«አዳብና» ለመስቀል | ባህል | DW | 25.09.2014
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

ባህል

«አዳብና» ለመስቀል

ርዕሰ አዉዳ ዓመት፤ ወርኃ አደይ ወርኃ ጽጌን ተከትሎ በኢትዮጵያ በተለያዩ ብሄር ብሔረሰቦች በልዩ ልዩ ዝግጅቶች ለመከበር በጉጉት የሚጠበቀዉ የመስቀል በዓል፤ ከሐይማኖታዊ ስርዓቱ ባሻገር ባህላዊ ገፅታዉ አከባበሩ ህብረ- ቀለማዊ ነዉ።

1600 እድሜን እንዳስቆጠረ የሚነገርለትና፤ በተለያዩ ቱፊቶች እና ቀለሞች የደመቀዉ የኢትዮጵያዉ የመስቀል በዓል አከባበር፤ በተባበሩት መንግስታት የሳይንስ የትምህርትና ባህል ማዕከል /UNESCO/መዝገብ በዓለም ቅርስነትም መመዝገቡ ይታወቃል። የዕለቱ ዝግጅታችን በጀርመን ፍራንክፈርት ከተማ የአዳብና ክትፎ ቤት ባለሞያዎችን በመስቀል በዓል ስለሚዘጋጀዉ የተለያየ አይነት ክትፎ እና ስለመስቀል አከባበር እንዲያጫዉቱን ጋብዘናል።


አዳብና ክትፎ ቤት ይላል መኃል ፍራንክፈርት በተለይ በልዩ ልዩ ክትፎዎቹ የሚታወቀዉ የኢትዮጵያ ምግብ ቤት። በጀርመን ሀገር የከፍተኛ ትምህርቱን በኮምፒዩተር ሳይንስ ያጠናቀዉ የምግብ ቤቱ ኃላፊ አቶ ብሩክ ወልዴ ሃርት ማን፤ ለመስቀል በዓል የተለየ ቦታን እንደሚሰጥት ይናገራል፤
«አዳብና» በጉራጌ ባህል ልዩ ቦታ የሚሰጠዉ በመስቀል በዓል የሚደረግ ባህላዊ ሥነ- ስርዓት ነዉ።የመስቀል በዓል አከባበር ሲጀምር በመጀመርያዉ ቀን የጎመን ክትፎ ይበላል፤ በሚቀጥለዉ ቀን ለእርድ የቀረበ ሰንጋ ይታረዳል፤ ቁርጥ ሥጋ ይቀርባል፤ በዝያን ዕለት የጨፊ የሚባል ነገር አለ። ጨፊ ስንል ከቅቤ፤ ከሚጥሚጣ እንዲሁም ሃሞት ጋር ተቀላቅሎ ጥሪዉ ስጋ የሚበላበት ነዉ። ይህ ጥሪ ስጋ የመብላት ሥነስርዓት የበዓሉ ማሟሻ የእርዱ ሟሟሻ አይነት ነዉ፤ ጥሪዉ ስጋ ከተበላ ከሰዓታት በኋላ እንደ የፍላጎት የክትፎ መብላት ሥነ-ስርዓቱ ይቀጥላል። ከዝያ ከአንድ ሳምንት በኋላ የተራረፈዉ ስጋ ፤ ተዘልዝሎና ደርቆ፤ ቋንጣ ሆኖ ፤ ቋንጣዉ ተቀቅሎና በእጅ እንደ እንደ ክትፎ ተከትፎ በሚጥሚጣና በቅቤ ልክ እንደ እርጥብ ክትፎ ተለዉሶ ይቀርባል። ይህ የተቀቀለ ቋንጣ የሚበላበት ቀን አዳብና ይባላል» ሲል ወጣት ብሩክ በጀርመን ፍራንክፈርት ከተማ «የአዳብና ክትፎ» ቤት ባለቤት አጫዉቶናል። ይህንንም በማሰብ ነዉ የኢትዮጵያ ባህላዊ ምግቤቱን አዳብና ሲል የሰየመዉ።


የመስቀል በዓል እጅግ የምንጠብቀዉ ቤተሰብ ጓደኛን ጎረቤትን የሚያያስተሳስር የሚያጠያይቅ በአዛዉንቶች ምርቃት ከወላጅ ምርቃት የሚገኝበት ልዩ በዓል ነዉ ስትል የምትገልፀዉ ወጣት ሮዛ ወልዴ በበኩሏ፤ መስቀል ማለት በመላዉ የክርስትና ሐይማኖት የመስቀሉን መገኘት ምክንያት በማድረግ የምናከብረዉ በዓል ነዉ። በጉራጌ ደግሞ ይህ በበዓል በተለየመልኩ ይከበራል። ሁሉም ማኅበረሰብ ያገባ፤ ያላገባ አዛዉንት፤ ህፃን፤ ሽማግሌ፤ ወጣቱ ሁሉ፤ በዚህ በዓል አንድ የሚሆንበት፤ የሚገናኝበትና፤ ተመራርቆ አብሮ በልቶ የሚለያይበት ግዜ ነዉ። ይህ በዓል ልዩ የሚያደርገዉ ለብዙ ጊዜ ተለያይቶ የነበረ ቤተሰብም የሚሰባሰብበት ነዉ። በጉራጌ ባህል በዚህ በዓል የወደፊት እቅድ የሚወጣበት፤ ወጣቱ የሚተጫጭበት፤ ለስራ ቆርጦ የሚነሳበት፤ ስለ ወደፊት ዓላማ ቤተሰብ በጋራ እቅድ የሚያወጣበት፤ ተመራርቆም የሚለያየበት እጅግ የተከበረ በዓል ነዉ።»


በጉራጌ ማኅበረሰብ ስለ መስቀል በዓል አከባበር ይህን ያህል ካልን፤ የክትፎ የቆጮ አዘገጃጀትስ እንዴት ይሆን? እንደሚታወቀዉ ከእንሰት መቁረጥ መፋቅ የጀመረ ቆጮዉ ደርሶ እስኪጋገር የሚደረገዉ ዝግጅቱ ረዘም ያለ ግዜን ይወስዳል። ለመስቀል በዓል የሚበላዉ ቆጮ ዝግጅት የሚጀምረዉ ቀደም ሲል መሆኑን የአዳብና ክትፎ ባለሞያዋ ወጣት ሮዛ አጫዉታናለች፤ ስለተለያዩ የክትፎ አይነቶች፤ ስለመብያ እቃዎቹና ስለ በዓሉ ሂደትም አጫዉታናለች።
በተለይ በልዮ ልዩ ዩ ክትፎዉ የሚታወቀዉ በፍራንክፈርት ጀርመን አዳብና የኢትዮጵያ ባህላዊ ክትፎ ቤት፤ የመስቀል በዓልን በማስመልከት ለፊታችን ቅዳሜ ልዩ መሰናዶን አዘጋጅቶአል። በዝግጅቱ የተለያዩ አይነት ክትፎዎች ሙዚቃ እና ባህላዊዉ የኢትዮጵያ ቡና መኖሩን የነገሩንን፤ የጉራጌ ቅቅል ክትፎ « አዳብና» ባለቤትን እናመሰግናለን። ስለባህላዊዉ የመስቀል በዓል አከባበር እና ስለ ባህላዊዉ ክትፎ አዘጋጃጀት የሚያወሳዉን ሙሉ ቃለ ምልልስ የድምፅ ማዕቀፉን በመጫን ይከታተሉ!
አዜብ ታደሰ
አርያም ተክሌ

Audios and videos on the topic