አዲስ የድርቅ አደጋ ስጋት በኢትዮጵያ | ኢትዮጵያ | DW | 13.02.2017
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

ኢትዮጵያ

አዲስ የድርቅ አደጋ ስጋት በኢትዮጵያ

በኢትዮጵያ መጭዉ የበልግ ዝናብ ወቅቱን ጠብቆ ካልዘነበ ለድርቅ ተጋላጭ የሚሆኑ ሰዎች ቁጥር ሊጨምር ይችላል ሲል የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ገለፀ። የብሄራዊ የአደጋ ስጋት ስራ አመራር በበኩሉ አደጋዉን ለመቀነስ ከመቼዉም ጊዜ በላይ እየሰራሁ ነዉ ብሏል።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 04:19

የድርቅ ስጋት በኢትዮጵያ።በአሁኑ ወቅት በሶማሌ ክልል ብቻ ለ አንድ ነጥብ ስድስት ሚሊዮን  ሰዎች የአስቸኳይ ጊዜ እርዳታ እየተደረገ ነዉ። ችግሩ በተከሰተባቸዉ ሌሎች  ክልሎችም  የእንስሳት መኖ የማጓጓዝ ስራ እየተሰራ መሆኑን የኮሚሽኑ የህዝብ ግንኙነት ሀላፊ አቶ ደበበ ዘዉዴ ገልጸዋል።

በኤል ኒኖ የአየር መዛባት ሳቢያ የምስራቅ አፍሪካ ሀገራት ላለፉት ሶስት አመታት በድርቅ እየተጠቁ እንደሚገኙ መረጃዎች ያመለክታሉ። ችግሩ ከጠናባቸዉ የቀጠናዉ ሀገሮች መካከል ኢትዮጵያ አንዷ ስትሆን በሀገሪቱ ደቡብና ደቡባዊ ምስራቅ አካባቢዎች በተለይም በኦሮሚያ ፣በደቡብና በሶማሌ ክልሎች የሚገኙ አርብቶ አደሮችና አርሶ አደሮች ለከፋ ችግር ተጋልጠዋል። ባለፉት ሁለት አመታት የመኸር ዝናብ ወቅቱን ጠብቆ ባለመምጣቱ የተከሰተዉ ድርቅ  በሀገሪቱ ችግሩ በለባቸዉ  አካባቢወች የሚገኙ አርብቶ አደሮችና እንስሳቶቻቸዉ ለረሃብ አደጋ ተጋልጠዋል። ድርቁን ተከትሎ የተከሰተዉ የረሃብ አደጋ በአሁኑ ወቅት በሀገሪቱ 5 ነጥብ 6 ሚሊዮን  ሰወችን የአስቸኳይ ጊዜ እርዳታ ጠባቂ አድርጓል።
ሰሞኑን የወጣዉ የተባባሩት መንግስታት ዘገባ እንዳመለከተዉ መጭዉ የሚያዚያ እና የግንቦት ወር የበልግ ዝናብ ወቅቱን ጠብቆ ካልዘነበ ድርቁ ሊባባስና የተረጂዉ ቁጥርም ሊያሻቅብ ይችላል

ሲል አስጠንቅቋል።  ዶይቼ ቬለ ያነጋገራቸዉ በብሄራዊ የአደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን የህዝብ ግንኙነት ሃላፊ አቶ ደበበ ዘዉዴ እንደሚሉት፣  መስሪያ ቤታቸዉ በዋናነት በቅድመ ማስጠንቀቅ ስራ ላይ ተመስርቶ አደጋን ለመከላከልና ለመቀነስ ፣ እንዲሁም፣ በቀጣይም በጥናት ላይ ተመስርቶ የዝግጁነት አቅምን የማጠናከር ስራ እየሰራ ነው።
በአሁኑ ወቅት በቆላማዉና በአርብቶ አደሩ አካባቢ የተከሰተዉ  ድርቅ የጎላ መሆኑን የሚናገሩት የህዝብ ግንኙነት ሃላፊዉ ድርቁ በሰዉና በእንስሳት ለይ የከፋ ጉዳት ሳያደርስ  ለመቆጣጠርም የአስቸኳይ ጊዜ እርዳታ እየተደረገ መሆኑን አቶ ደበበ ገልጸዋል። ሰሞኑን  በሶማሌ ክልል ብቻ ለአንድ ነጥብ ስድስት ሚሊዮን ሰዎች አስቸኳይ የምግብ እርዳታ የተደረገ ሲሆን፣ ለሌሎቹ ለችግር  ተጋላጭ ክልሎችም በአንድ ሺህ ዘጠኝ መቶ ጣቢያዎች  የአልሚ ምግብና  ሌሎች ምግብ ነክ ነገሮች ለተረጅዎች በማከፋፈል ህብረተሰቡ ቀየዉን ሳይለቅ  ድርቁን ለመቆጣጠር ጥረት እየተደረገ ነዉ ብለዋል።
ወደ ሁለት ነጥብ አምስት ሚሊዮን ሰዎች ለችግር እንደተጋለጡ የሚነገርለት የኦሮሚያ ክልልን ጨምሮ ለደቡብና ለሶማሌ ክልሎችም ለሰዉ ከሚደረገዉ ድጋፍ በተጨማሪ ለእንስሳቱም መኖ እየቀረበ መሆኑን አቶ ደበበ ጨምረዉ ገልጸዋል።
በኤል ኒኖ የአየር ንብረት መዛባት ሳቢያ በአሁኑ ወቅት በአፍሪቃ ከ36 ሚሊዮን በላይ ሰወች ለድርቅና  የተጋለጡ ሲሆን ከነዚህም ዉስጥ 20 ሚሊዮን በምስራቅ አፍሪካ የሚገኙ ናቸዉ። በኢትዮጵያ ደግሞ  10 ሚሊዮን ሰወች ለድርቅ ተጋልጠዉ የቆዩ ሲሆን በአሁኑ ወቅት ግን አምስት ነጥብ ስድስት ሚሊዮን ሰዎች ለአስቸኳይ ጊዜ እርዳታ የተጋለጡ መሆናቸዉን መረጃዎች ያመለክታሉ።

ፀሐይ ጫኔ 

አርያም ተክሌ 

Audios and videos on the topic