አዳጊ ሴቶች እና ሳይንስ  | ወጣቶች | DW | 03.08.2018
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ወጣቶች

አዳጊ ሴቶች እና ሳይንስ 

ዛሬም ድረስ ሳይንስና ሒሳብን ለወንዶች ብቻ የተተዉ አድርጎ የመቁጠር ዝንባሌ ይታያል። ይኸ አይነቱ እምነት በኬንያ አሁንም ተቀባይነት ያለው ነው። ይሁንና በሞምባሳ ወጣት ሴቶች ከከፍተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት እስከ ዩኒቨርሲቲዎች ከፍተኛ ውጤት በማምጣት እንዲህ ዓይነቱ ዕምነት ዋጋ እንደሌለው እያሳዩ ነው።  #77በመቶው #77% 

የፕዋኒ ቴክኖውጋልዝ አባላት እየተሳሳቁ ከስዋሒሊፖት ሕንጻ በር ላይ ተቀምጠዋል። ድርጅቱ ከሦስት አመታት በፊት በትምህርት ቤቶች እና ዩኒቨርሲቲዎች ያሉ ታዳጊ ሴቶች በሳይንስ፣ ቴክኖሎጂ፣ ኢንጂኔሪንግ እና ማቲማቲክስ ዘርፎች እንዲሳተፉ እና ለሙያቸው መሠረት እንዲጥሉ ለማበረታታት የተቋቋመ ነው። 

ላቲፋህ ዋንጃ የ20 አመት ወጣት ሳለች ጀምሮ የድርጅቱ አባል ነች። ላቲፋህ "ኮምፒዩተር፣ ሳይንስ እና ቴክሎጂ ላጠና ኮሌጅ ስገባ በመማሪያ ክፍሌ ውስጥ ያገኘሁት ሦስት ሴት እና 30 ወንድ ተማሪዎችን ነበር። የዚያን ጊዜ ሴቶች ቴክኖሎጂን እንዲጠቀሙ ልናበረታታ እንደሚገባ አሰብኩ። በዚህም በሁሉም ዘርፎች ቁጥራችን ካደገ ቴክኖሎጂ የፈለግንውን ችግር ሁሉ ለመፍታት ጥቅም ላይ ሊውል ይችላል" ስትል እንዴት ወደ ዘርፉ እንደተቀላቀለች ትናገራለች። የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቷን እንዳጠናቀቀች ኡሳላማ ፕላስ ፕላስ ፕላስ የተባለ የሞባይል መተግበሪያ (አፕልኬሽን) አዘጋጅታ ነበር። ኡሳላማ የስዋሂሊ ቃል ሲሆን ደኅንነት የሚል ትርጉም አለው።  

"የመጀመሪያው ፕላስ ስለ ደኅንነት ነው። ሁለተኛው ፕላስ የቆሻሻ ማጠራቀሚያዎች የሚገኙበትን ቦታ ለመለየት የሚያገለግል አቅጣጫ ጠቋሚ ነው። ምክንያቱም በሞምባሳ በርካታ ቆሻሻ ይገኛል። ሦስትኛው ደግሞ ያልታጋበዘ ሰው ድንገት ወደ መኖሪያ ቤታችን ሲመጣ በእጅ ስላካችን አማካኝነት ጥቆማ የሚሰጠን ነው"ትላለች ስለ ሰራችው መተግበሪያ ስታስረዳ። 

ላውራ አቺየንግ 17 አመቷ ነው። እንደ ላቲፋህ ሁሉ ሺኔ የተባለ የሞባይል መተግበሪያ ሰርታለች። ዋና ዓላማው በትምህርት ቤቶች የሚታየውን የማመሳከሪያ ጽሁፎች እጥረት መፍታት እና ሥርጭታቸውን ማቃለል ነው።  "ማኅበረሰቡ የሚገጥሙትን ችግሮች በመለየት መፍትሔ ለመፍጠር ስናስብ ተማሪዎች መጽሐፍት ለማግኘት ያለባቸውን ችግር ተመለከትን። ከዚያ ተማሪዎቹን መጻሕፍት ለትምህርት ቤቶች ከሚያቀርቡ ነጋዴዎች ጋር የሚገናኙበት መተግበሪያ ለማዘጋጀት ወሰንን። ሁሉም ተማሪዎች ስኬታማ ሆነው እንዲያንጸባርቁ ስለምንሻ አንጸባራቂ ስንል ጠራነው። ቴክኖሎጂ በፍጥነት እየተለዋወጠ በመሆኑ ገና ለገበያ አላቀረብንውም። ልናሻሽለው እና በቴክኖሎጂ የደረጀ ልናደርገው እንችላለን። በዚያ መተግበሪያ መሠረት ራሴን ከቴክሎጂ ጎራ ቀላቅያለሁ።"

አሁን ከቀኑ ዘጠኝ ሰዓት ነው። በስዋሂሊፖት የቴክኖሎጂ ማዕከል የሚሰጠው ትምህርት ሊጀመር ነው። ሁሉም መምህራን ለሴት ተማሪዎች ሲባል የተመረጡ ናቸው።  የዛሬውን ትምህርት ለመከታተል 15  ሴቶች በመማሪያ ክፍሉ ውስጥ ይገኛሉ። አይሻ አብዱል ቃድር የድርጅቱ ሠራተኛ ነች። አይሻ እንደምትለው በሳይንስ ነክ የትምህርት ዘርፍ የሴት መምህራን እጦት በኬንያ ከፍተኛ ችግር ነው።  "አፍሪቃ በሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ዘርፍ ለሴቶች የሚሆኑ በርካታ ዕድሎች አሉ። እንደ አለመታደል ሆኖ ለሳይንስ እና ለቴክኖሎጂ ጥልቅ ፍላጎት ያላቸው በርካታ እንስቶች በትምህርት እና በሙያ ሕይወታቸው የሚረዷቸው አስጠኚ፣ አስተማሪ እና መንገድ መሪ እንስቶች እጥረት አለባቸው። አብዛኞቹ ሴቶች የሶፍትዌር ዝግጅት፣ ኮዲንግ እና ፕሮግራሚንግ የመሳሰሉ ሥራዎች ለወንዶች የተሰጡ አድርገው ይቆጥሩታል። ስለዚህ ፕዋኒ ቴክኖውጋልዝ የተባለው ተቋማችን ያንን ክፍተት ለመሙላት ጥረት እያደረገ ይገኛል። ሴቶች እርስ በርስ የሚነጋገሩባቸው፣ የሚተጋገዙባቸው እና ልምዳቸውን የሚለዋወጡባቸው መድረኮች አዘጋጅተናል። በዚህ መንገድ አንዳቸው ሌላቸውን ያሰለጥናሉ። ይህ የአቻ ሥልጠና የምንለው ማለት ነው" 

የዛሬ መምህራቸው ሩት ካቬኬ ናት። ሩት መምህር ብቻ ሳትሆን የፕዋኒ ቴክኖውጋልዝ ዋና ሥራ አስፈፃሚ ጭምር ነች። ሩት በሙያዋ የድረ-ገጽ አዘጋጅ ነች። ወይም ድረ-ገፅ ትሰራለች። አጭር ሥልጠና በምትወስድበት ወቅት ከወንድ ባለሙያዎች የገጠማት ማሸማቀቅ ይኸን ተቋም ለመመሥረት መነሳሳት እንደፈጠረላት ትናገራለች። 
"የዩኒቨርሲቲ ተማሪ ሳለሁ ለአጭር ሥልጠና ወደ አንድ ተቋም ሔጄ ነበር። ኩባንያው ምን እንደሚፈልግ አውቃለሁ፤ የሚጠቀሙባቸውን ሶፍትዌሮች እና መሳሪያዎችም ለይቻለሁ። እጅግ ተስፋ ያስቆረጠኝ አለቃዬ ሩት እርግጠኛ ነሽ ይኸን ስራ ትችይዋለሽ ሲለኝ ነበር። እጅግ ተበሳጨሁ። ምንም ነገር ሳልናገር ጊዜ እንዲሰጠኝ እና ሥራውን እንዴት እንደምሰራው ታያለህ አልኩት። በሥራዬ ጎበዝ ለነበርኩ ቀድመው ለአችር ሥልጠና ወደ ተቋሙ የደረሱ ሰልጣኞችን እንድቆጣጠር ኃላፊነት ተሰጠኝ። ጓደኞቼን ሳነጋግራቸው እነሱም በሔዱበት ተመሳሳይ ችግር እንደገጠማቸው አጫወቱኝ። ስለዚህ በጋራ እነዚህ ወጣቶች ለማሰልጠን ወሰንን። እኛ አሰልጥነናቸው ገቢ ማግኘት የጀመሩ ሴቶች ጭምር አሉ። ለሰዎች ድረ-ገፅ ሰርተው ጥሩ ክፍያ ማግኘት ይችላሉ" 

ሩት በ2017 ከአፍሪቃ፤ መካከለኛው እና ደቡብ እስያ እንዲሁም ከመካከለኛው ምሥራቅ አገሮች ወደ አሜሪካ ተጉዘው በቴክኖሎጂ የስራ ዘርፍ የተሰማሩ እንስቶች በተካፈሉበት ትምህርታዊ እና ሙያዊ ሥልጠና ላይ ከተካፈሉ 100 ሴቶች መካከል አንዷ ነበረች። 


"በድረ-ገጽ ደኅንነት ላይ ያለንን ክኅሎት ማሳደግ እፈልጋለሁ። ሞዚላ በተባለው ኩባንያ ውስጥ ተመድቤ ከጠበኩት በላይ እውቀት አግኝቻለሁ። በሳንፍራንሲስኮ የተማርኩት ስልጠና የሰጡን ሴት የምኅንድስና ባለሙያዎች ነበሩ። በአንድ ወቅት እንዲያውም እርጉዞች ሁሉ ነበሩ። እርጉዝ ቢሆኑም ወደ ቢሮ ይሔዳሉ፤ የመውለጃ ጊዜያቸው ቢቃረብም ረዣዥም ሕንፃዎች ላይ ይወጣሉ፤ ሳይንቲስቶች ከሆኑ በቤተ-ሙከራዎቻቸው ውስጥ ይገኛሉ። ሴት በመሆናችን ያሉብን ፈተናዎች ሁሉ ወይም አፈጣጠራችን በሳይንስ ዘርፍ ስኬታ ከመሆን አያግዱንም። በሳይንስ ዘርፎች ላይ የሚሰጡ ስልጠናዎች እና እንደ ፕዋኒ ቴክኖውጋልዝ ያሉ ተቋማት በርካታ ታዳጊ ሴቶች ወደ ቴክኖሎጂ እና ሳይንስ እንዲያዘነብሉ እያገዟቸው መሆኑን ተመልክተናል"

ፕዋኒ ቴክኖውጋልዝ በሞምባሳ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች እና ዩኒቨርሲቲዎች ከሚገኙ 180 ታዳጊ ሴቶች ጋር ሰርቷል። በቴክኖሎጂ እና ሳይንስ ዘርፎች ከተሰማሩ 400 በላይ ሴቶች ጋር በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ ግንኙነት አለው። በዝግታም ቢሆን በሳይንስ እና በቴክኖሎጂ ዘርፎች የተሰማሩ ሴቶች ቁጥር ሲጨምር መልካም ለውጥ በመታየት ላይ ይገኛል። ሁሉም ግን እጅግ በርካታ ሥራዎች እንደሚጠብቋቸው ያውቃሉ። 


ዲያና ዋንዮኒ/እሸቴ በቀለ

ሸዋዬ ለገሠ