ የሚሹት የተ መድ ልዩ የሱዳን ተጠሪ ፕሮንክም ከብዙ ዓመት የርስበርስ ጦርነት በኋላ ባለፈው ወር የሰላም ውል በደረሱት የሱዳን ማንግሥትና በደቡብ ሱዳን ሕዝብ ነፃ እጪ ጦር ኤስፒ ኤል ኤ መካከል የተቋቋመው የሀገሪቱ ብሔራዊ አንድነት መንግሥት በዚሁ ጥረት ላይ ወሳኝ ሚና እንዲይዝ አሳስበዋል።