አዲስ የወባ ክትባት ተስፋ | ጤና እና አካባቢ | DW | 15.10.2013
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ጤና እና አካባቢ

አዲስ የወባ ክትባት ተስፋ

የወባ በሽታን ለመከላከል የሚረዳ ክትባት የመገኘቱ ዜና በተለይ በበሽታዉ ክፉኛ ለሚጠቁ ሀገራሃት ታላቅ የምስራች ነዉ። የወባ በሽታን ጨርሶ ለማጥፋት ግን ዘመናትን የሚጠይቅ እንደሆነ ባለሙያዎች ይናገራሉ።

በዓለማችን የወባ በሽታ በሰዉ ህይወት ላይ ከፍተኛ ጉዳት የሚያደርሰዉ አፍሪቃ ዉስጥ ነዉ። በዚህም ጨቅላ ሕጻናት ግንባር ቀደም ሰለባዎች ናቸዉ። እዛዉ አፍሪቃ ዉስጥ ደግሞ በተለይ ናይጀሪና፣ ዴሞክራቲክ ሪፑብሊክ ኮንጎ፣ ታንዛኒያ፣ ዑጋንዳና ኬንያ በከፍተኛ ደረጃ በወባ የሚጠቁ ሀገራት ናቸዉ። ደቡብ አፍሪቃ ላለፉት 12 ዓመታት ባደረገችዉ የተጠናከረ ዘመቻ ወባ ታጠፋዉ ከነበረዉ ህይወት 85 በመቶዉን ማትረፍ መቻሏ ተነግሮላታል። በደርበኑ ጉባኤ ላይ በቀረበዉ ዘገባ መሠረትም ባለፈዉ ዓመት በወባ ምክንያት የ70 ሰዎች ህይወት ነዉ ያለፈዉ። የሀገሪቱ የጤና ጥበቃ ሚኒስትር አሮን ሞሶአሊዲ እንደሚሉትም ሀገራቸዉ አሁን ከወባ በሽታ ነጻ ለመሆን መስመሩን ይዛለች፤ ዳርዳር እያለች ነዉ። የደቡብ አፍሪቃ ባለስልጣናትም በዚህ ጊዜ ብለዉ ቀን ባይቆርጡም ከአህጉሩ ባለጸጋና እጅግ የለማችዉ ሀገር ወባን ፈጽማ የምታጠፋበት ጊዜ ቅርብ መሆኑን እየጠቆሙ ነዉ። ዘገባዎች እንደሚሉት ደቡብ አፍሪቃን ከዚህ ዉጤት ያደረሳት በጎሮጎሪዮሳዊዉ 2000ዓ,ም ሀገሪቱ በወባ በሽታ በከፍተኛ ደረጃ በተጠቃችበት ወቅት ለዓመታት ጥቅም ላይ እንዳይዉል አድርጋዉ የነበረዉን ዲዲቲ የተባለ ጸረ ተህዋሲ ወባ በሚያጠቃቸዉ አካባቢዎች በጥንቃቄ ዳግም ተጠቅማ ነዉ። የፕሪቶሪያ ዩኒቨርሲቲ ፕሮፌሰር የሆኑት ቲያን ደ ያገር ዲዲቲ ለስነተዋልዶ ችግርም ሆነ ለካንስር የማጋለጥ የጎንዮሽ አሉታዊ ጉዳቱ እንዳለ ሆኖ የወባ በሽታ ተህዋሲን የማጥፋት ዉጤታማነቱ ሊሸፈን አይገባም ባይ ናቸዉ። ዲዲቲን ከመጠቀም ጎን ለጎን ቤቶችን የማናፈስ፤ የአካባቢን ንጽህና መጠበቅና ዉሃ የሚጠራቀምባቸዉን አካባቢዎች የማድረቅ ርምጃም አብሮ መሄድ ይኖርበታል።

Kenia Kind im Krankenhaus mit Malaria

ኬንያ ሃኪም ቤት፤ በወባ የተያዘች ሕጻን

ባለፈዉ ሳምንት በደቡብ አፍሪቃዋ ደርበን ከተማ በተካሄደዉ ጉባኤ ላይ ከ1,800 የሚበልጡ የሕክም ባለሙያና ተመራማሪዎች፣ የመድሃኒት አምራች ፋብሪካ ተወካዮችና ጉዳዩ የሚመለከታቸዉ ወገኖች ተገኝተዉ ይህች አነስተኛ ፍጥረት ግዙፉን ሰዉ የምትፈጅበትን ተህዋሲ ማዳከም በሚቻልበት ስልት ላይ መክረዋል። ተሰብሳቢዎቹ ከእግዲህ በወባ በገፍ ህይወት የምትቀጥፍበት ዘመን ያከትማል የሚል ተስፋ እንዲያሳድሩ ያደረገዉ አዲስ የተገኘዉ በእንግሊዝኛዉ ምህጻር RTSS የተሰኘዉ ክትባት ከተወለዱ ከስድስት እስከ 12 ሳምንታት በሆናቸዉ ጨቅላዎች፤ እንዲሁም ከአምስት እስከ 17 ወራት ለሞላቸዉ ህጻናት ተሰጥቶ በበሽታዉ የመያዝ አጋጣሚዉን በግማሽ ቀንሶ መታየቱ ነዉ። አፍሪቃ ዉስጥ ወባ በየዓመቱ ከሁለት ሚሊዮን በላይ ሰዎችን ትይዛለች። በተመሳሳይ ጊዜም ወደስድስት መቶ ሺህ የሚገመቱ ሰዎች በአብዛኞዉም ህፃናትን ህይወታቸዉን ያጣሉ። ደርባን ላይ የተወያዩት ከአፍሪቃ፣ ከእስያ፣ አዉሮጳና ከአሜሪካ የተዉጣጡት ባለሙያዎች ወባ የምታደርሰዉን ጉዳት ለመቀነስ ብቻ ሳይሆን ጨርሶ ለማጥፋት ይበጃል የተባሉ መድሃኒቶችን ዉጤት ገምግመዋል። ግላክሶ ስሚዝ ክላይን የተሰኘዉ ኩባንያ ያቀረበዉ RTSS ባካሄደዉ ሙከራ ያስገኘዉን ዉጤት በመያዝም የመጀመሪያዉ የወባ መከላከያ ክትባት ሆኖ በቅርብ ጊዜ ለገበያ እንዲቀርብ ፈቃድ የማግኘት ተስፋዉን ሰንቋል። የክትባቱን ምርምር ያስተባበረዉ ፓዝ የወባ ክትባት ዘመቻ አስተባባሪ የተሰኘዉ ዓለም ዓቀፍ ተቋም ዳይሬክተር ሙከራዉ በሰባት የአፍሪቃ ሀገራት ዉስጥ በአስራ አንድ የምርምር ማዕከላት መካሄዱን ይገልጻሉ። ዶክተር ሳሊ ኤተልስቶን እንደሚሉትም ክትባቱ በወባ የሚያዙ ሕፃናትና ጨቅላዎችን ቁጥር በግማሽ መቀነስ አስችሏል።

«ለRTSS በተወሰነ ደረጃ ቦታ መስጠት አስፈላጊ ነዉ። ይህ የመጀመሪያዉ የክትባት ግኝት ነዉ። ከሰሃራ በስተደቡብ በሚገኘዉ የአፍሪቃ አካባቢ በቅርቡ የተገኙትን ዉጤቶች አያየን ነዉ። በቀጣይ በሚደረገዉ ሙከራ የተሳካ ዉጤት ያስገኛል ተብሎ ሲታሰብም ይህ በእርግጥም ለሕዝብ ጤና ቀላል የማይባል ተጽዕኖ አለዉ።»

ዶክተር ኤተልሰተን እንደሚሉትም የዓለም የጤና ድርጅት ይህ የወባ መከላከያ ክትባት ከአዉሮጳ የመድሃኒት ተቋም የይለፍ ፈቃድ ከተሰጠዉ ከጎርጎሪዮሳዊዉ 2015ዓ,ም መባቻ አንስቶ በይፋ እንደሚቀርብ ፍንጭ ሰጥቷል።

Malaria Mücke

የወባ ትንኝ

«ዉጤቱ ማለትም የዚህ ምርምርና ሙከራዉ ምዘና የመጨረሻ ዉጤት ይፋ ሊሆን የሚችለዉ በመጪዉ 2014ዓ,ም ብቻ እንደሚሆን እንጠብቃለን። ይህ ዉጤት ነዉ ለአዉሮጳ የመድሃኒት አስተዳደር ባለስልጣናትና ለዓለም የጤና ድርጅት የሚቀርበዉ። የዓለም የጤና ድርጅትም ሁሉም በመልካም ሁኔታ ከተጠናቀቀ በ2015ዓ,ም ይህን ክትባት የመጠቀም መመሪያ እንደሚያስተላልፍ ነዉ ያመለከተዉ።»

በደርበኑ ጉባኤ የተሳተፉት ናይጀሪናዊዉ ፕሮፌሰር አዴጋቦይጋ ኦላዲፖ የመጀመሪያዉ የወባ መከላከያ ክትባት በቅርቡ ገበያ ላይ ይቀርባል የሚለተዉ ተስፋ ለናይጀሪያና ሌሎች ወባ ከፍተኛ ጉዳት ለምታደርስባቸዉ ሀገራት ታላቅ እፎይታ ነዉ ባይ ናቸዉ። ስለወባ መድሃኒት ሲታሰብም ዋናዉ ምርመራዉ መሆኑንም ያስገነዝባሉ፤

«ይህ አዲሱ ሕክምና በጣም አስፈላጊ ነዉ። እናም ስለሕክምና ከማዉራት አስቀድሞ መታሰብ ያለበት የምርመራዉ ጉዳይ ነዉ። እዚህ ጉባኤ ላይ ብዙ ሲነገርነት የቆየዉ ነገር ከዚህ ሌላ RDT ማለትም ፈጣን የምርመራ ሙከራ ነዉ። ፈጣን የምርመራ ሙከራ አስቸኳይ ምርመራ በሚያስፈልግበት በተለይም ኤሌክትሪክ በሌለበት በመስክ ሥራ ላይ እና በገጠራማ አካባቢዎች ብዙ ይጠቅማል ብዬ አስባለሁ። RTSSም ወደፊት መራመድን የሚያረጋግጥ ነዉ ብዬ አምናለሁ።»

ሌላዉዋ በጉባኤዉ የተሳተፉት የወባ በሽታን ከአፍሪቃና ከሌሎች አዳጊ ሃገራት ለማጥፋት የሚንሠሩ ከ130 በላይ መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች በአባልነት የሚገኙነት ዓለም ዓቀፍ የጸረ ወባ መቋቋም ስብስብ የምርምር ዳይሬክተር ዶክተር ካሮል ሲብሊ ናቸዉ። እሳቸዉ እንደደሚሉት የወባ በሽታ በዓለም ላይ ለበርካታ ዓመታት ተንሰራፍቶ የሰዉ ህይወትም እየቀጠፈ ኖሯል። ይህን በሽታ ለማጥፋትም እንዲሁ ለዓመታት ሰፊ ጥረት በየደረጃዉ ሲካሄድ ቆይቷል። ዶክተር ሲብሊ ወባን ፈጽሞ ለማጥፋት ተጨማሪ 35ዓመታት ይጠይቃል ባይናቸዉ።

Senegal Gesundheitswesen OP-Saal in Dakar

ሴኔጋል ሃኪም ቤት፤ ወባ የማትጥለዉ የለም

«በሽታዉን ፈጽሞ ለማጥፋት ማለትም በየትኛዉም የዓለማችን ክፍል ምንም ዓይነት የወባ ተህዋሲ የማይኖርበት፤ ማንም በወባ የማይያዝበት የጊዜ ገደብ የሚሆነዉ 2050ዓ,ም ላይ ነዉ፤ ያም አብዛኞቻችን እስከዚያዉ በዚሁ ከዘለቅን ማለት ነዉ። ሆኖም ግን ይህ በየጊዜዉ እየጨመረ የሚሄድ ሂደት ነዉ። እቅዶቹም እንዲሁ በተደጋጋሚ የተለየ ቃል ላይ ያተኩራሉ ይህም ፈጽሞ ማጥፋት የሚለዉ ነዉ፤ ይህም ወባ በአንድ በተወሰነ አካባቢ ከሰዉ ወደሰዉ አትተላለፍም ማለት ነዉ።»

የወባ በሽታን ለመከላከል በሚደረገዉ ጥናት ግንባር ቀደም ተመራማሪ ከሆኑት አንዱ በታይላንድ የባንኮክ ዩኒቨርሲቲ ፕሮፌሰር የሆኑት ኒክ ኋይት ናቸዉ። ኒክ ኋይት በአሁኑ ወቅት በብሪታኒያ የኦክስፎርድ ዩኒቨርሲቲ ተጋባዥ ፕሮፌሰር ሲሆኑ ወባን ለማጥፋት ያለመዉ ጉባኤ አፍሪቃ ዉስጥ መካሄዱ የችግሩ ተጠቂ ሃገራት ምሁራን በሽታዉ ላይ የተከፈተዉን ዘመቻ በባለቤትነት እንዲያራምዱ እድል ሰጥቷል ይላሉ፤

«ይህ ወደትክክለኛዉ አቅጣጫ የሚያመራ ሌላ ርምጃ ነዉ። የወባ ማጥፋት ተነሳሽነት ጉባኤዉ ወባ በከፍተኛ ደረጃ የተስፋፋባትና በበሽታዉም በርካቶች የሚሞቱባትና የሚሰቃዩባት አፍሪቃ ዉስጥ መካሄዱ ትልቅ ነገር ነዉ። የአፍሪቃ ተመራማሪዎች ጉዳዩን ላይ ያላቸዉን ጥልቅ ግንዛቤ መመልከትም ግሩም ነዉ። ሰዎች ችግሩን በባለቤትነት መረከባቸዉ በጣም ጠቃሚ ነዉ ብዬ አስባለሁ።»

እሳቸዉ እንዳሉትም ከተለያዩ የአፍሪቃ ሃገራት የዘርፉ ተመራማሪዎች ወባን ለማጥፋት ይበጃል ያሉትን የየግላቸዉን ግኝት እንዲያቀርቡና ለቀጣይ ምርምር መንገድ እንዲከፈት ጉባኤዉ እድል ሰጥቷል። ደቡብ አፍሪቃ የደረሰችበት የወባ ትንኝ የምታደርሰዉን ጉዳት የመቀነስ ርምጃም ለብዙዎቹ ተጠቂ ሃገራት ተስፋ የሰጠ ሆኗል።

ሸዋዬ ለገሠ

አርያም ተክሌ

Audios and videos on the topic