አዲስ ግጭት በደቡብ ሱዳን ተቀሰቀሰ | አፍሪቃ | DW | 10.07.2016
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

አፍሪቃ

አዲስ ግጭት በደቡብ ሱዳን ተቀሰቀሰ

የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የጸጥታው ምክር ቤት በደቡብ ሱዳን በተቀሰቀሰው አዲስ ግጭት ላይ ለመምከር በዕለተ እሁድ ይሰበሰባል። ፕሬዝዳንት ሳልቫ ኪር ሁለቱም ወገኖች ግጭቱን በአፋጣኝ እንዲያቆሙ ጥሪ አስተላልፈዋል።

በደቡብ ሱዳን ዋና ከተማ ጁባ በዛሬው ዕለት በፕሬዝዳንቱ እና ምክትል ፕሬዝዳንቱ ኃይሎች መካከል ግጭት በድጋሚ መቀስቀሱ ተነገረ። ከዓርብ እለት አንስቶ በመዲናዪቱ በተፈጠሩ ግጭቶች የተገደሉት ሰዎች ቁጥር ቢያንስ 272 መድረሱ ተዘግቧል። ከሟቾቹ መካከል 33ቱ ሰላማዊ ሰዎች ናቸው ተብሏል። የዐይን እማኞች ለአሶሼትድ ፕሬስ እንደተናገሩት የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የስደተኞች መጠለያ ሰፈር በግጭቱ ጉዳት ደርሶበታል።

በጣቢያው በሚገኝ የህክምና ማዕከል የጸጥታ ጥበቃ የሚያደርጉት ቡድቡድ ቾል ከ50 እስከ 60 የሚደርሱ ቁስለኞች በዛሬው ዕለት ብቻ መኖራቸውን ተናግረዋል። የአማጽያኑ ቃል አቀባይ ዊሊያም ጋትጃት ዴንግ የደቡብ ሱዳን መንግስት ሦስት ሔሊኮፕተሮች በይዞታቸው ላይ ጥቃት መፈጸማቸውን ተናግረዋል።

የአገሪቱ ጦር ቃል አቀባይ ሉል ሩዓይ ኮንግ ግጭት መቀስቀሱን አረጋግጠው እንዴት እንደተጀመረ አይታወቅም ብለዋል። ሬውተርስ የዜና ወኪል የምክትል ፕሬዝዳንት ሪየክ ማቻር መኖሪያ ቤት በሳልቫ ኪር ታማኞች ሁለት ጊዜ ጥቃት እንደተፈጸመበት ቃል-አቀባዩን ጠቅሶ ዘግቧል። ቃል አቀባዩ በጥቃቱ ታንክ እና ሔሊኮፕተሮች ጭምር ጥቅም ላይ ውለዋል ሲሉ ለሬውተርስ ነግረውታል። ግጭቱ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ቢሮ እና የተቃዋሚ ኃይሎች በሚገኙበት ጀበል እና የተቃዋሚዎች ተጨማሪ የጦር ሰፈር በሚገኝበት ጉደሌ አካባቢዎች መቀስቀሱን አሶሼትድ ፕሬስ ዘግቧል። ደቡብ ሱዳን ከሱዳን ተነጥላ ራሷን የቻለች አገር መሆኗን ካወጀች ትናንት አምስተኛ ዓመት ሞልቶታል።

እሸቴ በቀለ

ማንተጋፍቶት ስለሺ